በቅርቡ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆኖ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጧል፡፡ በሚቀጥለው ጃንዋሪ 20 2025 ኋይት ሐውስ ገብቶ ስራውን ይጀምራል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በ 2016 ሂለሪ ክሊንተንን አሸንፎ ስልጣን ሲይዝ በአሜሪካና በተለይም በተቀረው አለም ትልቅ መረገምና ፍርሀትን ፈጥሮ ነበር፡፡ አሁን፣ መገረሙ ቢቀንስም በሱ ስልጣን መያዝ ፍርሀትና ሀዘን በብዙ የአለም ክፍሎች ተከስቷል፡፡
አውሮፓውያን፣ ትራምፕ ኔቶን ቢያንስ ያዳክማል ሲከፋም ጥሎ ይወጣል ብለው በእጅጉ ሰግተዋል፡፡ ቻይኖች ከፍተኛ የንግድ ታሪፍ ይጥልብናል ብለው አንቅልፍ አጥተዋል፡፡ ጃፓንና ደቡብ ኮርያ በየአገሮቻቸው ላሉት የአሜሪካ ጦር ሰፈር ወጪ ጠቀም ያለ ገንዘብ መድቡ ይለናል ብለው ፈርተዋል፡፡
በተለያዩ አምባገነን መሪዎች ስር ያለው የኤሽያ እና አፍሪካ ህዝብ ትራምፕ የአምባገነኖች አድናቂ እና በተለይ ስለ አፍሪካ ደንታ የሌለው በሆኑ ስለ ሰብዐዊ መብት ረገጣ መባባስ በአያሌው ሰግተዋል፡፡
ወደድንም ጠላንም ይህ ሰው ተመልሶ ዙፋኑ ላይ ስለተሰየመ በተቻለ መጠን ምን አይነት ሰው እንደሆነ በተለይም እንዴት አይነት ፕሬዚዳንት እንደሚወጣው ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ‘’ፖፑሊዝም’’ የሚባል የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ተከታይ ነው፡፡ ስለዚህም እሱን በበለጠ ለመረዳትና ለማወቅ ፖፑሊዝም ምን እንደሆነ ከትራምፕ ጋር እያመሳከርን ለመተንተን እንሞክራለን፡፡
ለመሆኑ ፖፑሊዝም ምንድነው?
‘’ፖፑሊዝም ‘’የህዝብ’’ ሀሳብ የሚያጎላ እና ብዙ ጊዜ ይህንን ቡድን ተቃዋሚ ከሚመስለው ከልሂቃን ቡድን ጋር በተቃርኖ የሚያስቀምጥ የፖለቲካ አቋም ነው፡፡ ፖፑሊዝም በይዘቱ ከፀረ-መንግስት ተቋማት እና ፀረ-ፖለቲካዊ ስሜት ጋር ይዛመዳል።’’ (Cas Mudde & Cristobal Rovira :POPULISM, Oxford University Press, 2017)
ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካም ከዚህ ብዙም ባልተለየ መስኩ ፖፑሊዝምን ሲገልጸው..
‘’ፖፑሊዝም እንደ አንድ የፖለቲካ ፕሮግራም ወይም እንቅስቃሴ ’የተራው ሰው’ ጠበቃ እና ከሱም በተቃራኒ ናቸው የሚላቸውን ልሂቃንና ተቋማትን የምታገል ነኝ ባይ ነው’’ (Encyclopedia BritannicaWritten by Andre Munro, Fact-checked by The Editors of Encyclopedia Britannica Last Updated: Nov 22, 2024 • Article History)
ይሄ የፈረደበት ‘’ሰፊው ሕዝብ’’ መቸም ቆሜልሀለሁ የማይለው የፖለቲካ ኃይል የለም፡፡
እንግዲህ ዶናልድ ትራምፕ በፖለቲካ ስልቱ ፖፑሊስት ከሚባለው ወገን የሚመደብ ነው፡፡ በአንድ ወቅት
‘’እጅግም ያልተማሩ ሰዎችን አወዳለሁ’’ (Reuters, By Melissa Fares and Gina Cherelus February 24, 2016)
ብሎ ነበር፡፡ በፖፑሊስት ፖለቲካ መሰረት ሕዝብና ልሂቃን እንዲሁም ተቋማት ተቃራኒ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕዝብን ከወደድክ ልሂቃንና ተቋማትን መጥላት አለብህ፡፡ ትራምፕም ልሂቃንና ተቋማት በተለይ መገናኛ ብዙሀንና ፍርድ ቤቶች ጠላቶቹ ናቸው፡፡
ካስ ሙደ የሚባለው የፖለቲካል ሳይንስ ተንታኝ ፖፑሊዝምን የሚያዩው እንደ ሀሳብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ማህበረሰብ በሁለት የማይስማሙ ቡድኖች ይከፍላቸዋል፡፡ አንደኛው “ንጹህ ህዝብ” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የልሂቃን ቡድን ነው፡፡
ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ቢሊዮነሩ እና በርካታ መቶ ሰዎችን ቀጥሮ የሚያሰራው ትራምፕ የህዝብ ወገን የመሆኑ ነገር የይምሰል ብቻ ነው፡፡
ትራምፕም አሜሪካን እንደገና ታላቅ እናድርጋት ሲል እሱ ህዝብ የሚለው ‘’ንጹህ አሜሪካውያን” በተለምዶ “ዋስፕ” ማለትም በቆዳ ነጭ፣ በዘር አንግሎ ሳክሶን፣ በሀይማኖት ፕሮቴስታንት የሆኑትን ነው፡፡ ለሱ ጥቁሮች እና መጤዎች የአሜሪካ ችግር ናቸው፡፡
እንግዲህ በአጠቃላይ ያየን እንደሆነ ከአሜሪካ ህዝብ ከፍተኛው የህዝብ ቡድን ከዚህ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ሁሉም ዋስፖች የፖፑሊስት ሀሳብ አማራጆች ባይይሆኑም አብዛኛዎቹ ሀሳቡን ይቀበሉታል ወይም ደሞ አይቃወሙትም፡፡
ለመሆኑ ፖፑሊስቶች እነማን ናቸው?
ፖፑሊስቶች ዲሞክራትም አምባገነንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አሁን ባለም ላይ ያሉ ፖፑሊስት መሪዎችን ብንመለከት እነ ትራምፕ፣ የቱርኩ ኤርዶጋን በዲሞክራሲያዊ ሂደት ወደ ስልጣን የመጡ እና በስልጣን ዘመናቸውም ከሞላ ጎደል በዲሞክራሲያዊ አሰራር አልፈው ደግመው (ትራምፕ)፣ ደጋግመው (ኤርዶጋን) በህዝብ ተመርጠዋል፡፡ በተመሳሳይ የህንዱ ናሬንድራ ሞዲ፣ የኢጣልያው ሴልቪዮ ቤልስኮኒ፣ እና የእንግሊዙ ቦሪስ ጆንሰን እንዲሁ በዲሞክራሲያዊ ሂደት ወደ ስልጣን የመጡ ናቸው
በሌላ በኩል የቬኑዙዌላዎቹ ፕሬዚደንቶች ሁጎ ቻቬስ እና ተከታዩ ማዱራ ፣ የፊሊፒንሱ ሮድሪጎ ዱቴርቴ፣ እና የሀንጋሪው ቪክቶር ኡርባን በምርጫ ስልጣን ቢያገኙም አምባ ገነን ናቸው፡፡
በይበልጥ ፖፑሊዝምን አስፈሪ የሚያደርገው አንዳንዶቹ አምባገነን ሆነው ግን በህዝብ ተመርጠው ስልጣን ካገኙ በኃላ ለተሰወሰነ ጊዜ የተሰጣቸውን መሪነት አለአግባብ በመጠቀም አምባገነንነትን የሚያሰፍኑ በዘላቂነት የሚያሰፍሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ሁጎ ሻቬዝ በምርጫ ስልጣን ከያዘ በኃላ ዲሞክራሲን አፍኖ በሀይል እና ምርጫን በማጭበረበር የቬኑዙዌላን አገዛዝ ወደ አምባገነንነት ቀይሮታል፡፡
ሂትለርም በዲሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፎ ነበር የጀርመን ዲሞክራሲን አፍርሶ ፍጹማዊ አምባ ገነን መንግሰት ያነበረው፡፡
ዶናልድ ትራምፕ አምባገነንነት የማይዳዳው ሰው አይደለም፡፡ የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ፒን የስልጣን ዘመኑን በህገመንግስቱ ከተሰወነው ጊዜ በላይ በፓርላማው አስወስኖ የእድሜ ልክ መሪ ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ አድናቆቱን እና ድጋፉን በይፋ ነበር የገለጸው፡፡ የቭላዲሚር ፑቲንን አምባገነንነት ሊቃወም ቀርቶ በግልጽ አድናቂው እና ደጋፊው እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ በ 2020 በተደረገው የአሜሪካ ምርጫ በህዝብ ድምጽ ሲሸነፍ ላለመውረድ ከማንገራገሩም ባለፈ የአሜሪካውን ኮንግረስ ደጋፊዎቹን በማነሳሳት አስወርሮ ስልጣኑን ሊያራዝም ቃትቶት ነበር፡፡
“ከ 2017 እስከ 2021 የነበረው የትራምፕ አስተዳደር እንዲሁ አንዳንድ
የአምባገነናዊ ፖፑሊዝምን መልኮች አሳይቶ ነበር፡፡ ለምሳሌም ያህል፤
ሴራ ሽረባ፣ አፍሪካ አሜሪካውያንን እና ነጭ ያልሆኑ ፍልሰተኞች ላይ
ዘረኛ አቋም መውሰድ፣ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን አለማመን፣ እንዲሁም
የሬፐብሊካን ፖለቲካ ፓርቲን አድር ባይ እንዲሆን ማድረግ፡፡” (op.cit Encyclopedia Britannica)
ፖፑሊስቶች ግራ ወይም ቀኝ ዘመም ሊሆኑ ይችላሉ
በመሰረቱ ፖፑሊዝም ምሉዕ በኩለሔ የሆነ ፍልስፍና ስለሌለው፣ ትልቁ ግቡም “ሀይል” እና “ሀይል” ብቻ ስለሆነ ለዚህ እስከጠቀመው ድረስ የትኛውንም ወገን ሊሆን ወይንም ሊቀላቀል ይችላል፡፡ የቬኑዙዌላው ማዱሮ ለምሳሌ ግራ ክንፍ ሲሆን የብራዚሉ ጄየር ቦልሶናሮ ቀኝ ክንፍ ነበር፡፡ አንዳንዶቹም ሐይማኖታዊ አክራሪዎች ናቸው ለምሳሌ ኤርዶጋን፣ እንዲሁም ናሬንድራ ሞዲ፡፡
ፖፑሊስቶች በጋራ ያላቸው አንድ ባህሪ በአንድ ግለሰብ ተክለሰውነት ላይ የተተገኑ መሆናቸው ነው፡፡ አንድ ግርማ ሞገስ ያለው፣ ወይም በአነጋገር ለዛ የተካነ ግለሰብ የፖፑሊስቶች ዋና ኃይል ነው፡፡ ያ ግለሰብ ምን ያህል ዋልታ ረገጥ ቢሆን፣ደጋግሞ ስህተት ቢፈጽም፣ ለመሪነት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ባይፈጽም፣ መሪ ማድረግ ወይም መናገር የሌለበትን ቢናገር ለተከታዮቹ ፖፑሊስቶች ምናቸውም አይደል፡፡
እስቲ ዶናልድ ትራምፕ አንድ መሪ መሆን የሌለበትን ሆኖ፣ መፈጸም የሚገባውን ሳይፈጽም፣ ማድረግ የሌለበትን እያደረገ እንደቀጠለ እና ከአንዴም ሁለቴ እንደተመረጠ እንመልከት
- አንድ መሪ ለመሆን የሚዘጋጅ ግለሰብ የፈጠጠ ውሸት መለያው እስኪሆን ድረስ እየደጋገመ አልተመረጠም፡፡ ላቲን ፍልሰተኞች የአሜሪካውየያንን ውሻ እና ድመት ይበላሉ፣ መጤዎች ወንጀለኛ እና ሴት ደፋሪዎች ናቸው፣ ባራክ ኦባማ አሜሪካ አልተወለደም፣ ኮቪድን ለመከላከል ጭምብል ማድረግም ሆነ ክትባት አያስፈልግም…እና ሌሎች ለቁጥር የሚታክቱ ውሸቶችን አየተናገረ ነው ሚሊዮን አሜሪካኖች የሚመርጡት
- የተጻፈ ህግ ባይሆንም በተለምዶ አንድ የአሜሪካ እጩ ፕሬዚዳንት የሀብቱን መጠንና የግብር አከፋፈሉን ለመራጩ ግልጽ ማድረግ አለበት፡፡ ትራምፕ ግን በምን እዳው
- አሁንም በተለምዶ አንድ በወንጀል ተከሶ ተረጋግጦበት የተቀጣ ግለሰብ ፕሬዚዴንት መሆን አይገባውም፡፡ ይህም ተወንጅሎ ከተረጋገጠበትና ከተቀጣ አመት እንኳን ሳይሞላው ተመርጧል፡፡
ሌሎችንም መዘርዘር ይቻላል፣ በኮረና ወረርሺን ጊዜ የሱ አስተዳደር በፈመጸው ቸልተኝነትና ባልፈጸመው ጥንቃቄዎች ሳቢያ አሜሪካኖች በመቶ ሺ ዎች ማለቃቸው እንኳ ለደጋፊዎቹ ሰለሱ የመሪነት ብቃት በቂ ግንዛቤ በሰጣቸው ነበር፡፡
ሌላው የፖፑሊስቶች መለያ…
“ፖፑሊስቶች ንግግሮችን፣ ማለትም አንድ ምሁር እንዳለው ”ባለጌ ባህርይ” በመፍጠር ይታወቃሉ፡፡ ይህም ማለት አናዳጅ ቃሎችንና ስድቦችን በመጠቀም እንዲሁም በፖለቲካ አንጻር ትክክል ያልሆኑ አረፍተ ነገሮችን መናገርን እንደ ታክቲክ ይጠቀሙበታል” (The Conversation)
በፕሬዚዳንትነቱ ዘመን አፍሪካውያንን ‘’የሰገራ ቱቦ’’ (አስ ሆል) ብሎ የተሳደበ ሰው ነው፡፡ ሌላ ግዜ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ‘’ ግብጽ በቦምብ በታፈርሰው አይገርመኝም’’ በማለት ኢትዮጵያውያንን አስደንጦን ነበር፡፡ በሌላ ጊዜም አንድን ጋዜጠኛ በአካል ጉዳተኝነቱ ተሳልቆበት ነበር፡፡
እስካሁን ያልነውን በማለታችን ግን ዶናልድ ትራምፕ ጭራሽ ውሸታም ነው፣ ለአሜሪካም ሆነ ለህዝቡ ምንም ፋይዳ የሌለው ሰው ነው ማለታችን ግን አይደለም፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በፖለቲክስ ከፍተኛ ኃይል እና ተሰሚነት ያላቸውን የጆርጅ ቡሽን ቤተሰብ ከረፓብሊካን፣ የክሊንተንን ቤተሰብ ከዲሞክራቲክ ፓርቲ አሸንፎ ፕሬዚዳንት የሆነ ሰው ነው፡፡ አለምንም የፖለቲካ ችሎታና ግርማ ሞገስ (ካሪዝማ) ይህን ማድረግ አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ቃል የገባውን በመፈጸም ከዲሞክራቶች በእጅጉ የተሻለ ፓለቲከኛ ነው፡፡
ለማንኛውም ግን ፖፑሊዝምን ተመራጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ምንድናቸው? የሚለውን ጥያቄ እንመርምር- ዘ ኮንቨርሴሽን የሚለውን ጆርናል ብንመለከት ለፖፑሊዝም መነሳት ብሎ ያስቀመጣቸው ምክንያቶች ሊታዩ የሚገቡ ናቸው
“ፍልሰት፣ዘረኝነት፣ እና ሐይማኖት ለፖፑሊዝም ፖለቲካ ማዕከላዊ
ማጠንጠኛዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪ ግን ምጣኔ ሐብታዊ ሁኔታዎች
ለምሳሌ ደካማ ምጣኔ ሐብት፣ አለምአቀፋዊ ንግድ፣ የኢንደስትሪያዊ
ሮቦቶች እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለፖፑሊዝም መነሳሳት ከፍተኛ
አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ አንዳንድ በሳሎች ያስባሉ፡፡”(ፐ.ቺተ)
የስራ ዋስትና ማጣት፣በፍልሰተኞች ሳቢያ የጉልበት ገበያው መዳከም፣ የብዙ ነገሮች በኮምፒዩተር መሰራት ፣ ሲደማመሩ ህዝብ – ፍልሰትን ሊጠላ እና የውጪ ንግድን እንዲገደብ ሊጠይቅ፣ የኮምፒተሮች የሰው ስራ መሻማትን ሊቃወም ይገባዋል፡፡
ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ፖለቲከኞች ተገቢውን መፍትሄ በአፋጣኝ ካላገኙ፣ በንድፈ ሀሳብ የረቀቁ ንግግሮችን ቢያደርጉ፣ መሳጭ ጽሁፎችን ቢያቀርቡ ብዙም ውጤታማ አይሆንም፡፡ በዚህን ግዜ አክራሪ ብሕረተኞች፣የውጭ ንግድ ጠሎች፣ የማይገባቸው የመረጃ ቴክኖሎጂ ርቅቀት የማይጥማቸው ፖፑሊስቶች ወደ ህዝቡ ፕሮፓጋንዳቸውን ይዘው ብቅ ይላሉ፡፡ ተሰሚነትም ያገኛሉ፣ ለምን?
ዩቫል ኖህ ሀራሪ ለዚህ ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባል፡፡
“የፖፑሊስቶች ሀሳብ በሁለት ምክንያት ተመራጭነት ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም..
1ኛ በጣም ቀላልና ሁሉም በሚገባው መንገድ ችግሩን
ይዘረዝራሉ፣ መፍትሄ ያሉትንም ያስቀምጣሉ፡፡
2ኛ ሀሳባቸው ውስጥ እውነት አለበት” (Nexus)
በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በለሙት ሀገራት ፖፑሊዝም ሰፊ ሰሚ ጆሮ ያገኘው ከ 2008 የኤኮኖሚ ቀውስ ጀምሮ ነው፡፡ ቀውሱን የፈጠረው የባንኩ ክፍለ ኤኮኖሚ ሲሆን ችግሩ ግን ሁሉንም ክፍለ ኤኮኖሚ እና ህዝብ የደቆሰ ሆነ፡፡ ስራ ፈት በዛ፣ የእቃዎች ዋጋ ንረት ጣራ ነካ፣ቤት መገንባትም ሆነ መግዛት የማየይቀመስ ሆነ፣ የንግድሚዛን መዛባት አስጊ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡
በዚህን ግዜ ማርያ ለ ፔን በአውሮፓ እነ ትራምፕ በአሜሪካ ብቅ አሉአ!
“እኛ የህዝቡ ችግር የሚገባን ነን፡፡ ችግሩን ያመጡት በባንክና በመንግስት ስልጣን የያዙ ልሂቃን ናቸው፡፡ ለመሆኑ በባንኩ ቀውስ ባለ ባንኮች ሲከስሩ አያችሁ? በመንግስት ያሉ ልሂቃን ወዳጆቻቸው ከናንተ ከህዝቡ የሰበሰቡትን ቀረጥ መንትፈው ረብጣ ረብጣ ዶላሩን አሸከሟቸው እንጂ!’’
ችግሩን ያባባሱት ደሞ በዘርም በኃይማኖትም የማይገጥሙን ፍልሰተኞች ናቸው፡፡ በርካሽ ጉልበታቸውን አቅርበው እናንተን ስራ ፈት ያደረጉ፡፡
ችግሩን ያባባሰው የውጭ ሸቀጥ ማራገፊያ ስላደረጉን ነው፡፡ ማን? የቢሮክራሲና መንግስት ልሂቃን!
መፍትሄውስ? እኛን ምረጡን፣ በውጪ ንግድ ቀረጥ ጥለን የሀገራችንን ፋብሪካዎች እንደገና እናንቀሳቅሳለን እናንተም ስራ ታገኛላችሁ፣ ሸቀጦችም ዋጋቸው ይረክሳል፡፡ መጤውን ጠራርገን እናስወጣለን የናንተን ስራ እና ቤት የሚሻማችሁ አይኖርም”
ይህ ቀላል አቀራረብ የህዝቡን ልብ አያሸፈትም?
ሌላውና ዋናው ጉዳይ ደሞ፣ መፍትሄ ብለው የዘረዘሩት ነው እንጂ ችግር ብለው ያስቀመጡት እውነት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ቀውስ መሐል ችግሩን ለመፍታት ከመስራት የችግሩን ምክንያት በንድፈ ሐሳብ እና በቻርት የራቀቀ ዲስኩር የሚያቀርቡትን ዲሞክራቶች ትቶ ህዝቡ ፖፑሊስቱን ቢመርጥ ፈረድበታል?
መፍትሄው ምንድነው?
ፖፑሊዝም እንዳይስፋፋ ተብሎ ብቻ ሳይሆን የተፈጠረው ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስን ፈትቶ የህዝቡን ሰላምና ኑሮ ወደ ቀደመው መመለስ ዋናው መፍትሄ ነው፣ ለዚህም
- ሰራተኛው በአዳዲስ ክህሎቶች እንዲካን ስልጠናዎችን ማቅረብ
- የፍልሰትን መጠን በመገደብ የጉልበት ገበያን ማረጋጋት
- በቴክኖሎጂ ርቅቀት ስራ ያቆሙ የምጣኔ ሀብት አውታሮች ሰራተኞችን በሌላ መስክ እንዲሰማሩ ድጎማ፣ስልጠና እና ብድር ማመቻቸት
- የንግድ ሚዛን መዛባቱን ለማስተካከል መለስተኛ ቀረጥ መጣልና አንዳንድ ምርቶችንም (እንደ ብረታ ብረት ያሉ) ከውጭ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንዳይገቡ ማድረግ
- በምጣኔ ሀብት ቀውሱ ሳቢያ ስራ አጥ ለሆኑ ተመጣጣኝ ወርሐዊ ክፍያ ማድረግ
- ለስራ ፈጠራ ሲባል መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት
እነዚህና የመሳሰሉ እርምጃዎችን በጊዜ መተግበር ምጣኔ ሐብቱ ቶሎ እንዲያንሰራራ፣ የቀውሱ ሰለባዎችን ለመሰረታዊ ችግር እንዳይዳረጉ ማድረግ በዚህም ማህበራዊ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ተገማች መፍትሄዎች ናቸው፡፡ ከምጣኔ ሐብት ቀውስ በተጨማሪ የፖፑሊዝም ምንጮች ለምሳሌ ዘረኝነት እና አክራሪ ሐይማኖተኝነት በሰላሙ ጊዜ በትምህርት በገለጻና በመሳሰሉት ሊረግቡ የሚችሉ ሲሆን እንደ ምጣኔ ሐብታዊ ችግር የመሰለ ቀውስ ካልመጣ በራሳቸው ትልቅ ችግር የሚያመጡ አይደሉም፡፡
ትራምፕ ለምን እንደገና ተመረጠ?
ባለፉት አራት አመታት በስልጣን የነበሩት ዲሞክራቶች የወረሷቸውን ችግሮች አልፈቷቸውም፣ ለምሳሌ
- የዋጋ ንረት እየጨመረ መምጣቱ
- የፍልሰት መጠን ከትራምፕ ዘመን በአራት ጊዜ እጥፍ ማደጉ፡፡ የፍልሰት መጠን ማደጉን አይተው ድንበሩን አለመዝጋታቸው፡፡
- በአፍጋኒስታን ጦርነት ማብቂያ ላይ የባይደን አስተዳደር ያሳየው ችሎታ ቢስነት
- ለምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች የሰራቸውን መፍትሄዎች ለህዝቡ በደንብ ደጋግሞ ለመሸጥ ባለመቻሉ
- ባለፉት አራት አመታት በትራምፕ ላይ ቁጥራቸው የበዛ ክሶች መደረጋቸው በሕዝቡ ዘንድ ትራምፕ ተበዳይ ሆኖ እንዲሳል አድርጎታል
- በተለይ ምርጫው ሲቃረብ እጅግ የሸመገለውና በየሄደበት ሚዛኑን መጠበቅ እየተሳነው የሚወድቀው ባይደን ለሌላ አራት አመት እወዳደራለሁ ማለቱ
- ዲሞክራቶቹም በጊዜ ባይደንን አሳምነው እንዳይወዳደር ለማረግ ባለመቻላቸውና፣ በዘገየ ሰዐት ከውድድሩ ሲወጣ በቂ እጩዎችን አወዳድረው የተሻለ ለማቅረብ ባለመቻላቸው
- ባይደን ተቀባይነቱ በጣም እየቀነሰ መሄዱ በግልጽ እየታየ ካማላ ሃሪስ ብትመረጪ ከባይደን የተለየ ምን ትሰሪያለሽ ስትባል “ምንም” ማለቷ በጣም ትልቅ ስህተት መሆኑ
ዶናልድ ትራምፕ በአሳማኝ ሁኔታ አሸንፎ ወንበሩን ይዟል፡፡
ትራምፕ
“ኋይት ሐውሰ የገባሁ የመጀመርያ ቀን ብቻ ነው አምባ ገነን የምሆነው፣ ከዚያ በኋላ ግን አልሆንም” (The Guardian us-news › dec › donald…)
ሲል ቃል ገብቷል፡፡ በዚያ በመጀመርያ ቀን አምባ ገነንነቱ ምን ይፈጽም ይሆን?
በሱ ቀስቃሽነት ተነሳስተው የአሜሪካ ኮንግረስን በመውረር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ለማስቆም በመሞከራቸው ተከሰው ወህኒ የወረዱ ደጋፊዎችን ምህረት ሰጥቶ ወደ ቀድሞ ኑሯቸው (ምናልባትም ረብሻቸው) እንደሚመለሱ እንደሚያደርግ የብዙዎች ግምት ነው፡፡
ይህን መጣጥፍ እውቁ የፖሊቲካ ምሁር እና የ ሲ ኤን ኤን ጋዜጠኛ ፋሪድ ዘካርያ ‘’Age of Revolutions’’ በሚል የቅርብ መጽሀፉ ስለ ዶናልድ ትራምፕ የጻፈውን በመጥቀስ እንጨርሰው፡፡
‘’Trump’s hour-long campaign speeches could be boiled
down to the four lines: The Chinese are taking away your
factories, The Mexicans are taking away your jobs.
The Muslims are trying to kill you. I will beat them all
up and make America great again’’
ምንጮች
BBC, 6 March 2018
Cas Mudde & Cristobal Rovira Kaltwasser, POPULISM, Oxford University Press 2017
Reuters, By Melissa Fares and Gina Cherelus February 24, 2016
THE CONVERSATION, Academic rigour, journalistic flair, June 26/2024
The Guardian, 07/12/2023 us-news
Yuval Harari NEXUS, , Great Britain; Fern Pres 2024