ልጅ ሆነን ሀብት የእግዜር ስጦታ እንደሆነ ነበር የሚነገረን፡፡ በል ካለው አምላክ እማትሸከመውን አዱኛ ይሰጥሀል፣ በፀሎት መበርታት ብቻ ነው ዋናው፡፡ ታድያ እንዲያ የሚመስለን ልጆቹን ብቻ አልነበረም አዋቂዎቹን ጭምር እንጂ፡፡ አዋሽ ሰባት ኪሎ ለገሀር ከዋናው ቢሮ በስተግራ መኪና እህል የሚያራግፍበት ሰፊ የሲሚንቶ በረንዳ ነበር፡፡ ከሰዐት ከ10 ተኩል በኃላ ጸኃዩዋ በረድ ስትል የለገር ሀማሎች ተቀምጠው ጫታቸውን ይቅማሉ፡፡ በመሀል ከከተማዋ የመጣ አንድ ደረሳ (የሙስሊም ዲያቆን) ተቀላቅሎአቸው እየቃመ፣ሙስባሐውን እየቆጠረ አላህን ይለማመናል፡፡
“ያ አላህ ኧረ በ ርዝቅህ (ድንገተኛ ሐብት) አትርሳኝ፡፡ አሁን በረካህን አንዴ ብታዘንብብኝ ምን ይጎልብሀል? ያ አላህ በል እንጂ!”በማለት ሁለት እጆቹን ከፍቶ ወደ ሰማይ እያየ ይጸልያል፡፡ምንም ጠብ አላለም፣
“እንዴ አትርሳኝ እንጂ!”
ምንም የለም
“አቦ ርዝቅ ከሌለህ መዐቱንም ቢሆን አዝንበው ብቻ ዝም አትበለኝ”
ከማለቱ ሁለት እርግቦች በተከታታይ አይነምድራቸውን የተዘረጋ እጁ ላይ ለቀቁበት፡፡
“ለዚህ ለዚህማ ማን ቀድሞህ”
ብሎ ሃማሎቹን አሳቃቸው፡፡
በዚህ መጣጥፍ ገድሉን የምንዘግበው ኤሎን መስክ ቀላል ሰው አይደለም፡፡ አሁን አሁን ፖለቲካው እየሸፈነው መጣ እንጂ ኤሎን መስክ ፈልሳፊ (ኢንቨንተር) ነው፡፡ የስፔስX መስራች ሲሆን ሰውን ወደ ቀዩ ፕላኔት ስለመላክ አብዝቶ ያስባል፡፡ የፔይ ፓል ተባባሪ መስራች፣ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመስራት ዝናን ያገኘው የቴልሳ ኩባንያ ቀዳሚ ዋና ኢንቨስተሮች አንዱና ዋና ስራ አስፈጻሚ ነው፡፡ የትዊተርን ድርጅት በመግዛት X በሚል ክርስትና አስነስቶ ከ 200 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በአለም የመጨረሻው ከበርቴ መሆኑን ሳንረሳ ነው፡፡
እንግዲህ የኤሎን መስክ ሀብት የእግዚአብሔር ይሁን የሌላ ሞልቶ የተረፈ ነው፡፡ በቅርቡም “የአለም አንደኛ ባለሀብት” ብሎ ፎርቹን መጽሔት ሰይሞታል፡፡ ቡመራንግ እንደተከታተለው ከሆነ በኖቨምበር አንድ፣ ማለትም ከምርጫው ጥቂት ቀደም ብሎ የመስክ ሀብት $263 ቢሊዮን ይገመት ነበር፡፡ ይህንን ስንጽፍ ማለት በ 19/12/2024 $458 ቢሊዮን ገብቷል፡፡ (THE WASHINGTON POST)
በዚህ መጣጥፍ ከ “ዘኢኮኖሚስት” (9/11) እና፣ኒውዮርክ ታይምስ (22/11)፣ቢቢሲ፣ እና ፖሊቲኮ ኢሮፕ፣ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ፣ እንዲሁም ታይም መጽኄት የከበርቴዎች ከበርቴ ስለሆነው ኤሎን መስክ የጻፉትን ከራሳችን አስተያየት እና ምልከታ ጋር እንደሚከተለው አዋዝተን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
ከስር መሰረቱ እንነሳ ካልን ኤሎን ሬቨ መስክ የተወለደው በጁን 28 1971 ፕሪቶርያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ አባቱ ደቡብ አፍሪካዊ እናቱ ደሞ የካናዳ ዜጋ ናት፡፡ ገና በወጣትነቱ ለኮምፒዩተር እና ስራ ፈጠራ ስሜት እንዳለው ያስታውቅ ነበር፡፡ በ12 አመቱ የቪዲዮ ጨዋታ ሰርቶ ለአንድ የኮምፒዩተር መጽሄት ሸጧል፡፡ የደቡብ አፍሪካን አፓርታይስ ስርአት ስለሚጠላ በወታደርነት ግጃጅ ከመመልመል የእናቱን የካናዳነት ዜጋ አውጥቶ በ1988 በርካታ የስራ ፈጠራ እድል ወደሚገኝባትአሜሪካ ገባ፡፡ (ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ)
የአስራ ሁለት ልጆች አባት ነው፡፡ አንዱ ሲሞት የቀሩት በህይወት አሉ፡፡
በካናዳ ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ ሁለት አመት ከተማረ በኃላ ወደ ፔንሲልቪያ ዩኒቨርሲቲ ተዛውሮ ከአምስት አመት ትምህርት በኃላ በኤኮኖሚክስ እና ፊዚክስ የባችለር ዲግሪውን አገኘ፡፡ ከዚያም ወደ ሳንፎርድ ዩኒቨርሲቲ አቅንቶ በፊዚክስ ዶክትሬት ዲግሪውን ሊሰራ ከጀመረ በኃላ የካሊፎርኒያ የጦፈ ኢንተርኔት ንግድ ስቦት ከሁለት ቀን ትምህርት በኃላ አቋርጦ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አብዮትን ተቀላቀለ፡፡በ2002 ዓ.ም የአሜሪካ ዝግነቱን አገኘ፡፡(Biography)
መስክ ከፍተኛ እውቀት እና ክህሎት ያለው የፈጠራ እና የቢስነስ ሰው መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህን እንኳን ወዳጆቹ ተቃራኒዎቹም ሳይቀር መስክረውለታል፡፡ በግራ ክንፍ አክራሪነት የሚመደቡት ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ስለ መስክ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት…
’’ኤሎን መስክ ሊያከናውን በቻለው ነገር በጣም በጣም አስገራሚ ሰው ነው፡፡ መስክ እንደሚለው፣ መንግስት በአምስት አመታት ከሚፈጽመው ይልቅ እሱ በሳምንት የሚሰራው ይበልጣል፡፡ በአንዳንድ በኩልም ትክክል ነው፡፡’’
ከአሜሪካ የኖቨምበር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በኃላ፣ በለስ ከቀናው ዶናልድ ትራምፕ አጠገብ ከማይጠፉት ሰዎች አንዱ ኤሎን መስክ ሆኗል፡፡ እስከ ኖቨምበር አምስት ድረስ ኤሎን መስክ ከትራምፕ ጋር እጅግ በጣም ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው የተገናኘው፡፡ ከኖቨምበር አምስት በኃላ ግን ሁሉንም ጊዜውን በሚያስብል መጠን ከትራም ጎን አይጠፋም፡፡ ከትሕትና ጋር እምብዛም ትውውቅ የሌለው ኤሎን መስክ፣አንገት ላንገት ትንቅንቅ የበዛበትን የትራምፕ ቧለሟልነት እየተለማመደው ነው፡፡ ያን ሁሉ አጃቢ አሸንፎ ተሰሚ የመሆን እድሉ ምን ያህል ይሆን? ቶሎ የምንመልሰው ነገር አይደለም፡፡ (ኒውዮርክ ታይምስ)
ኤሎን መስክ ከሌሎቹ የትራምፕ የሽግግር ወቅት ዋና ዋና ተዋናዮች በተለየ፣የትራምፕን ችሎት አሰራር በለብ ለብ ኮርስ እየተማረ ነው፡፡ሌሎቹ የቧለሟልነቱን አሰራርና ሴራ ጥርሳቸውን የነቀሉበት በመሆኑ፡፡ የትራምፕ ውስጣዊ ቢሮክራሲ ጥምዝምዝ አሰራር፣ ከከባድ ማኑፋክቸሪንግ ስራ አመራርና ከሮኬት ሳይንስ የበለጠ ተግዳሮትና አሳሳች ነውና፣ ትሕትና እና ትዕግስት ጓደኞቹ ላልሆኑት ኤሎን መስክ ትግሉ ቀላል አይሆንም፡፡
በ2028 የትራምፕ ፕሬዚደንት ሲያበቃ ኤሎን መስክ በትራምፒዝም የባለ አራት አመት ባለዲግሪ ተመራቂ የመሆኑ ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ በዚህ በዋሽንግቶን የገና ጨዋታ የትራምፕ እና ኤሎን መስክ ግንኙነት ምን ያህል ሊዘልቅ እንደሚችል ብዙ ጥርጣሬ አልጠፋም፡፡ ይህን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ውስጥ የትራምፕ የመጀመርያ ፕሬዚደንትነት ጊዜ አዋቂዎች በገደምዳሜ የሚሉት፣ የኤሎን መስክ በዚህ ረገድ የሚኖረው ስኬት ትራምፕን በማቆለጳጰስ፣ እዩኝ እዩኝነትን በመቀነስ እና የውስጥ ተቃራኒዎችን በዘዴ እና በጓደኝነት ለመያዝ ባለው ችሎታ መጠን የሚለካ መሆኑን ነው፡፡(ኒውዮርክ ታይምስ)
በአጭሩ የትራምፕ አለምን ፖለቲክስ እንዴት መጫወት እንደሚቻል ማወቅ፡፡
ቢቢሲ ምስል ኤሎን መስክ
ትራምፕን ከበው የሚገኙት ሰዎች በብዛት ባለፈው ትግል ከጎኑ በመሆን ታማኝነታቸውን በእሳት ያስፈተኑት ረዳቶቹ፣ ወይም ሳለፉት ረዢም አመታት ጓደኞቹ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ኤሎን መስክ ለሁለቱም ቡድን አይመደብም፡፡ ኤሎን መስክ እንግዲህ 200 ሚሊዮን የኤክስ (የቀድሞ ትዊተር) ተከታዮቹንና ለትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻ ያወጣውን 200 ሚሊዮን ዶላር ይዞ ነው የመጣው፡፡ ሁለቱም ስጦታዎቹ ትራምፕን አስደንቀዋል፡፡
ከምርጫው በኃላ በማር ኣ ላጎ (የትራምፕ መኖርያ) በሚደረጉ ስብሰባዎች ሁሉ ከጎኑ ነበር፡፡ አንዴም መስክ ትራምፕን፣ ሪዮ ጋርድነር ሸለቆ ቴክሳስ ወስዶት ሰፔስ X ወደ ሕዋ ስትመጥቅ እንዲያይ ጋብዞታል ነበር፡፡ እንግዲህ ከሁለት የቅርብ ምንጮች እንደተረዳነው፣ በማር ኣ ላጎ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ኤሎን መስክ ስለቀረቡት የፖሊሲ አማራጮችም ሆነ በየቦታው ሊደለደሉ ስለታሰቡ ሰዎች ምንም የመረዳት መንፈስ አላሳየም፡፡ ግን ደግሞ ደጋግሞ የሚያነሳው አንድ ነጥብ ነበር፡፡ ይህም የመንግስት አካላትን “መሠረታዊ ለውጥ” አስፈላጊነትና እነማን ይህን መሰረታዊ ለውጥ መምራት እንዳመባቸው ነው፡፡ (ኒውዮርክ ታይምስ)
ረቡዕ ሚስተር ኤሎን መስክ አዘውትሮ ከሚተቻቸው የዜና አውታሮች በአንዱ፣ ማለትም በዎል ስትሪት ጆርናል አንድ መጣጥፍ ከሚስተር ሳማሰዋሚ ጋር አውጥቶ ነበር፡፡ በዚህም እነሱ “የመንግስት ውጤታማነት ሚኒስቴር” ወይም ዴፓርትመንት ኦቭ ገቨርመንት ኢፊሸንሲ (DOGE) በሚሉት መስሪያቤት የሚመራበትን ዝርዝር መርሐ ግብር አቅርበዋል፡፡ ምንም እንኳ ኤሎን መስክ በሚኒስቴሩ ስለሚኖሩት የበላይ አለቆች የስም ዝርዝር ባያስቀምጥም፣ በቴክኖሎጂው አውታር ያለው ተጽዕኖ የበለጠ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ቀደም ሲል የትራምፕ ሁለተኛ የቢሮ ኃላፊ (ቺፍ ኦቭ ስታፍ) የነበረው ሚክ ሙለቫኒ፣ አሁን ለሚሰራበት የአገናኝ (ሎቢንፍ ፋየርም) ኩባንያ ለደንበኞቹ እንደነገራቸው ከሆነ፣ በሚቀጥለው የትራምፕ አስተዳደር የቴክኖሎጂ ኩባንያ አለቆች እንደ ልብ የሚገቡበት እና የሚወጡበት ይሆናል፡፡ሚስተር ሙለቫኒ፣ ኤሎን መስክ ቃል የገባውን የበጀት ቅነሳ ለማስፈጸም ያለውን ችሎታ ይጠራጠራል፡፡ እንዲያውም ይህን ከማከናወን “ወደ ማርስ መሄድ ይቀላል” ባይ ነው፡፡
ሌሎችም በማር ኣ ላጎ ስለሚከናወኑ ጉዳዮች የቅርብ እውቀት ያላቸው ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ምንጮጫችን እንደገለጹልን.. የኤሎን መስክ ጓደኖች የሆኑት የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኃላፊዎች ማር ኣ ላጎ ውስጥ ሲታዩ ከርመዋል፡፡ አንዳንዶቹ ለስልጣንም ታጭተው የያዙትን ስራ ለማጥበቅ ስለወሰኑ ያልተቀበሉት ሲሆን፣ ሌሎቹም ጥሪ እየተደረገላቸው ማር ኣ ላጎን እንደጎበኙ ታውቋል፡፡ የቀሩትም የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኃላፊዎች ከኤሎን መስክ ጋር ለመተዋወቅ እየሞከሩ ነው፡፡ በሲልኮን ሸለቆ በአጠቃላይ በመንግስት ውጤታማነት ሚኒስቴር ውስጥ ለመታቀፍ ከፍ ያለ ፍላጎት ታይቷል፡፡ ከነዚህም አንዱ የ”ኮይንቤዝ” ኩባንያ ኃላፊ በዚህ ሚኒስቴር ውስጥ መመደብ.. “በአሜሪካ የኤኮኖሚ ነጻነትን ለማሳደግ እና የመንግስትን ኃይልና መጠንን ለመቀነስ ይህ በሕይወት አንዴ ብቻ የሚመጣ እድል ነው” ሲል ገልጾታል፡፡
ከነዚሁ ምንጮቻችን እንደተረዳነው ኤሎን መስክ ጓደኖቹን በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ሲያጣራ እንደሚገኝ አውቀናል፡፡ ሰዎችን በስልጣን ቦታዎች በማስመደብ ረገድ ኤሎን መስክ አንዳንድ ስኬቶችን አግኝቷል፡፡ አንዳንዶች ጥቆማዎቹ ግን ተቀባይነትን አላገኙለትም፡፡ የትራምፕ ረዳቶች ቢሆኑ በኤሎን መስክ ሚና ላይ የተለያየ አስተያየት ነው ያላቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንደ ስቴፈን ሚለር ያሉት የትራምፕ ረዳት መስክ “ጉዳት የሌለው” ማለት ሀርምለስ ይሉታል፡፡ ሌሎቹ በሰውየው በፊት በሌለው ቅርበት አሁን ማር ኣ ላጎን የሙጥኝ ማለት ተናደዋል፡፡
መስክም ቢሆን በሰዎቹ ደስተኛ አለመሆን ሀሳብ የገባው ይመስላል፡፡ በቅርቡ በአንድ ጋዜጣ ርዕስ ላይ እሱን የትራምፕ “የቅርብ ምስጢረኛ” ተብሎ ሲገለጽ ወዲያው ነበር አለ ልማዱ የትራምፕ ረዳቶችን…“በማር ኣ ላጎ የሚገኙት በጣም ከፊሉ ታማኝ እና ጥሩ ሰዎች ሲሆኑ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለረዢም ጊዜ የሰሩ ናቸው”(ዘ ኤኮኖሚስት) በማለት አሞካሽቷቸዋል፡፡ በማር ኣ ላጎ፣ የራሱን ድርሻ በተመለከተ..
“ግልጽ ለመሆን፣ ምንም እንኳ ለአንዳንድ የካቢኔ ቦታዎች አስተያቴን ብሰጥም፣ ብዙዎቹ ምርጫዎች የተፈጸሙት አለ እኔ እውቅና መቶ በመቶ በፕሬዚዳንቱ አማካይነት ነው” ሲል በኤክስ ላይ ጽፏል፡፡በዚህም በትራምፕ አለም ውስጥ ያለውን ዋና ትምህርት “ለጥቂት ጊዜ እንኳን ለመቆየት ከፈለግህ ከአለቃው ልቀህ አትታይ” ሚለው ገብቶታል ማለት ነው፡፡
መስክ እና ትራምፕ
በቀድሞው የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣን የነበረው ሚስተር ሙለቫኔይ የኒውዮርክ ታይምስ “ሚስተር ኤሎን መስክት ዋጋ ያለው አማካሪ የሚያደርገው ምንድነው?” ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ “በቂ ገንዘብ እንዲሁም በቂ ሌሎች የሚሰሩ ነገሮች ያሉት ሰው ነው፡፡ ስለዚህም እውነተኛ የሆነ ምክርና መረጃ ለመስጠት በተስማሚ ሁኔታ ላይ ነው ያለው’’፡፡ሲል መልሷል፡፡
ፎቶ ፎርቹን መጽሄት ኤሎን መስክ በካፒቶል ሂል ከረፓብሊካን ፖለቲከኞች ጋር
እንደ ዘ ኤኮኖሚስት ግምት የትራም እና የኤሎን መስክ ግንኙነት ለአሜሪካ ደብዛዛ ነገር ነው፡፡
“ተወዳዳሪ የለሽ ኃይልና ሀብት በሁለቱ እፍረት የለሽ፣ራስ አምላኪነት ያሳበዳቸው፣ለሕግና ለመተዳደሪያ ደንብ ጥቂትም ደንታ የማያሳዩ ሰዎች ውህደት ከጥፋት ሌላ ምንም ውጤት አይኖረውም፣ቀደም ብለው እርስ በርስ ካልተጣሉ በስተቀር” (ዘኤኮኖሚስት (9/11/2024)
የባሰውን አደጋ ዘ ኤኮኖሚስት እንደሚከተለው ያቀርበዋል
“ፊዮና ሂል የምትባል የቀድሞ የትራምፕ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ለፖለቲኮ የዜና መረብ ላይ በሰጠችው ቃለ ምልልስ የባሰው አደጋ ምን እንደሆነ አስቀምጣለች፡፡ ኦሊጋርኪ(ጥቂት ሰዎች ብቻ ገበያን የሚቆጣጠሩበት ስርዐት)፣’ሚስተር መስክ ከትራምፕ እና ከፑቲን እንዲሁም ከአንዳንድ የቻይና መሪዎች ጋር ያለው ግንኙነት በአለም አካባቢ አውቶክራሲን ሊያነብር ይችላል”፡፡
ኤሎን መስክ በራሱ በግል አመራሩ ላይ በስሩ ለሚያስተዳድራቸው ሰዎች በገደብም ቢሆን ጭካኔ የተመላባቸውን እርምጃዎች የሚወስድ ሰው ነው፡፡ ወጪን በመቆጠብ ረገድ ጨካኝ ነው፡፡ በትዊተር የነበሩትን የጽዳት ሰራተኞች በማባረሩ ሰራተኞች የየግላቸውን ሶፍት ፔፐር ተሸክመው ለመምጣት ተገደው ነበር፡፡ ሲቆጣ መልስ የሚሰጠውን እዛው ነው የሚያባርር፡፡ በመንግስት ስራ ግን የሰራተኞች ማህበራት ሊገሩት ይችሉ ይሆናል፡፡ (ኒውዮርክ ታይምስ)
ለአሁኑ ትራምፕ ለ ኤሎን መስክ የሰጠው ስልጣን ምንድነው?
ኤሎን መስክ እና ቀደም ሲል ለሬፓብሊካን ፓርቲ እጩ ፕሬዚዳንትነት ተወዳዳሪ የሆነእ ቪቪክ ራማሰዋሚ በጋራ አዲስ የሚዋቀረውን ዴፓርትመንት ኦፍ ገቭመንት ኢፊሸንሲ (DOGኢ) እንዲመሩ መርጧቸዋል፡፡ ስለ ሹመቱ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጠው ዘ ጋረዲያን ጋዜጣ እንዲህ ይላል
“ስሙ ዴፓርትመንት ይሁን እንጂ (DOGE) መዋቅራዊ የመንግስት አካል አይሆንም፡፡ ትራምፕ በሰጠው መግለጫ፣ መስክ እና ራማሰዋሚ ከመንግስት ውጪ እየሰሩ ለኃይት ሀውስ ‘ምክር ይሰጣሉ አቅጣጫ ያመላክታሉ፡፡ ካለ በኃላ በመቀጠል (DOGE) ከ ማናጅመንት እና በጀት ቢሮ ጋር ፓርትነር ሆኖ ‘ሰፋ ያለ መዋቅራዊ ሪፎርም በማከናወንና ከዚህ በፊት ያልታየ የስራ ፈጠራ መንፈስ በመንግስት እንዲፈጠር’ ይረዳሉ’’ ፡፡ ብሏል
በቅርቡ ቪቪክ ራማሰዋሚ ከኃላፊነቱ ስለቀቀ አሁን ኤሎን መስክ የ DOGE ብቸኛ ኃላፊ ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ግን ዴፓርትመንቱ እንዴት እንደሚሰራ ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባትም በፌዴራል አድቫይዘሪ ኮሚቴ ድንጋጌ መሰረት፣ አማካሪ አካላት እንዴት እንደሚሰሩ እና ለህዝብ ያላቸውን ተጠያቂነት በተወሰነው መሰረት ሊሆን ይችላል፡፡ (ዘ ጋርዲያን)
በዚህ የ DOGE ሀላፊነቱ መስክ የአሜሪካን መንግስት ወጪ ላይ 2 ትሪሊዮን ዶላር ለመነስ ቃል ገብቷል፡፡ ወግ አጥባቂ የፋይናንስ በሳሎች እንኳ ይህን ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡ ይህን ለማሳካት የህክምና እና ብዙ የማሕበራዊ ዋስትና ወጪዎችን መቀነስ ይሆናል፡፡(ታይም መጽሄት)
ከዚህም በላይ ይህ የ DOGE ኃላፊነቱ በበርካታ የአሜሪካ መንግስት የቁጥጥር መስሪያ ቤቶች ላይ ባለ ተጽዕኖ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደሞ የጥቅም ግጭት (ኮንፍሊክት ኦፍ ኢንተረስት) መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ባሁኑ ወቅት የመስክ ኩባንያዎች በመንግስት የቁጥጥር አካላት ከሀያ በላይ የሚመረመር ጉዳይ አላቸው፡፡(ዝኒ ከማሁ)
መቼም ኤሎን መስክ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ የ አዲስ ነገር ፈጣሪነት ዝና ያለው ሰው ነው፡፡ የኤሌክትሪክ መኪናዎቸን እና የኅዋ ጉዞን ለበጎ በመቀየር ረገድም ጥሩ ስም አለው፡፡ በቅርቡ ግን በፖለቲካ የተጠመደ ሆኗል፡፡
ኤሎን መስክ በትራምፕ በዐለ ሲመት ላይ
ኤሎን መስክ መቼ እና አንዴት የትራምፕ ደጋፊ ሆነ?
ከቢዝነስ ታይምስ ባኘነው መረጃ እንጀምር
በአፕሪል 2024፣ ኤሎን መስክ ኔልሰን ፔልትዝ የተባለ ፖለቲከኛ ኢንቨስተር ፓልም ቢች ፍሎሪዳ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ይገኛል፡፡ ፔልትስ በስብሰባው የጠራው ወግአጥባቂ(ኮንሰርባቲቭ) ቢሊዮኔር ኢንቨስተሮችን ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ ከተገኙት አንዱ በሰጠው መረጃ መሰረት፣ የስብሰባው አጀንዳ እንዴት የሬፓብሊካን ፓርቲ እንደሚጠናከርና በተለይም ሴኔቱን እንዴት መልሶ እንደሚይዝ ለመነጋገር ነበር፡፡
ሆኖም ኤሎን መስክ ይነሳና ‘’የሚቀጥለው ምርጫ በአሜሪካ የመጨረሻው ነጻ ምርጫ እንደሚሆን – ምክንያቱም ፕሬዚደንት ባይደን ካሸነፈ በሀገሪቱ ያሉትን ብዙ ሚሊዮን ወረቀት አልባ ሰዎች ህጋዊ ያደርጋል፡፡ በዚህም ዲሞክራሲ ያበቃለታል’’ ብሎ ተናገረ፡፡
በሬፓብሊካን ፖለቲክ ከሱ የተሻለ ልምድ ላላቸው ተሰብሳቢዎች ‘’ስለዚህ ትራምፕ ማሸነፍ አለበት’’ አላቸው፡፡ እስካሁን እነሱ በፖለቲካው ፕሮፖጋንዳ እያደረጉት ያለው ቦታውን የሳተ እንደሆነም አሳሰበ፡፡ የሱ ኩባንያ ቴልሳ ብዙም ማስታወቂያ አልሰራም፡፡ ግን በግል ቅስቀሳ ብዙ ተከታዮችን አፍርቷል፡፡ እነሱስ ለምን እንደዚያ አያደርጉም? የቀድሞው ፕሬዚዳንት እንዳደረገው፣ ሁለት ሰዎች ትራምፕን እንደዲግፉ ማድረግ፣ እነሱን ሌላ ሁለት ሰዎች እንዲያምኑ መገፋፋት፡፡ እንዲያ በመቀጠል ብዙ ደጋፊ ማፍራት ይቻላል፡፡ የሚል ነበር ምክሩ፡፡ (ቢዝነስ ታይምስ)
ለመሆኑ የ ኤሎን መስክ የፓለቲካ አመለካከት ምን አይነት ነው?
መስክ በርዕዮተ አለም ረገድ ቀደም ብሎ ባራክ ኦባማን የመሳሰሉ ዲሞክራቶች ደጋፊ ነበር፡፡ ዋሽንግተንንም አያዘወትርም ነበር፡፡ ከባራክ ኦባማ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረው፡፡ ‘ቴልሳ’ እና ‘ስፔስ ኤክስ’ ለተባሉ ኩባንያዎቹ ድጋፍ ለማግኘት ደጋግሞ ኃይት ሀውስን ጎብኝቷል፡፡ በጥቅሉ ግን ፖለቲከኞችን አይወድም ነበር፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርገውን መዋጮም እንደማይቀር መጥፎ ግዴታ ነበር የሚመለከተው፡፡
ስለ መስክ የፖለቲካ ህይወት በቅርቡ ታይም መጽሄት የጻፈውን ብንመለከት
‘’ የመስክን ፖለቲካ እንዲህ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ በበጋ ወራት (2024) ራሱን እንደ ‘ሞደሬት ዲሞክራት’ አስቀምጦ ነበር፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ የዚህ ዘመን ወሳኝ ተግዳሮት እንደሆነ ያምናል፡፡ ባራክ ኦባማ በ2008 ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደር ኤሎን መስክ የኦባማን እጅ ለመጨበጥ ስድስት ሰአት ሙሉ ተሰልፏል ፡፡’’ (ታይም)
ከ 2016 ምርጫ በፊት ኤሎን መስክ ከ CNBC ባደረገው ቃለ ምልልስ ‘’ትራምፕ በአሜሪካ ተቀባይነት ያለው ባህርይ የለውም’ ብሎ ነበር፡፡ በ 2020 ከአንድ ሰው ጋር ባደረገው የሀሳብ ልውውጥ ትራምፕን ‘’የማይለወጥ ተሸናፊ’’ ብሎታል (ቢዝነስ ታይምስ)
ሆኖም ወደኋላ ኤሎን መስክ በሊበራሎች (ዴሞክራትስ) የፍልሰተኞች አያያዝ፣ የጾታ ፖለቲካ እና ባይደን ኩባንያው ላይ አለው በሚለው አቋም በጣም ተናዶ ነበር፡፡ ትራምፕ የመግደል ሙከራ ከተደረገበት ሰላሳ ደቂቃ በኃላ ግን ጠንካራ የትራምፕ ደጋፊ ሆኗል፡፡ ይሁንና ለጊዜው ድጋፉን ይፋ ማድረግ አልፈለገም፡፡ የፕሬዚዳንት ባይደን የምርጫ ቡድን ነው ኤሎን መስክን ኢላማ ባደረገ ቅስቀሳው አቋሙ እንዲታወቅ የሆነው፡፡
በዚህም የአቋም ለውጥ አድርጎ የሬፐብሊካን ፓርቲ ዋና ደጋፊ ሆነ፡፡
በመጀመርያው ትራምፕ አስተዳደር በብሪታንያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዉዲ ጆንሰን፣ የኤሎን መስክን የርዕዩተ ለውጥ እና የሬፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊነትን በደስታ ነበር የተቀበለው –
‘’የተለያዩ ሀሳቦችን አገናዝቦ የተሻለውን ያዘ፡፡ በአለም እሱን የሚያክል የለም፡፡ከትራምፕ ቀጥሎ ትልቅ የሀሳብ አፍላቂ የሆነውን ኤሎን መስክን በማግኘታችን እኛ አሜሪካኖች እድለኞች ነን’’ ሲል አሞካሽቶታል (ቢዝነስ ታይምስ)
ኤሎን መስክ ከምርጫው በኃላ በሁሉም ቦታ ጣዱኝ ባይ ሆኗል፡፡ ዶጅ የተባለው የበጀት ቅነሳ አማካሪ ኮሚሽንን ስብሰባ በሊቀመንበርነት መርቷል፣ ኮንግረስን ጎብኝቷል፣ እንዲሁም ለጀርመን አክራሪ ቀኝ ክንፍ ፓርቲ ድጋፉን አጉልቶ አሰምቷል፡፡
የድሉ ቀን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር
ባለፈው ረቡዕ እለት (ዲሰምበር 20/24)፣ ኤሎን መስክ በ ኤክስ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀኑ፣ የአሜሪካ ኮንግረስ የደረሰበትን የበጀት ስምምነት አንድ መቶ ሀያ ጊዜ ፖስት በማድረግ አምርሮ ተቃውሞታል፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኃላ በኮንግረስ የሬፓብሊካን አባላት፣ በዚያው በኤክስ ላይ ኤሎን የቀረበውን ሀሳብ እንዲቃወሙት ነግሯቸው እንደነበረ ጻፉ፡፡ ትንሽ ቆይቶም ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ከሬፓብሊካን ፓርቲ የተመረጡት ጄ. ዲ. ቫንስ ከትራምፕ ጋር በመሆን ውሳኔውን ተቃወሙ፡፡ (ዘ ኒው ዮርከር)
ለማገናዘብ እንዲረዳችሁ ውሳኔው ምን ነበር?
‘’የአሜሪካ መንግስት የበጀት ስምምነት ላይ ላይ በመድረሱ የመንግስት አካላት ከመዘጋት ተርፈዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ስምምነት የተደረሰበትን በጀት 336 ለ 34 እንዲሁም ሴኔቱ 85 ለ 11 በሆነ ድምጽ ነው ያጸደቀው፡፡ ስምምነቱ ትራምፕ የመንግስትን የመበደር ጣርያ እንዲጨምር ያቀረቡትን ሀሳብ አያጠቃልልም’’ (BBC News 21 December 2024)
ብዙም ሳይቆዩ ትራምፕ እና መስክ የበጀት ስምምነቱን እንዳይግፉ ነግረዋቸው ያንን ችላ ብለው የድጋፍ ድምጽ የሰጡ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን አስፈራሩ፡፡ (ዘ ኒው ዮርከር) ልብ በሉ እንግዲህ ከላይ ባስቀመጥንላችሁ ቆጠራ መሰረት አብዛኛዎቹ የሬፐብሊካን ምክር ቤት አባላት የትራምፕ-መስክን ምክር ትተው ድምጻቸውን ለድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ስለዚህ የነ ኤሎን መስክ ማስፈራርያ ለራሳቸው ለሬፓብሊካኑ ነው ማለት ነው፡፡
ይህ ምን ያሳየናል? የኤሎን መስክ ተጽዕኖ በሬፓብሊካን ፓርቲ ውስጥ ምን ያህል እየጨመረ እንደ መጣ ነው፡፡
ዴሞክራቶች መስክን ‘’ፕሬዚዳንት መስክ’’ ማለት ጀምረዋል፡፡ (ዘ ኒው ዮርከር)
ግን ደሞ በመስክ እና ትራምፕ መካከል ልዩነት እንዳለም ያሳያል፡፡ መስክ እንግዲህ የመንግስት ወጪ እንዲቀንስ ነው የሚፈልገው፣ በዶጅ (DOGE) ሹመቱም ይህንኑ እንዲያከናውን ነው የሚጠበቀው፡፡ በሌላ በኩል ደሞ ትራምፕ የመንግስት የመበደር ጣርያን መጨመር ይፈልጋል፡፡ ማለትም መንግስት የበለጠ ወጪ ለማውጣት እንዲችል፡፡ ስለዚህ የሁለቱ ሰዎች አቋም እንግዲህ እየተቃረነ ሊሄድ የመቻሉ ጥቂት ቢሆንም እድል አለ ማለት ነው፡፡
ሌላው በቅርቡ በመስክ እና በሬፓብሊካን ፓርቲ መካከል የሚኖረው ክፍተት የቻይና ጉዳይ ነው፡፡ የመስክ ኩባንያ የሆነው ቴስላ ከቻይና ጥብቅ የቢዝነስ ግንኙነትና ጥቀም አለው፡፡ ትራም ደሞ በቻይና ላይ ትልቅ ታሪፍ እጥላለሁ ባይ ነው፡፡ ሬፓብሊካን ባጠቃላይ ደሞ የቻይና አደገኝነት እየጨመረ የመጣ ነው ብለው በጥብቅ ያምናሉ፡፡
በሬፓብሊካን ፓርቲ ውስጥ ኤሎን መስክ ያለው ተጽዕኖ ሀብታምነቱ ብቻ አይደለም፡፡ የተደራሽነቱም መጠን ሌላው እሴቱ ነው፡፡ መስክ የ ኤክስ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን ባለቤት ነው፡፡ በዚህም ይመስላል ከ 200 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት፡፡ ሌላ ማንም ይህን ያህል ተከታታይ ያለው በፕላኔታችን ውስጥ የለም፡፡
ለማንኛውም ኤሎን መስክ በአሁኑ ግዜ በሚያገባውም በማያገባውም ውስጥ እየገባ መዳከር ይዟል፡፡ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በኢሮፕ ፖለቲክስ ውስጥም ጣልቃ ገብነቱ ብዙዎችን እያስገረመም እያናደደም ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ፖለቲኮ ኢሮፕ በ ጃንዋሪ ስምንት 2024 እትሙ የሚከተለውን አስቀምጧል
ኤለን መስክ ባጭሩ ራሱን እየተቆጣጠረ አይደለም፡፡ ከሬፓብሊካኖች ጋር ሳይነጫነጭ በሚተርፍ ጊዜው ጣቱን በውጪ መንግስታት ጉዳይ ውስጥ በመዶል ነው፡፡ ይህ ደሞ በኢሮፕ ቅሬታን የፈጠረ ነገር ነው፡፡ ከዚህ በታች ሰውየው ከአሜሪካ ውጪ ካሉ ፖለቲከኞች ጠብ ያለህ በዳቦ ያለበትን 13 አጋጣሚዎች እንዘረዝራለን… (POLITICO Europe)
እንግሊዝ
የሌበር መንግስት ስልጣን ላይ በወጣ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ኤለን መስክ ‘‘(በእንግሊዝ)የእርስ በርስ ጦርነት አይቀሬ ነው’’ ብሎ ተነበየ፡፡ ከዚያ ጀምሮ የጭቃ ጅራፉን ያወርደው ገባ፡፡ ‘’ብሪታንያ አምባገነናዊ የፖሊስ መንግስት ነች’’
የቀኝ ክንፍ ተቃውሞን አስመልክቶ በስታርመር አስተዳደር…
‘’ኤሎን መስክ ነጭ ቀኝ አክራሪ ተቃዋሚዎች ከሌሎች ተቃዋሚዎች በበለጠ ክፉኛ ይያዛሉ የሚል የሴራ ቲዎሪ እየነዛ ነው” (POLITICO Europe)
‘’እንግሊዝ የውርስ ህግን በመለወጥ የለየላት ስታሊናው መንግስት ሆናለች’’
የሚገርመው ሌላው ቀርቶ በፊት ያሞካሸው የነበረውንና የትራምፕ ዋና አድናቂ የሆነው ኒጀል ፋራዥ እንኳን አልተረፈውም ‘’ኒጀል ፋራዥ ስለ ቀኝ አክራሪው ፖለቲከኛ ቶሚ ሮቢነሰር እስር ብዙም አልተጨነቀም’’ ሲል ወርፎታል፡፡ የስኮትላንዱን የቀድሞ ዋና ሚኒስቴር ዩሳፍ ‘’ሱፐር ሬሲስት’’ ሲል ሰድቦታል
በጀርመን የፓርላማ ምርጫ ጣልቃ በመግባት መራጮች የቀኝ ክንፍ አክራሪ ፓርቲን እንዲመርጡ ምክሩን ደጋግሞ ሰጥቷል፡፡ (POLITICO Europe)
እንዳያው እንግሊዝና ጀርመንን እንደምሳሌ አነሳን እንጂ በፖለቲኮ ኢሮፕ ኤሎን መስክ በውስጥ ፖለቲካቸው ጣልቃ ገብቶ ያስቀየማቸው ዩክሬን፣አየርላንድ፣ ሩማንያ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፊንላንድ እና ኢዩ ናቸው፡፡ ከኢሮፕ ውጪ ካናዳ፣ ቬኑዙዌላ፣ ብራዚል እና፣ አውስትራሊያ መንግስታት ይገኛሉ፡፡
ይህ አካሄዱ ከቀጠለ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አድርጎ ከመደበው ሴናተር ማርክ ሩቢዮ መጋጨቱ አይቀሬ ነው፡፡
የዚህ ሰሞነኛ የፖለቲካ ሰው አካሄድ እና ህልም፣ በቅርብ እንደታየው የመንግስትን ወጪ በከባዱ መቀነስ እና ሰውን ማርስ ላይ ማሳረፍ ነው፡፡ ከዚህ ብዙሀን የሆነው ተራው አሜሪካዊ ምን ያተርፋል?
‘’ጤናችንን የሚጠብቁልን፣ የምንጠጣው ውኃ ንጹህ እንዲሆን የሚታትሩ፣ልጆቻችንን የሚያስምሩ ተቋማት ልክ እንደ አትራፊ ኩባንያዎች ሊመሩ አይገባም፡፡ ለትርፍ የተቋቋሙም አይደሉም፣ ይህ ደሞ የጠቀሜታ እሴታቸውን አይቀንሰውም፡፡ በተለይም እነዚህን አገልግሎቶች ከፍለው ለማያገኙ ዜጎች፡፡ መስክ ለሚፈልገው ውጤታማነት ሲባል የነዚህ ተቋማት ወጪ ተመርጦ ከተቀነሰ ከነዚህ ዜጎች ችግሩ ጊዜያዊ ሳይሆን የዘለቄታ ነው፡፡ ሰውን ማርስ ላይ የማስቀመጡ ውጥን የነዚህን ዜጎች የዛሬ ስቃይ በምንም መንገድ አይቀንሰውም፡፡’’ (ታይም)
በመጨረሻም የቢዝነስ ሰው ከትራምፕ ጋር ሲሰራ ሊደርስ የሚችለውን ነገር የቀድሞ የኤክሶንሞቢል አለቃ የነበረውና ለትራምፕም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኖ ለአጭር ጊዜ የሰራው ሬክስ ቲለርሰን፣ የትራምፕና ኤሎን መስክ ግንኙነት ምን ሊመስል እንደሚችል ሲገልጽ፣ “ሁለቱም ሰዎች ማንም ከነሱ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል በጭራሽ አይገምቱም፡፡ ይህ አብሮ ለመስራት የሚዘልቅ ጓደኝነትን ለመገንባት የሚያስችል አይደለም፡፡ የሁለቱ ፍቅር በቶሎ በኃይል ቦግ ይላል፡፡ ብዙም ጊዜ ሳይወስድ ድርግም ይላል” (ዘ ኤኮኖሚስት)
ተፈራ ካሳ
እፍፍ ያሉት ፍቅር የያዙት ቸኩሎ
በጣም ይግልና ይጠፋል ተቃጥሎ
እንዲል
ምንጮች
BBC News፣ Max Matza and Anthony Zurcher፣ US avoids government shutdown after days of political turmoil፣21 December 2024
Biography.com Editors, Tyler Piccotti and Catherine Caruso Updated: Jan 17, 2025
Encyclopaedia Britannica Written byErik Gregersen Fact-checked byThe Editors of Encyclopaedia Britannica Updated: Jan. 18, 2025
POLITICO Europe Tue 6 Aug 2024 18.30 CEST)
POLITICO Europe January 8 2024
The Business Times, How Elon Musk chose Trump Published Sun, Jul 21, 2024 · 09:00 AM
The Economist September 9
The Guardian፣Wed 13 Nov 2024 06.29 CET
The New Yorker: The G.O.P.’s Elon Musk Problem By Benjamin Wallace-Wells December 21, 2024
The New York Times, November 11
THE WASHINGTON POST, Putting Elon Musk’s post-election wealth surge into perspective, December 19, 2024
TIME vol. 204. Nos. 19-20 /2024