ትንሿ ሜትሮፖሊታን – አዋሽ 7 ኪሎ
ክፍል ሁለት
የሸዋና ሐረር መገናኛ ኪዳነ ምህረት አበበች ባቡ ቡና ቤት
ሲመሰረት በዚህ ረዢም ስም የሚጠራው ቡና ቤት፣ ዛሬ ቤቱን የሚያስተዳድሩት የቆርቋሪዋ ልጆች አሳጥረውት ‘’አበበች ባቡ መታሰቢያ ቡና ቤት’’ ይባላል፡፡ ስለ ቅድመ ኢሕአዴግ አዋሽ ስንተርክ ዘለን የማናልፋቸው የዚህ ንግድ ቤት ባለቤት እና መስራች እትዬ አበበች ባቡን ነው፡፡ እትዬ አበበች የአዋሽ ሰፈር አድባር ነበሩ፡፡ ዘለግ ያለ ቁመት ሙሉ ሞንዳላ ሰውነት አላቸው፡፡ መልካቸው ቀይ ሆኖ ጉንጫቸው ሞላ ያለ በመጠኑ ሰልከክ ያለ አፍንጫ ትንንሽ የተስተካከሉ ነጫጭ ጥርሶች ያላቸው መልከ መልካም ወይዘሮ ነበሩ – እትዬ አበበች፡፡
ከጠላት በኃላ አዋሽ በአከባቢዋ ላሉ አርብቶ አደርና አርሶ አደር የንግድና የስራ መስህብ ነበራት፡፡ በባቡሩ ምክንያት ንግዱ የደራ ነው፤ የወረዳ ርዕሰ ከተማ እንደመሆኗ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የሚመጣው ሰው ትንሽ አይደለም፡፡ ስለዚህም ከአፋሮች፤ ከአርጎቦች እና ከአረቦች በተጨማሪ ምንጃሬዎች (እንደ ግራዝማች መካሻ እና እትዬ አበበች)፤ ጠራዎች (እንደ እናቴ ሙላት እንግዳወርቅ) የመሳሰሉት መጥተው የኖሩባት ሆናለች፡፡
በኛ እድሜ ከትንሽ ተነስተው በራሳቸው ልፋትና ጥረት ሐብታም ሆነው፣ ዘመዶቻቸውን ከተማ አምጥተው አስተምረው፤ ለበርካታ ሌሎች ሰዎችም የስራ እድል ፈጥረው ተከብረውና ተወደው ፣ኖረው ካለፉት መሀል እትዬ አበበች አንዷ ናቸውና እስቲ የምናቀውን ያህል ስለ እሳቸው እንተርክ፤ ‘’እግረ መንገዳችንንም ሌሎችን እናነሳ እንጥል ይሆናል’’፡፡
ትውልዳቸው ምንጃር ነው፤ ታድያ በወጣትነታቸው ቆንጆ እንደመሆናቸው አንዱ የባንዳ ሹምባሽ ጠልፎ ጋራ ሙለታ ይወስዳቸዋል፡፡ ጊዜው የጠላት ዘመን እንደመሆኑ የባንዳ አለቆች ባለጊዜ ናቸውና ነው ይህ የሆነው፡፡ ሆኖም የኢጣልያንና የባንዳው ጀግንነት በሴቶቹ ላይ እንጂ በሸፈቱት አርበኞች ላይ አልነበረም፡፡ በዚያን ዘመንም ገና በወጣትነቱ እምቢኝ አልገዛም ብሎ የሸፈተ የአጎታቸው ልጅ የሆነ አቶ አፍራሳ የሚባል ዘመድ ነበራቸውና ጋራ ሙለታ ወርዶ በጉልበት የተወሰዱትን ዘመዱን በጉልበት መልሶ ሀገራቸው አገባቸው፡፡
አበበች ባቡ ምንጃር ቢመለሱም በተጠለፉበት ወቅት ብዙ አይተው ብዙ ሰምተው ነበር፡፡ በመንገዳቸውም ስለ አዋሽ ከተማ ስለ ንግዱ ስለ ባቡሩ የሰሙት ሁሉ ማረካቸውና ልባቸው ሸፈተ፡፡ ሁለት እህቶቻቸውን ማለትም የነቲቸር በለጠን እናት ይናፍቁን እና ይደነቃል ባቡን ይዘው አዋሽ ገቡ እድላቸውን ሊሞክሩ
የአባዎች ሙዚቃ
…Movie stars
find the end of the rainbow
with a fortune to win
It is so different from the world I am living in…
እንደሚለው እትዬ አበበችም ከባላገር የተዳፈነ ኑሮ ብርሐንና ሀብት ፍለጋ አዋሽ ገቡ፡፡ የእህታቸው ልጅ ደሞም አንደኛ ደረጃ አስተማሪዬ የነበረው ቲቸር በለጠ አንደነገረኝ ራሴም ከሌሎች እንደ ሰበሰብኩት ታሪካቸው የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ከባለቤታቸው አንድ ወንድ ልጅ አላቸው ፡፡ በኃላ አዋሽ እንደገቡ አሁን መኖርያ ቤታቸው ባለበት ቦታ ላይ ያለች አንዲት አነስተኛ የጭቃ ቤት በሶስት ብር ተከራይተው የጠላ ንግድ ይከፍታሉ፡፡ እንደ ባለሙያነታቸው ጠላቸው ተወዳጅ ስለነበር ገበያቸው ቀላል አልነበረም፡፡ ገበያም ወጣ እያሉ ከአፋሮች ቅቤ እየገዙ በታኒካ ያስሞላሉ፡፡ ታኒካው በ 18 ብር ይሞላል፤ናዝሬት ይወሰድና ከ 30-35 ብር ይሸጣል፡፡ ትንሽ ጥሪት ሲቋጥሩ በአፈር ሰፈር ወደ ለገሀር መውጫው ላይ በኃላ አርጅተው ከሞቱት እማማ ጌጤ ከምንላቸው ሴትዮ ላይ ቦታ ይገዙና ቤት ሰርተው የጠጅ ንግድ ይጀምራሉ፡፡
ገበያው ሲደራ አንድ በአንድ ዘመዶቻቸውን ከምንጃር አዋሽ ያስመጣሉ፤መጀመርያ የመጡት አይናቸውን ያዝ ያደርጋቸው የነበሩትና በኃላም ጨርሶ የታወሩት እህታቸውን እና ልጆቻቸውን ረሱ እና በለጠ ግዛውን ነበር፡፡ ቲቸር በለጠ እትዬ አበበች አዋሽ እና ናዝሬት እስከ አስረኛ አስተምረውት ከዛም ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ተመርቆ የኛ ሁሉ አስተማሪ የነበረ ነው፡፡ የእንግሊዘኛውን Old Mcdonald had a farm የሚለውን መዝሙር
ወንድሜ እርሻ አለው
በጣም ጥሩ ነው
በዚያ እርሻ በሬ አለው
በጣም ጥሩ ነው
በዚያ እርሻ ላም አለው
በጣም ጥሩ ነው
እዚህ እምቧ እዚያ እምቧ የትም እምቧ እምቧ
ብሎ በመተርጎም አስተምሮናል፡፡ ስለ ጠንቋይ አባይነት የሚያስረዳ ቲያትር ደርሶ ከወረዳ አስተዳዳሪው ጋር ተጣልቶ ነበር፡፡ የሱ ወንድም ረሱ ፈጣንና ኮሚክ ነበር፤ ልጅ ሆኖ እንደ ላሊበላ እየዘመረ ገንዘብና እንጀራ ይሰበስብና ጓደኞቹን ያበላል፡፡ እንደ ደረሳዎች እየዞየረ አረቦቹን ያስቃቸው ነበር፡፡ አንዲት ደከም ያለች ሴት በርሚል ስትገፋ ካየ ተቀብሎ እየገፋ ቤቷ ያደርሳል፡፡ አርጎባ ሰፈር እናቶች እንጨት ሲፈልጡ ካየ መጥረቢያውን ነጥቆ ይፈልጣል፡፡ ብቻ በትልቅ በትንሹ የተወደደ ነበር፡፡ ሲሞትም ትልቅ ትንሹ፤ ክርስቲያን እስላሙ በነቂስ ወጥቶ ቀበረው፡፡
ቀጥሎ ከጋራሙለታ ጠለፋ አስጥለው ያወጧቸውን ጋሽ አፍራሳንና ሁለት ሴት ልጆቻቸውን ማለትም በየነች አፍራሳን እንዲሁም የኔ እኩያ እና አብሮ አደጌን የውብነሽ አፍራሳን… ከዛ አበራሽን…. ቀስ በቀስ ሌሎችንም እያመጡ እያስተማሩ ማሳደግ ቀጠሉ፡፡
ሂደቱን እትዬ አበበች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ከ ቢየሁሉ እና ምንጃር የመጡ ሁሉ አድርገውታል፤ ግን የእትዬ አበበች በቁጥር ያይላል፡፡ የጠጅ ንግዳቸውን በአንድ በኩል እያካሄዱ በሌላ በኩል ከመኖርያ ቤታቸው አካባቢ ከነ ሰቃፍ ዑመር ቦታ እየገዙ ሰፊ ቦታ በመያዝ በጊዜው አስር አልቤርጎ የነበረውን ቡና ቤታቸውን ከፈቱ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና በደርግም የመጀመርያ አምስት አመታት ገደማ ቡና ቤታቸው በአዋሽ ከነበሩት ባለደረጃ ቡናቤቶች በቀዳሚነት ከሚመደቡት ነበር፡፡
ታታሪነታቸው እና በሳል አእምሯቸው ንግዳቸው እንዲስፋፋ ሀብታቸው እንዲጨምር ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከምንጃር አዋሽ ገብተው እየነገዱ ሲከብሩ አድማሳቸውን እንደብዙዎቹ ዘመነተኞቻቸው (ኮንቶምፖራሪስ) በአዋሽ ሳይገድቡ አንድ ልጃቸውን ለትምህርት ናዝሬት ልከው፤ እዛም ቤት ሰርተው ሌላ ቡና ቤት ከፈቱ፡፡ ስለዚህ አሁን ይዞታቸው አዋሽ ብቻ ሳይሆን ናዝሬትም ሆነ፡፡
ከገጠር አውጥተው ከተማ ካገቧቸው መሀል ስለ የአክስታቸው ልጅ ጋሽ አፍራሳ ትንሽ እናውጋላቸው እስቲ!
ጋሽ አፍራሳ በጠላት ጊዜ ገና ሰውነታቸው እንኳ በደንብ ሳይጠነክር በአካባቢው የጎበዝ አለቃ ስር ሆነው ተዋግተዋል፤ እልኸኛ እና ጀግና ሰው ነበሩ፡፡ በኃላም ሁለት ወንድ ልጆቻቸው በሳቸው ወጥተው ኢሕአዴግ ምንጃር ሲገባ ከሕወኃት ወታደሮች ሲዋጉ ሞተዋል፡፡ ጋሽ አፍራሳም እንድሜያቸው ሲገፋ ልጃቸው የውብነሽ ጋ እየተጦሩ ሲኖሩ ቁርባን አስቆርባቸዋለች፡፡ ታድያ የቁርባኑ ለት ከቤተክርስቲያን መልስ የውብነሽ አባቷን
‘’እንግዲህ አባዬ ከአሁን ወዲያ ሰው ቢናገርህም እንደበፊቱ በእልህ እየተቆጣህ መልስ መስጠት መጣላት የለብህም’’ ትላቸዋለች
‘’ለምን ቢሉ?’’
‘’እንዴ! ቆርበሀላ!’’
‘’እንዲህ ነኝና አፍራሳ! ታድያ የቆረብኩ እንደሆነ መጫወቻ ልሆን በጭራሽ!’’
ሰውነታቸው ነው እንጂ የደከመ ወኔያቸው አልነበረም፡፡ ወንድ ልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ሴቷ የውብነሽም እንዲሁ አትንኩኝ ባይ ኩሩ እና ቀጥተኛ ባህርይ ያላት ሰው ናት፡፡ እንግዲህ ልጅ ሆነን ቄስ አስተማሪ ማለት እንደ ጌታ ነው፡፡ እንኳን ቄስ አስተማሪ የመንግስት ት/ቤት ግብረገብ መምህር የነበሩት የኔታ ጽጌ እንኳ ተማሪዎችን በጎቻቸውን ማታ ማታ በረታቸው እንዲያስገቡላቸው ያስደርጉ ነበር፡፡ ታድያ አንድ ቀን መምሬ ማሞ የሚያስተምሯቸውን ልጆች ግቢያቸውን ያስጠርጋሉ፡፡ ከሚጠርጉት መካከል የአበራሽ ልጆች (የእትዬ አበበች የአክስት ልጅ የነበረች እና ቡና ቤቱ ውስጥ የነበረ በቡታ ጋዝ የሚሰራ ማቀዝቀዣ ፈንድቶ የገደላት) ይታክቱ፤ጸኃይ ፤አገኘሁ እና ማሙሽ ግቢውን ከሚጠርጉት መካከል ናቸው፡፡ የውብነሽ በአጋጣሚ በዚያ በኩል ስታልፍ ይህን ታያለች፡፡
‘’ገንዘብ ከፍለን አይደለ እንዴ የሚያስተምሩልን ለምንድነው እንደ አሽከር የምታሰሯቸው?’’
ብላ በመቆጣት ልጆቹን መንጭቃ ቤት ወስዳቸዋለች፡፡ ካደገች በኃላ በባህርይዋ ቀጥተኝነትና በጸባዩዋ የቡና ቤቱ ጠቅላላ አዛዥ አደረጓት፡፡ በደርግ የመጀመርያ አመታት ምድረ ካድሬ ሀብት አለው የተባለውን ሁሉ በሚያጠቃበት ወቅት የአዋሽ ባለ ጊዜዎችም እትዬ አበበችን ለማጥቃት ዳር ዳር ማለት ጀመሩ፡፡ ምንም ነገር ቢያጡባቸው
‘’የጸረ አብዮተኛ ኢዲዩ መሳርያ ይደብቃሉ፤ ገንዘብም ይልካሉ’’
በሚል ሊያስሯቸው አስበው የውብነሽን ያስሩና በሀሰትም ቢሆን እንድትመሰክርባቸው ግርፍ ይፈጽሙባታል፡፡ እሷ ግን ወንዶቹ እንኳን ከምንችለው በላይ ተቋቁማ አንድም ነገር ሳትወሻክት ከእስር የወጣች ጀግና ናት፡፡ ብዙ ወንዶች እንኳን ወፌላላ ግርፍ በጥፊ ብቻ ስንት ነገር ሲዘላብዱ የውብነሽ ግን በቆራጥነት ሁሉንም ተቋቁማ አልፋዋለች፡፡
እትዬ አበበችም የውብነሽን ስለመውደዳቸው ወሰን አልነበረውም
‘’ፊናንስ ሰፈር ቡና ቤት ልክፈትልሽ?’’
ብለዋት ነበር፤ ከየውብነሽ ተክለ ሰውነት (ፐርሰናሊቲ) ጋር የሚሄድ ስራ ስላልነበር አልተቀበለችውም፡፡ ይሁንና የውብነሽ ስታገባ በአዋሽ በኛ ጊዜ ድል ያለ ሰርግ ደግሰው ነበር የዳሯት፡፡ ምናልባት የአቡበከር ሰርግ ካልሆነ በስተቀር የየውብነሽን ሰርግ የመሰለ በዚያን ግዜ አላየንም፡፡
ወደ በኃላ እትዬ አበበች እጅግ ደርጅተው አንድ የስራ ፒክ አፕ ፔዦ 404 ሌላ የመጓጓዣ ፔዦ 505 ገዝተው በምቾትና በድሎት ኖረው ጊዜያቸው ሲደርስ አርፈው አዋሽ ደብረሳሌም ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ቀብረናቸዋል፡፡
በእትዬ አበበች የተጠቀሙ ዘመዶቻቸው ብቻ አልነበሩም ከሰራተኞቻቸው ብዙዎቹን ኩለው ድረው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል፡፡ ብዙዎች በሳቸው መኪኖች እጆቻቸውን አፍታትተው መንጃ ፈቃድ አውጥተው ራሳቸውን ችለውበታል፡፡ ናዝሬት ባለው በልጃቸው (ጋሽ ደምሴ) ቤትም ብዙ የአዋሽ ልጆች አርፈው ተምረውበታል፡፡
እነዚህ እንግዲህ በቀጥታ እትዬ አበበች ቤት ኖረው ተምረውም ሆነ ሰርተው ራሳቸውን የቻሉ ከሰላሳ በላይ ይሆናሉ በሞት ከተለዩት ጥቂቶች በስተቀር፡፡ ከነዚህም ውጪ በሳቸው ስር ተቀጥረው ሰርተው ተድረው ቤተሰብ የመሰረቱ ጥቂት አይደሉም፡፡ይህን ሁሉ ሀብት ያፈሩትና የዘመድ አዝማድ ዋርካ ሆነው የዘለቁት እትዬ አበበች ምንም ትምህርት ሳይኖራቸው ነው የቄስ ትምህርት እንኳን አልነበራቸውም፡፡
ልክ አስራ ሁለት ሰአት ላይ ከመኖርያ ቤታቸው ተነስተው ድንክ ውሻቸውን አስከትለው ወደ ቡና ቤቱ ያመራሉ፡፡ እዛም ቡና ተፈልቶ እጣን ተጪሶ ሞቅ ሞቅ ብሎ ይጠብቃቸዋል፡፡ እስከ አንድ ሰዐት ወይም ከዚያ በላይ እዚያው ቡናው እየተጠጣ፣ ጨዋታ ደርቶ ሲጫወቱ፣ ትዕዛዝ ሲሰጡ፣ጥፋት ካዩ ሲገስጹ ይቆዩና ተነስተው ወደ መኖርያ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ መሀል ቡና ቤቱ በሰው ተመልቶ ይቆያል፡፡ እንዲሁ ግርማ ሞገሳቸው ብቻ የተለየ መስህብ ነበረው፡፡
ይህ ሲተረክ ቀላል ይመስላል ግን እትዬ አበበች የነበራቸው ግርማ፣ ተሰሚነትና ተወዳጅነት ዲካ/ወሰን አልነበረውም፡፡ እሳቸው ከሞቱ በኃላ ቡና ቤቱ ግርማ ሞገሱን አጥቶ አሁን በድሮ ጥላው ብቻ የቀረ ሆኗል፡፡
የአዋሽ አድባር
ግራዝማች ሰይድ አሊ አቡበከር መደበኛ ሹመት ሳይኖራቸው በአዋሽ ዋና የአገር ሽማግሌ እና በብዙ ጉዳዮች በተለይም ጸጥታን እና የከተማ ቦታ ምደባን በተመለከተ አዛዥ ናዛዥ የነበሩ የከተማው አድባር ነበሩ፡፡ በተለይ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን፡፡ ቤታቸው ቢሆን ባለ አንድ ፎቅ ሆኖ ከፎቁ ፊት ለፊት ባለው ሰፊ በረንዳ ወንበር አስመጥተው በመቀመጥ ይፋዊ ያልሆነ ችሎት ያስችሉ ነበር፡፡ የባለጉዳዩ ብዛት ወረዳ ገዢው ግቢ ካለው አያንስም ነበር፡፡ ባህላዊ ጉዳዮች ሁሉ የሚታዩት በግራዝማች ሰይድ አሊ ችሎት ነበር፡፡በደርግ ጊዜም ቢሆን ጸጥታውንና የከተማ ቦታን ትተን የመጋላው ሰው ሌላ ሌላ ችግሩን የሚፈታው በሳቸው ችሎት ነበር፡፡
ልክ እንደ ሰይድ ሰቃፍ ሁሉ ግራዝማችም ስማቸው አሊ አቡበከር ሲሆን ሰይድ የማዕረግ ስማቸው ነው፡፡ ጃንሆይ በጣሊያን ጊዜ ከራስ አበበ አረጋይ ስር ሆነው ያደረጉትን ተጋድሎ እና ባንዲራ ከተመለሰ በኃላም አዋሽ አካባቢ ባሉት በአፋሮች ጉዳይ አስተርጓሚ እና ጉዳይ ፈጻሚ በመሆን ያደረጉትን ግልጋሎት ከግምት በማስገባት ይመስላል የግራዝማችነት ማዕረግ ሰጧቸው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊው ማዕረግ ሰይድ እና አለማዊው ማዕረግ ግራዝማች አንድ ላይ ቀላቅለን ግራዝማች ሰይድ አሊ እንላቸዋለን፡፡
አባታቸው አቡበከር ዋና ነጋዴ ነበሩ ከአልዩ አምባ ወሎን ይዞ እስከ አሰብ ግመል፣ ቅቤ፣ ከብት ይሸጡ ይለውጡ ነበር፡፡ ሶስት ልጆች ነበሯቸው፡፡ አሊ፣ዘይን እና አይደሩስ የሚባሉ፡፡ አይደሩስ በመካከለኛው አዋሽ ዘመናዊ የጥጥ እርሻ ከነበራቸው አረቦች አንዱ ሲሆን አሁንም አይደሩስ ካምፕ በመባል የሚታወቅ ካምፕ አለ፡፡ ዘይን አቡበከር በአዋሽ ነዋሪ ነበር፡፡ ግራዝማች አፋርኛ በደንብ በመቻላቸው በአፋር ጉዳይ ለጃንሆይ ሳይቀር አስተርጓሚ የነበሩት፡፡
ትንሽ የሚገርመኝ ነገር ግን፤ዘይንና አይደሩስ የሚታወቁት በስማቸው ሲሆን ሰይድ አሊ ግን የሰይድነትን ማዕረግ እንዴት ህብረተሰቡ እንደሰጣቸው ነው፡፡
ሰይድ አሊ አጠር ብለው ወፈር ያሉ የቀይ ዳማ ባለ ክብ ፊት ናቸው፡፡ ሰልካካ አፍንጫ፤ ትንንሽ ግን ጠልቀው የሚያዩ ቡናማ አይኖች ነበሯቸው፡፡ ጥርሰ ፍንጭት ሲሆኑ ሲቀመጡ እግራቸውን በስልት አጣምረው ነው፡፡
ግራዝማች የናጠጡ ሀብታም ነበሩ፡፡ ፊናንስ ሰፈር የጉምሩክ ጽ/ቤትና የንግስት ቡና ቤት የሳቸው ቤት ነበር፤ ክራዩ ጥሩ ስለነበር በደርግ ጊዜ ሲወረስ በወር የመጨረሻውን ክፍያ (250) ይከፈላቸው ነበር፡፡ ከሲቲዬ መቃሂ ፊት ለፊት የነበረው ትልቁ በረታቸው ሌላው የገቢ ምንጭ ነበር፡፡ በግመል አንድ ብር በከብት ሺልንግ በፍየልና በበግ ስሙኒ ይከፈልበታል፡፡ ብሩ በሳምንት ተጠራቅሞ ሲመጣ በስልቻ ተሞልቶ ነበር፡፡ የአዋሽ የመጀመርያ ወፍጮ ቤትም የሳቸው ነበር፡፡ የአካባቢው አፋሮች እንደ ባላባት ስለሚያዩዋቸው በየጊዜው የሚያመጡላቸውን ስፍር ቁጥር የሌለው ቅቤ በታኒካ እያሸጉ ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባሉ፡፡ ከወረዳ አስተዳዳሪውም ሆነ ከማዘጋጃ ቤቱ ሹም ያልተናነሰ ስልጣን ስለነበራቸው ጉዳይ እያስፈጸሙ የሚያገኙት ገቢም ቀላል አልነበረም፡፡ ቦታ ተገዛ ተሸጠ ተለወጠ ማለት እሳቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ አገኙ ማለት ነው፡፡ ማንንም እስረኛ ማስፈታት ይችሉ ነበር፡፡
ግራዝማች ደግም ነበሩ የተቸገረ መጥቶ ካለቀሰ ባዶ እጁን አይመለስም ነበር፡፡ በጣም ታማኝም ስለነበሩ ደርግ ከገባ በኃላም ቢሆን ሳዑዲ እና አዲስ አበባ ያሉ የየመን ከበርቴዎች የዘካ ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው እንዲያከፋፍሉ የሚሰጡት ለሳቸው ነበር፡፡
በከተማው ችግርም ተካፋይ ናቸው፡፡ የሰብለወንጌል ት/ቤት የእረፍት ቀን እሑድና ሰኞ እንዲሆን ያስደረጉ እሳቸው ነበሩ፡፡ ተማሪዎች በገበያው ቀን ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ለራሳቸውም ገንዘብ እንዲያገኙ ተብሎ፡፡
የተጣሉ ሰዎች በተለይም አርጎባ አፋርና አረቦች ፍ/ቤት ከመሄድ ግራዝማች ችሎት ቀርበው መዳኘትን ይመርጣሉ፡፡
ባለቤታቸው እመት ሲቲ ቀደም ሲል የቃሲም አፎይኔ (ባለ ትልቅ አፍ) ባለቤት ነበሩ፡፡ ግራዝማች ስለወደዷቸው ጠልፈው ነበር ያገቧቸው፡፡ ሴትዮዋ ሾተላይ ነበረባቸው፤ ከቃሲም ብዙ ግዜ አርግዘው ምጣቸው የሞት ያህል ነበር የሚያሰቃያቸው፡፡ ሲወለድም የሞተ ይሆናል ወይም ይሞታል፡፡ ግራዝማች ግን ስለወደዷቸው ጠለፏቸው፡፡ ቃሲም ኃይለኛ ስለነበር ጠብ ያነሳል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ እሱ ግን
‘’ገላገለኝ አቦ! ባረገዘች ቁጥር ስቃዬን ነበር የማይ’’ ብሎ ነገሩን ተወው፡፡ ግራዝማች ያላቸውን ስልጣን አመዛዝኖም ይሆናል፡፡ እሜት ሲቲ ከግራዝማች አቡበከርን ብቻ ነው የወለዱት፡፡ እሱንም በደንብ ነበር ያሳደጉት፡፡ በጊዜው ማትሪክን በጥሶ አለማያ ኮሌጅ የገባ ብቸኛ የአዋሽ ልጅ ነበር፡፡
ሰይድ አሊ አንድ አጭር መትየስ ነበራቸው (ከፊሻሌ ሽጉጣቸው ሌላ)፡፡ በደርግ ጊዜ ካድሬዎች መጥተው በወሬ የሰሙትን ጠየቋቸው
‘’መትረየስ አለዎት አሉ፤ያስረክቡን?’’ ብለው ይጠይቋቸዋል፡፡
‘’አዎን አለኝ ሰሜን ሸዋ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር በሽፍትነት ዘመኔ ከጣልያን የማረክሁት ነው፡፡ ጠላትን ነው የተዋጋሁበት፡፡ አሁንም እናንተ ለሀገር ጠላት መግደያ ከፈለጋችሁት ውሰዱት’’ አሏቸው፡፡ አመስግነው ተዉላቸው፡፡
የግራዝማች ችሎት
ቀደም ሲል ጠዋት ነበር ችሎት የሚቀመጡት፡፡ እንግዲህ ችሎት እንበለው እንጂ መደበኛ ችሎት አይደለም፡፡ ሁሌ ጠዋት ማዘጋጃ ይሄዳሉ፤ ጉዳይ ኖራቸውም አልኖራቸውም፡፡ ከዚያ ምንም ነገር ከሌለ ወደ አምስት ሰአት ቤት ሲመጡ ባለጉዳዮች ካሉ ፎቃቸው ላይ ይወጡና ያነጋግራሉ፡፡ ይህንን ነው ችሎት ያልነው፡፡ ብዙ ጉዳዮች ማህበራዊም፣ ህጋዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ይታያሉ በችሎቱ፡፡ ተበድያሁ የሚል በዳዩን ይከሳል፤ ግራዝማች ጉዳዩን ሰምተው አንዳንዴ እዚያው አንዳንዴ ሌላ ቀን ተመለስ ይሉና የሚመስሏቸውን አነጋግረው ጉዳዩን አጥንተው ይወስናሉ፡፡ የተጣላ ይታረቃል (አንዳንዴ ያልተጣላም ይጣላል)፤ የቸገረው ፈረንካ ይቸረዋል፤ በቢሮዎቹ ጉዳይ ያለበት መታያ ይከፍላል፡፡ ከአንዱ ይቀበላሉ ለሌላው ይሰጣሉ፡፡ መቸም ከተቀበሉት የሚሰጡት ማነሱ እንዳለ ሆኖ፡፡
አፋሮች የከተማውን ሰው ሲገድሉ በማጣራቱ፣ ገዳዩን ፈር በማስያዙ፣ ጉዳዩን ከተቻለ በጉማ በማስጨረስ የግራዝማች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እንኳን ትተዋል ያኔ አፋሮች የከተማ ሰውን ባጋጣሚ ወጣ ብሎ ካገኙት ይገድሉና ሰልበው ይሰወራሉ፡፡ አላማቸው ሁለት ነው አንደኛ የከተማ ሰው ሁሉ ክርስቲያን ይመስላቸዋል ስለዚህም ካፊር መግደል ጀነት ያስገባል ብለው ያምናሉ፡፡ ሁለተኛ የሰለቡትን ሰው ብልት ወስደው በማሳየት እየፎከሩ ወንድነታቸውን(ጀግንነታቸውን) ያስመሰክራሉ፡፡
በዚህም የተነሳ ከከተማው ትንሽ ወጣ ከተባለ አደጋ ነበረው፤በተለይ እንጨት ለቃሚዎችና ድንጋይ አውጪዎች ከከተማው ውጪ ስለሚታትሩ ኢላማዎቻቸው ነበሩ፡፡ በከተማውም ቢሆን ከአራት ሰዓት በኃላ እንደ ሰዓት እላፊ አይነት ነገር ነበር፡፡ ከአገር ግዛት ግቢ ደወል ይደወላል ከዚያ በኃላ ለገሀር ካልሆነ በስተቀር ሌላው ከተማ እርጭ ይል ነበር፡፡ ወደ በኃላ ግን ይሄ እየተቀየረ ሄዷል፡፡
የከተማው የእሰላም ሰፈር ጉዳዮች (ፍጥምጥም፣ሰርግ፣ህመም፣ሞትና የመሳሰሉት) ይነሳሉ ይጣላሉ በችሎቱ፡፡ በርካታ አፋሮች ከዚህ ችሎት አይታጡም፡፡
ለማንኛውም ግን አፋሮች ከመንግስት መስሪያ ቤት የሚያገናኝ ጉዳይ ካላቸው ዋናው አስፈጻሚያቸው ግራዝማች ነበሩ፡፡
በኃላ በኃላ ደርግ መጥቶ ስልጣናቸው ሲቀንስ ችሎቱ ወደ ከሰዓት በኃላ ተቀየረ፡፡ ወደ 10፡30 ገደማ ላይ ከሐጂ ሙክታር ቤት ፊት ለፊት ካለው ትልቅ ዋርካ ስር ይሰየማሉ ግራዝማች ፡፡ እግራቸውን አነባብረው የሚቀመጧት ቄንጠኛ አቀማመጥ ነበራቸው፡፡ ከዚያ ሰዉ ቀስ በቀስ ይመጣል፤ ጨዋታው ይሞቃል፡፡ በጨዋታው መካከል አንዳንድ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ነገሮችም ይነሳሉ ይወሰናሉም፡፡ ለአማላጅነት ይጠየቃሉ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ምክራቸው ይጠየቃል፣በሌሎች ጉዳዮች ደሞ እርዳታቸውን፡፡
ባለቤታቸው እሜት ሲቲም የአረብና አርጎባ ሴቶች የበላይ ነበሩ፡፡ የአርጎባ እና የአረብ ሴቶች ገንዘብ ሲቸግራቸው እሳቸው ጋ መጥተው ወርቅ አስይዘው ገንዘብ ይበደራሉ፡፡ ገንዘቡ ከተመለሰ ወርቁም ይመለሳል ካለሆነ…
ሲሞቱ ለአንድ ልጃቸው አቡበከር ከአምስት ኪሎ በላይ ወርቅ አውርሰውታል፡፡ አቶ ከበደ ተክሌ እንደነገረኝ ከሆነ
‘’እኔ ራሴ በትልቅ የማስታጠቢያ ሳህን ሙሉ ወርቁን ሲያስረክቡት እማኝ ነበርኩ’’ ብሎኛል፡፡
እሜት ሲቲ ከናቴ ጋር በጣም ቅርበት ነበራቸው፤እናቴ ለእስላም ዓመት በአሎች ፍየል ገዝታ ትልክላቸዋለች እሳቸውም ለኛ ፋሲካ ሁለት ወይም ሶስት ዶሮች ከአስራሁለት እንቁላሎች ጋር ይልካሉ፡፡ ልጅ ሆኜ እናቴን ተከትዬ ቤታቸው እሄድ ነበር፡፡ ለረዢም ሰዓታት ባለማቋረጥ ይጫወታሉ፡፡ እናቴ ልትሄድ ስትል በር ድረስ ይሸኟትና እንደገና በሩ ላይ ሰፊ ወሬ ያወራሉ፡፡ ያኔ ታድያ እነሱ አውርተው እስኪጨርሱ መጠበቁ ያሰለቸኝ ነበር፡፡ አሁን ደሞ ያንን ሁሉ ሰዓት ምን ያወሩ እንደ ነበር ይገርመኛል፡፡
አንዴ መጋላ በላይ ወደ መስጊድ በሚወስደው ዘቅጡጣ በኩል ስሄድ እሳቸው በአግድመቱ ሙስባሀቸውን እየቆጠሩ ይሄዳሉ፡፡ አባይ ደሴ የምትባል አንዲት ወፍራም ደሀ ሴትዮ ነበረች እና አግኝታቸው
‘’የአቡበከር እናት ደህና ዋልሽ?’’
‘’አልሀምዱሉላሂ አንቺስ’’
‘’ደህና ነኝ፣ የምልሽ- ሙስባሂሺን በመንገድም አትተዩውም?
‘’አላህን እየለምኩ ነዋ!’’
‘’አንቺ ደሞ ምን አጣሽና ነው አላህን የምታስቸግሪው፤እንዴ? እናንተም ከለመናችሁ እኛን ድሆቹን እንዴት ይስማን? ለምን ትሻሚናለሽ?’’ አሏቸው
‘’አይ እኔስ ምንም አላጣሁ አልሀምድልላሂ እንዲያው ብቻ ሙላትን ቢያሰልምልኝ ብዬ ነው’’ ሲሏት ክው ብዬ ደነገጥሁ፡፡ በልጅነት አእምሮዬ ተረብሼ ነበርና እናቴን ነገሩን አስረድቻት እንድትጠነቀቅ ነግሬያት ነበር፡፡
እንግዲህ ያኔ እንዲህ ሙስሊምና ክርስትያን ተዋዶ ተፋቅሮ መኖር ይችል ነበር፡፡ ለሙስሊማን የወደዱት ሰው እንዲያገኝ የሚፈልጉት ትልቅ ነገር እስላምነትን ስለሆነ ነው ለእናቴ ያንን የተመኙላት፡፡
የአቡበከር እናትን ስናነሳ እሕትየው እሜት ሞሚናን ሳላነሳ ማለፍ ትልቅ ግድፈት ይሆናል፡፡ እሜት ሞሚና የሚታወቁት በትልቅ መቀመጫቸው ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም ሆነ በኃላ እንደ እሜት ሞሚና አይነት መቀመጫ አይቼ አላቅም፡፡ ትልቅነት ብቻ ሳይሆን በሚሄዱበት ጊዜ የራሱ ልዩ እንቅስቃሴ ነበረው፡፡ ሁለቱ መንታ መቀመጫዎቻቸው የየራሳቸው እንቅስቃሴ አላቸው፡፡ እዛው ያደግነው እንኳን እሜት ሞሚና ሲሄዱ የምንሰራውን ወይም መንገዳችንን አቁመን ለላንቲካ ነበር የምናያቸው፡፡ የማያቃቸውማ ሲሆን ገምቱት፡፡
ታድያ እሜት ሞሚና ብዙ ልጆች ቢኖሯቸውም እኔ በጣም የማስታውሰው አሊ አብዶን፤ ማለት ትንሽ ልጃቸውን ነበር፡፡ አንዴ ናዝሬት ይዟቸው አብረው ሲሄድ የናዝሪት ማቲዎች ከማርስ ድንገት ዱብ ያለ አረንጓዴ ፍጡር ያዩ ይመስል እናቱ ላይ ሲያፈጡ አሊ አብዶ
‘‘ምን አባትህ ይገትርሃል?ጢዝ አይተህ አታውቅም?’’
እያለ ከአላፊ አግዳሚው ጋር ሲጣላ ነበር አሉ፡፡ አንዴ ደሞ መጋላ በርሜል ላይ ተቀምጠን ወሬ ስንቆምር እትዬ አበበች ባቡ ባጠገባችን ያልፋሉ፡፡ እሳቸውም ራቅ እንዳሉ አንደኛው
‘‘ልጆች ከወ/ሮ አበበች እና ከሞሚና መቀመጫ የትኛው ይበልጣል?’’ ብሎ ሲጠይቅ አሊ አብዶ እዚያው ስለነበር ጠብ ይነሳል ብለን ደነገጥን፡፡ አሊ አብዶ ግን ትንሽ አሰብ አደረገና
‘‘ሊሻን አበበች ባቡ መዓ ፍሉስ አባለሃ፤ ላኪን ኡማ ሀቂ ኪዳ ጠፈጠፈሀ’’ ሲል ሁላችንም በሳቅ ፈረስን
‘‘አበበች ባቡን ከገንዘብ ጋር ነው የሰጣት፤ የኔን እናት ግን ዝም ብሎ ነው የጠፈጠፈባት’’
እንደማለት ነው፡፡ ብዙ ግዜ በትንሽ ነገር ከሰው የሚጣላው አሊ አብዶ ጓደኞቹ ስለ እናቱ ሲፈትሉበት የነበረው ትዕግስት ይገርመኝ ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ በርጫ ላይ ለመቃም እየተሰናዳን እያለ አንድ የአሊ አብዶ ጓደኛ ከመስጊድ ይመጣል፡፡ እንግዲህ እስላሞች ከመስገዳቸው በፊት ይተጣጠባሉ፡፡
‘‘ስሙ! ዛሬ መስጊድ ኡዱ ስናረግ የእሜት ሞሚናን ባል ብልት አየሁት ይሄን ያህላል’’ ብሎ የእጁን መዳፍ አሳይን፡፡ ቁጭ ብሎ ይከዝን የነበረው አሊ አብዶ ተወርውሮ አነቀው ስል ረጋ ብሎ
‘‘ይሄን አከለ (መዳፉን እያሳየ) ወላ ይህን (ክንዱን እያሳየ) የምትችለው ሞሚና አንተ ምን ፈደለህ?’’ ብሎ ነገሩን አለፈው እኛም ሳቅን፡፡
አዲስ አበባ እናቱን ይዞ የያኔ ሴይቸንቶዎችን ያስቆምና
‘’ሁለት ሰው መርካቶ’’
ሲል ስቀውበት ነበር የሚያልፉት፡፡ የኃላውን መቀመጫ ብቻቸውን ካላስያዛቸው ሌላ ሰው መቀመጥ ስለማይችል ነው፡፡
ግራዝማች ቀስ በቀስ እያመማቸውና እየደከሙ ሲመጡ የከተማው ዋና ዋና አረብ፤ አርጎባ እና አፋሮች ፎቃቸው ላይ ይፈረሽላቸውና ከቀኑ ስምንት ሰአት እስከ አስራ ሁለት ሰአት ሲያጫውቷው ይውላሉ፡፡ እንደዚያ ደክመው እንኳ ተወዳጅነታቸውና ተሰሚነታቸው አልቀነሰም ነበር፡፡