(የአለም አቀፍ ግንኙነቶች አምድ)
አሜሪካ በአለም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላት ልዕለ-ኃያል መንግሥት ናት፡፡ በተለይ እንደ ሀገራችን ባለው ገና በመልማት ላይ ባለ ሀገር የሚኖራት ተጽዕኖ ሊጋነን የሚችል አይደለም፡፡ ስንክሳርም እንዲሁ በየእትሟ ቢያንስ አንድ ከአሜሪካ ጋር የሚያያዝ መጣጥፍ ማቅረቧ የውዴታ እና ጥላቻ ስሜት ሳይሆን የአስፈላጊነት ጉዳይ ነው፡፡
ሰሞኑን የአሜሪካን የውጭ እርዳታ ለ30 ቀን እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ዘርፈ ብዙ እርዳታ በጤና እና ምግብ ልማት ያቀርብ የነበረው ዩስ ኤይድ ወይም የአሜሪካ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት እንዲሁ ታግዷል፡፡ ይህም እንዲሁ በሀገራችን ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ከዕውቀት ነጻ የሆነው ዶናልድ ትራምፕ ለሰው ልጅ ሊራራ የሚችል ልብም እንዲሁ እንደሌለው እያሳየን ነው፡፡
ሰሞኑን ስለ ፕሬዚዳንቱ የተነገረ አንድ ቀልድ ቀልቤን ስለሳበው ላካፍላችሁ፡፡ ዘራቸው እንግሊዝ፣ ሩስያ፣ ጀርመን እና አሜሪካን የሆኑ የሕክምና ጠበብቶች በአንድ አጋጣሚ ተገናኝተው በየአገራቸው ስለተከናወነው አስገራሚ የሕክምና ስራ የየራሳቸውን እያጋነኑ ይተርካሉ፡፡
የጀመረው እንግሊዛዊው ነው፣ ‘’እኛጋ ያሉ ዶክተሮች አንድ በስቃይ ላይ የነበረ በሽተኛን የታደጉበት ዘዴ ‘’ዋው’’ የሚያስብል ነው፡፡ ታማሚው ጉበቱ ተጎድቶ እየተሰቃየ ነበር፡፡ ዶክተሮቹ ታድያ ከሌላ ጤነኛ ሰው ጉበት ቆርጠው ለታማሚው ያስገቡለታል፡፡ በስድስት ሳምንት ውስጥ ሙሉ ጤነኛ አይሆንላችሁም? አሁን ስራ እያፈላለገ ነው፡፡ አሉ፡፡ ሌሎቹም አድናቆታቸውን ገለጹ፡፡
ከዚያ ጀርመናዊው ቀጠሉና በሚዩኒክ ሆስፒታል የተከናወነውን ተናገሩ፡፡ በሚዩኒክ ጠቅላላ ሆስፒታል በአእምሮ ቁስል የሚሰቃይ ሕመምተኛ ነበር፡፡ በተሳካ ቀዶ ጥገና የሚያመውን ክፍል ቆርጠው አከሙት፡፡ በአራተኛው ሳምንት በሽተኛው እረፍት ከርሞ የተመለሰ ሰው መስሎ፣ ፍጹም ድኖ ቤተሰቡን ተቀላቀለ፡፡ አሁን ስራ እያፈላለገ ነው፡፡
ይኽኛውም እንዲሁ ‘’ይበል’’፣ ‘’ይበል’’፣ ‘’ይበል ግሩም ሰናይ ውዕቱ’’ ተባለ፡፡
ራሽያዊው ዶክተር ከሳቸው በፊት የተናገሩ ጓዶቻቸውን ታሪክ በድጋሚ አድንቀው የራሳቸውን ቀጠሉ፡፡ ሞስኮ ልዩ የልብ ሆስፒታል ግማሽ ልቡ የታወከበት ታማሚ ነበር፡፡ ‘’ታድያ ይኸውላችሁ ዶክተሮቹ ከልብ ባንክ ሌላ ጤነኛ ልብ በቀዶ ጥገና አስገብተውለት ሁን ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ወጣ፡፡ አሁን ስራ እያፈላለገ ነው፡፡ እንዳሉ የእንግሊዛዊውና ጀርመን ዶክተሮች የሩስያን ዶክተሮች አድንቀው ሳይጨርሱ አሜሪካዊው ጣልቃ ገባና…
ሁላችሁም የተናገራችሁት አፈጻጸም ጥሩ ሊባል የሚችል ቢሆንም፣ ግና በአሜሪካ ከተከናወነው ጋር ጭራሹን አይወዳደርም፡፡ የአሜሪካን ዶክተሮች ከጊዜው እንተዋቸው፡፡ የነሱን ስራና ውጤት ልንገራችሁ ብል ጊዜም አይበቃም፡፡ የአሜሪካ ተራ ህዝብ ከጥቂት ወራት በፊት አዕምሮም ልብም የሌለው ሰው አለምንም ቀዶ ጥገና ፕሬዚዳንት አድርጓል፡፡ አሁን ሁሉም አሜሪካዊ ስራ ፈላጊ ሆኗል፡፡
ከመመረጡ በፊት ‘’ለአንድ ቀን ብቻ ነው አምባገነን የምሆነው’’ ያለው ሰውዬ ይኸው ወሩን ሙሉ በቀን በቀን ሕጋዊነታቸው የሚያጠራጥር ድንጋጌዎችን እያጎረፈ ነው፡፡ የሚገርመው የሱ ተግባር ሳይሆን፣ ድርጊቱን ለመቃወም የነበረው ዝምታ ነበር፡፡
እስቲ መጀመርያ ትራምፕ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ለመቋቋም የተደረጉ እርምጃዎችን እንመልከት፡፡
በተመረጠ በነጋታው አሜሪካን ከተባበሩት መንግሥታት የፓሪስ የአየር ለውጥ ስምምነት አስወጣት፡፡ ይህም ማለት ለዚህ የተባበሩት መንግስታት አንድ አካል እንቅስቃሴ አሜሪካ ታዋጣ የነበረው ገንዘብ (88ሚሊዮን ዶላር) ይቆማል ማለት ነው፡፡ ወዲያውኑ የብሎምበርግ ኩባንያ አክሲዮን ከፍተኛ ባለድርሻ የሆነው ማይክል ብሉምበርግን ጨምሮ ሌሎች ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ ሀብታሞች፣ ይህንኑ የአሜሪካን መዋጮ ከራሳቸው አዋጥተው እንደሚሸፍኑ አሳወቁ፡፡ (284 Media 2025/01/27) በዚህም በተባበሩት መንግስታት የፓሪስ የአየር ለውጥ ስምምነት አስፈጻሚ አካል ላይ ሊደርስ የነበረውን የገንዘብ ችግር ተወግዷል፡፡

ማይክል በሉምበርግ
በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች ትራምፕ አዟቸው የነበሩትን፣ ለምሳሌ…
- አሜሪካ በመወለድ የሚገኝን የዜግነት መብት እንዲቀር
- DOGE የሚባለው በኤሎን መስክ የሚመራው መ/ቤት ከአሜሪካ ግምጃ ቤት ሰነድ እንዲያገኝ
- DOGE የሚባለው በኤሎን መስክ የሚመራው መ/ቤት ከሰራተኞች ሚኒስቴር ሰነድ እንዲያገኝ
- ከፌዴራል መ/ቤቶች ሰራተኞች በፍቃደኝነት እንዲለቁ
- ወጪ እንዲታገድ የወጣውን ትዕዛዝ
- ጾታቸውን የቀየሩ እስረኞች ወደ ወንዶች እስር ቤት እንዲገቡ
- የአሜሪካ አለም አቀፍ እርዳታ መ/ቤትን እንዲዘጋ
ትዕዛዛት አግደዋል (USA Today፣ 08/25/2024 Judges are pausing Trump’s policy changes.) በዚህም ለጊዜውን ቢሆን በነዚህ ትዕዛዛት ሊደርሱ የነበሩት ጉዳቶች ቆመዋል፡፡
የዲሞክራቲክ ፓርቲው በኖቨምበር ከገጠመው ሽንፈት ድንጋጤ ገና ያልነቃ ስለሆነ ይሄ ነው የሚባል ተቃውሞ አላሰማም፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስ ካፒቶል ሂል
በጣም የሚገርመው ግን የሬፓብሊካን ፓርቲ የኮንግሬስ አባላት ለትራምፕ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ መገዛታቸው ነው፡፡ መቸም ትራምፕ እውቀት አነሰው ብንል እንኳ እነዚህ የሬፐብሊካን ሴናተሮች በዚህ ረገድ ችግር ያለባቸው አይደሉም፡፡ ግን ሰውየው ሕገመንግስቱን በመጣስ፣ የፓርላማውን ስልጣን በመተላለፍ፣ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ህጎችን በመረጋገጥ የሚሰራውን ሁሉ በዝምታ እያለፉት ነው፡፡
በእርግጥ ከራሳቸው ፓርቲ የተገኘን ፕሬዚዳንት ተቃዋሚ ሆነው ይንቀሳቀሱ አይባልም፡፡ ነገር ግን የሀገሪቱን ደህንነት ሊጎዱ የሚችሉ ስራዎች ሲፈጸሙ አለመተንፈስ፣ እነሱም የሚደግፉት ሕገ መንግሥት ሲጣስ ተመልካች መሆን፤ የዲሞክራሲ ስርአቶች እዚህም እዚያም ሲረገጡ ድምጽ አለማሰማት፣ የራሱ የፓርላው የስራ ድርሻ ሲወሰድ እያዩ እንዳላዩ መሆን ምን ይባላል?
ከሁሉም ከሁሉም ግን፣ ዝምታቸውን እንኳ ዝም ተብሎ ቢታለፍ፣የፌዴራል ቢሮዎችን ለመምራት ብቁ ያልሆኑ ሰዎች በእጩነት ሲቀርቡላቸው መደገፍ በምንም ምክንያት ይቅር የማይባሉበት ስህተት ነው፡፡
እዚህ ላይ ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ በአሜሪካ አንድ ፕሬዚዳንት በሚኒስተርነትና ሌሎች ዋና ዋና የመንግሥት መ/ቤቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮችን ለሹመት እጩ አድርጎ ለ ሴኔቱ(ፓርላማ) የያቀረባል፡፡ ሴኔቱ የቀረቡለትን እጮዎች ሰነድ ይመረምራል፡፡ ማለት የሕይወት ታሪካቸውን፣ በዚህ ቀደም የጥፋት ሬኮርድ እንዳለባቸው፣ የትምህርት እና የስራ ልምድ መረጃቸውን የይመረምራል፡፡ በዚህ ብቁ ከሆኑ እጩዎቹ ሴኔቱ ፊት ቀርበው የማጣርያ ቃለ መጠይቅ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በኃላ ሹመታቸውን በድምጽ ብልጫ ያጸድቃል፣ ወይም ይጥላል፡፡
በዚህ የትራምፕ እጩዎች ማጣራት ወቅት አንዳንድ አሉ የሚባሉ የሬፓብሊካን ፓርቲ ሴናተሮችን አፈጻጸም ዘ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቦት ነበር፡፡ እስቲ ለናሙና አንዳንዱን እንይ
ለምሳሌ ራሳቸው ሕክምናን ያጠኑት ሴናተር ቢል ካሲዲን እንውሰድ፡፡ ስለ ሕክምና ጠቅላላ ዕውቀት እንኳን የሌለው ጸረ-ክትባት እምነቱን እንደ ደህና ነገር በይፋ እስከማወጅ የደረሰው ሮበርት ኤፍ ኬኒዲ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ታጭቶ ይቀርባል፡፡ በዚህ ውቅት እኚህ ሴናተር ያቀረቡለት ጥያቄዎች እና የሰጣቸው መልሶች ለቦታው ብቁ እንደማይሆን በፊትም የነበረውን ግምት ሙሉ በሙሉ ያረጋገጠ ነበር፡፡ ሌላ ይቅር ስለ ዋና የሚኒስቴሩ አገልግሎቶች ምንነት አጥንቶ እንዳልመጣ እኚሁ ሴንተር ባቀረቡለት ጥያቄ አረጋግጦ ነበር፡፡
ሮበርት ኬኔዲ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ብቁ ነው ወይ? ተብሎ ድምጽ ሲሰጥ ሴናተር ቢል ካሲዲ በመደገፍ ነበር ድምጽ የሰጡት፡፡ (The Washington Post February 6, 2025)
ቀጥሎ የምናያት ደሞ የሬፐብሊካን ሴናተር ጆኒ ኤርንስት ናት፡፡ እቺ ሴትዮ በመከላከያ ሚኒስቴር በነበረችበት ወቅት ስለሴቶች መብት ሽንጧን ገትራ በመከራከር ስም ያላት፣ ራሷም ኢራቅ ዘምታ በክብር ሜዳልያ የተሸለመች ናት፡፡ ለመከላከያ ሚኒስትርነት እንዲጸድቅ የቀረበው እጩ ፒት ሄግሴዝ የሚባል የፎክስ ኒውስ ጋዜጠኛ የሆነ፣ ሴቶችን በመተናኮል የተከሰሰ፣ በግልጽ በተቀዳ ንግግር ሴቶች በጦርነት ማገልገል አይገባቸውም ብሎ የተናገረ ሰው አሜሪካ ሴኔት ቀርቦ ሚኒስቴርነቱ ጸድቆለታል፡፡ ለዚህም የበቃው የሴናተር ጆኒ ኤርንስት የድጋፍ ድምጽ ታክሎበት ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
በዛኛው ተገርመን ብዙ ሳንቆይ
የዚህኛው መባስ አያስቅም ወይ
(ዘንድሮ ከተባለው የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን የተወሰደ፡፡ ግጥም ተስፋዬ ለማ)
አሁን የምናየው ደግሞ የርፓብሊካን ሴናተር ቶድ ያንግ ነው፡፡ እኚህ ሴናተር የባህር ወለድ ጦር ውስጥ የመረጃ ቢሮ መኮንን ሆነው ሰርተዋል፡፡ ጥሩ፡፡ ለብሔራዊ ጸጥታ ዳይሬክተርነት እጩ ሆና የቀረበችው ቱልሲ ጋባርድ፣ ደጋግማ የቭላድሚር ፑቲን እና በሽር አል አሳድ አመለካከቶች የምትደግፍ ናት፡፡ ኤድዋርድ ስኖውደን የተባለው የአሜሪካን ምስጢር ሰነዶች ጸኃይ ላይ ያሰጣ ሰውን ከሃዲ፣ የማስጠንቀቂያ ደወል የሰጠ እንጂ ከሀዲ አይደለም ብላ አስተያየቷን የሰጠች ግለሰብ ናት፡፡ ታድያ በአሜሪካ ምድር ከዚች የተሻለ፣ ሰው ጠፍቶ ቱልሲ ጋባርድ ለዚህ ትልቅ ምስጢራዊ ቦታ፣ ሴናተር ቶድ ያንግ ደግፋት ዳይሬክተር ሆናለች፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ከላይ ለትልልቅ ቦታዎች በእጩነት የቀረቡት ሰዎች ሌላው ሁሉ ቀርቶ የትምህርት እና የስራ ልምድ ዝግጅታቸው ውሱንነት ብቻውን ሊመሩት ለታሰቡት ቦታ ውድቅ ባደረጋቸው ነበር፡፡ እንዲያ ቢሆን’ኮ ሌላ ብቃት ያለው ሬፓሊካን ሰው ሊተካ በቻለ ነበር (እንዲያው ገለልተኛ የሆነ ወይም ወደ ሊበራልነት ያደላል ተብሎ የሚጠረጠረው ቀርቶ)
እንዲያው ሌላ ሌላውን ትተን የኮንግሬሱ መሪ ማይክ ጆንሰንን ጉድ እንስማ፡፡ ትራምፕ ከናትናያሁ ጋር ከተወያየ በኃላ፣ አንድ እውቀት ብቻ ሳይሆን ጤንነት የጎደለው ሀሳብ አቀረበ፡፡ አሜሪካ ሁለት ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎችን ከቀያቸው ፈንቅላ ታስወጣለች፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ጋዛን የቀለጠች የምቾት ባህር ዳር መዝናኛ ታረጋታለች የሚል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሌላውን እንተወውና በመካከለኛው ምስራቅ የትራምፕ ወዳጆች የሆኑት ሳዑዲ አረቢያ፣ ጆርዳን እና ግብጽ ‘’ ሀሳቡ ወይም የቁም ቅዠቱ የለየለት እብደት ነው’’ ነበር ያሉት፡፡
ይህም ሆኖ ታድያ ከሬፐብሊካን ፓርቲ ሆነው ድምጻቸውን ባመኑበት መንገድ ብቻ ሲሰጡ የከረሙትን ሴናተር ሚች ማክኮኔልን በማድነቅ አምዳችንን እንደመድማለን፡፡እንደመድማለን፡፡
ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን