ከዛሬ አምስት ወይም ስድስት አመት በፊት ይመስለኛል ሀይሌ ገብረስላሴ እና ሌሎች አትሌቶች ለአንድ የስፖርት ዝግጅት አሰላ ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ሁሉም ለማለት ይቻላል በነበረው ሙቀት በጣም ተገርመዋል፡፡ ያ የሚያውቁትና ያደጉበት አካባቢ በዚህ ደረጃ ተለውጦ ሞቃታማ መሆኑ ብዙ አነጋግሯቸዋል፡፡ በእርግጥ ወቅቱ በጋ ነበር፣ ቢሆንም በከፍተኛ አልቲትዩድና በደጋ አየር ጠባዩዋ የሚያውቋት ከተማ ሸሚዝ አስወላቂ መሆኗ አስደንቋቸዋል፡፡
እሩቅ ሳይኬድ አዲስ አበባ ቀበና ወንዝ ሲዋኙ ያደጉ ልጆች አሁን ትልቅ ሰው ሆነው ሲያዩት ቀበና “ወንዝ የነበረ” እንጂ አሁንስ ወንዝ እንዳይደለ በቅሬታና መገረም ይናገራሉ፡፡ ይህን ሁሉ የምንለው የአለማያን ሐይቅ መድረቅ ሳናነሳ ነው፡፡
አለም እየሞቀች ነው፣ ወትሮ በቀላሉ ያልፉ የነበሩ ከአትላንቲክ እና ሰላማዊ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚነሱ ማዕበሎችና አውሎ ነፋሶች ዛሬ አስፈሪ፣ ሕይወትና ንብረት አጥፊ ሆነዋል፡፡ በቅርቡ ሰፔይንን የመታት ማዕበል ያስከተለው ጎርፍ ከ 200 በላይ ሕይወት ቀጥፏል፣ የንብረት ጉዳቱን ትተን፡፡
አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቻይና እና የሕንድ ትላልቅ ከተሞች አየሩ በሚታይ መልኩ ጸኃይዋን ሸፍኗት ሰዉ ጭምብል ለብሶ፣ መኪኖች ፊት ለፊታቸውን ለማየት ተቸግረው እጅግ በቀስታ ሲንቀሳቀሱ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡
በቅርቡ በስፔይን በደረሰ ከፍተኛ ዝናብ እና ዝናቡ ባስከተለው ጎርፍ ከ 219 ሰዎች በላይ ሲሞቱ 93 ሰዎች ጠፍተዋል፣ የደረሰው የንብረት ጉዳት በቢሊዮን ኢሮ የሚገመት ነው (ERESA MEDRANO (Associated Press) MADRID Nov. 7, 2024 7
2024 ትን እንዳየነው እጅግ ሙቀት የበዛበት፣ ማዕበል ጎርፍና፣ መሰል መቅሰፍቶች የብዙ መቶ ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈው፣ የበዛ መፈናቀልና የንብረት ጉዳት ያደረሱበት አመት ነበር፡፡
ምን መዐት መጣ? ወይስ ስምንተኛው ሺ ደረሰ?
የከባቢ አየር ብክለት ዋናው ተጠቃሽ ነው
የአየር ጠባይ ለውጥ እና የአየር ብክለት
እንግዲህ የአየር ብክለት ስልን በከባቢ አየር ውስጥ አጉዳፊ ንጥረ ነገሮች ሲጨመሩበት የሚመጣ ክስተት ሲሆን፣ የአየር ለውጥ ደግሞ ከተለመደው የአየር ንብረት በተለወጠ መልኩ የሚከሰት የአየር ሁኔታ ነው፡፡ ይህም ለረዢም ጊዜ ከተለመደው የአየር ሁኔታ ቅይይር ውጪ የሆነ አየር ጸባይ ለውጥ ነው፡፡ ስለዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ከዋና ዋና ከባቢያዊ ጉድፎች (ኢንቫይሮንሜንታል ፖሉሽን) ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለምሳሌም የአየር ፣የውኃ ፣ የአፈር መበከል፣ የድምጽ ብክለት እና የመሳሰሉት፡፡ (MPDI journal, dr Shan Zou 2024)
የዋንዴ አዌ፣ በአለም ባንክ ገዲም( ሲንየር) የአካባቢ ጥናት መሐንዲስ ናቸው፡፡ በከባቢ ብክለት አየር እና በአየር ጠባይ ለውጥ መካከል ስላለው ግንኙነት ሲያብራሩ የከባቢ ብክለት ማስወገድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አይነተኛ ዘዴ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
ለመሆኑ የከባቢ ብክለት ምን ያህል ችግርነት አለው?
የአለም ባንክ ካደረጋቸው በርካታ ጥናቶች ተነስቶ ከባቢ ብክለት የሚያስከትላቸው አደጋዎችን እንደሚከተለው ያስቀምጣል፡፡
“ከባቢ ብክለት ለበርካታ አካባቢያዊ (ኢንቫይሮንሜነታል)ሕመሞችና
አለጊዜ ሕልፈት ምክንያት ነው፡፡ ፒኤም2.5 የሚባሉት ቅንጣቶች (ፓርቲክልስ)
በየአመቱ ለ 6.4 ሚሊዮን በልብ ሕመም፣ለሾጤ (ስትሮክ)፣ የሳምባ ነቀርሳ፣
የሳምባ ምች፣ ታይፕ 2 የስኳር በሽታ፣እና የመሰል ሕመሞችመነሻ ጉድፍ አየር ነው”፡፡
( WORLD BANK GROUP.Future Story, September 1 2024)
የአለም ባነክ እንደሚለው
“የሚያሳዝነው እጅግ ከፍተኛው በነዚህ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች
የሚገኙት በአዳጊ አገሮች ነው፡፡ ለምን ቢሉ በታዳጊ አገሮች የሚገኙ
በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ውጪ ረዢም ጊዜ እና አንዳንዶችም
ኑሯቸው ራሱ ከቤት ውጪ በመሆኑ ለፒኤም 2.5 ተጋላጭ በመሆናቸው ነው”፡፡
በአጠቃላይ በጉድፍ አየር ምክንያት የሚደርሰው የምጣኔ ሐብት ጉዳት
8.1 ትሪሊዮን ዶላር ወይም የአለም ጥቅል ብሔራዊ ምርት 6 በመቶ ይሆናል፡፡(op.cit)
የአካባቢ ብክለት እና የአየር ንብረት ለውጥ
የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ በእጅጉ የሚያሳስቡ ችግሮች ናቸው፣ ምክንያቱም
1ኛ የሚደጋገሙ ብክለቶች የአየር ንብረት ለውጥን ስለሚያስከትሉ፣
2ኛ ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ሁኔታ በቁሳዊውና በባዮሎጂካል ፍጡራን ላይ ጉዳት ስለሚያመጣ፣
3ኛ እንደ ፕላስቲክ ምርቶች እና የመሳሰሉት ተጠቅመን የምንጥላቸው ነገሮች የራሳቸው አስተዋጽዖ አላቸው፣
በዚህም ሳቢያ የከባቢ ብክለት አየርና የአየር ንብረት ለውጥ አለምአቀፋዊ ችግር ሆኗል፡፡
የአለም መሞቅ (ግሎባል ዎርሚንግ) ምንጮች አንዱ እና ዋናው የቅሪተ አካል ነዳጅ ነው፡፡
የአየር በካዮችና ግሪን ጋዝ የሚመጡት ከተመሳሳይ ምንጮች ነው፣ እነዚህም የኃይል ምንጮች ሲሆኑ በተለይም በድንጋይ ከሰል የሚረሩ ፋብሪካዎች እና በነዳጅ ዘይት የሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎች እና ተንቀሳቃሾች (መኪና/ባቡር/መርከብ/አውሮፕላንና የመሳሰሉት) የሚያወጡት ጪስ ለአየር ብክለት ዋናው ምክንያት ነው፡፡
በብዛት ይህ ጪስ በከባቢ አየር የሚገባውን የካርቦንዳኦክሳይድ በጣም እንዲጨምር ስለሚያደርግ ግሪን ሐውስን ይፈጥራል፡፡
ሌሎች አጉዳፊዎችም እንዲሁ ለሰው ጤንትም ሆነ ስነ ምሕዳር (ኢኮሲስተም) ጎጂ ከመኖናቸውም ለአየር ንብረት ለውጥም የራሳቸውን አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪም እነዚህ አጉዳፊዎች የጸኃይ ብርሀን በከባቢ አየር የሚመጠጥበትን እና የሚንጸባረቅበት ክስተት ላይ ተውሳክ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ የኦዞን ሽፋን ሽንቁር እንዲኖረው በማድረግ ኦዞን የሚከላከልልን ልዕለ ሐምራዊ ጨረሮች (አልትራ ቫዮሌት ሬይስ) ወደ ምድራችን እንዲገቡ ይሆናል፡፡
የአየር ንብረት ለውጦችን የሚከላከሉ እርምጃዎችን መውሰድ ከባቢ ብክትን ከመቀነሱም ንጹሕ አየር እየበዛ ሲሄድ ዝገ ከባቢ አየር ትነትን (ግሪን ሀውስ ኢሚሽን) ይቀንሳል በተያያዘም የአለማዊ ሙቀትን ያሳናሳል፡፡
የአለም እየሞቀች መሄድ በራሱ የሚያስከትላቸው መዘዞች ቀላልና ትንሽ አይደሉም፡፡ የአለም መሞቅ የውኃ ምንጮችን በማድረቅ፣ የውኃን የስርጭት መጠን፣ጥራትና ጊዜ በአሉታዊ መልኩ ይቀያይራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞው በበለጠ ማዕበልና ጎርፍ የውኃ ብክለትን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን እየተከሰቱ ነው፡፡ በነዚህ ምክንያት የሚፈጠር ድርቅ የምግብ እና ውኃ ችግርን አብዝቶ የሰዎችን ጤና ይነካል፡፡
የውኃ አካላት መበከል ከባቢ አየርን ከማቆሸሹም አልፎ ተክሎችና አልጌዎች እድገትን ያቀጭጫል፡፡የካርቦን መጠጣ (ካርቦን አብዞርቤሽን) እንዲሁም በተራው የአየር ንብረት በውኃ ብክለት በጣም ይጎዳሉ፡፡ በተጨማሪ አፈር ከውቅያኖሶች ቀጥሎ የጎደፈ አየር ለመቀነስ ሁለተኛው ትልቁ የካርቦን ገንዳ ነው፡፡ የፍጥረታት እና ስነ-ምህዳር ስልቶችም ለተክሎች እድገት ውኃ እና ምግብ የሚያገኙት፣ የውኃ ኡደት የሚቀነባበረው እና ካርቦንም የሚከማቸው በአፈር ከአፈር ነው፡፡ በተያያዘ አፈር ሲበከል የካርቦን መምጠጥ አቅሙን ስለሚቀንስ ካርቦን በብዛት ወደ ከባቢ አየር ይገባና የአየር ንብረትን ለውጦ የዝናብ መጠን ላይም አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡ (MPDI)
በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የአካባቢ ብክለት እና የአየር ንብረት መዛባት እየተመጋገቡ በአለም ላይ ብዙ መዘዝ ያስከትላሉ፡፡ ስለዚህ ለሁለቱም ክስተቶች ጥልቅ ጥናት እያደረጉ መፍትሔ ማበጀት አስፈላጊ ነው፡፡
አንዳንድ የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦች
የአለም ባንክ በሳሎች በዚህ ረገድ አንዳንድ ምክር ያቀርባሉ፣-
በመጀመርያ ደረጃ የችግሩን መጠን (ብክለቱን) በየጊዜው መከታተል እና መለካት አስፈላጊ ነው፡፡ የችግሩ መጠን ካልታወቀ መፍትሄውን በትትክክለኛ መጠን ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡
“የ ፒ ኤም 2.5 ከመሬት ለመለካት ዝቅተኛ ገቢ ሀገራት አንድ መለኪያ ለ 65 ሚሊዮን ህዝብ ሲኖራቸው፣ አንድ ለ 28 ሚሊዮን ህዝብ ከሳህራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የምናየው ቁጥር ነው፡፡ በሌላ በኩል የበለጸጉት ሀገራት አንድ መለኪያ ለ 370.00 ሺ ሰዎች ይሆናል፡፡” ( WORLD BANK GROUP, Future Story, September 1 2024)
ችግሩ ምን ያህል ከባቢ አየርን እየጎዳው እንደሆነ በቁጥር በተደገ ማስረጃ ካልተረዳነው ወደ ፊት ከእንቅልፋችን ነቅተን ለመንቀሳቀስ ስንሞክር ጉዳቱ እማይድን ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህም ይላል የባንኩ ግኝት – ሀገራት በቂ የመከታተያ መሬት ላይ የሚገኙ መረቦችን ማዘጋጀት እና በየጊዜው መጠገን አለባቸው፡፡ ይህ ከሆነ የየአካባቢውን የአየር ጥራት ለመተንተን የሚያስችል መረጃ ይኖራል፡፡
“ሌላው መፍትሄ በአንድ አካባቢ የሚገኙ የአየር በካይ ምንጮችን መለየት ነው፡፡ ለምሳሌ ሀ በሚባል ከተማ መጓጓዣ ከፍተኛው የብከላ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ከየቤቱ ወደ አየር የሚተኑ ቆሻሻ የማብሰያ ፈሳሾች ደሞ በከተማ ለ ዋናው በካይ ነው፡፡ አሁን እንደ ችግሩ መፍትሄውን መውሰድ ይቻላል፡፡ የከተማ መጓጓዣን ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር አንዱ መንገድ ነው፡፡” (op. cit)
የባንኩ ግኝት ይቀጥልና በየመለኪያዎቹ የተገኘውን ውጤት ወዲያውኑ እና ደጋግሞ ለህዝቡ ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ እንዲህ ሲደረግ ባለስልጣናት ችግሩ በሰፊው መታወቁን ተከትሎ እርምጃ ለመውሰድ ይገፋፋሉ ወይም ይገደዳሉ፡፡
መፍትሄዎቹን ሁሉ ስንጨምቃቸው የአየር ብክለትን ቅነሳ ቁሳዊ ውዕሎተ-ንዋይ እና በተጨማሪም የፖሊሲ ለውጦችን ይፈልጋል፡፡ ለየ አካባቢው አስፈላጊ እርምጃ ተመራጭ ነው፡፡ ለሁሉም አንድ እርምጃ ውጤታማ አይሆንም፡፡ ነገር ግን በማናቸውም ግንባታ እና ሌሎች የፖሊሲ ውሳኔዎች ሁሉ ብክለትን መቀነስ እንደ አንድ መታሰብ የሚገባው ጉዳይ መወሰድ አለበት፡፡
የኃይል ምንጭን ከዲዜል ወደ ኤሌክትሪክ፣ በየፋብሪካው ፈሳሽም ሆነ ጭስ ከመለቀቁ በፊት የማጣራት ዘዴዎችን መተግበር፣ ምንጫቸው ናይትሮጂን የሆነ ማዳበሪያዎችን አለማበረታታት ወዘተረፈ መፍትሄዎች ናቸው፡፡
በቅርብ የወጣ የ ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት እትም በመፍትሄ ረገድ አንዳንድ አዎንታዊ ውጤቶች እንደተመዘገበ ያበስራል፡፡ ከነዚህም አንዱ በየጊዜው እንደ ኤሌክትሪክ መኪናዎች እና ባትሪዎቻቸው የጸኃይ ኃይል ፓነሎች እና የመሳሰሉ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ዋጋ በየጊዜው እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡(The Economist, September 6/2023)
ለዛሬው ማተኮር የምንፈልገው ይህንን አለም አቀፍ የሆነ ችግር ለመወጣት አለም አቀፍ መፍትሄ የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑንና በዚህ ረገድ በቅርቡ ምን ሊደረግ እንደታሰበ ለመግለጽ ነው፡፡
እንግዲህ የተባበሩት መንግስታት ይህን የአካባቢ ብክለት እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግር በተመለከተ አመታዊ ስብሰባ እያደረገ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማግኘት ይሞክራል፡፡ ስብሰባውን በፕሬዚዳንትነት የሚመራው አገር ከአምስቱ አህጉራት በተዘዋዋሪነት እየተቀያየረ ይመደባል፡፡ ስብሰባውም በፕሬዚዳንቱ አገር ውስጥ ይካሄዳል፡፡
ይህ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ፣ ወይም በአጽርሆተ ቃል ሲ ኦ ፒ (COP) በመባል ይታወቃል፡፡ በ 2015 በፓሪስ የተደረገው ይህ የሲ ኦ ፒ ስብሰባ የበለጸጉ አገራት የአለም የሙቀት መጠኝ በ2050 ድህረ ኢንዱስትርያል አብዮት በነበረበት 1.50c እንዲደርስ ስምምነት እንዲፈርሙ አስደርጓል፡፡(BBC, Georgina Ranard, & Esme Stalard, Climate reporters in Baku 24 November 2024)
ይህም በጣም ጥሩ ውጤት ነበር፡፡
ሀያ ዘጠነኛው ይህ ስብሰባ በባኩ አዘርባጃን ባለፈው ኖቨምበር ተካሂዷል፡፡
ስብሰባው ከብዙ አተካራና መተላለፍ በኋላ ሲጠናቀቅ አንዳንድ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ ችሏል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በታዳጊ አገሮች ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቅረፍ በ 10 አመት ውስጥ 300 ቢሊዮን ዶላር ለአገሮቹ ለመስጠት ወስኗል፡፡ በዚህ ገንዘብ ታዳጊ አገሮቹ አሁን ከያዙት የከሰል እና ነዳጅ ኃይል ፈንታ የኃይል ምንጮታቸውን ወደ ታዳሽ የሀይል ምንጭ እንዲቀይሩ ያግዛቸዋል፡፡
ለዚህ ጉዳይ በታዳጊ ሀገራትየተጠየቀው 1.3 ትሪሊዮን ዶላር መሆኑን ስንረዳ ውሳኔው ምን ያህል ከተገመተው በታች እንደፈየደ እንረዳለን፡፡ የአፍሪካ ቡድን ተደራዳሪዎች ገንዘቡ “በጣም ትንሽ እና የዘገየ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የሕንድ ተወካይ በበኩሉ “ዋጋ ቢስ” ሲል አጣጥሎታል” (op.cit)
ይሁንና በመጨረሻ ታዳጊ አገራቱ የተሰጣቸውን ለመቀበል ተስማምተዋል፡፡ ሌላ አማራጭም አልነበራቸውም፡፡
በመልማት ላይ ላሉ ሀገራት ይህን በተመለከተ ብዙ ገንዘብ ለማዋጣት መስማማት ማለት የለሙት ሀገራት ችግሩን በመፍጠርና በማባባስ ያደረጉትን አምኖ መቀበል ነው፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ ገንዘቡ በቂ ባይሆንን ያንንም ለመክፈል መስማማታቸው ጥፋተኝነታቸውን እንደማመን ይወሰዳል
ለአሁኑ ግን ገንዘቡን የሚያዋጡት የበለጸጉ ሀገሮች ተወካዮች ከዚህ በላይ ምንም ለመክፈል ዝግጁ አደሉም፡፡ እነዚህ ሀገራት አካባቢን ከኢንዱስትርያል አብዮት ጀምሮ እስካሁን ሲበክሉት ኖረዋል፡፡ አሁንም እየበከሉ ነው፡፡ ያልለሙት ሀገራት በሌላ በኩል ብክለት በመፈጸሙ ረገድ ባይኖሩበትም ብክለቱ ያመጣውን ገፈት በሰፊው ቀማሽ ናቸው፡፡
ፈረንሳዮች እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥማቸው “ሴ ላ ቪ” ይሉታል፡፡ “ምን ታረገዋለህ!”
ይበልጡኑ አሁን ያሰጋው የአሜሪካ ጉዳይ ነው፡፡ በአካባቢ ብክለትም ሆነ በአየር ንብረት የማያምነው ዶናልድ ትራምፕ በተመረጠ በሳምንቱ ነው ስብሰባው የተካሄደው፡፡ ከዚህ በፊት በ2015 በፓሪስ የተደረገው ስብሰባ የተስማማበትን ጉዳይ ትቶ ከመሰል ስብሰባ አሜሪካን ከፈራሚነት አስወጥቷት ነበር፣ ዶናልድ ትራምፕ፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደን ደሞ የትራምፕን ውሳኔ ሽረው አሜሪካን ወደ ማህበሩ መልሰዋታል፡፡ አሁን ታድያ ትራምፕ መልሶ አሜሪካን ያስወጣት ይሆን? ይህ ከሆነ ትንሽ ነው ተብሎ የተናቀው ገንዘብ ራሱ ሙሉ በሙሉ መገኘቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ዋናዋ አዋጪ አሜሪካ ነበረቻ? በዚህ ረገድ አሜሪካ ከማህበሩ ውሳኔ ራሷን ካስወጣች፣ አገሪቱ ከዋና ዋናዎቹ ሁለት በካይ አገሮች አንዷ ሆና ለመፍትሄው ግን የመሪነት ሚና መጫወት ቀርቶ ጭራሹኑም ተሳታፊ መሆኗ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡
በመልማት ላይ ላሉ ሀገራት ይህን በተመለከተ ብዙ ገንዘብ ለማዋጣት መስማማት ማለት የለሙት ሀገራት ችግሩን በመፍጠርና በማባባስ ያደረጉትን አምኖ መቀበል ነው፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ ገንዘቡ በቂ ባይሆንን ያንንም ለመክፈል መስማማታቸው ጥፋተኝነታቸውን እንደማመን ይወሰዳል
በሁለተኛ ደረጃ በበካይነት የተቀመጠችው ቻይና ነች፡፡
በስብሰባው የቻይና መልዕክተኛ ዝምታን መርጠው በመጨረሻ የ 300 ቢሊዮን ዶላር ውሳኔው ለድምጽ ሲቀርብ በድጋፍ እጃቸውን አንስተዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ቻይናን አሁንም የሚመድባት በመልማት ላይ ካሉ አገሮች ተርታ ነው፡፡ ስለዚህም የግሪን ሀውስ ልቀትን ለመቀነስም ሆነ ለችግሩ መፍትሄ ገንዘብ እንታዋጣ ግዴታ የለባትም፡፡
ይሁን እንጂ ቻይና በመልማት ላይ ላሉ አገሮች እርዳታ ለሚወሰነው ገንዘብ የራሷን መዋጮ ለማድረግ በፈቃደኝነት ተስማምታለች፡፡ የትራምፕ አሜሪካ እንደተፈራው ጭራሹኑ ከዚህ አይነት ውሳኔ ራሷን ብታገል፣ ቻይና አሜሪካን ተክታ በአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረግ ጥረት ግንባር ቀደም ሀገር ልትሆን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በማምረት ተገድም ቻይና ቀዳሚውን ስፍራ እንደመያዟ ለወደፊቷ አለማችን ደህንነት ገንቢ ሚና እንደያዘች ጠቋሚ ነው፡፡ (The Economist November 24/2024)
ምንጮች
BBC, Georgina Ranard, & Esme Stalard, Climate reporters in Baku 24 November 2024
(ERESA MEDRANO (Associated Press) MADRID Nov. 7, 2024 7:
MPDI journal, dr Shan Zou 2024
The Economist, September 6/2023
BBC, Georgina Ranard, & Esme Stalard, Climate reporters in Baku 24 November 2024
(ERESA MEDRANO (Associated Press) MADRID Nov. 7, 2024 7:
MPDI journal, dr Shan Zou 2024
The Economist, September 6/2023
The Economist November 24/20
WORLD BANK GROUP, FEATURE STORY September 1, 2022