መንደርደሪያ
በልጅነቴ አዋሽ 7ኪሎ የሰብለወንጌል አንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ዳይሬክተራችን አቶ ፀጋዬ፣ በጠዋቱ የባንዲራ ማውጣት ሰልፍ ላይ ዛሬ ከቀትር በፊት ትምሕርት እንደሌለ ነገረን፡፡ ምክንያቱ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዐት ጀምሮ እስከ ስድስት ሰዐት ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግና ተማሪዎችም በብሄራዊ በዐላት እንደምናደርገው በስነ-ስርዐት ተሰልፈን ሰላማዊ ሰልፉን እንደምናደምቅ ነገረን፡፡
ለካ ትናንትና (ሰኞ) መምህራኑ እና ትልልቆቹ ተማሪዎች ለሰልፉ ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በእንጨት ላይ በጨርቅ የተጻፉ መፈክሮች ሲያዘጋጁ፡፡ በዚያኑ ሰሞን አንድ ይሁን ሁለት አሁን ተዘንግቶኛል የኢትዮጵያ አየርመንገድ አውሮፕላኖች ተጠልፈው ነበር፡፡ እና በሬድዮ እንደሰማነው፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ፣ በአንዳንድ የአረብ ሐገራት የተገዙ፣ ‘’ኤርትራን ከእናት ሀገሯ አስገንጥለው ቀይ ባሕርን የአረብ ሐይቅ ለማድረግ የሚታገሉ ኤርትራዊያን’’ የአይሮፕላን ጠለፋውን እንዳደረጉት ተገልጾ ነበር፡፡ ከነዚህ የአረብ ሀገራት ግንባር ቀደም ተወቃሿ ደሞ ሶርያ ነበረች፡፡
ይህንንም በመቃወም በአዲስ አበባ ተጀምሮ በየከተሞቹ ‘’አረቦች ካገራችን ይውጡ’’ የሚሉ በርካታ ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ ስለማድረጋቸው ሰምተን ነበር፡፡ አባቴ በባቡር ጋዜጦች ይመጡለት ስለነበር በአዲስ ዘመን እና የኢትዮጵያ ድምጽ የሰላማዊ ሰልፎቹ ፎቶዎች ተለጥፈው ተመልክቻለሁ፡፡ በሰልፎቹ ከተያዙት መፈክሮች ብዙዎቹ ለማለት ይቻላል፤
‘’አረቦች ካገራችን ይውጡ’’
‘’ሶርያ ተገንጣዮችን የምትረዳ ጠላታችን ነች’’
የሚሉ ነበሩ፡፡
እንደ ሌሎቹ ከተሞች ሁሉ አዋሾችም ሶርያን ያወገዘ ሰላማዊ ሰልፍ አደረግን፡፡
እንግዲህ በሕይወቴ የመጀመርያውን ሰላማዊ ሰልፍ የተካፈልኩት ሶርያን በማውገዝ ነበር!!
ያኔ ስለ ሶርያ የማውቀው በሬድዮ የሰማሁትንና በጋዜጦች ያነበብኩትን ሲሆን፣ በ 1967 ዓ.ም ከግብጽ እና ጆርዳን ጋር በመሆን ከእስራኤል ጋር ጦርነት ገጥማ፣ እስራኤሎች ‘’ጄኔራል ሞሼ ዳያን’’ በተባለ የጦር መሪ ድል አድርገዋት የሆነ ተራራ እንደወሰዱባት ሰምቻለሁ፡፡
ታድያ እኛን ለቀቅ አድርጋ ዳያን ላይ ብታተኩር አይሻላትም? ለማንኛውም በዚያን ሰሞን በጋዜጣውም በሬድዮውም ሶርያ ትወገዝ ነበር፡፡ የያኔው ዕውቅ ደራሲ አቤ ጉበኛ ‘’መስኮት’’ በተባለ የግጥም መጽሐፉ ስለ ሶርያ አንድ ግጥም ጽፎ ነበር፡፡ ግጥሙ ረዘም ያለ ነው፣ እኔ ግን የማስታውሰው
‘’ሶርያ ምንችክ
የገማች የስጋ ብልት
ዳያን መልካም ባለሙያ ቢጠብሳት በእሳት
ስትንጨረጨር ሸተተው የኛን አፍንጫ የሷ ግማት’’
በኃላም እንደተረዳሁት እነ ጀብሀ (የመጀመርያው የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅት) ዋና ቢሮውም፣መሰልጠኛውም አሌፖ ከተማ ሲርያ ውስጥ ነበር፡፡
ለማንኛውም የዚህ መጣጥፍ አላማ ስለ ሶርያ ታሪክ አጠር ያለ ጽሁፍ ለማቅረብ ነው፡፡ ለምን ሶርያ? የስንክሳር መጽሔት አንዱ አላማ ‘’ማሳወቅ’’ ነው ‘’ከማስተማር እና ከማዝናናት’’ ሌላ ፡፡ የዚህ ዲሰምበር ዋና የአለምአቀፍ ዜና ደሞ በእጅጉ ያተኮረው በሶርያ ስለተደረገው የመንግስት ለውጥ ነው፡፡
እንግዲህ አንባቢዎቻችን በየቴሌቪዥን መስኮቱ ፣ በሶርያ ቀደም ሲል አማጽያን እየተዋጉ ከተሞችን ሲያዙ በኃላም የሀገሪቱ ከተሞች አደባባዮችን በሰልፍ ሲያጥለቀልቁ፣ ሁሉም ቲቪ ስለ ሶርያ አንድ ወይም ሌላ ሲዘግብ፣ ሶርያ ማነች? ለምንስ በዚህ ልክ ትኩረት አገኘች? ማለታችሁ ስለማይቀር፣ ስለ ሶርያ አጠቃላይ ዕውቀት እንዲኖራችሁ በማሰብ የተዘጋጀ መጣጥፍ ነው፡፡
ለወደፊቱም ቢሆን ወርሃዊዋ የናንተው ስንክሳር እንዲህ አይነት የአለምን ትኩረት በእጅጉ የሳበ ክስተት ሲፈጠር ስለሁኔታው መሰረታዊ መረጃዎችን እንደምታቀርብላችሁ ከወዲሁ ቃል እንገባለን፡፡
ሶርያ ባጭሩ
የሶርያ አረብ ሬፐብሊክ ከመካከለኛ ምስራቅ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ከመልእዐ-ምድር አንጻር በምስራቅ እስያ የምትገኝ፣ በምዕራብ የሜዲትራንያን ባሕር፣ በሰሜን ቱርክ፣ በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢራቅ፣ በደቡብ ጆርዳን ፣ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ እስራኤልና ሊባኖስ ያዋስኗታል፡፡ ዋና ከተማዋ ደማስቆ ስትሆን የሀገሪቱ ዋና ቋንቋ አረብኛ ነው፡፡ሶርያ የቆዳ ስፋቷ 185.180 ኪ/ሜ ካሬ ሲሆን 22 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ይኖርባታል፡፡ (BBC Country profile, Syria. January 14/2019)
ሶርያ ከፈረንሳይ ነጻነቷን አግኝታ ሀገር የሆነችው በ 1946 ዓ.ም ነው፡፡ ቀደም ሲል ፈረንሳይ ሊባኖስ እና ሶርያን እንደ አንድ አገር ስታስተዳድር ቆይታ ስትለቅ ግን ቅኝ ገዢዎች አንዳንዴ እንደሚያደርጉት አንዷን ሀገር ሁለት አድርገው ነጻነት ሰጥታለች፡፡ ከነጻነት በኃላ ሁለቱ አገራት ሲዋጉ እንዲኖሩ፣
ፈረንሳይ ማሪን ማሪን
የነጻነት ነገር ምንም አላማረን
እንዲሉ፡፡ልክ እንግሊዝ በሕንድና ፓኪስታን እንዳደረገችው፡፡ ለማንኛውም ከነጻነት በኃላ የተከተሉት አመታት ብዙም ጥሩ አልነበሩም፡፡ በተለይም ከ 1949 እስከ 1970 አገሪቱ በመፈንቅለ መንግስት ትታመስ ስለነበር ሰላምና መረጋጋት አልነበራትም፡፡
ገማል አብደል ናስር የአረብ ብሔረኝነትን ሲያቀነቅንና በመላው አረቢያ ‘’አል ረዒስ’’ እየተባለ አሰርት ሚሊዮኖች ስሙንም የአረብ አንድነትን ባቀነቀኑበት ወቅት፣ ሶርያም ወጀቡን ተከትላ በ 1958 ከ ግብጽ ጋር በመቀላቀል ‘’የተባበሩት የአረብ ሬፐብሊክ’’ በሚል አንድ አገር ሆና ነበር፡፡ ውህደቱ ግን ቀስ በቀስ በሶርያ ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው በ 1961 ጨዋታ ፈረሰ፣ ዳቦ ተቆረሰ አሉና ሁለቱም እንደ በፊቱ ራሳቸውን ወደቻሉ አገራትነት ተመለሱ፡፡
ከዚያ በኃላ ሶርያ ከእስራኤል ጋር ባላት ድንበር ብዙ መቆራቆሶች ገጥሟት ነበር፡፡ መሬታቸውን የተቀሙት የፍልስጥኤም ተፋላሚዎችን ትረዳ ስለነበር በየጊዜው ከእስራዔል ጥቃት ይደርስባት ነበር፡፡ በ1967 ሶርያ በናስር መሪነት ከግብጽ እና ከጆርዳን ጋር በመሆን የ 1967ቱን የአረብና እስራዔል የስድስቱን ቀን ጦርነት አደረገች፡፡ በጦርነቱም ሽንፈት ገጥሟት የጎላን ኮረብታዎቿን በእስራዔል ተቀማች፡፡ ግዛቶቿን ለማስመለስ በድጋሚ 1973 ከግብጽ ጋር በመሆን የ17 ቀናት ጦርነት አድርጋ ነበር፣ አልቀናትም፡፡ እስካሁንም ግዛቶቿ አልተመለሱላትም፡፡
በፖለቲካው ረገድ በ 1963 የተደረገው የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የ በዐዝ ፖለቲካ ፓርቲን ወደ ስልጣን አመጣው፡፡ ይህ የበዐዝ ፓርቲ ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም በዚሁ አመት በኢራቅም በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ይዞ ነበር፡፡ በሶርያ ግን የበዐዝ ፓርቲ እስከ እዚህ ወር መጀመርያ ድረስ በወንበሩ ላይ ነበር፡፡
በ 1967 ቱ ጦርነት የሶርያ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት፣ እንዲሁም አናሳ ከሆነው ከአላዋይቲ ዘር ሺዐይት ሙስሊም ወገን የሆኑት ሐፌዝ ኤል አሳድ በ1970 የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ያዙ፡፡ከዚያ አንስቶ ሞት እስከገላገላቸው ድረስ ለ 29 አመት የሶርያ መሪ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ የሳቸውን ሞት ተከትሎም በ 2000 ዓ.ም ልጃቸው፣ የጥርስ ሐኪሙ በሽር አል አሳድ አባታቸውን በመተካት ፕሬዚዳንት ሆነው በዚህ ወር መጀመርያ ላይ በሶርያ አማጽያን ከስልጣን ተባረዋል፡፡
ሶርያ ለረዢም ጊዜ በሊባኖስ ብጥብጥ ውስጥ ተካፋይ ነበረች፡፡የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነት በተከፈተ በአመቱ በ 1976 ሶርያ ጦሯን ወደ ሊባኖስ አስገባች፡፡ ቀስ በቀስም የጦሯ ቁጥር እስከ 30 ሺ ደርሶ ነበር፡፡ በኃላ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤትን ቁጥር 1559 ውሳኔ እና የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊቅ ሀራሪን ግድያ ተከትሎ ሶርያ በ 2005 አፕሪል መጨረሻ ላይ ጦሯን ከሊባኖስ አስወጣች፡፡ (Lawson, Fred H (2010), Demystifying Syria)
ሶርያ እጅግ ጥንታዊ ሀገር ስትሆን የብዙ የተለያየ ዘር እና ሐይማኖት ተከታዮች ሀገር ናት፡፡ ለምሳሌም ኩርዶች፣ አርመናውያን፣ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች፣ አላዋይቲ ሺዐቶችና አረብ ሙስሊሞች ይኖሩባታል፡፡ (ቢቢሲ ዜና 5/12/24)
የዘር ስብጥሩን በተመለከተ ከቢቢሲ ያገኘሁትን መረጃ በ ፓይ ቻርት ምስል ሲቀነባበር ይህን ይመስላል፡፡
በአረብ ሐገራት በ 2011 የተፈጠረውን የሕዝብ መነሳሳት ተከትሎ በሶርያ ባለ ብዙ-ጎን እርስበርስ ጦርነት ፈነዳ፡፡ በዚህ እንደ ቱርክ፣ ኢራን፣ አሜሪካ እና ራሽያን የመሳሰሉ ሀገራት በየደጋፊዎቻቸው አማካይነት በተካፈሉበት ውጊያ፣ከ 6 ሚሊዮን በላይ ሶርያውያን አገራቸውን ጥለው ተሰደዱ፡፡ በራሽያ ከፍተኛ ድጋፍ የበሽር አል አሳድ መንግስት ለጊዜውም ቢሆን ለመክረም ቻለ፡፡
የተቃዋሚው ጎራ የተከፋፈለ ስለነበር በሽር አል አሳድን ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ይሁንና በዚህ አመት እስራኤል በኢራን የሚደገፈውን ሂዝቦላህ ቡድን በማጥቃቷ እና የኢራንንም የመከላከያ ይዞታዎች በኢራንና በሶርያ ክፉኛ ደብድባ በማዳከሟ፣ ራሽያም በዩክሬን ጦርነት በመጠመዷ፣የሶርያ አማጽያን አገግመው እንደገና ተነሱ፡፡
እነዚህ ሀይላት ቀደም ሲል አሳድን በመደገፍ ተቃዋሚዎቹን ሰለሚረዱ አሳድን ማሸነፍ ከባድ ነበር፡፡ አሁን ግን በዲሰምበር መግቢያ ላይ እነዚህ ኃይላት በሀያት ታህሪር ኤል ሻም የፖለቲካና ሚሊታሪ ኃይል በመመራት መብረቃዊ ጥቃት አካሂደው ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ደማስቆን በመቆጣጠር የበሽር አል አሳድን አገዛዝ ገርስሰዋል፡፡
እንግዲህ በአረብ ሀገራት በ 2011 የፈነዳው አመጽ የቱኒዚያን፣ ግብጽን፣ እና ሊቢያን አምባገነኖች ከስልጣን ገርስሷል፡፡ ሌላው ዋና አምባገነን ሳዳም ሁሴንም በአሜሪካኖች ከስልጣን ወርዷል፡፡ ከሁሉም ህዝባዊ አመጽን ተቋቁሞ በመንበሩ የቆየው የሶርያው በሽር ኤል አሳድ ነበር፡፡
ሶርያ ከመካከለኛ ሀገራት ሁሉ ለራሽያ በጣም ወዳጅ የሆነች ናት፤ በግዛቷም ላለፉት 50 አመታት የራሽያ የጦር ሰፈር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የበሽር አል አሳድ አላዋይቲ ነገድ የሺዐት እስልምና ተከታይ በመሆኑ ኢራን ዋና ወዳጁ ናት፡፡ በሶርያ አንድ ተቃውሞ ኮሽ ከማለቱ የራሽያ የጦር ጀቶች ተቃዋሚዎችን በቦንብ ይደበድባሉ፣ ኢራንም በሊባኖስ ያደራጀችውን ሺዐይት የሆነ የሂዝቦላ ጦር ደሞ በምድር ከሶርያ ጎን ተሰልፎ ተቃዋሚዎችን በምድር ያጠቃል፡፡
በዚህ አይነት የበሽር አል አሳድ ዘለአለማዊ መስሎ በነገሰበት ጊዜ፣ ሳይታሰብ በሁለት ሳምንታት እድሜ ንፋስ እንደጠራረገው አቧራ ከሶርያ የፖለቲካ መድረክ በዚህ ዲሰምበር ወር ተሰናበተ፡፡ አሳድም ቤተሰቡን ይዞ ሞስኮ ከተመ!
በአሁኑ ወቅት በሶርያ የሚገኙ ዋና ዋና የፖለቲካ ኃይላት
1ኛ ከሁሉም የላቀው ሀያት ታህሪር አል ሻም የሚባለውና በአህመድ አል ሻራ የሚመራው በምጽሀረ ቃል ኤች ቲ ኤስ በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ ቡድን ቀደም ሲል የአል ቃይዳ አንድ ክንፍ የነበረ ሲሆን፣ ከ 2017 ጀምሮ ግን ከአል ቃይዳ ተነጥሎ በመውጣት ከሌሎች እስላማዊ አንጃዎች ጋር በመጣመር ሀያት ታህሪር አል ሻም መስርቶ ይንቀሳቀሳል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ደማስቆን ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ መሪው ቀደም ሲል መሐመድ አል ጆላኒ በመባል በትግል ስም ሲጠራ የነበረ አሁን ግን የአቋም ለውጥ አድርጌአለሁ ብሎ በዋና ስሙ አህመድ አል ሻራ ተብሎ መጠራት ይዟል፡፡
ቀደም ሲል አህመድ አል ሻራ በአሜሪካ፣ ኢሮፓን ዩንየን እና የተባበሩት መንግስታትበአሸባሪነት ተፈርጆ ሲፈለግ የነበረ ነው፡፡ አሁንም በዋናነት የሶርያን መንግስት በጊዜያዊነት እየመራ ይገኛል፡፡
2ኛ የሶርያ ዲሞክራቲክ ኃይሎች
ሲሪያን ዲሞክራቲክ ፎርስስ (SDF) የሚባለው በአሜሪካ የሚደገፍ ነው፡፡ ይህ ቡድን በሰሜንና ምስራቅ ሶርያ ግዛቶችን ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ ቡድኑ የሚመራው በኩርዲሽ ፒፕልስ ፕሮቴክሽን ዩኒት (YPG) ሲሆን ሌሎች የአረብ ሚሊሽያ እና አናሳዎቸቹ አሲሪያንና አርመኖችን ያጠቃልላል፡፡ በሚከተለው አለማዊ (ሴኩላር) እና ዲሞክራሲያዊ ርዕዮት ምክንያት አለም አቀፍ ድጋፍ አለው፡፡ በተለይ አሜሪካ ለቡድኑ በቀጥታ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡ በሌላ በኩል ቱርክ አስ ዲ ኤፍን ከኩርዶች ጋር ባለው ቅርበት ምክንያት ትቃወመዋለች፡፡
ከቪ ኦ ኤ ያገኘው ማፕ የቡድኖቹን የኃይል ስብጥር እንዲያሳይ አስቀምጠነዋል
3ኛ የሶርያ ናሽናል አርሚ
ሶርያ ናሽናል አርሚ (SNA) ወይም ኤስ ኤን ኤ በአሳድ መንግስት ላይ ባመጹ ወታደሮች የተገነባ እና ከሌሎች እንደ ፍሪ ሶርያን አርሚ ካሉ ቡድኖች ጋር ጥምረት መስርቶ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በዚህ ስብስግ አለማዊ እና እስላማዊ አንጃዎችም አሉበት፡፡ ቱርክ በቀጥታ የምትደግፈው ይህን ቡድን ነው፡፡ ኤስ ኤን ኤ በሰሜyናዊ ምስራቅ ሶርያ የሚቆጣጠረው ግዛት አለው፡፡
ምንም እንኳ አሳድ ተወግዶ አህመድ ኤል ሻራ ጊዜያዊ መንግስት እየመራ ቢሆን የሶርያ ጉዳይ የተቋጨ እና ያለቀለት አይደለም፡፡ እስካሁን አህመድ አል ሻራ ከተባበሩት መንግስታት ዋና መልዕክተኛ፣ ከብሪታንያ፣ፈረንሳይ፣ ኳታር፣ ቱርክና ከሌሎችም ሐገራት መልዕክተኞች ጋር ተነጋግሯል፡፡
ኤል ሻራ በተጨማሪም ከአናሳ ቡድኑ ድሩዝ ተወካይና በምዕራብ ሶርያ ተቃውሞውን ከመራው ቡድን ጋር መነጋገሩ ተዘግቧል፡፡ እስራኤል በሶርያ ይዞታዎችን በቦንብ ደብድባለች፡፡ ቱርክ የኩርዶች ስብስብ ያለበትን ቡድን ለመውጋት በቋፍ ነች፡፡
ኤል ሻራ ሁሉንም አቃፊ መንግስት ለመመስረት፣ የአናሳ ቡድኖች እና የሴቶችን መብት ለማክበር ቃል ቢገባም መጪው ሳምንታት እና ወራት ይህ ምን ያህል ተግባራዊ እንደሚሆን ገና የሚታይ ነው፡፡ በሶርያ ምድር ያለው የሩስያ ጦር ሰፈር መጻዒ እድል ገና አልተወሰነም፡፡ አውሮፓውያኑ በሶርያ ላይ የተጣለውን እቀባ ለማንሳት እንደ አንድ ቅደመ ሁኔታ እያቀረቡት ነው፡፡ (The Economist December 21st 2024)
ምንም እንኳ ሶርያ ቀድሞ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ባንረሳም ‘’ክፉን በክፉ አትመልሱ ነውና’’ ሶርያ በጎው እንዲገጥማት እንመኛለን፡፡
ምንጮች
BBC, News Country profile – Syria (10/12/2024
Encyclopedia Bitannica, The Winds of Syria
Lawson, Fred H (2010), Demystifying Syria
The Economist December 21st 2024
VOA, By Alex Gendler December 16, 2024 4:37 PM