እንዴት ከረማችሁ? ስንክሳራችን እየዳኸች ሶስተኛ ወሯን ያዘች፡፡ አሁን ታድያ እየተላመድን የመጣን ይመስለኛል፡፡ በናንተ በኩል አስተያየታችሁን ለዚሁ በተዘጋጀው ቦታ ብትልኩልን ይበልጥ ለማሻሻል የይረዳናል፡፡ ሰብስክራይብ ብታደርጉም ጥሩ ነው፡፡ ፡፡ ከሶስት እትሞች ካገኘችው ልምድ ተነስታ ከአፕሪል ጀምሮ በቀላል ክፍያ ስትቀርብ የበለጠ አርኪ እንድትሆን ምክራችሁን እና አስተያየታችሁን በጣም፣ በጣም እንፈልጋለን እና አደራችሁን፡፡
የፌብርዋሪ እትም ስድስት መጣጥፎችን ይዛለች፡፡ የመጀመርያው አምድ ቤተሰብና ልጆችን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ እንዲህም ስለተባለ ለሌላው ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እንዳው ግን በይበልጥ ትኩረቱ ስለ ሂሳብ ትምህርት ጠቃሚነት እና ልጆቻችንን ገና ከጅምሩ አንደኛ ደረጃ እያሉ ሂሳብን በመዝናኛ መልኩ በማቅረብ እንዲወዱት ስለማድረግ የተዘጋጀ ጽሁፍ ነው ለማለት ነው፡፡
ስለዚህ በዚህ ወር የሳይንስ አምድ ‘’ጊዜ ቤትን እንማር’’ በሚል ፈገግ በሚያደርግ ርዕስ ከጊዜ ቤት ከፍ ያለ ነገር ስለ ሂሳብ አቅርበናል፡፡
የዚህ ወር የአሰሳ አምዳችን በ ‘’ጸኃይ’’ ላይ ያተኩራል፡፡ እቺ በቀን በቀን ሙቀትና ብርሀን በነጻ የምትሰጠን ጸኃያችን ምንድን ናት? እንዴት እና መቼ ተፈጠረች? በውስጧስ ምን ምን ነገሮችን ይዛለች? የጠለቀም ባይሆን ለጠቅላላ እውቀት ያህል እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ ስለ ቅርቧ ኮከባችን ጸኃይ ትንሽ እናትታለን፡፡
የባህል እና ስነጥበብ አምዳችን ስለ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የጀመረውን ትርክት ሶስተኛ ክፍል ያቀርባል፡፡ ይህን አምድ ይበልጥ ለመረዳት ያለፉትን ሁለት የባህል እና ስነጥበብ አምድ ማንበብ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ በታሪክ ፍሰት የተያያዙ ስላልሆኑ የደረሳቸችሁበትን ማንበቡ ችግር አይኖረውም፡፡
ወዳጆቼ፣ በአሁኑ ዘመን ደጋግመን ከምንሰማቸው ነገሮች አንዱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ወይንም INFORMATION TECHNOLOGY (IT) ነው፡፡ ሁሉም ስለሚያውቀው አይ ቲ እንበለው፡፡ ደጋግመን እንደመስማታችን ግን ሰለ ጽንስ ሀሳቡ ጥሩ እውቀት ወይንም መረዳት ያለን ሰዎች ጥቂት ነን፡፡ በዚህ አጭር መጣጥፍ የአይቲን ምንነት እና ታሪክ በአጭር ከቀረበበት መጽኃፍ የበለጠ አሳጥረን እናቀርበዋለን፡፡
ይህን ስራ በአይ ቲ በሳል የሆነ ሰው በአማርኛ ቢያቀርበው ምንኛ በተሻለ፡፡ እስከዚያው ግን የአይ ቲ ን ጽንሰ ሀሳብ ምንነት እና ታሪክ ሁሉም እንዲገባው በቀለለ ሁኔታ እናቀርበዋለን፡፡ ስዚህም የዚህ ወር ከመጻኃፍት አምዳችን ‘’የአይ ቲ አጭር ታሪክ’’ በሚል ርዕስ ይቀርባል
በታሪክ አምዳችን ወደ ህንድ ብቅ ብለን በአለም በትልቅነቱ ወደር ስለሌለው በፈቃደኞች የተገነባ ድርጅት የምንላችሁ ይኖረናል፡፡
በዚህ ወር የአለም አቀፍ ግንኙነት አምድ አንድ ወር ስላለፈው የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ትንሽ እናትታለን፡፡
መቸስ ሰው የወለደውን ሲስሙለት፣ የደገሰውን ሲበሉለት፣ የጻፈውን ሲያነቡለት ደስ ይለዋልና ስንክሳር አንብቡኝ ትላችኃለች፡፡
ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን