ከአንድ አመት ከሶስት ወር በፊት ያኔ ጋዛን የሚያስተዳድረው የሀማስ ቡድን በእስራኤል ላይ ድንገተኛ እና አስደናቂ ጥቃት ፈጸመ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመበት እለት የጥቃቱን ያህል አስገራሚ እና ታሪካዊ ነበር፡፡
ኦክቶበር 7 ቀን 2023
ልክ በዚህን እለት ማለት ኦክቶበር ሰባት 1967 ዓ.ም ግብጽ እና ሶርያ በ 1967 ዓ.ም በእስራኤል የተወሰዱባቸውን የጎላን ኮረብታ እና የሲናን ምድር ለማስመለስ ድንገታዊ ጥቃት በእስራኤል ላይ የከፈቱበት ቀን ነው፡፡ ያንን ጥቃት ተከትሎ የ17ቱ ቀን የእስራኤልና አረቦች አራተኛው ዙር ጦርነት ተካሄደ፡፡
ልክ ከ 57 አመት በኃላ ሀማስ እስራኤል ሳትዘጋጅ እና ሳትጠብቀው ኦክቶበር 7ቀን 2024 ጥቃት አካሄደባት፡፡ በዚህም ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሀማስ ተዋጊዎች ሮኬቶችን፣ እና ድሮኖችን በመጠቀም ጥቃት ፈጸሙ፡፡ በዚህም ጥቃት‘’ከ 1200 በላይ እስራኤላውያን እና የውጭ ዜጎች ’46 አሜሪካውያንን ጨምሮ ተገድለዋል፡፡ እንዲሁም ሀማስ 251 ሰዎችን በእገታ ይዟል’’ (Congressional Research Service, October 4, 20240)
በመሰረቱ ባለፉት 75 አመታት እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ እጅግ ሀይለኛዋ አገር ናት፡፡ በአካባቢው ከሚገኙ ሀገሮች እጅግ የላቀ እና በተግባር የተፈተነ መከላከያ ሰራዊት አላት፡፡ ይህም መከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ መሳርያ በደንብ የታጠቀ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የእስራኤል ስለላ ድርጅት ሺን ቤት በጣም ውጤታማ የሆነ የስለላ ተቋም እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ አነስተኛው አካል የፍልስጥኤሙ ድርጅት ሀማስ እንዴት ይህን የተሳካ ጥቃት ሊፈጽም በቃ?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በርካታ ምንጮችን አሰስን፡፡ ከሁሉም ዘ ኒው አረብ የተባለው ጋዜጣ በ 12/10/2023 እትሙ የዘገበው የተሻለ ስለመሰለን ከዚህ በታች አስቀምጠነዋል፡፡
የጋዛ ሰርጥ (ካርታ ጎግል)
አንደኛ – የእስራኤል-ጋዛ ወሰን አጥርን ጥሶ መግባት – ሀማስ ቡልዶዘሮችን፣ ፈንጂዎችን፣ ድሮኖች እና ሌሎች መሳርያዎችን በመጠቀም በደንብ የተመሸገውን የወሰን አጥር አፈራረሰው፡፡ ይህም ሀማስ ተዋጊዎቹን ወደ እስራኤል በእግር፣ በሞተር ብስክሌት እና ፓራግሊደርስ (Paragliders0 በመጠቀም ወሰኑን አቋርጦ ወደ እስራኤል ገባ፡፡
ሁለተኛ – ሀይለኛ ሮኬቶችን መተኮስ – ሀማስ በሺ የሚቆጠሩ ኃይለኛ ሮኬቶችን በተከታታይ ወደ እስራኤል ተኮሰ፡፡ ይህም አይረን ዶም የተባለው የእስራኤል የመከላከያ ስልት ትኩረቱን ወደ ድንበር ጥሰቱ እንዳያተኩር አደረገው፡፡
ሶስተኛ – ድሮኖችን መጠቀም – ሀማስ ድሮኖችን በማስወንጨፍ የእስራኤል መቆጣጠሪያ ማማዎች ስለሚካሄደው ተግባር የሁኔታዎች መረጃ ክፍተትን ፈጠረባቸው፡፡
አራተኛ – ቅንጅት እና ድንገቴ (ሰርፕራይዝ) – ጥቃቱ ቢያንስ ለበርካታ ወሮች በከፍተኛ ጥንቃቄና ዝርዝር የተሰናዳ በመሆኑ እስራኤል ተዘናግታ ድንገቴው እንዲደርስባት አድርጓል፡፡ የእስራኤል ደህንነት ተቋም የሀማስን ችሎታ አሳንሶ በመመልከት፣ በጣም በሚበልጠው የእስራኤል ሚሊታሪ ላይ እርምጃ ይወስዳል ብሎ አልገመተም ነበር፡፡
አምስተኛ – ታክቲካል እንቅስቃሴዎች – ወደ እስራኤል ዘልቀው እንደገቡ የሀማስ ተዋጊዎች የሲቪል ማህበረሰቦችን፣ የወታደራዊ ተቋማትንና፣ ቀኑ በእስራኤል የሀይማኖት በአል እንደመሆኑ ድግሶችን አልመው አጠቁ፡፡ በፍጥነትም እንደመንቀሳቀሳቸው ግርግር እና ከፍተኛ ድንጋጤ በፍጠር በርካቶችን አገቱ፡፡
ስድስተኛ – የማስጠንቀቂያ ስልት ድክመት – የእስራኤል የደህንነት ተቋማት ማለት ሺን ቤትም ሆነ የወታደሩ ኢንተለጀንስ አካል ጥቃቱ ስለመምጣቱ የሚያሳዩ ምልክቶችን መረዳት አልቻሉም፡፡ የጥቃቱ መጠንና መራቀቁ ተዘናጊ ሊያደርጋቸውና፣ ጥቃቱ ከደረሰም በኃላም ፈጥነው አጻፋዊ እርምጃ ለመውሰድ አላስቻላቸውም፡፡ (The New Arab)
እንግዲህ አሁን ጥቃቱ ከተፈጸመ አንድ አመት ከሶስት ወር በላይ ሆኖታል፡፡ በጃንዋሪ 16 2023 ሀማስና እስራኤል ከብዙ ውጣውረድ እና ሙከራ በኃላ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ቀጥለን መጀመርያ ጥቃቱ በእስራኤልና ሀማስ በተለይ፣ በአረብ-እስራኤል ግንኙነት በአጠቃላይ ያስከተለውን ውጤን እንመረምራለን፡፡ በሁለተኝነትም ስለ ስምምነቱም (ቸኮላችሁ አትበሉንና) ይዘት አጭር ማብራሪያእናቀርባለን፡፡
ሰቆቃወ ፍልስጥኤም
በፍልስጥኤም በኩል
ከ 7 ኦክቶበር 2023 ጀምሮ እስራኤል 46.707 ፍልስጥኤማውያንን ገድላለች 110.265 አቁስላለች፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ (አልጀዚራ 15 ጃንዋሪ 2024)
በሌላ በኩል በዚሁ ጊዜ በጋዛ ሰርጥ በምጣኔ ሀብት ረገድ የደሰው ጉዳት ማለትም ከ 7/10/2023 እስከ 20/5/2023 ብቻ የጋዛን ነፍስ ወከፍ ጥቅል ብሄራዊ ምርት (GDP per capita) በግማሽ ቀንሶታል፡፡ በሌላ በኩል ከ 7/10/2023 እስከ 1/2024 ድረስ ብቻ በመሰረተ ልማት የደረሰው ጉዳት 18.5 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ይህም ማለት የጋዛን 2022 ጂ ዲ ፒ ሰባት ጊዜ እጥፍ ማለት ነው፡፡ (UNCTAD Report (A/79/343)
በጋዛ በአሁኑ ወቅት መጠነ ሰፊ የሰብአዊ ቀውስ ሰፍኗል፡፡ ከፍተኛ ረሀብ እና በሽታ ጸንቷል
የጋዛ ውድመት
በወታደራዊ አቋም ከሄድን ሀማስ ከኦክቶበር 7/2023 ከነበረው አቋም አንጻር በጣም የደከመበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገባው፡፡ ዋና ዋና የወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎቹን አጥቷል፡፡ ለምሳሌም
1ኛ ኢስማዔል ሀኒያ ለረጂም ጊዜ የሀማስ ዋና መሪ
2ኛ ያህያ ሲንዋር ከፍተኛ የወታደራዊ አዛዥ እና የ ኦክቶበር 7 ቱ ጥቃት ቀያሽ
3ኛ ሳሌህ አል አራውሪ የኢስማኤል ሀኒያ ምክትል
4ኛ ማርዋን ኢሳ የሀኒያ ከፍተኛ የወታደራዊ አዛዥ
5ኛ መሐመድ ዲየፍ የእስማኤል ሀኒያ የቅርብ ረዳት፣ ነባር ታጋይ፣ ሰባት የመግደል ሙከራዎችን ያመለጠ (The Guardian)
በእርግጥ መሪዎች ሲገደሉ በሌሎች ታጋዮች ይተካሉ፡፡ ቢሆንም በአንድ ጊዜ ከአምስት በላይ ዋና ዋና መሪዎችን ማጣት ከባድ ጉዳት ነው፡፡ አገግሞ ወደፊቱ ይዞታ ለመመለስም ጊዜ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡
የጋዛ ነዋሪዎች አመት ከሶስት ወር ከፈጀው የእስራዔል ያላሰለሰ ጥቃት ከፍተኛ መማረር ያለባቸው ሲሆን፣ ለዚህ ምክንያት የሆነውን ጥቃት ምን ያህል ይደገግፉታል? በዚህም ሳቢያ የሀማስ በጋዛ ፍልጥኤሞች የነበረው ድጋፍ ሊቀንስ አይችልም ወይ?
በዚህ ረገድ ሀማስ የገጠመው ሁኔታ ከ አልቃይዳ ጋር በመጠኑም ቢሆን ይመሳሰላል፡፡ የ ሰብተምበር 2001 ጥቃት ኒውዮርክ ላይ ሲታቀድ አሁን የአል ቃይዳ መሪ የሆነው ሰይፍ አል አብደል ጥቃቱን ተቃውሞ ነበር ይባላል፡፡ምክንያቱም እንዲህ አይነት ከባድ ጥቃት ባንዴ ስንፈጽም፣ አሜሪካ ባለ ኃይሏ ስምታጠቃን በጣም ልንዳከም እንችላለን የሚል ነበር፡፡ በእርግጥም አሁን አል ቃይዳ በአሜሪካ ቋሚ ጥቃት እጅግ መዳከሙ የሚታይ ነው፡፡
ሀማስም በአንዴ እንዲያ ያለ ጥቃት እስራዔል ላይ ፈጽሞ በደሰበት ውርጅብኝ ቶሎ ያገግም ይሆን?
በእስራኤል በኩል
እስራኤልም በኩል አመት ከሶስት ወር በፈጀው በዚህ ጥቃት ጉዳት ደርሶባታል፡፡ በወታደራዊ በኩል 464 ወታደሮች ተገድለውባታል፡፡ እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ ደሞ በርካታ ወታደሮቿ ለስነልቡና ህመም ተዳርገዋል፡፡ በተጨማሪም
1ኛ እስራኤሎች በፍልስጥኤም ባደረሱትና እያደረሱት ባለው ሰብአዊ ጥፋትና ቀውስ በአለም ተወግዘዋል፡፡ ከአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥማቸው፣ ከአሜሪካም ጋር ቢሆን አለመግባባቶች አሉ፡
2ኛ ከገልፍ ስቴትስ በተለይም በሳዑዲ አረብያ ጋር ሊደረግ የነበረው ውል ቆሟል፡፡
3ኝ የአለም ፍርድ ቤት ናትናያሁንና የእስራኤልን የመከላከያ ሚኒስቴር በጦር ወንጀለኝነት ከሷል
4ኛ በእስራኤል ታጋቾቹን በተመለከ መንግስት ላይ ተቃውሞ ይካሄዳል
በወታደራዊ መስክም ቢሆን እስራኤል ጉዳት አስተናግዳለች
‘’የእስራኤል ባለስልጣኖች በጋዛው ጦርነት የሞቱ የ 840 ወታደሮችንና 69 ፖሊሶችን ስም ዝርዝር ይፋ አደረጉ፡፡ ከነዚህም መሀል ስድስቱ ኮሎኔሎች ናቸው፡፡ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ከፍተኛ መኮንኖች ሲገደሉ የአሁኑ ከፍተኛው ነው፡፡ 405 የእስራኤል መከላከያ ኃይል አባላት በምድር ውጊያ ተገድለዋል፡፡ (The Times of Israel)
የእስራኤል ካቢኔ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሲያጸድቅ ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል
በአሁኑ ወቅት ከብዙ ጊዜ ሙከራ በኃላ እስራኤልና ሀማስ በኳታርና ግብጽ ሸምጋይነት ጦርነቱን ለማቆም ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ስምምነቱ ለዘላቂ ሰላም መንገድ ከፋች ይሁን አይሁን ወደፊት የሚታይ ሆኖ፣ ለአሁኑ ግን የጋዛ ፍልስጥኤማውያን ሰቆቃ እረፍት ሊያገኝ መሆኑ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የስምምነቱ ዜና እንደተነገረ ፍልስጥኤማውያን ድጋፋቸውንና ደስታቸውን በሰልፍ ሲገልጹ ታይተዋል፡፡
በእስራኤል የድጋፍም የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡ ለማንኛውም ስምምነቱ ምን የይመስላል?
ስምምነቱ በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚካሄድ ነው እያንዳንዱም ምዕራፍ ስድስት ሳምንታትን ይፈጃል- ስለዚህም
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ። እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች። የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።
በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ይፈቀዳል።
በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና “ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት” ያለመ ሲሆን ይህም የሚተገበረው የመጀመሪያው ዙር 16 ቀን ሲሞላው ነው።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል። በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል። (BBC Amharic, Saturday 18 January 2025)
እንግዲህ በወረቀት ሲታይ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይህን ይመስላል፡፡ ስንክሳር በጋዛ ቋሚ ሰላም ሰፍሮ ፍልስጥኤማውያን እና እስራኤሎች በሰላም ወጥተው መግባት እንዲችሉ ምኞቷን ትገልጻለች፡፡
Al Jazaara 15 Jan 2024
Congressional Research Service, October 4, 20240
BBC Amharic, Saturday 18 January 20250
Economic costs of the Israeli occupation for the Palestinian people: the economic impact of the Israeli military operation in Gaza from October 2023 to May 2024 – UNCTAD Report (A/79/343
The Guardian October 17/20240 The Hamas and Hezbollah leaders killed by Israel since October 7/2023:…
The New Arab ; 12 October 2023
The Times of Israel: By Emanuel Fabian Follow, :8 October 2023, 2:30 pm Updated: 13 January 2025, 7:01 pm