ይህ መጣጥፍ ስለ የመረጃ ቴክኖሎጂን (INFORMATION TECHNOLOGY) (IT)ምንነት፣ እድገት እና አሁን ያለበትን ደረጃ ከአንድ ጸኃፊ አረዳድ አንጻር ለማስቀመጥ የሚሞክር ጥረት ነው፡፡ ታዋቂው እስራኤላዊ የታሪክ ምሁር ዩቫል ኖሕ ሐራሪ 2024 ኔክሰስ በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ይህ ጸኃፊ ቀደም ሲል ሳፒያን በተኘውና በአለም አካባቢ በዘጠኝ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ከ45 ሚሊዮን በላይ ቅጂ የተሸጠው መጽኃፍ ደራሲ ነው፡፡ ለአንድ ኢ-ልብወለድ መጽኃፍ ይህን ያህል አንባቢ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም፡፡
መጽኃፉን በማንበብ ላይ እያለሁ እና አንብቤም ከጨረስኩ በኃላ ፍሬ ሀሳቡን በምጥን ይዘት በአማርኛ ለማቅረብ እየሞከርኩ ነበር፡፡ ወደ በኃላ ግን ሳስበው ይህ ከሚሆን ራሱ ደራሲው የጻፈውን አሳጥሮ እና ቀለል አድርጎ በአማርኛ ማቅረቡ የተሻለ ስለመሰለኝ ይህንኑ አደረግሁ፡፡ በብዛት እንኳ የተለመደው እንደዚህ አይነት እጅግ ጠቃሚ የሆነ መጽኃፍ ሲወጣ ለመጽኄት እንዲሆን በጣም አጠር አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን አንባቢዎች ግን ከዚህ ይልቅ የራስ መግቢያና አስተያየት ተጨምሮበት ዋና ዋና ይዘቶችን ብቻ ማቅረቡ …
አንደኛ በአጠቃላይ የማንበብ በተለይ ደሞ ኢ-ልቦለዳዊ መጻህፍትን የማንበብ ልምድ ባልዳበረበረት
ሁለተኛ በይነ-መረብ (ኢንተርኔት) እና ማህበረሰባዊ መገናኛ ብዙሀን የህዝቡን ቀልብ በያዘበት ሁኔታ
መጣጥፉ አጥሮ፣ቀለል ብሎና አዝናኝ በሆኑ ሰዋዊ ወይም ግላዊ ትርክት (anecdot) ተቀናብሮ መቅረቡ ተነባቢነቱን ይጨምረዋል በሚል እምነትና ተስፋ በዚህ መልኩ ቀርቧል፡፡ ይህም ሲሆን በመጣጥፉ ያሉት የዋና ዋና ጽንሰ ሀሳቦች ትርጉም በቀጥታ የሀራሪ (ደራሲው) መሆናቸው ይሰመርበት፡፡

ዩቫል ኖህ ሀራሪ
ክፍል አንድ
ምዕራፍ አንድ
በአንድ ኢ-ልቦለዳዊ ጽሁፍ ከሁሉም በፊት የጽሁፉን ዋና ዋና ጽንሰ ሐሳቦችን ትርጉም ማስቀመጡ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህም ሀራሪ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) የሚለውን ቃል በመጽሀፉ የተጠቀመበት በምን እሳቤ ነው?
መረጃ የአመለካከት ጉዳይ ነው፣ይላል ሀራሪ፡፡ ቀጠል ያደርግናም በቀጥታ መረጃ ማለት ይህ ነው ከማለት ይልቅ እንደ መረጃ ማንነት የተወሰዱ ግን መረጃ ያልሆኑ ሀሳቦችን ይዘረዝራል፡፡ለምሳሌም መረጃ የኅላዌ ወይም የዕውነታ ነጸብራቅ ስለሆነ ዕውነታ (ትሩዝ) ነው የሚለውን ሀሳብ እንደማይቀበል ያስቀምጣል፡፡
በደራሲው እምነት ማንኛውም ነገር ለምሳሌ ኮከብ፣መጋረጃ፣ ወይም ወፍ በትክክለኛው አውድ ከተገኙ መረጃዎች ናቸው፡፡
የበዙት መረጃዎች ምንም ነገርን አይወክሉም፡፡ ስለዚህ ዕውነትንም አይወክሉም፡፡ በመሰረቱ እውነት የሚባለው የአንድ ዕውነታ ከፊል ገጽታን እንድናተኩርበት ሌላውን ደሞ የምንዘነጋበት አካሄድ ነው፡፡ ያ ከፊል ገጽታ ነው እውነታ፡፡
እዚህ ላይ የራሴን ልምድ ብጨምር፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ለጋስ ሰው ነው ስንል ያ ሰው ሁልግዜ ለሁሉም ሰው ለጋስ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሰውየው ብዙውን ግዜ ለብዙ ሰዎች ለጋስ ሲሆን አንዳንድ ግዜ ለአንዳንድ ሰዎች ንፉግ ነው፡፡ ግን ካጠቃላይ ሰውነቱ የጎላውን ገጽታ እንደ ሙሉ ባህርይ እንወስድና እከሌ ደግ ነው ብለን እንደመድማለን፡፡
ይህ ለግለሰብም፣ለኅብረተሰብም፣ለክስተቶችም ይሰራል፡፡ ለምሳሌ አይሁዶች ገብጋባ ናቸው ሲባል እሰማለሁ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዳንድ ቀልዶች ይነገራሉ፡፡ አንድ በጣም ቸር የሆነች ጀርመናዊ ታማ ብዙ ደም ያስፈልጋታል፡፡ ነገሩን የሰማው ጎረቤቷ አይሁዳዊ አንድ መቶ ማርክ ከከፈለችው የሚያስፈልጋትን ደም ሊሰጣት ቃል ይገባላታል፡፡ በዚያም መሰረት ሴትየዋ ደም ካገኘች በኃላ ድና ቤቷ በገባች በነጋታው አይሁዱ መቶ ማርኩን እንድትሰጠው ይጠይቃታል፡፡ ያች እንኳን ለራሷ ለሌላውም ቸር የነበረች ሴትዮ ምክንያት እየፈጠረች ታመላልሰው ጀመር፡፡
አይሁዱም ነገሩ ስለጠነከረበት እሱንም ሴትየዋንም የሚያውቁ ሽማግሌዎችን ‘‘መቶ ማርኬን ከለከለችኝ’’ ብሎ ቢያማክር አንዱ፣
‘’ሴትየዋ ንፉግ አይደለችም፣ እንዴት ከለከለችህ? ለመሆኑ መቶ ማርኩን መቼ ነው ያበደርካት?’ ብሎ ይጠይዋል፡፡ የአይሁድ ነገር ትናንት አበድሮ ዛሬ ውለጂ ብሏት እንደሆነ በመገመት፡፡
‘’አበድሬያት አይደለም ታማ ደም አስፈልጓት በነፍሷ ደርሼ ደሜን ነጥቻት ነው፡፡ በምትኩ መቶ ማርክ ልትሰጠኝ ተስማምታ ነበር፡፡ መቸም ታሞ የተነሳ እግዚአብሔርን ረሳ አይደል የሚባለው ይኸው አሁን ነገ ተነገወዲያ እያለች ከለከለችኝ’’ አለ አይሁዱ፡፡
‘‘አዪ በዚህ ጉዳይ እንኳ አንገባም፡፡ አሁንኮ እሷ ያላት የአይሁድ ደም ነው፡፡ እንዴት ብላ ነው መቶ ማርክ ባንዴ ላጥ አርጋ የምትሰጥህ፡፡ ይሄን ቀደም ብለህ ደምህን ስትሰጣት መገመት ነበረብህ’’
ብለው አሰናበቱት፡፡
እዚህ ላይ ምናልባት ብዙ አይሁዶች ብዙውን ግዜ ገንዘብ ከማውጣታቸው በፊት የበዛ ጥንቃቄ ያደርጉ ይሆናል፡፡ ይህን ከፊል እውነታ ሙሉ አድርጎ ሁሉንም አይሁድ አባሀና ማድረጉ እውነታን በትክክል መወከል አይሆንም፡፡
አንግዲህ ሀራሪ የሚለው ምንድነው መረጃ የተለያዩ ነገሮችን አንድ ላይ በመቋጠር አንድ አዲስ እውነታን ይፈጥራል፡፡ አንድ ወንድ ና ሴትን አጣምሮ ትዳርን ከአንድ በላይ የሆኑ የተለያዩ ነገዶችን አያይዞ ሀገርን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህም ዋና ባህርዩ የተለያዩ አካላትን (entity) አገናኝቶ አንድ መረብ (network) ያቆማል፡፡ ስለዚህ ዋና ባህርዩ ማያያዝ (connection) እንጂ ውከላ (representation) አይደለም፡፡ መረጃ ነገሮችን መመስረት ነው ወይም ነገሮችን በአንድ መልክ እንዲመሰረቱ ማድረግ፡፡
ለምሳሌ ኮከብ ቆጠራ ፍቅረኞችን ይወክላቸዋል በሚላቸው ከዋክብት መሰረት በፍቅር ያዋህዷቸዋል፡፡ ፕሮፓጋንዳ የተለያዩ ሰዎችን በአንድ ፓርቲ ያደራጃቸዋል፣ የማርሽ ሙዚቃ የወታደሮችን ሰልፍ ይመሰርታል፡፡
ስለዚህም መረጃ የተለያዩ ነገሮችን አያይዞ አዲስ በይነ-መረብ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ሂደት መረጃ ሰዎችን በእውነት ላይ በተመረሰተ ክስተት ሊያገናኝ ይችላል፡፡ በዚህም እውነትን ወከለ ማለት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በኦገስት 1969 ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቴሌቪዥን ፊት ለፊት ተቀምጠው ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ሳይ ሲራመድ ተመልክተዋል፡፡ የዛ ትርዒት ይዘት እውነታ ነበር፡፡
በሌላ በኩል ግን የዘረመል መረጃ (ጄኔቲክስ ኢንፎርሽን) በተፈጥሮ ሂደት እልፍ አዕላፍ ሴሎችን ሲየቀናጅ ወይም የሙዚቃ ኖታ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲያስደንስ መረጃው እውነታን በትክክልም ሆነ በስህተትም አቀናጀ አንልም፣ አቀናጀ (connect) ብቻ እንጂ፡፡
እዚህ ላይ የተሳሳተ መረጃ (mis information) እና የተዛባ መረጃን መለየት ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ ኮከብ ቆጣሪዎች በከዋክብት ምልክት ሰጪነት አምነው ፍቅረኞችን ‘’ኮከባችሁ ግጥም ስለሆነ ብትጋቡ ጥሩ ነው’’ ሲሉ የተሳሳተ መረጃ ነው የሰጡት ግን አውቀው ፍቅረኞቹን ለማታለል ሲሆን የሁለቱ ሰዎች ኮከቦች ቢዋሃዱ ውጤታማ ናቸው ብለው ስላመኑ፣ በተሳሳተ እውቀት የተሰጠ መረጃ ስለሆነ የተዛባ መረጃ እንለዋለን፡፡
በሌላ በኩል አክራሪ ሁቱዎች በ ሬድዮ ቱትሲዎች የተረገሙ በረሮዎች ስለሆኑ ፍጇቸው በማለት ሲቀሰቅሱ በተሳሳተ መረጃ (disinformation) የዘር ፍጅት አስፈጽመዋል፡፡
መረጃ የተለያዩ ነጥቦችን በአንድ በይነመረብ (network) አያይዞ አዲስ እውነታን መፍጠር ነው፡፡
መረጃ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ
መረጃ አንዳንዴ እውነታን ቢያመለክትም ሌላ ጊዜ ደሞ ከዚህ በተቃራኒ እናገኘዋለን፡፡ ሁሌም ግን ያገናኛል ወይም ትስስር ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳ ያገኘነው መረጃ ምን ያህል እውነታን ይወክላል ብለን መጠየቁ አግባብ ቢሆንም፣ መረጃ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሚጫወተው ሚና ይበልጥ ግልጽ የሚሆንልን – እንዴት አድርጎ ሰውን ከሰው አገናኘ፣ በዚህ ሂደትስ ምን አይነት አዲስ የትስስር መረብ ፈጠረ? ብለን ስናጠናው ነው፡፡
ምክንያቱም የትስስር መረብ መፍጠር ወይም ማገናኘት የመረጃ ዋናው ባሕርይ ስለሆነ፡፡
ተመልከቱ እንግዲህ ብዙ መረጃ ባገኘን ቁጥር ይበልጥ ወደ እውነታ እየቀረብን እንመጣለን የሚለው የየዋሆች አስተያየት የተሳሳተ የሚሆነው ስለዚህ ነው፡፡ የመረጃ ብዛት ብቻውን እውነታን አያመለክትም፡፡ የናዚዎች የፕሮፓጋንዳ አለቃ ዮሴፍ ጎብልስ ‘‘አንድን ሐሰት ደጋግሞ በመናገር እውነት ማድረግ ይቻላል’’ የሚለው በመረጃ ብዛት የሌለ እውነታ መፍጠር እንደሚቻል ለማሳየት ነው፡፡
በኛ በሐበሾች ልምድ ብንሄድ
‘‘ይህን ነገር ከየት ሰማኸው?’’ ተብሎ ሲጠየቅ
‘‘እንዴ ! ይኸማ ሁሉም የሚያወራው እኮ ነው’’ የሚለው መልስ ሁል ግዜ ትክክል አይሆንም፡፡
ከድንጋይ ዳቦ ዘመን አንስቶ እስከዛሬው የመረጃ ቴክኖሎጂ ወቅት በርካታ በእውነታም ሆነ በጥበብ/ጥልቅነት ላይ ያልቆሙ ግንኙነቶችን እናገኛለን፡፡ የሰው ዘር አለምን ለመግዛት የበቃው መረጃዎችን ሁሉ ወደ እውነታ በመቀየሩ ሳይሆን ብዙ ሰዎችን አገናኝቶ እና አስተሳስሮ ችግሩን ለመፍታትም ሆነ ኑሮውን ለማሸነፍ ስለቻለ ነው፡፡
ግዙፍ እንስሳትን ለማደንም ሆነ በፋብሪካ ምርትን ለማግኘት የበርካታ ሰዎች ትብብር/ቅንጅት ወሳኝ ነው፡፡
የሰው ዘር ኑሮውን ለማሸነፍና አለምን ለመግዛት በመጀመርያ ስራ ላይ ያዋለው የመረጃ ቴክኖሎጂ መጠርያ ታሪክ/ተረት (story) ይባላል)፡፡ በምዕራፍ ሁለት ታሪክ/ተረትን በሰፊው እንመለከታለን፡፡
ምዕራፍ ሁለት
ትርክቶች፣ ገደብ የለሽ ግንኙነቶች ወይም ትስስሮች
Stories: Unlimited Conecctions
በዚህ መጣጥፍ ላይ ስቶሪ የሚለውን ቃል ታሪክ/ትውስት/ትርክት እያልን በማቀያየር እንጠቀምበታለን፡፡
የተለያዩ ቤተሰብ አባላትን ለማስተባበር ያስቻለው ዝግመታዊ ለውጥ የመጣው ሰዎች የመናገርና ቋንቋ ችሎታቸውን እያዳበሩ በመምጣቻው ነው፡፡ አደን ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን ትብብር የግድ ስለሚል ይህም ግዴታ ሰዎች የመናገር ክህሎታቸውን እያዳበሩ እንዲሄዱ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡
አንድ ቤተሰብ ብቻውን ለማደን ቢችል እንኳ ሁሌ ውጤታማ አይሆንም፡፡ በስንት ትብብርና ጥረት አውሬውን ቢገድል እንኳ፣ የገለደውን አውሬ ሊቀማው የሚመጣውን አንበሳም ሆነ ነብር ለመቋቋም መተባበርና ይህንንም ትብብር ለማሳለጥ በጎሣ መረብ (tribal network) ግንኙነቱን ማደራጀት ነበረበት፡፡
ይህ በሰዎችና-ሰዎች ያለ ግንኙነት ጥንካሬ እና ዘለቄታ እንዲኖረው ጎሣውን ሊያሰተባብር የሚያስችል ትርክቶች ቀስ በቀስ እየዳበሩ ሄዱ፡፡ የአያት ቅድመ-አያቶችን ገድል እና ከሌሎች ጎሣዎች ጋር በሚኖረው ትግል የፈጸሙትን ገድል በማስዋብ እና በማራቀቅ ትርክቶች ዋና የመረጃ ቴክኖሎጂ ሆነው ብቅ አሉ፡፡
ስለዚህም በሰዎችና-ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ሰዎችና-ትርክት ሰንሰለት አደገ፡፡ ወይንም (ሰው – ትርክት – ሰው)
ትርክቱ ለአደን የረዳቸው፣ወይም ከበሽታና መቅሰፍት የጠበቃቸው አምላክ/አማልክትን ማምለክን እየጨመረ ሄደ፡፡
በይነ-ነቢባዊ አካላት (inter-subjective entities) ወይም የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት
የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላትን ለማስረዳት ዩቫል ሀራሪ የሄደበት መንገድ ነገሮቹን በደንብ እንድረዳቸው ይጠቅመናል፡፡
እውነታ ሶስት አይነት ነው ይለናል ሀራሪ፡፡
የመጀመርያው ተጨባጭ እውነታ ነው (objective reality) ፡፡እነዚህ በእውን ያሉ ነገሮች ናቸው ለምሳሌ ድንጋይ፣ ወንዝ፣ ተራራ፡፡እኛ አሰብናቸውም አላሰብናቸውም አሉ -ይኖራሉ፡፡
ሁለተኛው ሕሊናዊ እውነታ (subjective reality) ነው፡፡ ስቃይ፣ደስታ፣ፍቅርን እንውሰድ፡፡ እነዚህ ጭንቅላታችን/ስሜታችን ውስጥ ያሉ እንጂ በተጨባጭ ያሉ ነገሮች አይደሉም፡፡ ካላሰብናቸው/ካልተሰሙን የሉም፡፡
ስሜቶች ደግሞ ቀስ በቀስ የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላትን ፈጠሩ፡፡
ሶስተኛ በይነ-ነቢባዊ አካላት (inter-subjective entities) ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት ሆነው ግን በአንድ ጊዜ በብዙ ሰው ጭንቅላት ውስጥ የሚገኙ፣ በሰዎች መካከል ያሉ ግንኙነት ክፋዮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሐይማኖት፣ ሕግ፣ እና ገንዘብን ብንወስድ በተጨባጭ ምድር ላይ ያሉ እውነታዎች አይደሉም፡፡
እንደ ፍቅር እና ጥላቻ በአንድ ሰው ውስጥ የሚፈጠሩ ስሜቶች ሆነው ስለሌላ ሰው ወይም ነገር የሚሰሙን ስሜቶች ናቸው፡፡ ካላሰብናቸው አይኖሩም፡፡ በይነ ነቢባዊ አካላት ግን የብዙ ሰዎች ግንኙነት የፈጠራቸው አካላት ስለሆኑ አሰብናቸው አላሰብናቸው አሉ ይኖራሉም፡፡ አንድ ግለሰብ ስለ ሀገሩ ህግ ምንም ላያውቅ፣ምንም ላይሰማው ይችላል፡፡ ግን አንድ ጥፋት ቢፈጽም ለምሳሌ ሰው ቢገድል፣ ሰው መግደል ህገወጥ እንደሆነና ከባድ ቅጣት እንደሚያስከትል አሰበም አላሰበም ህጉን ከመኖር እሱንም ከመቀጣት አያድነውም፡፡
የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት የሚፈጠሩት በመረጃ ልውውጥ ምክንያት ነው፡፡ በአንድ እንጀራ ውስጥ ያለውን የብረት ማእድን ይዘት በኛ አእምሮ ወይም እምነት ላይ አይወሰንም፡፡ ነገር ግን የእንጀራው ገንዘባዊ ተመን በሰዎች ግምትና እምነት ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ሰው ፍላጎትና ግምት ላይ ብቻ ጥገኛ ሳይሆን ገዢ እና ሻጮች በሚያደርጉት የመረጃ ልውውጥ (መግባባት እና ስምምነት) አማካኝት የሚወሰን ነው፡፡ ገዢና ሻጭ ካላመኑበት የእንጀራው ዋጋ አይጸናም፡፡
በሰው ልጅ ግንኙነት ውስጥ ትርክቶች (የመረጃ አይነት ነው) ሰው አለምን እንዲገዛ ኃይል ቢሆኑትም ግን እንደ ገራገሮች እይታ (Naïve viez) ሁልግዜም ጥልቀት ያላቸው ጥበቦች ግን አይሆኑም፡፡
የገራገሮች እይታ መረጃ ወደ እውነት ሲወስደን እውነት ደሞ ሰዎችን ኃይልና ዕውቀትን/ጥበብን ያጎናጽፋቸዋል ብሎ ያምናል፡፡
እውቀት ያላቸው ሁሉ ኃይል የላቸውም፣ ኃይልን የተጎናጸፉ ሁሉም ጠቢቦች አይደሉም፡፡ ሁለቱ የሚገጥሙት በጣም አልፎ አልፎ ነው፡፡
ለምሳሌ ፊዚክስን ጠንቅቆ የሚያውቀው ሮበርት ኦፐንሄይመር የመጀመሪያውን የአውቶሚክ ቦምብ ሰራ(አሰራ)፡፡እውቀቱ አለው፡፡ ቦምቡ የትና መቼ ጥቅም ላይ እንደሚውል የወሰነው ግን ፕሬዚዳንት ሩዝቤልት ነበር፡፡ መጀመርያውኑም ኦፐንሄይመር የሩዝቬልት ተቀጣሪ ሆኖ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ነው ቦንቡን የሰራው፡፡
በታሪክ ብዙ ግዜ የሚሆነው ይህ ነው፣ ኃይል ያለው እውቀት ያለውን ያዛል፡፡
ግን ለምን ይህ ይሆናል?
ምክንያቱም ኃይል የሚመነጨው እውነትን ከማወቅ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ያ በከፊል እውነታ ነው፡፡ ሌላው አስፈላጊ የኃይል ምንጭ ሰላምና መረጋጋትን (social order) በብዙ ሰዎች መካከል የመፍጠር ክህሎት ነው፡፡
በይነ ነቢባዊ አካላት እንግዲህ የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሕግ፣ ሐይማኖት፣ ልምድ እና የመሳሰሉት፡፡ የበለጠ ወደ ምድር እናውርዳቸው ካልን – የፍትሀ ብሔር ሕግ፣ ክርስቲያንነት፣ እስላምነት፣ የጋብቻ ግርግር፣ የቀብር ስነስርዐት…
እንግዲህ ነገሩ እንዴት ነው፣ ኃይል እውነትም (ማለት እውቀት) ስነስርዐትንም ትፈልጋለች፡፡ ሁለቱ ካልገጠሙ ኃይል አይኖርም፣ ወይም አጥፊ ኃይል ነው ሊኖር የሚችለው፡፡
ምንም እንኳ ኃይል በእውነትም በስነስርዐትም የሚገኝና የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም፣ ብዙውን ግዜ ሁሉን አሳማኝ ርእዮት አስፍነው እና ማህበረሰባዊ ስርዐት መፍጠር የሚችሉት ናቸው በእውቀት ለተካኑት፣ ስለዚህም ብዙ ነገር መፍጠር ለሚችሉት መመሪያ የሚሰጡት፡፡ ለዚህም ነበር ሮበርት ኦፐንሄየመር ለሩዝቬልት የሚታዘዘው፡፡
ወደቀደመው ምሳሌያችን ብንመለስ መሪዎች የሚያውቁት ግን ምሁራን/ሳይንቲስቶች የማይረዱት ምንድነው፣ ስለ ብዙ ነገሮች (ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ጂዖግራፊ) እውነትን (እውቀት) ማወቅ ማሕበረሰባዊ ሰላምና መረጋጋትን በብዙ ሚሊዮን ሰዎች መካከል ለማምጣት በቂ ነገር እንዳይደለ ነው፡፡
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከሰዐሊው አፈወርቅ ተክሌ ጋር ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቁበት የነበረ አንድ ጉዳይ ነበር፡፡ ልባርጉ እንግዲህ ያኔ በነበረው ስርአት አንድ የታወቀ ሰው የንጉሠ ነገሠቱን ግብር አክብሮ መጋበዝ አለበት፡፡ አፈወርቅ ተክሌ ግን ከጊዜ በኃላ ግብር መቅረት አመጣ፡፡ ተጠራና ንጉሠ ነገሥቱ ጋር ቀረበ-
‘‘ለምንድነው አሁን አሁን ግብር ላይ የማናይህ?’’
‘‘ጃንሆይ እግዜር ያሳይዎ፣ክርስቶስ ያመልክትዎ አጋፋሪዎቹ እኔን መጨረሻው ረድፍ አካባቢ ከተርታው ሰው ጋር ያስቀምጡና በእውቀት ከኔ በጣም ያነሱትን ደሞ ፊት ወንበር ስለሚሰጡ ነገሩ ትክክል ስላልመሰለኝ ነው’’
ይላቸዋል፣ ፈገግ ብለው
‘’በፊትም ያልንህ ይኸንኑ ነበርኮ! አንድ ሰው በአንድ እጁ ብዕር በሌላው ሰይፍ ከሌለው በብዕሩ ብቻ ሰይፍ ከጨበጠው እኩል አይሆንም፡፡ አንተ ሚኒስቴር ደ ኤታውንም ዲሬክተርነቱንም አልፈልግም፣ እየሳልኩ ነው መኖር የምፈልገው አልክ፡፡ አሁንም ያ ቢቀር በፊት እንዳልንህ ሹመቱን እንሰጥህና የሚገባህ ቦታ ያስቀምጡሀል’’
ጃንሆይ እንግዲህ ሹመት እንሰጥሀለን ሲሉ ፊታውራሪ ወይም ደጃዝማች ማለታቸው ነው፡ ሰዐሊው አፈወርቅ ደሞ ይህን መጠሪያ አልፈለገውምና እጅ ነስቶ ሹመቱን ሳይቀበል ወጣ፡፡
ወደ በኃላ በእሑድ ጠዋት ፕሮግራም ላይ አለ ሹመት ግን እኩዮቼ ናቸው ከሚላቸው ጋር በሁሉም ፕሮቶኮል ቦታዎች እንዲቀመጥ በተለይ አዘውለት እንደነበር ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡
ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና
የማሕበረሰባችንን መረብ አስተሳስረው ያያዙት ልብወለድ ትርክቶች፣ በተለይም ስለ ፈጣሪ፣ገንዘብ፣ አገር እና መሰል ነገሮች የተወሳሰቡ ስሜቶች አካላት (Intersubjective entities) ናቸው፡፡
አንድ ሳይንቲስት የሳይንስ አካዳሚ አባላትን ሰብስቦ አዲስ ስላወጣው የፊዚክስ ግኝት በተሳለ ቋንቋ ቢያስረዳቸው ለሰዐታት አፋቸውን ከፍተው ያዳምጡታል፡፡ ያንኑ ዲስኩር በመገናኛ ብዙኀን ቢለቀውሳ? አድማጭ ተመልካቹ ጣቢያውን ቀይሮ ዘፈን ይኮመኩማል እንጂ ራሱን በተወሳሰበ ቀመር አይበጠብጥም፡፡ ኑሮ የሚያናጥበው ይበቃዋል፡፡
ሕዝብን በማስተባበር ረገድ የፈጠራ ታሪኮች ከዕውነት የሚበልጡበት ሁለት ምክንያት አላቸው፣ አንደኛ የፈጠራ ታሪኮች በምንፈልገው ልክ አቅለን ልናቀርባቸው እንችላለን – እውነት/እውቀት ግን ውስብስብ ነው፡፡ ሁለተኛ እውነት/እውቀት ብዙውን ግዜ ያማል አይመችም፡፡ ፈጠራ ግን አዝናኝ ነው በውሸትም ቢሆን፡፡
ካፒቴን ስምረት ብርሀኔ በሸገር የጨዋታ እንግዳ ሆነው የተናገሩት አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ እንግዲህ እሳቸው የአፍሪካ አየር መንገዶች ማሕበር መሪ ሆነው ሳለ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገር አየር መንገድ ኃላፊዎች ድርጅታቸው እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን ውጤታማ እንዳልሆነ እንዲያስረዷቸውና ምክር እንዲሰጧቸው ያስቸግሯቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ለሚጠይቃቸው ሁሉ
‘’ይቅርብህ ወንድሜ፣ ለጠየቅኸኝ ጥያቄ እውነቱን ከመለስኩልህ ትጣላኛለህ’’ እያሉ በጸባይ ይሸኙ ነበር፡፡ አንደኛው ግን አይ እውነቱን ነግረውኝ እመሸበት ልደር ብሎ አለቅ ይላቸዋል፡፡ ቃል ለቃል ባይሆንም የሚከተለውን ይነግሩታል
‘‘አየህ ችግሩ ያለው በከፊል እናንተ ስራ አስኪያጆቹ ጋ ነው፡፡ ገና እንደተሾማችሁ የሉፍታንዛ ስራ አስኪያጅ ደመወዝን ትጠይቁና የኛም በዛ ልክ ካልሆነ ትላላችሁ፡፡ ብትመከሩ እሺ አትሉም፣ እሱ ነጭ እኔ ጥቁር ስለሆንኩ ነው ትላላችሁ፡፡ ደሞ ያም በበቃ ሶስት አራት ረዳቶችን በወፍራም ደመወዝ ትቀጥራላችሁ፡፡ ለምሳሌ የአንደኛው ረዳት ስራ ለጉብኝት በሄዳችሁበት አገር የአልቤርጓችሁ አልጋ ላይ ሁለቴ ከነጠረ በኃላ ምቹ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ታድያ አየር መንገዳችሁ ይህን ሁሉ ወጪ ሸፍኖ እንዴት አትራፊ ይሆናል?’’ ብለው መለሱለት፡፡
ሰውየው ተናዶ ደህና ሁኑም ሳይላቸው የቢሯቸውን በር በርግዶ ወጣ፡፡
እና እውነት/እውቀት ይከብዳል
እስካሁንም እኮ ብዙዎቻችን የአነስታይንን የ ኢ ኤም ሲ ስኩየርን ቀመር አልተረዳነውም፡፡
በርግጥ አንዳንድ በጣም ጥቂት የሆኑ የእውቀትና የእውነት ሰዎች በብዙሀኑ ሊደነቁና ሊወደዱ በቅተዋል፡፡
አንድ ጊዜ በለንደን ለገሐር ይመስለኛል ጋዜጠኞች ቻርሊ ቻፕሊን እና አልበርት አነስታይንን አንድ ላይ ያገኟቸዋል፡፡
አንስታይን ቻርልስ ቻፕሊንን ‘’ስላንተ በጣም የሚገርመኝ ምን መሰለህ? ያንተ ጥበብ ሁለንተናዊነቱ (universality) ነው፡፡ ምንም ቃል አትናገርም፣ ከእንቅስቃሴህ ብቻ ሰው ሁሉ የይረዳሀል’’ አለው፡፡ ቻርሊ ቻፕሊንም ሲመልስ
‘’ያንተ ግን የበለጠ ይገርማል፡፡ ምክንያቱም፣ አለም ያደንቅሀል፣ የሚያደንቅህ ግን ሳይረዳህ ነው’’
ለማንኛውም አነስታይን ልዩ ሳይንቲስት ስለሆነ ነው ሰው የወደደው፡፡ብዙ፣በጣም ብዙ ግዜ ግን ሕዝብ ሳይንቲስቶች ስለመፈጠራቸውም አያስታውስም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ቲቪያችንና ሬድዮናችንን የሚያጨናንቁት ያወቁ ሳይሆኑ የታወቁ ሰዎች የሆኑት፡፡

እንዲህም ስላልን ግን ሁሉም ፖለቲከኞች ውሸታም ናቸው ሁሉም ብሔራዊ ታሪኮች ሐሰት ናቸው ማለታችን አይደለም፡፡ ልብ በሉ! ብዙውን ግዜ ምርጫው እንዲያው በቀላሉ እውነትን መናገርና መዋሸት እንዳይመስለን፡፡
ለምሳሌ የንግሥተ ሳባንና የሰለሞንን ታሪክ እንውሰድ፡፡ በጥንት ጊዜ ንገሥታቱ ተቀባይነትን ለማግኘት ስልጣነ-ቡራኬያቸው ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ መሆኑን ማሳመን ነበረባቸው፡፡ በዚህ ረገድ የኛ ሰለሞን ዘሮች ብቻ አይደሉም ይህን የሚያደርጉት፣ የዮርዳኖሱ፣የሞሮኮውና የሳዑዲ ነገስታት ሁሉም የነቢዩ መሐመድ የልጅ ልጆች እንደሆኑ ነው ሲተርኩ የኖሩት፡፡
ለዚያን ግዜው ማሕበረሰብ ሰላምና መረጋጋት ረድቶ ይሆናል ብለን እንለፈው፡፡
በዚህ ረገድ የፈጠራ ትርክቱ ውሸት የሚሆነው ትርክቱ እውነት ነው ብለን ከተከራከርን ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ትርክቱ የሀገርን በሀገርነት ለማቆየት አስፈላጊ የነበረ የተወሳሰበ ስሜት (ኢንተር ሰብጀክቲቭ ሪያሊቲ) ነው ማለቱ የተሻለ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አሁን አየተነገሩ ያሉ ፈጣጣ ውሸቶችን እውነት ናቸው ብለው ሊያሳምኑን የሚሞክሩ ፖለቲከኞች፣ የሳባ-ሰለሞንን ትርክት ውሸትነት ለማስረዳት ሲጥሩ ማየት ፈገግ አያሰኝም?
እዚህ ጋ አንድ ነጥብ አስቀምጠን እንለፍ፣ ማህበረሰባዊ ስርአት ማለት ከፍትህ እና ርትዕ ጋር እንዳናምታታው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካው ሕገመንግስት በሰው እንደተጻፈ እና ሊሻሻል የሚችልበትን አግባብ ያስቀምጣል፡፡ ይህ እንግዲህ በፍትህ እና ርትዕ ረገድ ያለበትን ክፍተት አምኖ ለማሻሻል እድል ያስቀመጠ ነው ማለት ነው፡፡
ሁሉም ሰው የዘረጋው የመረጃ መረብ ሁለት ነገሮችን በአንዴ ማሳካት አለበት እውነቱን ማስቀመጥ እና ስርአትን ማንበር!!
ከዚህ በተያያዘ ከመረጃ መረብ ጋር ያለው ችግር ምንድነው? በራሱ መረቡ እውነትን ሊሻና ለማግኘት የሚያበረታታ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህን የሚያደርገው በተወሰኑ መስኮች ብቻ ነው፡፡ የእነዚህ መስክ ጠበብቶች ተግባርም የማህበረሰቡን ስርአት ሳይነካ ወይም የፖለቲካ ፍልስፍናውን ጠብቆ ግን ኃይል ማሳደግ ይሆናል፡፡
በማርክሲስት ራሺያ፣ በናዚ ጀርመን፣ እና በሺአይት ኢራን ያሉ ሳይንቲስቶች ሁሉ ይህን ሲያደርጉ ነበር አሁንም ያደርጋሉ
ለማንኛውም የመጀመርያው የመገናኛ ቴክኖሎጂ፣ ማለት አይቲ ትርክት ነበር፡፡ የሚዘዋወርበት ዘዴው ደሞ ከአፍ- ወደ አፍ ነው፡፡
ሁለተኛው ትልቁ የመረጃ ቴክኖሎጂ አይነት ሰነድ ነው
ምዕራፍ ሶስት
ሰነዶች ፣ የሚናከስ የወረቀት ነብር (paper tiger?)

ጫካ ውስጥ የፈለጉትን እንደሚያገኙት እንደ አዳኞችና ፍራፍሬ ለቃሚዎች ሳይሆን የመዝገብ ቤት ሰራተኞች ዶሴዎችን በስነስርዐት የሚመሩበት ስርዐት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም ስርዐት ቢሮክራሲ ይባላል፡፡ ይሁንና ታድያ ቢሮክራሲም እንደ አፈታሪክ (ትርክት) ሁሉ እውነትን ስነስርዐት ለማንበር ሲል ይገለዋል፡፡
በዚህ የመረጃ ቴክኖሎጂ ዘመን ሰነዶች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መረጃዎች ሆነው ተገኙ፡፡ ለመሆኑ መሰነድ ለምን አስፈለገ? በአፈታሪክ ላይ ተመስርቶ የነበረው የመረጃ ስርዐት ራሱን ለማየት እና ለማስቀጠል ያለፉትን አፈታሪኮች ከአፍ ወደ አፍ እየተቀባበለ ያስተላልፋቸው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት አፈታሪኮቹ ቀስ በቀስ በትንሽ በትንሹ እየተለዋወጡና አንዳንዴም እየተሻሻሉ፣ ብሎም እየተቀያረየሩ ቀጠሉ፡፡
ይህ ማለት ምንድነው? አንዳንድ መረጃዎችን በቃል ማስተላለፍ እያዳገተ መጣ፡፡ ለምሳሌ በግብጽ ፋሮዎች ዘመን ቁጥሮች አስፈላጊ እየሆኑ መጡ፡፡ የአባይ ውኃ ደለል ይዞት የመጣው አፈርን እኩል ለገበሬዎች ለማከፋፈል ሂሳብ መስራት አስፈለገ፡፡ ያን በቃል አስታውሶ በትርክት ብቻ ማከናወን አይቻልም፡፡ ቁጥሮችን በስዕልም ሆነ በምስል ማስቀመጥ ግዴታ ሆነ፡፡
ወደ በኃላ የመጣው ማሕበረሰብ ግን እያደገና እየሰፋ የሚተዳደርበት ስርዐት ስርዐቱን የሚያስፈጽሙ አካላትን መገንባት አስፈለገው፡፡ እነዚህ አካላት ማሕበረሰቡን በስርዐት ለመምራት ሰዎችን መቅጠር፣ የተቀጠሩት ሰዎች የሚሰሩበት ቢሮ፣ ደመወዛቸውን ለመክፈል ደሞ ከማሕበረሰቡ ገንዘብ በቀረጥ መልክ መሰብሰብ አስፈለገ፡፡
እነዚህ ስራዎች በትውስታ ብቻ ሊከናውኑ አይችሉም፡፡ ነዋሪው መመዝብ፣ ለከፈለው ቀረጥም ደረሰኝ አስፈለገው፡፡ የከፈለውንና ያልከፈለውን ለመለየት፣ የተከፈለውን መጠን አስልቶ ለንጉሡ ለማስረገብ በጽሁፍ የተቀነባበሩ ዶሴና ሰነዶች እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡
መጀመርያ በጭቃ ከተሰሩ ሰሌዳዎች ላይ ነዋሪው ያለው ፍየል በቁጥር ይቀመጣል፣ ከዚያ ላይ አስራቱ ተሰልቶ እንዲያስረክብ ይደረጋል፡፡ የርክክብ ሰነድ እና ዶሴ ስራ ይጀምራሉ፡፡
በቁሙ ቢሮክራሲ መጻፊያ ጠረቤዛ ከሚለው ቃል የተወለደ ነው፡፡የንጉሥ ተቀጣሪው በቢሮ ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ በጠረቤዛው ላይ ዶሴዎቹን በጽሁፍ አዘጋጅቶ ይሰንዳል፡፡ በተፈለጉ ጊዜ ቶሎ እንዲገኙ የተለያዩ ሰነዶች በተለያዩት የጠረቤዛው መሳቢያዎች ያስቀምጣል፡፡ የየሰዉ ንብረት (ከብት፣እሕል፣ማር…ወዘተረፈ)ዝርዝር በአንድ መሳቢያ፣የተከፈለ ቀረጥ ደረሰኝ በሌላ፣ ያልከፈለ ሰው የእዳ ሰነድ በሶስተኛው መሳቢያ…እያለ ይቀጥላል፡፡
‘ከፋፍለህ ግዛ ሀ ተብሎ ተጀመረ’ – ቢሮክራሲ!!
ሰዉም ውል መዋዋል፣ ብድር መበዳደር ጀመረ፡፡ የውል ሰነድ፣ የእዳ ማረጋገጫ ሰነድ…
የከፈልክበት ደረሰኝ ወይም ያበደርክበት ውል ከሌለህ ክፍያህም አይጸና ያበደርከውም አይመለስልህም፡፡ እግዚአግሔርን የፈራ አምኖ ካልረዳህ፡፡
ቀረጥ ለመጣልም ሆነ ለመሰብሰብ የቃላት ሰነድ ብቻውን የተሟላ ስለማይሆን ቁጥሮችም ተፈልስመው ከቃላት ጋር ተሰናስለው አንድን ሰነድ የተሟላ መረጃ እንዲሆን አረጉት፡፡ አሁን ቢሮክራቶች ማንበብና መጻፍ ብቻ የተካኑ ሳይሆኑ ሒሳብ አዋቂዎችም ሆነ፡፡ ስለዚህ የሀይማኖት/ፍልስፍና እውቀት ላይ የሒሳብ ጥበብም በስራ ላይ መዋል ጀመረ፡፡ አልጀብራና ጂዖሜትሪ !
በዚህ አይነት ሰነዶች የእውነታ ነጸብራቅ ወኪል ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውም እውነታ ሆኑና አረፉት፣ መረጃውን የሚይዙት ደሞ ኃይለኞች እየሆኑ መጡ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰው የሌላቸው ግን እነሱ ያላቸው ነገር አለና! ይህም ሰነድ ነው፡፡ መረጃ
አንተ የበታች ሹም የኔ ሀሳብ ሰጪ
ዶሴዬን መርምረው አይሁን ተቀማጭ፡፡
እንዲታይ ነው እንጂ ወደ በላይ ቀርቦ
መች እንዲኖር ነበር መዝገብ ቤት አጣቦ
የአባይ በለጠ ቆየት ያለ ዘፈን፡፡ ምድር ጦር ሰራዊት ኦርኬስትራ
ከሰው-ወደ-ሰው የነበረው የመረጃ ግንኙነት ፍሰት ከሰው-ወደ-ሰነድ ሆነ
ሰዎች ባለስልጣንና ተራሰው ሆነው ተከፋፈሉ፡፡ቀለም ቀመሶቹ ቢሮከራቶች የማዕከላዊ አገዛዙን ኃይል አጠናከሩት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቢሮክራሲው እንዴት እንደሚሰራ እውቀት ስለሌለው ማዕከላዊ መንግስቱን መሸወድም ማምለጥም የማይችል ሆነ፡፡
በሌላ በኩል ግን መልክ ያለው ስርዐት ሰፈነ፡፡ ሰነድ የጊዜው የመረጃ ቴክኖሎጂ ሆኖ ነገሠ፡፡
እስካሁንም!!
የጽሁፍ መፈጠርና መሻሻል አፈታሪኮቹ እና ትርክቶቹ በጽሁፍ መልክ እንዲቀርቡ በር ከፈተ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱስ ቁርአን፤ የሕንዶቹ ቬዳ የየሕብረተሰቡ ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወት ጀመሩ
ምዕራፍ አራት
ሕጸጾች: የእምነቶችና የእምነት መጻሕፍት ምሉዕ-በኩለሄነት

የሰው-ሰነድ ግንኙነት የመረጃ ቴክኖሎጂ ቢሮክራሲያዊ ስርአትን እና ሒሳብን ብቻ ሳይሆን የቀድሞ አፈታሪክ እና ትርክቶችን በአንድ በመሰነድ ለየ ማሕበረሰቡ ለአለማዊው ሕግ ጋር ወይም ጎን ለጎን መሪ ሕግጋት ሆኑ፡፡
በየመጻሕፍቱ የተጠረዙት ሐይማኖቶች በሰው ከሰው አዕምሮ የፈለቁ በሰው እጅ የተጻፉ ሳይሆኑ መለኮታዊ ደራሲ አግኝተው የማይሻሩ የማይለወጡ ምሉዕ በኩለሄ ድንጋጌዎች ተደረጉ፡፡
እነዚህ መጻሕፍት ግን ራሳቸውን ስለማይተረጉሙ ቱርጁማኖች ተደረጉላቸው፡፡ ቀሳውስት፣ሼካዎችና ብራሀማዎች ከቢሮክራቶቹ እኩል እንዲያውም ቀደም ሲል ከነሱም የበለጠ ስልጣን ተጎናጸፉ፡፡
የሀይማኖት ጠቢባኑ ማለት ቴዎክራቶች ብዙ ጊዜ ከአለማዊው ዘውድ እኩል አንዳንዴም የበላይ እየሆኑ የሰው-ሰነድ መገናኛ ቴክኖሎጂውን ይመሩት ነበር፡፡
ቴዎክራቱን የተገዳደረ፣ለመገዳደር ያሰበ፣ በመገዳደር የተጠረጠረ አይቀጡ ቅጣት የሚቀበልበት አሰራር ተስፋፋ፡፡ ጠንቋዮችን የማስወገድ ዘመቻዎች፤ የአይሁድ ዕምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረው የስፓኒሽ ኢንኩዚሽንን ያስታውሷል፡፡
ሆኖም ከዕውነት ይልቅ እምነት ያመዘነበት አሰራር ዘለአለማዊ መሆን አልቻለም፡፡ ከዚህም ከዚያም ተገዳዳሪዎች ተነሱበት፡፡
በሰው-ሰነድ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ትልቁ እመርታ የደረገው ዮሐንስ ጉተንበርግ በ 1440 የሕትመት መኪና (Type Writer) ሲፈለሰፍ ነው፡፡
ከዛ በፊት ሰነዶች በሰው ሲጻፉና ሲገለባበጡ እንደ ከራኒው እውቀትና ትጋት ሊቀነሱ፣ሊዛቡ ከመቻላቸውም በላይ አንድን መጽሐፍ በብዙ ግልባጭ ለመጻፍ የሚወስደው ጊዜ እና የቅጂው ብዛት ውሱን ነበር፡፡ የህትመት መኪናው በዚህ ረገድ ያመጣው መሻሻል አብዮታዊ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ይህም ለእውቀት መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡

የጽህፈት መኪና ((Type Writer)
እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው (ሶቅራጥስ)
ጊዜው እየተሻሻለ ሲሄድ እና እውቀት እየስፋፋ ሲመጣ ቴዎክራቶቹ የሚመሯቸው የሀይማኖት ተቋማትና የማይሻሩ የማይለወጡ ሕግጋቶቻቸው ከዘመኑ ጋር ለመጣጣም አልቻሉም፡፡
አዲስ እያበበ የመጣው እውቀት ሳይንስ ነው
ልክ እንደ ቤተእምነቶች የሳይንስ አላማም እውነትን ማግኘት ነው፡፡ የበፊተኛው እውነትን በእምነት እንዳገኘ የሚያምንና ያም የማይለወጥ እና የማይሻሻል እውነት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
ሳይንስ በበኩሉ እውነትን ከእምነት ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በእውቀት በኩል ለማግኘት ይጥራል፡፡ የአንድን ነገር እውነታ ሙሉ በሙሉ ይሄ ነው ብሎ ለመደምደም ያለው እውቀት ውሱን መሆኑን አምኖ የተደረሰበት እውነት በፈቲነ-ግብር (Experiment) እየተረጋገጠ፣ እየተሻሻለ ሊለወጥ እንደሚችል እድል ያስቀምጣል፡፡
ስለዚህ ሳይንስ አንድን ነገር ሲመረምር ያን ነገር ሙሉ በሙሉ ካለማወቅ ይጀምራል፡፡ ላቲን ይህንን ኢግኖራሲየም ይለዋል፡፡ ሶቅራጥስም ‘’እኔ የማውቀው አለማወቄን ነው’’ እንዲል
እስቲ ለነገሩ ወይም ለችግሩ የተለያየ መፍትሔ እና መላምት እናስቀምጥለት፣ መላምቶቹን በፈቲነ ግብር ፈትሸን እውነቱ ላይ እንድረስ፡፡ የተደረሰበት እውነት በየጊዜው የሚፈተሸ፣ የሚሻሻልና ካስፈለገም የሚተካ ነው፡፡ በሚል ጽኑ መሰረት ላይ ነው የቆመው ሳይንስ፡፡
የአንድን እውቀት እውነታነት ለማረጋገጥ ተቆጣጣሪ ወይም አስተካካይ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ጥናትና ምርምር አድርገው ውሳኔያቸው እውነት እና እውነትን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ አይነት የተደረሰበት እውነት ወይም እውቀት ቢሆን በየጊዜው የሚፈተሸበት ስልት/ሕግ ይቀመጥለታል፡፡ ስለዚህም ገና ከመወለዱ የመሻሻልና የመለወጥ አንቀጽ ተቀምጦለት ነው የሚደነገገው፡፡
በሌላ አነጋገር የሳይንሳዊ አብዮት የተመሰረተው ለአለማወቅ (Ignorance) እውቅና በመስጠት ነው፡፡
የግለ–እርምት ዘዴ The limits of self-correction
ሁሉም ነገር ማለት ሰው፣ማህበረሰብ፣ ተፈጥሮም ጭምር የማያቋርጥ የራስ በራስ የማሻሻያ ዘዴ አለው፡፡ ይህ ዘዴ መስራት ሲያቆም ያ አካል (entity) ይሞታል፡፡
ሰውነታችን የሞቱና የደከሙ ሴሎችን አስወግዶ በአዲስ ይተካል፣ አዳዲሶቹ ሴሎች በተራቸው ሲደክሙና ሲያረጁ በሌላ ይተካሉ፡፡ ይህ ሂደት በሕይወታችን ሁሉ ሰውነታችን በራሱ የሚያካሂደው ክስተት ነው፡፡ ይህን ማካሄድ አቅቶት አሮጌ ሴሎችን በአዲስ ካልተካ እንሞታለን፡፡ ከዚያ የሚከተለው ስርዐተ-ቀብር ነው፡፡
የአሜሪካ ሕገመንግስት ከሁለት መቶ አመት በፊት ሲደነገግ ካስቀመጣቸው አንቀጾች አንዱ ሕገ-መንግስቱ በምን መንገድ እንደሚሻሻል ነው፡፡ በዚህም መሰረት እስካሁን ሀያ ሰባት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡ ባርነት እንዲቀር የተደረገው፣ ጥቁሮችና ሴቶች የመምረጥ መብት ያገኙት በነዚህ መሻሻሎች ነው፡፡
በሳይንስ አለም አንድ የተከበረ ግኝት ወይንም እውነታ በግለ-እርምት ዘዴ በሌላ ሲተካ ኹነቱ (event) ትልቅ በዐል ሆኖ ይከበራል፡፡ ለሁለት መቶ አምሳ አመት ጸንቶ የነበረው የአይዛክ ኒውተን ሎው ኦፍ ሞሽን በአልበርት አነስታይን ስፔሻል እና ጄኔራል ሪላቲቪቲ ሲሻሻል ትልቅ ደስታ ነው የፈጠረው እንጂ ቅሬታን አላስተናገደም፡፡ የጄኔራል ሪላቲቪቲን ፈቲነ-ግብር አፍሪካ ድረስ በመሄድ በተግባር ያረጋገጠው የኒውተን አገር ሰው እንግሊዛዊ ነው፡፡
ለዚህ ነው ሳይንስ ለእውነት በጣም የቀረበው፡፡
የግለ–እርምት ውሱንነት
ግለ-እርምትም ቢሆን ታድያ የራሱ ውስንነቶች አሉት፣ ምንም ነገር ምሉዕ-በኩለሄ አይደለምና!
ቀደም ሲል እንዳስቀመጥነው በመገናኛ ቴክኖሎጂ አሰራር የምንከተለው ቴክኖሎጂ ወደ እውነት የሚያደርሰን ብቻ ሳይሆን ማሕበረሰባዊ ስርዐትን የማያደፈርስ መሆን አለበት፡፡
ፖለቲከኖች ለስነስርአት ሲሉ እውነትን እንደሚጫኗት ሁሉ አንዳንዴ የምንጠቀምበት የመገናኛ ቴክኖሎጂ ለእውነት ሲል ማሕበራዊ ሰላምን ሊያደፈርስ እድል እንዳለው መገንዘብ ጠቢብነት ነው፡፡
የመገናኛ ቴክኖሎጂ ትልቅ ግብ ትልቅ የስነስርአት መዛባት ሳይደረስ የተገኘውን እውነት በስራ ላይ ማዋል ነው፡፡ በእውነትና በስነ-ስርአት መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡
በ 1983 ግንቦት ላይ የጊዜው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ራጂብ ጋንዲ በአንዲት አጥፍቶ ጠፊ ይገደላሉ፡፡ አጥፍቶ ጠፊዋ የሲክ ዘውግ አባል ነች፡፡ ሲኮች የእምነት ነጻነታችን ተነካ ባሉበት ወቅት ሀይለኛ ረብሻ ይፈጥራሉ፡፡ ቀደም ሲል የሲኮች ምኩራብ በሂንዲዎች ሲቃጠል ኢንድራ ጋንዲ ምንም እርምጃ አልወሰደችም በዚህም የድርጊቱ ተባባሪ ናት ብለው ያመኑ ሲክ ዘቦቿ እሩምታ ጥይት አርከፍክፈው ገድለዋታል፡፡
ወዲያውኑ ብዙሀኑ የሂንዱ ማሕበረሰብ በንዴት ግሎ በየቦታው ያገኛቸውን ሲኮች ከመግደሉም በላይ የንግድ ተቋሞቻቸውንና ምኩራቦቻቸውንም አንድዶባቸዋል፡፡ ረብሻውና ግድያው በመከራ ነበር የቆመው፡፡
አሁን ታድያ የኢንድራ ጋንዲ ልጅ በተመሳሳይ በሲክ አጥፍቶ ጠፊ ሲገደል የሕንድ መንግስት የወሰደው የመጀመርያ እርምጃ ወዲያውኑ ግድያውን የፈጸመችው የሲሪላንካ አክራሪ ድርጅት አባል የሆነች ሴት መሆኗን አሳወቀ፡፡ ሁሉም የመገናኛ ብዙሐን ይህንን ተቀብለው አስተጋቡት፡፡
ነገሩ ውሸት ነው፣ ግን የብዙ ሺ ሲካውያን ሕይወት ተረፈ፡፡ አገሪቱም ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ሳይገጥማት አለፈ፡
ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን
Yuval Noah Harari, Nexus: A brief History of Information Networks from Stone Age to AI: Penguin Random House UK, 2024