ጸኃይ
በ 2007 ድሬደዋ እያለሁ ለገሀር ከመኮንን ቡና ቤት አካባቢ በረንዳ ላይ የማይጠፋ አንድ ወፈፍ የሚያደርገው ወጣት ነበር፡፡ መልከ መልካም እና መለሎ የሆነውን ይህን ወጣት የማስታውሰው በአንድ ምክንያት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፊቱን ወደ ጸኃይ ቀና ያደርግና አይኑን በእጁ እንኳን ሳይሸፍን ትክ ብሎ ጸኃይቱን ያያል፡፡ ያውም እስከ ሶስት አራት ደቂቃ ድረስ፡፡ እንደምታውቁት የድሬ ጸኃይ ገና በጠዋቱ እንኳ ሀይለኛ ነች፡፡ ታድያ ይኼ ወጣት ምን አይነት ልዩ ኃይል ቢኖረው ነው ትኩር አድርጎ ጸኃይን ለማየት የቻለው?
ፈረንጅ አገር ቢሆን የሳይንስ እና ምርምር ተቋማቱ የዚህን ሰው አይኖች ልዩ ችሎታ ‘’አጃኢብ’’ እያሉ ባላሳለፉት፡፡
‘’ጸኃይ’’ የዚህ ወር የሳይንስ አምዳችን ትኩረት ነች፡፡ የኃይል እና የብርሀን ምንጭ፣ በአካባቢያችን ካሉት ዋና ዋና የፍጥረት አካላት ትልቋ፣ከጠቀሜታም አንጻር ጸኃይ ዋናዋ የተፈጥሮ አጋራችን ናት፡፡ መሬታችን ኃይሏን የምታገኘው ሙሉ በሙሉ ከጸኃይ ነው፡፡ ተክሎችና እጽዋት ለእድገታቸው ጸኃይ ወሳኙን ሚና ትጫወታለች ስለዚህ ነው አርሰን መብላት የምንችለው ፡፡ በዘመናችን ሳይንስ ጣራ ላይ በሚተከሉ ሰሀኖች አማካይነት የጸኃይ ኃይልን በመግራት ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት እያዋለ ነው፡፡ ጊዜን ማለትም ቀንና ሌሊትን እንዲሁም አመትን የምንቆጥረው አንዱም በጸኃይ ነው፡፡
ብቻ የጸኃይ ጠቀሜታ፣ ለምድራችንም ህልውና (በተለይም ለፍጥረታት) ወሳኝ አካል እንደመሆኗ ጸኃይን በደምብ ማወቅ ጠቃሚም አስፈላጊም ነው፡፡ እስቲ ጽሁፋችንን በቀላል ጥያቄ እንጀምር፣ ጸኃይ ምንድን ነች?
በዚህ መጣጥፍ የሰው ልጅ የጸኃይን ማንነት ለማወቅ ከጥንት እስካሁን ድረስ ያደረገውን ጥረት እንመለከታለን፡፡ ለዚህ ጽሁፍ ግብአት ብዙ ምንጮችን የተጠቀምን ቢሆነም፣ በዋናነት መነሻ ሀሳቡን እና አወቃቀሩን ያገኘው በ 1999 የቢቢሲ ቴሌቪዥን ካቀረበው ‘’The Planets’’ ከተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ በተጨማሪም ከናሳ ያገኘናቸውንም መረጃዎች ተጠቅመናል፡፡
መቼም ይህን ታሪክ አንድ የህዋ ሳይንስ ባለሙያ ቢተርከው እንደምን ባማረ፡፡ለአሁኑ ባለን የምንችለውን እናቀርባለን፡፡ የመስኩ ባለሙያዎች የምትሉትን ለመስማት፣ የምታቀርቡትን ለማተም ዝግጁ ነን፡፡
ባጭሩም ከዚህ በታች የምንተርክላችሁ ታሪክ ሰው ስለ ጸኃይ ለማወቅ ያደረገውን ጥረት፣ የጸኃይ ሀይል ወሰኑ እስከምን እንደሆነና፣ በተጨማሪም ጸኃይ በአጽናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) ውስጥ ያላትን ሚና መተንተን ይሆናል፡፡
ፕሮፌሰር ዲያጎ በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ላይ እንዳለው፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን ጸኃይን የሚመለከቷት እንደ አንድ ፀአዳ ፍጥረት ነበር፡፡ ምንም እንከን የሌለባት ዲስክ! ምንም እድፍ የሌለባት ፀአዳ (ፐርፌክት) ነገር፡፡ ሰማይ ፀአዳ ነው፣ ፀኃይ ደሞ በዚህ ፀአዳ ቀላይ ውስጥ ያለች የፀአዳ ፀአዳ፡፡ (BBC Documentary ; The Planets : 1999)
ደራሲና ጸኃፌ ተውኔት ከበደ ሚካዔል የቅኔ ውበት በተባለ መጽሀፋቸው ስለሙዚቃ ሲገጥሙ ከጸኃይ ፀአዳነት ጋር እያነጻጸሩ ነበር፣- ግጥሙ በደንብ ካስታወስኩት
ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ራስ
ከሾፐን ትካዜ ከያሬድ መንፈስ
ከሞዛርት ቅላጼ ከቤቶቨን ናላ
መዓዛ የሞላብሽ የብስጭት ቃና
ውቢቷ ድምጽ ሆይ ረቂቋ ሙዚቃ
ንጽኅት እንደ ጸኃይ ውብ እንደ ጨረቃ
ስለዚህም የሰው ልጅ በፈጣሪ ማመን ሲጀምር ‘’ጸኃይ’’ የመጀመርያዋ በፈጣሪነት የተመለከች አካል ሳትሆን አትቀርም፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው ‘’የጸኃይ አምላክ’’ በብዙ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ትልቅ ስፍራ የነበረው አምላክ ነበር፡፡ በግብጽ የጸኃይ አምላክ ‘’ራ’’፡፡ በጥንታዊ ግሪኮች ‘’ሂሊዮስ’’ እንዲሁ የተከበረ ነበር፡፡ በሀገራችንም ፍትሐ ነገሥት እንደተረከው፣ ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ንጉስ ሰለሞን ጋ ከርማ፣ ብሉይ ኪዳንን ተቀብላ ስትመለስ፣ ‘’እኔ ጸኃይን ሳይሆን፣ ጸኃይን የፈጠረውን አምላክ ነው የማምነው’’ ብላለች ይላል፡፡ ይህ ማለትም ከዚያ በፊት በሀገራችን ጸኃይ ትመለክ ነበር ማለት ነው፡፡
በሀገራችን ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው በቀጥታ ጸኃይ ወይንም ከጸኃይ ጋር የተያያዘ ስም ማውጣት ያዘወትራሉ፡፡ ጸኃይ፣ጸኃዬ፣ አለም ጸኃይ፣ ጸኃዩ…ወዘተረፈ
እንግዲህ ጸኃይ እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አምላክነቷ እየቀረ ቢመጣም ፀአዳ እንደሆነች መታመኑ ግን እንደቀጠለ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ታድያ አንድ የስነፈለክ አዋቂ ፍሎሬንስ ከተማ ላይ ይነሳና ቴሌስኮፕን ይሰራል፡፡ በዚህ አዲስ በፈጠረው ነገር ጸኃይን ሲመለከታት ነገር መጣ! ምንም እድፍ የሌለባት ተብላ ትታመን በነበረችው ጸኃያችን ላይ በርካታ ጥቋቁር ነቁጦች (ስፖትስ) ተመለከተ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ለካስ ጸኃይ ፀአዳ አይደለችም! ይኸው እድፎች አሉባት፣ እዚህም እዚያም፡፡
ይህ ግኝት እንግዲህ ለፍልስፍና ትልቅ አብዮት ነበር፣ እንዲሁም ለሳይንስ፡፡ ጋሌሊዪ በደንብ አትኩሮ ሲመለከት እነዚያ ጥቋቁር ነቁጦች በጸኃይ ምድር ላይ ሲንቀሳቀሱ ተመለከተ፣ በእርግም እየተሽከረከሩ ነው፡፡ ቀጥሎ በሚመጡት አመታት ሌሎች የጸኃይ ምስጢሮችም እንዲሁ እየተገለጡ መጡ፡፡ ይህ የጋሌሊዮ ጋሌሊይ ግኝት ስለጸኃይ ፍጥረት ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉትን ቀሰቀሰ፡፡ ይሁን እንጂ የስነፈለክ ጠበብቱ በጸኃይ ኃይለኛ ነጸብራቅ ምክንያት ብዙም ለማየት እና ለማወቅ አልቻሉም፡፡
ሆኖም ስለ ጸኃይ ጥያቄዎችን አላቆሙም፡፡ የጸኃይ ነቁጦች ምንድን ናቸው? ሌሎች ነገሮችስ ይኖሩ ይሆን? የጸኃይ ኃይል ምንጩ ምንድነው? ቀስ በቀስ ሳይንቲስቱ አንድ ነገር አስተዋሉ፡፡ በየአስር አመት በግርድፉ ስድስት ጊዜ፣ በአለም ላይ በተወሰነ ቦታ፣ጸኃይ በጨረቃ ትከለላለች፡፡ የጸኃይ ግርዶሽም ይሆናል፡፡ በዚህን ጊዜ የጸኃይ ነጸብራቅ ሳያስቸግር ጸኃይን በልዩ መነጽር መመልከት ይቻላል፡፡ ቢያንስ ዙርያዋን፡፡(ዝኒ ከማሁ)
ነገሩ እንዴት መሰላችሁ የጸኃይ ዙርያ የመሬትን አንድ መቶ ጊዜ ይተልቃል፡፡ ጨረቃ ደሞ ከምድርም ያነሰች፣ ማለት ዙርያ ስፋቷ የመሬትን አንድ አራተኛ ብቻ ነው የሚያክለው፡፡ ይህ ማለት የጨረቃ ዙርያ ስፋት ከጸኃይ አራት መቶ ጊዜ ያንሳል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ የሚገርም የተፈጥሮ ግጥምጥሞሽ ይከሰታል፡፡ ምንድነው እሱ? ከጨረቃ ጸኃይ ድረስ ያለው ርቀት ከምድር እስከ ጨረቃ ካለው ርቀት አራት መቶ ጊዜ ይረዝማል፡፡ ስለዚህም አንድ ላይ ስናያቸው ጨረቃ እና ጸኃይ ከሞላ ጎደል እኩል ዙርያ (ሰርከምፍራንስ) አላቸው፡፡ ስለዚህም ጨረቃ በምድርና በጸኃይ መካከል በምትሆንበት ገዜ፣ ለጥቂት ደቂቃዎች፣ በተወሰነ የአለም ክፍል፣ ጸኃይን ሙሉ በሙሉ መሸፈን ትችላለች፡፡(ዝኒ ከማሁ)
የጸኃይ ግርዶሽም ይሆናል!
ሙሉ የጸኃይ ግርዶሽ የጸኃይን ጠርዝ ማለት ኮሮናን እንድናይ ያስችለናል፡፡ሌላ ጊዜ የጸኃይ ጠርዝ (ኮሮና) በጸኃይ ነጸብራቅ እንዳይታይ ይሆን ነበር፡፡ ስለዚህም የስነፈለክ ሳይንቲስቶች ኮሮናውን ለማየት የጸኃይ ግርዶሽ አለ በተባለ ቦታ ሁሉ አህጉሮች እና ሀገራትን አቋርጠው ይሄዱ ነበር፡፡ በኮረና ተከባ ስትታይ ጸኃይ ጥቁር የእሳት ኳስ ትመስላለች፡፡ በኮረናው ውስጥ የሚነዱ ደመናዎች ይታያሉ፡፡ መቸም የሚታየው ነበልባል ስለሆነ እሳቱ ከጸኃይ ምድር ላይ የተነሳ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም ጸኃይ ንቁ /ተንቀሳቃሽ ማለትም አክቲቭ ነች፡፡
በጸኃይ ግርዶሽ ወቅት ምን እናያለን?
በዚህ ግዜ በዋናነት ጎልቶ የሚታየው ነገር ፕሮሚናንስ ይባላል፡፡ ፕሮሚናንስ ከጸኃይ ተነስቶ ወደ ላይ የሚጎን ቢጫ እና ቀይ ነገር ነው፡፡ በጸኃይ ግርዶሽ ወቅት የጸኃይ ዙርያ በትንሹ በሚምቦገቦግ እሳት መሰል ነገር የተከበበ ሲሆን፣ ፕሮሚናንስ ከዚህ ኮሮና ከሚባለው የጸኃይ ዙርያ ተስፈንጥሮ ወደ ላይ የሚጎን ቢጫ እና ቀይ ነገር ነው፡፡ ከታች ስዕሉ የበለጠ ይገልጸዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ይሁን እንጂ የጸኃይ ግርዶች በስንት ጊዜ አንዴ የሚገጥም እናም እጅግ በዛ ቢባል ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ የማይቆይ ክስተት ነው፡፡ ይህ ደሞ ለሳይንቲስቶቹ ጸኃይንም ሆነ ፕሮሚናንስን ለማጥናት የሚሰጠው እድል ውሱን ነው፡፡

ፕሮሚናንስ ይህ ነው፡፡ ከጸኃይ ተነስቶ ወደ ላይ የሚጎን ቢጫና ቀይ ነገር ከ ጌቲ ምስሎች
ጋሌሊዮ ጋሌሊይ ቴሌስኮፕን በፈለሰፈ በሁለት መቶ አመቱ ገደማ፣ አባ አንጄሎ ሳኪ የተባሉት የቫቲካን ዋና የስነፈለክ ሊቅ አንድ አዲስ ግኝት ለአለም አበረከቱ፡፡ ይህም ሰቴርዮስኮፒ የሚባል አዲስ የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ እንግዲህ ሰቴርዮስኮፒ ልዩ መሳርያ በመጠቀም በፎቶ፣ ፊልም ወይም ሌላ ምስል ላይ ለእያንዳንዱ አይን የተለያየ ምስል የማየት ኢምፕሬሽን መፍጠር ነው

ኦሪጅናል ስቴሪዮስኮፒክ ካርድ ይህን ይመስላል © The National Portrait Gallery, London
የአባ አንጄሎ ሳኪ ስቴሪዮስኮፒ የጸኃይን ብርሀን በተለያዩት ቀለሞቹ ይሰነጣጥቅና የአንዱን ክፍል (ሪጅን) ብቻ አጉልቶ ያሳያል፡፡ አሁን እንግዲህ ጸኃይን አለ ኮሮናዋ (ጠርዝ) ለማየት ተቻለ፡፡ ማለት የጸኃይ ነጸብራቅ የተቀረውን ጸኃይ አካል እንዳናይ አያደርገንም፡፡ ስለዚህም ስቴርዮስኮፒ የጸኃይን ገጽታ በሚገርም መልኩ ለማየት አስቻለ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
አሁን የጸኃይ ብርሀን ነጸብራቅ ስለማያስቸግረን ብዙ ነገር ማየት እንችላለን፡፡ የጸኃይን ጠርዝ ብቻ ሳይሆን ምድሩንም በደንብ ይታይ ጀመር፡፡ ስለዚህም ሳይንቲስቶች የጸኃይን ገላ ማየት ጀመሩ፡፡ የጋሊሌዮን ሰንሰፖትስ በቅርቡ በደንብ አዪዋቸው፡፡
የጸኃይ ገላ በሳይንቲስቶቹ ፊት ይፍለቀለቅ ጀመር፡፡ አሁን ፊት ለፊት የሚያዩዋቸውን ንጥረ ነገሮች (ኬሚካልስ) መመዝገብ ያዙ፡፡ በስፔክትረሙ የሚታዩት ጥቁር ቋሚ መስመሮች (ባንድስ) የሀይድሮጂን፣ ካልሲየም፣ እና ብረት መኖርን ያሳያሉ፡፡ እናም ወዲያው ምድር ላይ ጨርሶ የማያውቁትን ንጥረ ነገር አገኙ፡፡ ስሙንም በጸኃይ አምላክ ስም ሂሊዮስ አሉት፡፡ ሂሊየም፡፡ ትልቁ ግኝት የተመዘገበው ግን አባ ሳቺ ሰቴርዮቴስኮፓቸውን ወደ ከዋክብት አዙረው መመልከት ሲጀምሩ ነው፡፡ ወዲያው ፓተርኑ (ስርአተ ጥለት) ግልጽ ሆነላቸው፡፡ ንጥረ ነገሮቹ (ኬሚካልስ) ከ ጸኃይ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ! የአጥናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) ዋና እንቆቅልሽ ተፈታ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ጸኃያችን ኮከብ ነች !
ጸኃይ ቅርቧ ኮከብ ስትሆን፣ ከዋክብቱ ደሞ የሩቅ ጸኃዮች ናቸው፡፡ እንግዲህ ከዋክብት የአጽናፈ ሰማይ አይነተኛ አካል ናቸው፡፡ ልክ ሴሎች የሰውነታችን ዋና አካል እንደሆኑ፡፡ ስለዚህም ጸኃይን ማጥናት ማለት አንድ መደበኛ ኮከብን እንደማጥናት ነው፡፡ ይህ ደሞ የአጥናፈ ሰማይን ሁኔታ ለማጥናት ቀላሉ መንገድ ነው፡፡
የጸኃይ አይነተኛ ክፍሎች
የጸኃይ ምድር (ሰን ሰርፌስ)
ከመሬት የምናየው የጸኃይ ክፍል (እኛ የጸኃይ ገጽታ ወይንም ሰርፌስ የምንለው) ፎቶስፌር ይባላል፡፡ በእርግጥ ጸኃይ ገጽታ (ሰርፌስ) የላትም ምክንያቱም ጸኃይ የፕላዝማ ኳስ ስለሆነች፡፡ ይህ ክፍል ፎቶስፌር የተባለው ለኛ የሚታየን ብርሀን የሚገኝበት ስለሆነ ነው፡፡ ፎቶስፌርን እኛ ሰርፌስ እንበለው እንጂ ሳይንቲስቶች የከባቢ አየሩ የመጀርያ ንብርብር (ሌየር) ነው የሚሉት፡፡
ይህ ንብርብር ሁለት መቶ አምሳ ማይል ይደርሳል፣ሙቀቱ ደሞ እስከ አምስት ሺ አምስት መቶ ዲግሪ ሴንትግሬድ ነው፡፡ ይህ እንግዲሀ ከፍተኛ ሙቀት ሊመስለን ይችላል ከጸኃይ እንብርት ሙቀት ጋር ሲወዳደር ግን ቀዝቃዛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሙቀቱ እንደ አልማዝ እና ግራፋይት የመሰሉ የካርቦን ዘሮችን መስራት ይችላል፡፡ አብዛኛው የጸኃይ ብርሀን ከፎቶስፌር ተነስቶ ነው ወደ ሕዋ የሚጎነው፡፡ ቀጥሎ የምናገኘው የጸኃይን አትሞስፊር ሲሆን እዚህ ላይ ሰን ስፖትሰ፣ኮሮና፣ ሰን ፍሌየርስ፣ ፐሮሚናንስ፣ ኮሮናል ማስ ኢጀክሽን እና የመሳሰሉት ክስተቶች የሚታዩበት ነው፡፡ (NASA Science)

በጸኃይ ግርዶሽ ወቅት የሚታየው ኮሮና* Adobe Stock
አትሞስፊር
ኮሮና የጸኃይ አትሞስፊር ከፍተኛው ክፍል ነው፡፡ ከሚታየን የጸኃይ ገጽታ ብዙ ሺ ኪ/ሜትሮች ይነሳል፡፡ቀስ በቀስም ኮሮና ወደ ጸኃይ ነፋስነት ይቀየራል፡፡ ኮሮና በየጊዜው ቦታውን እና ቅርጹን ይቀያይራል፡፡ በጣም የሚገርመው የኮሮና ባህርይ ከጸኃይ ገጽታ የበለጠ ሙቀታማ መሆኑ ነው፡፡ (UCAR – center for science education: The hidden Corona, Suns atmpsphere)

ምስል ናሳ፡፡ሰንስፖቶቹ ጥቁር ነቁጥ ሆነው የሚታዩት ናቸው፡፡
ሰንስፖት በቢጫው የጸኃይ ገላ ላይ ጥቁር ጉድጓድ መስለው ይታያሉ፡፡ልክ ወደ ምስጢራዊ ክፍል እንደሚያሳይ መስኮት፡፡ ሰንሰፖቶች ጥቁር መስለው የሚታዩን ከአካባቢው ያነሰ ቅዝቃዜ ስላላቸው ነው፡፡ (ናሳ 16/08/2024)
ሰን ፍሌይርስ እነዚህ ደሞ በጸኃይ ላይ ኃይል (ኢነርጂ) በድንገት ሲፈነዳ የሚፈጠር ክስተት ነው፡፡ ይህም እንግዲህ በሰንስፖት አካባቢ በሚፈጠር የተቆላለፈ ማግኔቲክ ፊልድ (መግነጢሳዊ መስክ) ነው፡

ሰን ፍሌይርስ
ማግኔቶስፌር
እንግዲህ የጸኃይ ማግኔቶስፌር የጸኃይ መግነጢሳዊ መስክ ወይም ማግኔቲክ ፊልድ ሲሆን ይህም በመላው ስልተ ጸኃይ (ሶላር ሲስተም) ላይ የተንሰራፋ ነው፡፡ የጸኃይ መግነጢሳዊ መስክ በጸኃይ ነፋሳት ተሸካሚነት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በጸኃይ መግነጢሳዊ መስክ የሚፍለቀለቀው የህዋ ክፍል ሂሊዮስፌር ይባላል፡፡ (NASA Science (.gov)
የጸኃይ ባህርያት
የጸኃይ ገጽታ ትርምስ የበዛበት ቦታ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ የተመሉ (ኤሌክትሪካሊ ቻርጅድ) የሆኑ ጋዞች አሉት፡፡ እነሱም ሀይለኛ የማግኔቲክ ሀይል አካባቢን ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህም አካባቢዎች መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) ይባላሉ፡፡ የጸኃይ ጋዞች ዘወትር ተንቀሳቃሽ ናቸው፣ በዚህም የመግነጢሳዊ መስኩን እየሳቡ መልሰው ይለጥጡታል፡፡ ይህም ከፍተኛ እንቅስቃሴን በጸኃይ ገላ ላይ ይፈጥራሉ፡፡ የጸኃይ እንቅስቃሴ የሚባለው እንግዲህ ይህ ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ሆኖም ይህ እንቅስቃሴ ሁሌም ተመሳሳይ አይደለም፡፡ አንዳንዴ በጣም ይተራመሳል፡፡ አንዳንዴም ጸጥ ይላል፡፡ ይህ የእንቅስቃሴ ከፍታና ዝቅታ ደረጃ በደረጃ እየተለዋወጠ የጸኃይ ዑደቶችን ይፈጥራል፡፡ ይህ ተለዋዋጭ የጸኃይ ዑደት በግርድፉ በየ 11 አመቱ የሚመጣ ነው፡፡ በዚህም ጊዜ የጸኃይ እሳታማ አውሎ ነፋሶች ይበረታሉ፣ በምድር ላይም ተጽዕኖ ይኖራቸዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
በ 1973 ስካይላብ የተባለች የሶላር ላቦራቶሪ ወደ ጸኃይ ተላከች፡፡ ጊዜ ወስዳ ጸኃይን በደንብ ልታጠና፡፡ ለዘጠኝ ወራት ያህል የተለያዩ አስትሮኖቶች በተከታታይ ጥናት አካሄዱ፡፡ ጸኃይን በደንብ ለማየት የሚያግድ ከባቢ አየር በሌለበት የጸኃይ ጥናት የምር ተካሄደ፡፡ በዚህን ወቅትም አስትሮኖቶቹ ከ 160 000 በላይ የጸኃይ ምስሎችን አነሱ፡፡ በዚህም ብዙ ነገር አገኙ፡፡ ከነዚህም አንዱ የኮሮናል ማስ ኢጀክሽን ነው፡፡ ይህ ከሶላር ፍሌር እጅግ በበዛ መጠን ቅንጣቶች (ፓረቲክልሰ) ከጸኃይ ገላ ወደ ላይና ውጪ ሲፈነዱ ነው፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)

ኮሮናል ማስ ኢጀክሽን፣ የተቆጣች ጸኃይ ይህን ትመስላለች Space.com
እነዚህን አካባቢ አንቀጥቅጥ ፍንዳታዎች ምን ፈጠራቸው? የዚህ ጥያቄ መልስ መልሶ ወደ ሰንሰፖትስ ይወስደናል፡፡ በ ሀያኛው ክፍለዘመን መግቢያ ስፔከትሮስኮፒ ን የሚያግዝ አንድ ስፔክቶግራፍ የሚባል መሳርያ ተሰራ፡፡ ይህ መሳርያ የጸኃይን ብርሀን በኢነርጂ ኮምፖናንት ከፋፍሎ የሚያሳይ ነው፡፡ በነዚህ መሳርያዎች በመታገዝ በተደረገው ምርምር ሰንሰፖቶች የሚፈጠሩት በማግኔቲክ ዲስቶርቴሽን እንደሆነ ተደረሰበት፡፡ በዚህም ሰንስፖትስ አካባቢ የሚፈጠር ማግኔቲክ ዲስቶርቴሽን የጸኃይ ኃይለኛ አውሎ ነፋሶችን ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ሰቶርምስ (አውሎነፋሶች) በጸኃይ ገጽ ያለውን ፕላዝማ አፈንድተው ብዙ ሺ ኪ/ሜትሮች ወደ ሰማይ ካጎነኑት በኃላ ተመልሶ ወደ ሚንቀለቀለው የጸኃይ ምድር (ሰርፌስ) ላይ ያሳርፈዋል፡፡ ከነዚህም ተያይዞ የ ጸኃይ ማግኔቲክ ሰቶርም ይነሳል፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)
አነዚህ ከጸኃይ ንፋሶች በተገናኘ የሚነሱት ማግኔቲክ ስቶርምስ በይዘታቸው በኤሌክትሪክ የተመሉ ቅንጣቶች (ኤሌክትሪካሊ ቻርጅድ ፓርቲክልስ) ናቸው፡፡ እነሱም ከመሬት መግነጢሳዊ መስክ ጋር ሲገኛኙ የሰሜን ነፋሳትን ይፈጥራሉ፡፡ የመሬት መግነጢሳዊ መስክ ከጸኃይ የሚመጡ በኤሌክትሪክ የተመሉ ቅንጣቶችን የያዙ የጸኃይ ንፋሳትን ሲከላከል የሚኖረው ፍጭት ነው እንግዲህ አውሮራ ወይም የሰሜን ብርሀን የተባለውን ክስተት የሚፈጥረው፡፡ የሰሜን ብርሀን በዋልታዎች ላይ የመሬት መግነጢሳዊ መስክ መሬትን ከጸኃይ ነፋሳት ሲከላከል በሚኖረው ፍጭት የሚፈጠር የኅብረ ብርሀናት ዳንስ ነው፡፡ ለማየት እጅግ ስለሚያስደስት አገር ጎብኚዎች አውሮራ በሚበዛበት ወቅት (ሲዝን) ወደ ኖርዌይ ይጎርፋሉ፡፡

የአውሮራ ወይም የሰሜን ብርሀናት
የጥንት ሰዎች የሰሜን ብርሀናት እና እነሱም ሲታዩ የሚፈጠው ድምጽ፣የሟች ወታደሮች ነፍሳት በሰማይ ሲፋለሙ የሚፈጠር ነው ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ከብዙ ምርምር በኃላ ነው አውሮራዎች በጸኃይ ነፋሳት ሳቢያ የሚፈጠሩ ክስተቶች እንደሆኑ የተደረሰበት፡፡ ሆኖም ብዙ ሳይንቲስቶች ከጸኃይ የስበት ሀይል አምልጦ የሚፈተለክ ነገር መኖሩን ይጠራጠሩ ነበር፡፡ ሆኖም ዘግይቶ ይህ ሊሆን እንደሚችል ተደረሰበት፡፡
ናሳ በ 27 ኦገስት 1962 የማሪነር ሁለት የጠፈር መንኮራኩርን ወደ ጠፈር አመጠቀ፡፡ ማሪነር ሁለት ወደ ሌላ ፕላኔት የተላከች የመጀመርያዋ የጠፈር መንኮራኩር ነች፡፡ በተሳካው ተልዕኮዋ ከደረሰችባቸው ዋና ግኝቶች አንዱ፣ የጸኃይ ንፋስ ከጸኃይ አልፎ እንደሚበር ማረጋገጧ ነው፡፡ (NASA Jet Propulsion Laboratory (.gov) missions › mariner-2)
የጸኃይ እምብርት (ኮር)
የጸኃይ እምብርት ከጸኃይ አካላት ሁሉ እጅግ የሞቀው ክፍል ነው፣ ሙቀቱ እስከ 15 ሚሊዮን ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል፡፡ ወደ 138000 ኪ/ሜ ውፍረት አለው፡፡ይህ ሁሉ ሙቀት ሀይድሮጂን ወደ ሂሊየም የሚቀየርበት (fussed) ሲሆን፣ የጸኃይን ሀይል እና ሙቀት የሚፈጥረው ሂደት ይህ ነው፡፡ (NASA Science)
አንዳንድ ነጥቦች ስለ ጸኃይ
እኛ እዚህ ምድር ላይ ቀንና አመቱን የምንለካ ከጸኃይ አንጻር ነው፡፡ ምድራችን በራሷ ዛቢያ አንዴ ስትዞር አንድ ቀን ሆነ እንላለን፡፡ በጸኃይ ዙርያ አንዴ ተሸከርክራ ስትጨርስ ደሞ አንድ አመት፡፡
የጸኃይ ቀን እና አመትስ ምን ያህል ይሆን? ይህን ጥያቄ ልጅ ሆኜ ለቄስ አስተማሪዬ አባ ፍስሐ ባቀርብላቸው፣ አንዴ በመስቀላቸው ኮርኩመውኝ፣ አርፈህ አውደ ንባቡን ተወጣ ነበር የሚሉኝ፡፡
የጸኃይ አንድ ቀን ምን ያህል ርዝመት አለው የሚለውን ለማብራራት ትንሽ ይከብዳል፡፡ ጸኃይ የተሰራችው ፕላዝማ ከተባለ በኤሌክትሪክ በተሞላ ልዕለ ሞቃት ጋዝ ነው፡፡ ፕላዝማ ታድያ በተለያዩ የጸኃይ ክልሎች በተለያየ ፍጥነት ነው የሚሽከረከረው፡፡ ስለዚህ ጸኃይ በራሷ ዛቢያ ለመዞር፣ በመቀነቷ (ኢኩዌተር) ላይ ከሆነ 25 የመሬት ቀናት ይፈጅባታል፡፡ በዋልታዎቿ አካባቢ ከሆነ ደሞ ሰላሳ ስድስት ቀናት ይወስድባታል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ይቺ ቢጫ የብርሀን ኳስ፣ ይቺ ከኛ 150 ሚሊዮን ኪ/ሜ የምትርቀው ኮከባችን በዙርያዋ ስምንት ፕላኔቶች፣ ቢያንስ አምስት ሙት ፕላኔቶች (ድዋርፍ)፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አስትሮይዶች፣ እና ሶስት ትሪሊዮን ኮሜቶች እና በረዷማ አካላት ይሽከረከሯታል፡፡ በቅርብ የሚያዋስናት ባለ ሶስት ከዋክብት ስታር ሲስተሙ አልፋ ሳንታሪ ነው – ሶስቱ በዚህ የስታር ሲስተም የተጠቃለሉት የጸኃይ ጎረቤት ከዋክብቶች ደሞ
- ፕሮክሲማ ሳንታሪ የሚባለው 4.24 የብርሀን አመታት የሚርቃት ሙት ኮከብ እና
- አልፋ ሳንታሪ ኤ እና ቢ የሚባሉ ጸኃይን የሚመስሉ፣ እርስ በርስ የሚዟዟሩ በ 4.37 የብርሀን አመት የሚርቋት ኮከቦች ናቸው፡፡ ፡፡
ከላይ እንደነገርናችሁ ጸኃይ ዙርያዋን እየተሽከረከሩ የሚያጅቧት እጅግ ብዙ የስልተ-ጸኃይ አካላት እንዳሏት ሁሉ እሷም ይህን ሁሉ አጀብ አስከትላ የሚልኪ ዌይን ጋላክሲ ማዕከል ትዞራለች፡፡(ዝኒ ከማሁ)
አየንልሽ አየንልሽ
ይኸው ብቻ ነው ወይ አጀብሽ?
እያልን በሰርግ ጊዜ እንደምንዘፍነው ሳይሆን ጸኃይ አጀቧ ብዙ ነው፡፡
እንግዲህ ጸኃያችን የምትሽከረከረው በሰዐት ሰባት መቶ ሀያ ሺ ኪ/ሜ ቢሆንም፣ አንድ ሙሉ ሽክርክሪት ለማረግ ሁለት መቶ ሰላሳ ሚሊዮን አመታት ይፈጅባታል፡፡ ስለዚህ አንድ ቀን በጸኃይ የኛ 25 ወይም 36 አመት ሲሆን፣ የጸኃይ አንድ አመት ደግሞ የኛ ሁለት መቶ ሰላሳ ሚሊዮን አመት ነው፡፡
የጸኃይ ተጠቃሽ ባህርያት
በሁለት ዲሰምበር 1972 የአውሮፓው የህዋ ድርጅት እና ናሳ በመተባበር ሶሆ የሚባል የጠፈር መንኮራኩር ጸኃይን እንዲያጠና ወደ ጠፈር አመጠቁ፡፡ የሚገርመው ነገር የዚህ መንከኮራኩረ መሳርያዎች የጸኃይን ገጽታ መመልከት ብቻ ሳይሆን የጸኃይን እምብርት መስማት የሚችሉ ነበሩ፡፡ የጸኃይን እምብርት ዘልቀህ መመልከት አይቻልም፡፡ ነገር ግን መስማት ተቻለ፡፡ በእምብርቱ ውስጥ የሚገኙ ድምጾችን በመስማት የጸኃይን ውስጣዊ መዋቅር መረዳት ይቻላል፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)
በዚህ መንኮራኩር አማካይነት እንደታወቀው፣ የጸኃይ ገጽ እና እምብርቱም ይተነፍሳሉ (heaving)፣ በየስድስት ስኮንዱ ጠቅላላ የጸኃይ (ስታር) አካል ወደ ውስጥ እና ወደ ውጭ ይተነፍሳል፡፡ የእምብርቱ ጋዝማ ውቅያኖሶች በጥልቀት ወደ ውስጥ ይተነፍሳሉ በዚህም የተወሳሰቡ ትናንሽ ሞገዶች (ሪፕልስ) በገጽታው የተረማመሳሉ፡፡ እንዚህም የውስጡን መዋቅር ፍንጭ ይሰጡናል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
እንደማንኛውም ኮከብ ሁሉ፣ የጸኃይ እምብርት (ኮር) የንጥረ ነገሮች (ኬሚካልስ) ሁሉ ፋብሪካ ነው ህይወትንም ጨምሮ፡፡ ማለት ከሌላውም በተጨማሪ ለህይወት መሰረታዊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ሁሉ የሚፈበረኩት በጸኃይ እምብርት ነው፡፡ የጸኃይን (የኮከብን) መሰረታዊ ፊዚክስ ማወቅ መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በ ኮከቦች የሚኖረው ፊዚክስ ከፕላኔቶች ፊዚክስ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
አሁን ሶሆ የጸኃይን የላይኛው ክፍልን ማጥናት ጀምራለች፡፡ አዲስ የጸኃይ ገጽታ ክስተትንም አውቀናል፡፡ ከሶላር ፍሌር በኃላ ሺ ኪ/ሜትሮችን የሚሸፍን የመንቀጥቀጥ ክስተት ይፈጠራል፡፡ የነዚህን መንቀጥቀጥ ድምጾች ስለ ጸኃይ የውጭ ገጽታ ብዙ መማር እንችላለን፡፡ አሁን በተመሳሳይ ከድምጾቹ ተነስተን ውስጣዊውን የጸኃይ ሁኔታ ለማጥናት ይቻላል፡፡
ሁሉም ኮከብ ማለት ይቻላል እምብርት (ኮር) አለው፡፡ በእምብርቱም ኑክሌር ኢነርጂን ይፈጥራል፣ በዚህ ሂደትም አንድን ማቴርያል ወደ ሌላ ይለውጣል (ትራንሚዩቲንግ ኤለመንትስ)፡፡ በዚህም ሂደት የአጽናፈ ሰማይ ዋልታ እና ማገር የሆኑትን ከባባድ ኤለመንቶችን ይገነባሉ፡፡ ቀደም ብለን እንዳልነው የኮከብ ፊዚክስ እና የመሬት ተመሳሳይ ነው፡፡ የኮከብን መዋቅር በደንብ አወቅን ማለት የአጽናፈ ሰማይን መዋቅር እንዲሁ ተረዳን ማለት ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ጸሀያችን እንዴት ተፈጠረች?
በመጀመርያ በአጽናፈ ሰማይ የተከማቹት ንጥረ ነገሮች (ኤለመንትስ) ሀይድሮጂን እና ሂሊየም ብቻ ነበሩ ፡፡ በአስራ ሁለት ቢሊዮን አመታት ከዋክብት እነዚህን ንጥረ ነገሮች ወደ ተለቁ፣ የተራቀቁ ንጥረ ነገሮች ቀየሯቸው፡፡ የኛም ጸኃይ ከዚህ ሂደት የተገኘች ናት፡፡ የዛሬ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን አመት በፊት በጋላክሲያችን ጠርዞች ላይ የነበረ እጅግ ትልቅ ኮከብ (በሱፐር ኖቪ) መኖሩ አብቅቶ ተበተነ፡፡
የዚህ ግዙፍ ኮከብ ፍንዳታ በእምብርቱ የነበሩትን ንጥረ ነገሮች ወደ አካባቢው ጠፈር በተናቸው፡፡ እንዚሀ ልዕለ ሞቃት (ሱፐር ሂትድ) ሲሊከን፣ ብረትና ሌሎችም በአካባቢው በነበረው አፈርና ጋዝ ላይ ጭነቱን ስላበዙት ስብስቡ ጭነቱን መሸከም አቃተው፣ እነዚህ ከባባድ ንጥረ ነገሮች ወደ ማዕከሉ ተስበው ትልቅ የክሚካል ሪአክሽን አስነሱ፡፡ ፍንዳታም ሆነ፡፡ ጸኃያችን ከዚህ ፍንዳታ (ኬሚካል ሪአክሽን) ተስፈንጥራ ህያው ሆነች፣ ተፈጠረች፡፡ ከፍንዳታው የተረፈው ማቴርያልም በአክሬሽን ሂደት ፕላኔቶችን ፈጠረ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ቅዱስ መጽሀፍ ‘’ኦ አዳም! መሬት አንተ፡፡ ውሰጠ መሬት ትገብዕ’’ እንዲል፡፡ እኛ የኮከብ አፈር ነን ፡፡ ላለፉት አራት መቶ አመታት ሳይንስ የጸኃይን ዙርያ ሽፋኖች እየገላለጠ ኮከብን አገኘ፡፡ ይህ ፕላኔቶችን ያበጀው የስነፍጥረት ካልኩለስ ሞተር እኛንም ፈጠረን፡፡ አያት ቅምአያቶቻችን ጸዐዳ የሆነች የብርሀን ዲስክ አዩ፡፡ ሳይንስ ደሞ እነሱ ከሚገምቱት እጅግ ኃይለኛ የሆነ ኢንቲቲን ገለጸልን፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)
ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን
ምንጭ
BBC Documentary, THE PLANETS, 1999
NASA Science (.gov) Our Sun: Facts – NASA Science)
NASA 16/08/2024
NASA Jet Propulsion Laboratory (.gov) missions › mariner-2
© The National Portrait Gallery, London
UCAR – center for science education: The hidden Corona, Suns atmpsphere