Close Menu
  • መነሻ ገጽ
  • ጠቅላላ እውቀት
    • ባህል እና ስነ-ጥበብ
    • ዓለም አቀፍ ግንኙነት
    • አካባቢ ጥበቃ
    • ታሪክ
    • ከመፅሐፍት ሰፈር
  • ስለ እኛ
  • ያግኙን
  • ስንክሳር መፅሔት ለማዘዝ
Facebook X (Twitter) Instagram YouTube WhatsApp TikTok Telegram
Facebook X (Twitter) Instagram YouTube TikTok Telegram
  • ውሎች እና ሁኔታዎች
  • የግላዊነት ፖሊሲ
  • አካውንት
Saturday, July 19
0 Shopping Cart
ስንክሳር
  • መነሻ ገጽ
  • ጠቅላላ እውቀት
    • ባህል እና ስነ-ጥበብ
    • ዓለም አቀፍ ግንኙነት
    • አካባቢ ጥበቃ
    • ታሪክ
    • ከመፅሐፍት ሰፈር
  • ስለ እኛ
  • ያግኙን
  • ስንክሳር መፅሔት ለማዘዝ
ሰብስክራይብ
ስንክሳር
0 Shopping Cart
አካውንት
ባህል እና ስነ-ጥበብ

አዋሽ 7 ኪሎ

Having not yet visited Sector 10, follow these steps for a free upgrade.
Taye MohammedBy Taye MohammedJanuary 8, 2025Updated:January 13, 2025No Comments11 Mins Read
Facebook Twitter Pinterest LinkedIn Tumblr WhatsApp VKontakte Email
Share
Facebook Twitter LinkedIn Pinterest Email
Showing 1 of 1

(ትንሿ ሜትሮፖሊታን – አዋሽ 7 ኪሎ)

ክፍል አንድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የነበረው ኃይሉ ጎሹ የአዋሽ ምድር ባቡር ፖሊስ ሆኖ ከአንድ ጊዜ በላይ ለአዋሽ ምድር ባቡር ክበብ ተጫውቷል፡፡ እርግጥ ጨዋታው መጋላ እና ባቡር ተብሎ ይደረግ የነበረ የትንሽ ከተማ ጨዋታ ነው ፤ግን ተጫውቷል፡፡ ለልምምድ ከለገሀሩ ስልከኛ ከደመረው ጋር ኳስ እየተቀባበሉ ሲጫወቱ ልጅም ብሆን ትዝ ይለኛል፡፡ 

አቀንቃኙ አሊ መሐመድ ቢራም በአዋሽ 7 ኪሎ ለገሀር ቦምብዬ (የውኃ ክፍል) ሰራተኛ ነበር፡፡ የሽቦ ጊታር ነበረችውና በዚያች በኃላ ዝነኛ የሆነባቸውን ዜማዎች ሲያንጎራጉር አውቃለሁ፡፡ በጊዜው የከተማው ትልቅ ሰው ግራዝማች ሰይድ አሊ ልጃቸውን አቡበከርን ሲድሩ በሰፊው ሰርገው ነበር፡፡ ከአዋሽ በስራ እና በትምህርት እስከወጣንበት ጊዜ ድረስ እንደዚያ አይነት ሰርግ እንዳልታየ ብዙዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ለዚህ ሰርግ ዘፋኞች ከየመን ድረስ መጥተው ነበር፡፡ ሁለት ነበሩ የመናዊ ዘፋኞቹ፤ እናም ጊታር እየመቱ ለኛ ብዙም ያልጣመንን ዜማ እየጮሁ ያንቃርራሉ፡፡ አሊ ቢራ ቁጭ ብሎ ይቅም ነበር፤ሽቦ ጊታሩም ከጎኑ ነች፡፡ ወደ አስር ሰአት ገደማ የመኖቹ እረፍት ሲያደርጉ አሊ ‘’አዋሽ ነመሹኪሳ፤ዋኮ ነዲፍቴ፤ ኢቢዳ ጀለላን…’’ ሲዘፍን ትልቁ ድንኳን በጭብጨባና በጩኸት ተናጋ፡፡ የመኖቹ ተመልሰው መድረክ አላገኙም፡፡

አዋሽ 7 ኪሎ በዚህ ዓ/ም ተመሰረተች ለማለት ትንሽ ያስቸግራል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ከ አስር አመት በፊት 130ኛ አመቷን ቢያከብርም በመረጃ የተደገፈ ዋቢ አልነበረውም፡፡ ከሶስት አመት በፊት የሞቱት የቡፌ ደ ላጋር ባለቤት እድሜ ጠገቧ ማዳም ኪኪ አሲማኮፕሎስ እንደነገረችኝ  ከሆነ ድሮ ድሮ ከአልዩ አምባ በአዋሽ ወንዝ በኩል ወደ ጅቡቲ የሚሄድ ቅፍለትን ተከትሎ ባርያ ፈንጋዮችና ቱርኮች እንደ ማረፊያነት የከተሟት መንደር ነች ወደ በኃላ አድጋ አዋሽ 7 ኪሎ የሆነችው፡፡ መዳም ኪኪ እንደነገረችኝ ከሆነ የፈረንሳዩ የምድር ባቡር ኩባንያ ኩባንያ (ሸመን ደፌር) ሸዋና ሐረርን የሚያገናኘውን የአዋሽ ድልድይ ከከተማዋ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲገነባ መጠሪያዋ አዋሽ 7 ኪሎ ሆነ ብለውኛል፡፡ 

ሆኖም ወደ በኃላ እንዳረጋገጥኩት ከሆነ አዋሽ፤ አዋሽ ሰባት ኪሎ የተባለችው በሌላ ምክንያት ነው፡፡ ለአዋሽ ወንዝ ቅርብ ቦታ ላይ እንደመከተሟ አዋሽ ተብላለች፤ ሰባት ኪሎውን ያወጡላት ግን አፋሮች ናቸው፡፡ እንግዲህ ያኔ አዋሽ ለአካባቢው አፋሮች የመጀመርያዋ ትልቅ እና ዘመናዊ ከተማ ነበረች፡፡ በከተማዋ በቆመው ሳምንታዊ ገበያ ቅቤያቸውን በቀርበታ (ስልቻ መሳይ ነገር) ሞልተው ለመሸጥ የሚመጡት አፋሮች ከዚህ በፊት ያላወቁት አይነት አለካክ ገጠማቸው፡፡ እነሱ የለመዱት ቅቤውን ከቀርበታ ገዢው ወደሚፈልገው እቃ ገልብጠው በምትኩ ማርትሬዛ ብር ወይም በአይነት (ለምሳሌ እህል) መከፈል ነበር፡፡ የአሁኖቹ ነጋዴዎች ግን በርዳን (በእጅ የምትያዝ ሚዛን) ይዘው ጠበቋቸው፡፡ በርዳኑ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ የመንገድ ላይ አትክልት ነጋዴዎች የሚጠቀሙበት አይነት ነው፡፡ ከዛ በበርዳኑ የቀርበታውን ጫፍ ያስይዙና ቅቤው አስር ኪሎ ነው፤ወይም አስራ ሁለት ኪሎ ነው ብለው ዋጋውን በዚያ መሰረት ተምነውና ተከራክረው ነው የሚገዙት፡፡

በአፋርኛ ሱብሀ ቅቤ ማለት ነው፤ ቅቤ በኪሎ የሚሸጥበት ከተማ ለማለት ‘’አዋሽ ሱብሀ ኪሎ’’ ማለት ጀመሩ፡፡ በመዋል በማደር ሱብሀ ኪሎን ከተሜው ሰባት ኪሎ ይለው ጀመር – የት ትሄዳላችሁ ሲባል አዋሽ ሰባት ኪሎ መባል ተለመደና አዋሽም አዋሽ ሰባት ኪሎ ሆነች

አዋሽ ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ 230 ኪሜ ላይ ትገኛለች

የመንገደኞች ባቡር ኦተራይ አዋሽ ለገሐር ቆማ

አዋሽ ሰባት ኪሎ የሀረርጌ እና ሸዋ መገናኛ ድንበር ላይ የተከተመች ጥንታዊ ከተማ ናት፡፡ ከአዲስ አበባ ቢያንስ በሰላሳ አመት ትቀድማለች፡፡ በከተማው በኔ እድሜ አማርኛ፤ሶማልኛ፤አፋርኛ፤ አርጎብኛ እና አረብኛ በሰፊው ይነገራል፡፡ በለገሀር ደሞ ፈረንሳይኛ በትንሹም ቢሆን ይነገር ነበር፡፡ ስራው ማለት የለገሀር ግን ሙሉ በሙሉ በፈረንሳይና ነበር የሚነገረውም የሚጻፈውም፡፡

በሌላ በኩል ከ(Crozet, Jean-Pierre.) መጽኃፍ እንዳገኘሁት የዳግማዊ ምኒሊክ ዋና መሐንዲስ አልፍሬድ ኤልግ የአዋሽ ድልድይን በብረት 1882 (1890 እኤአ) አሰስገንብተውታል፡፡ ያ ማለት እንግዲህ ከ 130 ዓመት በፊት አዋሽ በከተማ ነበረች ማለት ነው፡፡ አሁንም በ 1916 (1923 እኤአ) በአዋሽ ፖስታ ቤት እንደተከፈተ እና በዚህም ረገድ አዋሽ ከአዲስ አበባ፤ ከድሬዳዋ እና ከሐረር ቀጥላ አራተኛዋ ፖስታ ቤት የተከፈተባት ከተማ እንደነበረች ነው፡፡ ያኔ የነበረው ፖስታ ቤት ከጅቡቲ የሚመጡ ፓስታዎች የሚያርፉበት እንጂ በራሱ ከከተማው እንቅስቃሴ ተነስቶ የተከፈተ አይመስልም፡፡ ቆይቶም የተዘጋ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም የአባቴ ጓደኛ የሙነሰር ልጅ የሆነው ንዑማን መሐመድ ሙነሰር በ 1963/64 የፖስታ ወኪልነቱን እስከወሰደ ድረስ ፓስታ ቤት አልነበረምና፡፡

ከኢንተርኔት እንዳገኘሁት መረጃ ከሆነ እንደ ግሪጎሪሳውያን ቀመር ጃነዋሪ 31 ቀን 1914 (ጥር 23 ቀን 1907) ሐዲዱ አዋሽ ወንዝን አቋርጦ አዋሽ ከተማ ገባ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ በጣም ማደግ ጀመረች፡፡ ለገሀሩ አጠገብ ‘’ቡፌ ደ ላጋር’’ የሚባል አሁንም ያለ የመንገደኞች ማረፊያ ሆቴል ተከፈተ፡፡ በባቡርም ምክንያት አዋሽ እያደገች መጣች፡፡ ካላት መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢያ ከተማይቱ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ መካከል ስለሆነች ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ቀጥሎ ትልቁ የምድር ባቡር ጣቢያ አዋሽ ነበር፡፡ ለገሀሩ ራሱ በጊዜው ትልቅ ህንጻ ሲሆን ዴፖውም (እንደ ጋራዥ ያለ ህንጻ) ትንሽ የማይባል ነበር፡፡ ባቡሮች በፊት ከሰል በኃላም ዲዜል የሚቀይሩት በዚህ ዴፖ ሲሆን ባቡሮች ኮንዲክተር እና ሸፍ ደ ትሬይን (የባቡር ነጂ እና በጉዞ ላይ የባቡሩ ኃላፊ) የሚቀይሩትም በአዋሽ ጣቢያ ነበር፡፡

ጊዜው ዳግማዊ ምኒሊክ ሐረርጌን ካቀኑበት አቅራቢያ ስለነበር የመንግስት ወታደሮችና ሹሞች ወደ ሐረር ለመሄድና ለመምጣት በአዋሽ በኩል እንደማለፋቸው ከተማዋ የወረዳ መዋቅርነት አግኝታ አስተዳዳር ተገነባባት፤አገረ ገዢም ተመድቦ ጽ/ቤቶችና እስር ቤት ተሰራ፡፡ይህንኑ ተከትሎ ንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱ የደብረሳሌም ቅድስት ማርያምን ተከሉ፡፡

በጣልያን ዘመን አዋሽ የአካባቢው ዋነኛ ከተማ ነበረች፡፡ ካቲካላ የገደለው አብዱሸርማኒ የተባለ የመኒ ሲነግረኝ፤ በጣሊያን ግዜ እሱ የጣልያኖቹ ዋና ታማኝ ሰራተኛ ነበር፡፡ 

’’አሁን የምታቃቸው ትልልቅ ሰዎች ሁሉ ያኔ ለኔ ይሽቆጠቆጡ ነበር’’ይለን ነበር አዘውትሮ፡፡ ’’ጣልያን ተሸንፎ ይወጣል ብዬ እንኳን  በውኔ በልሜም አላሰብኩት፡፡ ጣልያኖች ከወጡ ምንም አልቀናኝ ይኸው እንደምታየው አሁን ኩሊ ነኝ’’ ብሎኝ ነበር፡፡

በሳምባ ምች ተሰቃይቶ ሲሞት ልጅም ብሆን አስታውሳለሁ፡፡ በጣልያን ጊዜም ፓስታ ቤት የቴሌግራፍ ጣቢያና ሆቴል እና ምግብ ቤት ነበራት አዋሽ፡፡ የእንግሊዞቹ ሀያ ሁለተኛው የምስራቅ አፍሪካ ነፍጠኞች ብርጌድ ከድሬዳዋ ሶስት ቀን ተጉዞ እና ተዋግቶ አዋሽን በአፕሪል ሶስት ቀን 1941 ከጣሊያን አስለቅቋት ወደ አዲስ አበባ ገስግሷል፡፡( Michał Kozicki)

ጣልያኖች በአዋሽ የሰሩትና እስካሁንም ያለው የያኔው የከተማው ወረዳ ጽ/ቤት፤ ፍርድቤቱ፤ገንዘብ ሚኒስትር እና እስር ቤቱ ጣልያን በሰራው ህንጻ ውስጥ ነበሩ፡፡ ሌላው የጣልያን ቅሪት ከአሮጌው ቴሌኮሚኒኬሽን ፊት ለፊት ያለው ሐውልት ነው፡፡ ሐውልቱ 5 ሜትር ያህል ከፍታ ያለው በኛ ጊዜ እንኳን ዙርያውን ቅርጽ ባላቸው ድንጋዮችና ሰንሰለት የተከበበ ነበር፡፡

በጣልያን ጊዜ ከተማይቱ የአካባቢው አስተዳደራዊ ማዕከላዊነቷን ጠብቃ ነበር የዘለቀችው፡፡ ጣሊያን መቼም ትምህርት ቤት መክፈት አያቅም እንጂ የአስተዳደሩን ቢሮዎች (ባለ አንድ ፎቅ) ሰርቷል፡፡ በዚያው ፊት ለፊትም ባንዲራውን መስቀያ ነው መሰለኝ አሁን ከላይ የተረኩላችሁ ሐውልት አለ፡፡  ከቤተክርስትያኗ አጠገብ ጣልያን የሰራው በኃላ ፈርሶ ሰዎች የሚጸዳዱበት ባለ ሶስት ክፍል የሸክላ ቤት ነበር፡፡ ጣልያኖች ሆቴል ቤት እና ቴሌግራፍ እንደከፈቱ  አብዱሸርማኔ ነግሮኛል፡፡ 

ማዳም ኪኪ እንደነገረችኝ ከሆነ የአሁኑ ለገሀር ህንጻ ሳይገነባ እና ዘመናዊ የዲዜል ሎኮሞቲቮች ከመግባታቸው በፊት በነበረው ትንሽ ጣቢያ አስተናጋጅነት በቀን ሶስት የእንፋሎት ባቡሮች በጣቢያው ያልፉ ነበር፡፡ በቀትር፤ በአስራ ሁለት ሰአት እና ማታ በስድስት ሰአት፡፡

በጨዋታችን ላይ ባቡር የሚለው ቃል የተገኘው ከእነዚህ የእንፋሎት ሎኮሞቲቮች ነው፡፡ ማለቴ ቫፑር የሚለውን የፈረንሳይኛ ቃል ኢትዮጵያውያን በአማርኛ ሲናገሩት ባቡር አደረጉት፡፡ ስለዚህም የከሰልም ሆነ የዲዜል አሁን ደሞ የኤሌክትሪክ ሎኮሞቲቮች ሁሉም መጠሪያቸው ባቡር ሆነ፡፡

የከተማው ነዋሪ መተዳደሪያው ንግድ፤የመንግስትና የኩባንያ ስራ ናቸው፡፡ ከለገሀር ቀጥሎ የከተማው አስተዳደር ቢሮ እና ቴሌኮሚኒኬሽን ይገኛሉ፡፡ ከቴሌው ቀጥሎ ቤተክርስትያኑ፤ ከቴሌው ጀርባ የዲሬክተሮች መኖርያ ቤት አና ከዚያም ተያይዞ አማርኛ ተናጋሪዎች የሚበዙበት ሰፈር ነበር፡፡ ከዚህ ሰፈር ትይዩ የአፈር ሰፈር ይባል ነበር እዚያም እንዲሁ ከፊል አማርኛ ተናጋሪዎች የሚበዙበት ነው፡፡መኖርያ ቤት ጠላና ጠጅ ቤቶች ልኳንዳና ያኔ ትልቅ የሚባሉት የወ/ሮ አበበች፣ ወ/ሮ ዘነበች እና የአቦገድል ባለቤት ቡና ቤቶች ነበሩ፡፡ መካከል ላይም የወባ ማጥፊያ መስሪያ ቤት ነበር፡፡ ይህን ሰፈር ይዘን በሰፈሩ መካከል ስንጓዝ ቤተክርስትያኑን ይዞ ትምህርት ቤቱ የሚደርስ መንገድ አለ፡፡ የፊናንስ መፈተሻም እዚያ ሲሆን ከትምህርት ቤቱ ትይዩ የአየር መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት ነበር

ያኔ የነበረው የአዋሽ ኳስ ሜዳ የጎል እንጨትም ሆነ መረብ አልነበረውም፡፡ ጨዋታ ያለ ቀን ከከተማ ቋሚና አግዳሚ እንጨቶችን እንዲሁም አመድ ይዘን እንሄድና እንጨቶቹን ጎል እናደርጋቸዋለን፡፡ ከዚያ በእግር እርምጃ እየተለካ የመሀል ሜዳ ቅርጽ ይሰራል፡፡ ቀጥሎ የቅጣት ምት ክልል እና መምቻ ስፍራ ጎሉ አስራ አንድ እርምጃ ተኬዶ ምልክት ይደረግበታል፡፡ ሁሉም ቅርጾች ላይ አመድ ይነሰነስና የኳስ ሜዳ መልክ ይይዛል፡፡

በልጅነት እሳቤ ስንመለከተው የነበረ ቢሆንም በደንብ ቢያዙ ትልቅ ቦታ ሊደርሱ የሚችሉ ኳስ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ከሁሉም ተደናቂው አባይነህ ነበር፡፡ ጠቆር ብሎ ቆንጆ ፊትና እንደ አረቦች ሉጫ ጸጉር የነበረው አባይነህ ጥሩ ችሎታ ነበረው፡፡ አባይነህ ጎበዝ የማዕረግ ተማሪ የነበረ ሲሆን በኛ ዘመን በትምህርት መዝለቅ የማይችሉ የደሀ ልጆች እንደሚያደርጉት ከአስረኛ ክፍል ቲ ቲ አይ (መምህራን ማሰልጠኛ) ገብቶ በአስተማሪነት ኖሮ ያለፈ ሰው ነው፡፡ ቢመቸው ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ብዙ ቦታ ሊደርስ የሚችል ነበር፡፡ሌላው ሳላህ ነበር፤ ሳላህ ሌላው ቀርቶ ለናዝሪቱ ሕብረት በልጅነት የተጫወተ ወጣት ነበር፡፡ ወደ በኃላ ከተነሱት ደሞ ሐሰን ፋራህ አብዶኛ ተጫዋች ነበር፡፡ ሮናልዲሆን ሳይ ሐሰን ፋራህ ትዝ ይለኛል፡፡

ያኔ እንግዲህ ኳስ ጨዋታ ይደረግ የነበረው በአዋሽ እና በአሰቦት  በአዋሽና በመተሀራ እንዲሁም በአዋሽ እና መርቲ እግር ኳስ ቡድኖች መካከል ነበር፡፡ ከውልንጪቲም ጋር አንዴ ተደርጎ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ አሰራሩ እንዴት ነው? ለምሳሌ የአዋሽ ”አዳል ምንጭ” ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ በሚቀጥለው እሁድ እናርግ ብሎ በደብዳቤ ግብዣ ለአሰቦት ቡድን ይልካል፡፡ ብዙውን ግዜ የተላከለት ቡድን መልስ  አይልክም ግን ቅዳሜ ከመጣ ግብዣውን መቀበሉ ይታወቅና ሜዳው ከላይ በጠቀስኩት መልኩ ይሰናዳል፡፡ ለመጣው ቡድን ማደሪያ (አንድ ሰፊ ክፍል ውስጥ መሬት ላይ ተነጥፎ) እና ምግብ ይቀርባል፡፡ በበነጋው በ 10 ሰአት ጨዋታው ይደረግና ማታውኑ ተጫዋቾቹ ወደየከተማቸው ይሄዳሉ፡፡ ለመጓጓዣ የእቃ ባቡርን ወይንም ሰማንያ የተባለ ባለ ነጭና ሰማያዊ ፉርጎ ያለው ባቡርን ነበር የሚጠቀሙት፡፡

ግብዣ የተላከለት ቡድን የሚቀርበት አጋጣሚም አለ፡፡

ይህ እንዳይሆን ተብሎ አንዳንዴ ለሁለት ቡድኖች ደብዳቤ ይላክና ከሁለት አንዱ መጥቶ ጨዋታው ይደረጋል፡፡ አንዴ ታድያ የመርቲ እና የአሰቦት ቡድኖች ሁለቱም መጡ፡፡ ያን እለት የአዋሽ ቡድን ከቀኑ 8-10 ከአሰቦት ጋር ተጫውቶ ሁለት ለዜሮ፤ ከ 10-12 ከመርቲ ጋር ተጫውቶ አንድ ለዜሮ ያሸነፈበትን ክስተት አልረሳውም፡፡ በዚያ የአዋሽ ሙቀት 180 ደቂቃ መጫወት እንዴት ከባድ እንደሆነ መገመቱ ቀላል ይመስለኛል፡፡

አንዴ ደሞ ”ኡላ ኡላ” የሚባል የመልካ ጂሎ ቡድን መጥቶ 12 ለ 0 መሸነፉን አስታውሳለሁ፡፡ እረፍት ስድስት ይሁን ሰባት ለዜሮ ነበር የወጡት፡፡ ከእረፍት መልስ እነ አባይነህ እና ሳላህ ያሉበት ዋናው ቡድን ወጥቶ ሌሎች ገብተው ነበር የተጫወቱት፡፡

የኳስ ነገር ከተነሳ አንዴ የመተሀራ ልጆች ጋብዘዋቸው የአዋሽ የጊዜው ወጣቶች ወደ መተሀራ ያቀናሉ። የመጓጓቸው ዘዴ (ሞዱስ ኦፐራንዴ) እንዴት መሰላችሁ? ያን እሁድ ጠዋት ከአዋሽ ውኃ ለቦርጨታ የሚወስድ ባቡር ነበር። ባቡሩ እስቴርና (የባቡር ቦቴ) ሙሉ የኮራ ውኃ ጭኖ ከአዋሽ እስከ ወለንጪቲ ያሉ ባቡር የማይቆምባቸውን ደረቅ ጣቢያዎች ለሚገኙ ሰራተኞች ውኃ ያድላል። ስለዚህም መጀመርያ ከአዋሽ መተሀራ በግማሽ ርቀት የሚገኘውን ለገበንቲን ካደለ በኃላ መተሀራ ሲደርስ ልጆቹ ይወርዳሉ። ከዚያ ባቡሩ ከመተሀራ አልፎ ሳቡበርን ከመልካጂሎ አልፎ ቦርጨታን አድሎ ሲመለስ በዛ ተሳፍረው 12 ሰአት አካባቢ አዋሽ ይመለሳሉ።

እስከዛ ባለው ጊዜ ነው የ 90 ደቂቃው ኳስ ጨዋታ መጠናቀቅ ያለበት፣ብዙ ጊዜ ባቡሩ ቦርጨታ ደርሶ ለመመለስ የበለጠ ጊዜ ይወስድበታል። ያን እሁድ ግን አንደ አለመታደል ሆኖ ባቡሩ የሆነ የቴክኒክ ችግር ገጥሞት ከመልካጂሎ በቶሎ ተመለሰ። ጨዋታው ተፋፍሞ አዋሾች አንድ ለዜሮ እየመሩ ከእረፍት መልስ አምስት ደቂቃም አልሞላም ነበር። ህዝቡ መተሀሮች ጎል አግብተው እኩል ለመሆን ባለ አቅማቸው በስሜት እንዲጫወቱ ያበረታታል፣አዋሾች ገትረዋል። በመሀል ኤስ ኤል ሟ ባቡር ጡሩባዋን ነፋች፣ መምጣቷን ለመንገር! የአዋሽ ልጆች ኳሱን ጥለው ልብሶቻቸውን አንጠልጥለው ወደ ለገሀር ሩጫ! ሰዉ እየጮኸ መሳደብ ቀጠለ።ሌላ መጓጓዣ የሌላቸው ልጆች ከኃላቸው የሚጮሁትንና የሚሳደቡትን ጥለው እመጭ ወደ ባቡራቸው!

በነገራችን ላይ ደረቅ ጣቢያ የሚለው ቃለ አጠቃቀም ቀደም ሲል ብዙም አይገባኝም ነበር፡፡ በረሀ መሀል ያሉ የትንንሽ ከተሞች መጠሪያ ነበር የሚመስለኝ፡፡ በቅርቡ አቶ በቀለ ገብሬ የተባሉ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን የመንግስት ማዕከላዊ ባለስልጣን በሸገር ሬድዮ ቃለ ምልልስ ሲሰጡ ትክክለኛው አግባብ ምን እንደሆነ ተረድቼዋለሁ፡፡ እንግዲህ የያኔ የከሰል ባቡሮች በየባቡር ጣቢያዎቹ ቦቴ ተሰቅሎላቸው ውኃ ይወስዳሉ፡፡ ባቡሮቹ ውኃ የማይወስዱበት ጣቢያዎች ደረቅ ጣቢያዎች ይባላሉ፡፡

ከመኪና መንገዱ ወርዶ የሰኞ ገበያ አለ፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ምእራፍ ስላለው እዚያ እንተርከዋለን፡፡ ለመቋጫ ያህል ወደ ሐረር በሚወስደው መንገድ ከከተማው በጣም ወጣ ብሎ የዲኝ ፋብሪካ እና መጀመርያ የካናዳ ግቢ የሚባል በኃላ የአውራ ጎዳና ካምፕ ይገኛሉ፡፡

ከአዋሽ አሰብ የአስፋልት ጎዳናን የሰራው ”ትራፕ” የሚባል የጀርመን ኩባንያ ነበር፡፡ በዚህን ግዜ ብዙ የአዋሽ ልጆች ተቀጥረው ሰርተዋል ሙያም ተምረውበታል፡፡ ጓደኛዬ የነበረው ሙሄ ብየዳን ያኔ ነበር የተማረው፡፡ መንገዱ ወደ አሰብ እየገፋ ከአዋሽ እየራቀ ሲሄድ እንኳን ሰራተኞቹ ቅዳሜ እና እሁድን አዋሽ ያሳልፉ ስለ ነበር ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት መነቃቃትን ፈጥሮ ነበር፡፡ ”የትራፕ ጊዜ” እየተባለ ሲወራ የጥጋብ ጊዜ እንደ ማለት ነበር፡፡

ትራፕ የአዋሽ-አሰብን አስፋልት መንገድ ካስመረቀ በኃላ አዋሽ ሸዋና ሐረርን ብቻ ሳይሆን መሐል አገርንና አሰብንም የምታገናኝ ከተማ ሆና ስልታዊነቷ ጨመረ

የልጅነታችን አዋሽ ብዙ ትዝታዎች አሏት ከነዚህ አንዱ አልፎ አልፎ የሚመጡት የሙዚቃና ልዩልዩ ትርዒት አድራጊዎች (ሰርከስ) ናቸው፡፡ በጣም ልጅ ሆኜ ትዝ የሚለኝ የወባ ማጥፊያ ድርጅት የሚያስመጣቸው ፊልሞች ነበሩ፡፡ አሁን ካለው ከኛ ቡና ቤት ጎን ከቢርካው በታች ኳስ የምንጫወትበት ሜዳ ነበር፡፡ እዚያ ላይ አቡጀዲድ ጨርቅ ይወጠርና ፊልሙ እዚያ ላይ ይታያል፡፡ ፊልሙን ብቻ ሳይሆን ከፕሮጀክቱ ፊልሙ እየተጠቀለለ ሲሄድ እናይ ነበር፡፡ ስለ ወባ ትንኝ አመጣጥና አረባብ ያሳያሉ ስለ መድሀኒቱም በተለይም ስለ ዲዲቲ ጥቅም በፊልም አስደግፈው ያሳያሉ፡፡ እግረ መንገዳቸውንም የዲዲቲ ፋብሪካውንና አሰራሩን ለማሳየት ሲሉ አሜሪካንና ፋብሪካው ያለበትን ከተማ ስለሚያሳዩ አፋችንን ከፍተን ነበር የምናየው፡፡ ከድሬ ዳዋም ሆነ ከአዲስ አበባ የተለቁ ከተሞች እንዳሉ የተረዳነው ከነዚህ የወባ ማጥፊያ ፊልሞች ነበር፡፡

በደረታቸው ድንጋይ የሚያስፈልጡ፤ በጊዜው በሳቅ ጦሽ የሚያደርጉ ሲራካዊ (ኮሜዲ) ትያትሮች የሚያሳዩ እንዲሁም ዘፈን የሚያቀርቡ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ጠርሙስ የሚበላው በየነ ይፍጠር መጥቶ ትርዒቱን አሳይቶናል፡፡ ቀን ማስታወቂያው በሰው አፍ እየተጮኸ ይነገራል፡፡ ማታ በሁለት ሰአት አካባቢ በፖሊስ ጣቢያው አንድ ክፍል (በኃላ ሲግናል ሆኖ የሬድዮ መልዕክት የሚተላለፍበት) ላይ ያሳያሉ፡፡ ክፍሉ በማዘጋጃ ቤቱ ትይዩ በርም ግንብም የለውም ስለዚህ ትርኢቱን ፊት ለፊት መከታተል ይቻላል፡፡ ወደ በኃላ ሙዚቀኞች ሲመጡ እትዬ አበበች ግቢ ፤በጣም ወደ በኃላ ደሞ መተባበር ቡና ቤት ያሳዩ ነበር፡፡ አያሌው መስፍን መተባበር ነበር ያሳየው፡፡  የመላኩ አሻግሬ ቡድን ሌላው ትርዒት አቅራቢ ነበር፡፡

ከነዚህ ትርኢቶች እስካሁን ትዝ የሚለኝ አንድ ቡድን የሰራው ሽወዳ ነበር፡፡ ቡድኑ ሁለት ሰዎችን ብቻ የያዘ ነው፡፡ አንደኛው ይዘፍናል አንደኛው ሀርሞኒካ ይጫወታል፡፡ ቀን መጥተው ማስታወቂያ አስነገሩ፡፡ ዋናው ቡድን ከአሰቦት እንደተነሳና በሰማንያ (ማታ ማታ በሳምንት እሑድና ሐሙስ የሚመጣ የመንገደኛ ፉርጎ ያለው የጭነት ባቡር) እንደሚገባ ለፈፉ፡፡ በ 12 ሰአት ሰማንያ ስትገባ ግን የተባለው ቡድን ሽታውም አልነበረም

”አዪ እንግዲህ ባቡሩ አልምጧቸው ነው’ንጂ ትናንት’ኮ አሰቦት አብረን ሰርተን እኛን ቅደሙ ብለው እነሱ ሊከተሉ ተስማምተን ነበር የመጣነው” አሉ፡፡ ብዙዎቻችን በየፉርጎው እየገባን ፈለግናቸው የሉም

”ቢሆንም ታድያ እኛ ሁለታችንም ብንሆን ጥሩ ትርዒት እናቀርብላችኃለን፤ቅሬታ አይግባችሁ” 

ብለው አንዱ ሀርሞኒካ እየነፋ አንዱ እየዘፈነ ሲያዝናኑን አመሹ፡፡ በኃላ ጎርምሰን ስናስበው ግን መጀመርያውኑ ቡድን የሚባል ነገርም እንዳልነበራቸውና ሺልንጋችንን እንደሸወዱን ገባን፡፡

ሺልንጌን!

አዋሽ ባቡር ጣቢያ የሚቆሙ ብዙ ፍርጎዎች ነበሩ፡፡ ኦተራይ ከመምጣቷ በፊት የነበሩ የመንገደኛ ፉርጎዎች ሲቆሙ ውስጡ ገብተን መጫወት ያስደስተን ነበር፡፡ የለገሀር ልጆች ድብብቆሽ ስንጫወት በፉርጎዎች መሀልና ውስጥ በመሸሸግ ነበር፡፡

Post Views: 388
Showing 1 of 1
culture leisure lifestyle picks Senksar tech ስንክሳር
Share. Facebook Twitter Pinterest LinkedIn Tumblr WhatsApp Email
Previous Articleስዩም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንኳን ደስ አለዎ!
Next Article C’est Passè    ሴ ፓሴ (ሁሉም አለፈ)
Taye Mohammed
  • Website

Related Posts

የሒንዱኢዝም እግረኛ ወታደሮች

February 28, 2025

በዘመነ ዶናልድ ትራምፕ

February 28, 2025

C’est Passé     ሁሉም አለፈ

February 28, 2025

የ አይ ቲ አጭር ታሪክ

February 28, 2025
Leave A Reply Cancel Reply

የእኛ ምርጫዎች

የሒንዱኢዝም እግረኛ ወታደሮች

February 28, 2025

በዘመነ ዶናልድ ትራምፕ

February 28, 2025

C’est Passé     ሁሉም አለፈ

February 28, 2025

የ አይ ቲ አጭር ታሪክ

February 28, 2025
እንዳያመልጥዎ
ባህል እና ስነ-ጥበብ
By Taye MohammedFebruary 28, 2025

የሒንዱኢዝም እግረኛ ወታደሮች

By Taye MohammedFebruary 28, 20250

ሕንድን የተመለከተው መጣጥፍ በቁም ነበር ከመጀመሩ በፊት በ 2001 ሕንድን ስጎበኝ ለአንድ ቀን ፣ባረፍንበት የአግራ…

በዘመነ ዶናልድ ትራምፕ

February 28, 2025

C’est Passé     ሁሉም አለፈ

February 28, 2025

የ አይ ቲ አጭር ታሪክ

February 28, 2025

የመፅሔታችን ደንበኛ ለመሆን ይመዝገቡ

አለም-አቀፍ ግንኙነቶች፣ባህልና ስነ- ጥበብ፣ታሪክ፣አሰሳ፣ከመጽሐፍት ሰፈር፣ ሳይንስ፣ እና አካባቢ ጥበቃን የሚመለከቱ መጣጥፎች ይቀርቡባታል፡፡

ስንክሳር መፅሔት
ስንክሳር መፅሔት

የስንክሳር በይነ መረብ ወርሀዊ መጽሄት የጠቅላላ ዕውቀት መንሸራሸሪያ መጽሄት ስትሆን
በውስጧም አለም አቀፍ ግንኙነቶች፣ባህልና ስነጥበብ፣ ታሪክ፣አሰሳ ፣ ከመጽሐፍት ሰፈር፣
ሳይንስ፣ እና አካባቢ ጥበቃን የሚመለከቱ መጣጥፎች ይቀርቡባታል፡፡
እንኳን በደህና ወደ ስክንሳር መጽሀሄት በይነ መረብ መጣችሁ!!
አድራሻ: ቤልጅየም ኮርትሪክ

ኢሜል : itaye4755@gmail.com

የቅርብ ግዜ ፅሁፍ

የሒንዱኢዝም እግረኛ ወታደሮች

February 28, 2025

በዘመነ ዶናልድ ትራምፕ

February 28, 2025

C’est Passé     ሁሉም አለፈ

February 28, 2025
የአንባብያን አስተያየቶች
    Facebook X (Twitter) Instagram Pinterest YouTube Telegram
    • ውሎች እና ሁኔታዎች
    • የግላዊነት ፖሊሲ
    • አካውንት
    © 2025 Senksar. Designed by Tatu Digitally Success.

    Type above and press Enter to search. Press Esc to cancel.