ግሪጎርያን የዘመን አቆጣጠር የሚባለው የአቆጣጠር ስያሜ ዘይቤውን በወሰኑት ጳጳስ በአቡን ግሪጎሪ ስምንተኛ ስም የተሰየመ ነው፡፡ የግሪጎርያን ዘመን አቆጣጠር በጸኃይ ቀን አቆጣጠር ላይ የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአለም በስፋት የሚሰራበት ነው፡፡ ጃንዋሪ የአዲስ አመት መግቢያ የሆነው የሮማውያንን ‘’የጅማሮ አምላክ’’ (ጎድ ኦፍ ቢግኒንግስ) ጃኑስ ለመዘከር፣ በዚያው ስም በሚጠራው የአዲስ አመት መግቢያ ወር እንዲሆን በ 1582 በያኔው የሮማ ጳጳስ ግሪጎሪ ስምንተኛ ውሳኔ ነው፡፡ይህም ማለት ጃንዋሪ የአመቱ መጀመረያ ወር ከሆነ፣ ጃንዋሪ አንድ የግድ የአመቱ መጀመርያ ቀን ይሆናል፡፡ በኃላ ግን በመካከለኛ ዘመን ክርስትያኖች የአመቱን መጀመርያ ቀን ሀይማኖታዊ ይዘት ባለው ቀን ለመቀየር ሙከራዎች ተደርገው ነበር፡፡
ሆኖም በሂደት ብዙ ሀገራት ይህን የዘመን አቆጣጠር መከተል ጀመሩ፡፡
የተለያዩት የጣልያን ግዛቶች፣ ስፔይን፣ ፖርቱጋል፣ እና የሮማን ካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑ የጀርመን ግዛቶች የግሪጎርያን ዘመን አቆጣጠርን በመጀመርያ ረድፍ የተከተሉ አገራት ናቸው፡፡ ቀጥሎም
- የፕሮቴስታንት ክርስትና ተከታይ የጀርመን ግዛቶች በ 1699፣
- ታላቋ ብሪታንያ እና ቅኝ ተገዢዎቿ በ 1752፣
- ስዊድን በ 1753፣
- ጃፓን በ 1873፣
- ቻይና በ 1912፣
- የሶቭየት ሕብረት በ 1918
- ግሪክ ደሞ በ 1923 ይህንኑ ዘመን አቆጠቆጣጠር አጽድቀዋል፡፡
(Written and fact-checked by the editors of Encycopedia Britanica Last Updated: Dec 19, 2024 • Article History)
በአንድ በኩል ስናየው ይህ የዘመን አቆጣጠር በአንድ ወይም በሌላ በኩል የገዢ መደቦች የዘመን አቆጣጠር ስለሆነ ይመስላል አንዳንድ ሀገሮች ዘውዳዊውን ስርዐት አፍርሰው በሌላ ሲተኩ፣ ከተቀረው የዘውዳዊ ስርዐት አካላት ጋር አብረው የዘመን አቆጣጠሩንም ወደ ግሪጎሪሳዊ ለውጠውታል፡፡ እንግዲህ እንዲህ ሲሆን የለውጡ ምክንያት ኃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በዚህም መሰረት ጃፓን የዘመን አቆጣጠሯን ወደ ግሪጎሪሳዊ የለወጠችው ከ 1868ቱ የፖለቲካ አብዮት በኃላ በ1873 ሲሆን፣ በተመሳሳይም ቻይና ለውጡን ያደረገችው የዘውድ ስርዐትን በረፓብሊክ ከተካች በኃላ በ1912 ላይ ነው፡፡ በሶቭየት ዩኒየን ቢሆን አገሪቱ የዘመን አቆጣጠሯን ከጁልያን ወደ ግሪጎሪሳዊ የለወጠችው የ 1917ቱን የሶሻሊስት አብዮት ተከትሎ በ 1918 ነው፡፡ ወደ አፍሪካ ስንመጣም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል ማለት በ 1991 ዘመን አቆጣጠሯንም ፈረንጅኛ አድርጋለች፡፡
የእስላም ሀገራት ቢሆኑ በአብዛኛው በምዕራባውያን ቅኝነት እንደመቆየታቸው የዘመን አቆጣጠራቸውን፣ ለስራ ሲሆን ግሪጎሪሳዊ ሲያደርጉት ከሐይማኖት አግባብነት ባላቸው ጉዳዮች ግን በጨረቃ ላይ የተመሰረተውን እስላማዊ ዘመን አቆጣጠር ይከተላሉ፡፡ (op.cit)
በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የግሪጎሪሳዊው የዘመን አቆጣጠር ከ ጁሊያን አቆጣጠር የተወሰደ እና እሱንም የተካ ነው፡፡ የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር ከፊል የጨረቃ/ጸኃይን ቀን አቆጣጠር የተከተለ ነው፡፡ ይህ አቆጣጠር በሮማው ንጉስ ጁልየስ ቄሳር የቀደመውን የሮማን ሬፐብሊካዊ አቆጣጠር በመተካት የተሰራ ነው፡፡ ጥቂት ስለ ጁልያን የዘመን አቆጣጠር
‘’በ 40ዎቹ አመተ-ፍዳ (bce) የሮማን ሲቪል የዘመን አቆጣጠር ከጸኃይ አቆጣጠር በ ሶስት ወር የቀደመ ነበር፡፡ የዘመኑ የሮማ ገዢ ጁልየስ ቄሳር በእስክድርያው የስነ-ፈለክ ሊቅ ሲሲጀነስ የተሰጠውን ምክር በመከተል የጸኃይ አቆጣጠር የሚከተለውን የግብጻውያንን ዘመን አቆጣጠር ተቀብሎ
በስራ ላይ አዋለው፡፡ ይህ አቆጣጠር የጸኃይን 3651/4 ቀን ይቀበላል፡፡ በዚህም መሰረት ወራቶቹ 30 እና 31 ቀን ይኖራቸውና ፌብርዋሪ በአራት አመት አንዴ 28 በተቀሩት 29 ቀን ይኖረዋል፡፡ ሆኖም የጁልየስ ቄሳር ዘመን አቆጣጠር ፌብርዋሪ 23 ሁለት ጊዜ ይውልና ፌብርዋሪ 29 የሚባል ቀን አይኖረውም፡፡’’ ይህ አቆጣጠር በዚህ አይነት ያልተስተካከለ ባህርይ ስላለው ከረዢም ጊዜ በኃላ በ 1582 በግሪጎሪሳዊው የዘመን አቆጣጠር ተተካ፡፡ ወደ ነሐሴ መጨረሻ ስንቃረብ ስለ እኛው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሊቃውንቱን አነጋግረን ሰፊ መጣጥፍ እናስነብባችኃለን፡፡ እስከዚያው …. እንደ ጥንት እስራኤላውያን በአለሙ ሀገራት በሙሉ ተበታትናችሁ ለከተማችሁት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰንክሳር የበይነ መረብ መጽሄት እንኳን ለፈረንጆቹ አዲስ አመት በሰላም አደረሳችሁ!! ትላለች