እንግዲህ ጊዜው ስለረዘመ ትክክለኛ ቀኑን አላስታውሰውም ብቻ በሰብተምበር ውስጥ 1989 የአንድ ጓደኛዬ እናት ስላረፉ ለቅሶ ለመድረስ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ወደሚገኝበት መርቲ ከተማ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ነገሩን የሰማሁት አርብ ሲሆን ቅዳሜ ጠዋትን እረፍት ወስጄ እሑድ ለመምጣት በማሰብ አርብ እለት ለፈቃድ ከሰዐት አለቃዬ ቢሮ ሄድኩ፡፡
አለቃዬ አንድ የኒውስዊክ መጽሄት እያገላበጠ ሲመለከት ደረስኩኝ፡፡ የመጣሁበትን አስረድቼ አዎንታዊ መልስ ከተቀበልኩ በኃላ ወዲያው ከመውጣት ትንሽ ሌሎች ጉዳዮችን አንስቶ መነጋገሩ የጨዋ ደንብ ስለመሰለኝ ስለሚያነበው መጽሄት ጠየቅሁት፡፡
‘’ከጌታቸው ተውሼ እያየሁት ነበር፣ እንካ ዋና ዋና ነገሩን ማየት ከፈለግህ፣የተዋስኩት ትናንት ስለሆነ በኃላ እመልስለታለሁ’’ ብሎ መጽሄቱን አቀበለኝ፡፡
የፊት ሽፋኑ ላይ በውሃ ሰማያዊ መደብ ላይ አንድ ደማቅ ሰማያዊ ነገር ፣መሀሏ ላይ አንድ ትልቅ ደማቅ ጥቁር ነጥብ እና ሰማዩም ደመና ጣል ጣል ያለበት ግዙፍ የቀላይ አካል ፎቶ አየሁ፡፡ ከስሩ ‘’ኢንካውንተሪን ዘ ብሉ ፕላኔት- ኔፕቹን’’ የሚል ጽሁፍ አለው፡፡ ስለ ፕላኔቷ ኔፕቹን መሆኑ ነው ፡፡ ሰማያዊ ነች እንዴ?
ነገሩ አጓጓኝና ትንሽ ዋና መልዕክቱን ሳነብ፣ ቮያጀር የምትባል የናሳ መንኮራኩር ኔፕቹን ደርሳ ያነሳችው የፕላኔቷ ፎቶ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ለንዲህ አይነት ዜናዎች ስስ ልብ ስላለኝ ሳላውቀው ንብቤን ቀጠልኩ፡፡ ሆኖም አለቃዬ ጉሮሮውን ጠራርጎ ሲስል ከመጽሄቷ ቀና አልኩ፡፡
‘’ይቅርታ ነገሩ ስለመሰጠኝ ንባቤን ቀጠልኩ፣ አይደል?’’ ብዬ መለስኩለት፡፡
ማንበብ እንደማዘወትር ስለሚያውቅ አልተቆጣም
‘’እኔ ጨርሼዋለሁ፣ እንካ እንዲያውም ለጌታቸው አመስግነህ መልስልኝና አንተ ደሞ በተራህ ጠይቀው’’ ብሎ መጽሄቷን ሰጠኝ፡፡ አመስግኜው ወደ ጌታቸው ቢሮ ሄጄ እንዲያውሰኝ ጠየቅሁት
‘’እናንተ ሰዎች እኔ ገና ከፖስታ ቤት እንዳመጣሁት ሻምበል ልየው ብሎ ወሰደብኝ፡፡ አንተ ደሞ ልዋስ ትላለህ፡፡ ባይሆን እኔ ቅዳሜና እሁድን ልደበርበት እና ሰኞ እሰጥሀለሁ’’
ባለፈው አመት የስራ ባልደረባዬ ጌታቸው ሁለት ወር ለሚፈጅ ጊዜ አጭር የስራ ስልጠና እድል አግኝቶ ለንደን ሄዶ ነበር፡፡ እናም ሲመለስ የኒውስዊክን መጽሄት የአመት ደንበኛ ሆኖ ነበር የመጣው፡፡ በዚህም መሰረት በየሳምንቱ በፖስታ ቤት ሲልኩለት እሱ ካነበበው በኃላ ያውሰኝ ነበር፡፡
‘’እየውልህ ጌቾ ነገ መተሐራ መንገደኛ ነኝ እሑድ እመለሳለሁ፡፡ በአውቶቡስ ውስጥ የማሳልፋቸውን ረዣዢም ሰአታት እንዴት እንደማሳልፋቸው እያሰብኩ ነው መጽሄቷን ያገኘዃት፡፡ እባክህ?’’ ብዬ ሙዝዝ ስላልኩበት አዋሰኝ፡፡
ማታውኑ ከመተኛቴ በፊት ትንሽ መጽኄቷ ላይ ያጓጓኝን ክፍል ገረፍ ገረፍ አድርጌ ለመተኛት ሞከርኩ፡፡
ግና ገረፍ ገረፍ አድርጌ የማልፈው አልሆነም ፡፡ አንደኛ ብዙ ነው፣ ሁለተኛ በጣም የሚስብ ነው፡፡ ጽሁፉ የመጽሄቱን አብዛኛውን ክፍል ከመያዙም ብዙ የማላቃቸውን አስደናቂ ነገሮች ይዟል፡፡ ይዘቱ ስለ ኔፕቹን ብቻ አይደለም፣ ይበልጡኑ ጽኁፉ የሚያትተው ከመሬት ተተኩሳ ሁለት ሚሊዮን ኪሎሜትሮችን በአምስት አመት አቋርጣ ኔፕቹን በመድረስ ፎቶ አንስታ በመላክ ኔፕቹን እንደመሬት ቀለሟ ሰማያዊ መሆኑን ስላበሰረችው የጠፈር መንኮራኩር ስለ ቮያጀር ሁለት እና ስለ መንትያዋ ቮያጀር አንድ ነው፡፡
ሁለተኛ ክፍል እያለን አለምን በእግሩ ስለዞረው ኢብን ባቱታ ያነበብኩት ትዝ አለኝ፡፡ በዚያ እድሜያችን የሱ አለምን ለመዞር መነሳቱ ሲያስደንቀን ነበር፡፡ አሜሪካኖቹ ስርዐተ-ጸኃይን የምታካልል ነገር ሰርተዋል ለካ !
እንግዲህ ባለፉት አምስት አመታት ስለዚህ ጉዳይ ምንም መረጃ አልነበረኝም፡፡ ያኔ ኢንተርኔት የለም፣ የቀረ ቀርቶ አለምአቀፍ ተደራሽነት ያላቸው መገናኛ ብዙሀን ገና አገራችንን አላጥለቀለቋትም፡፡ ታድያ ይሄን ባላቅ ይፈረድብኛል?
ማታውን አገባድጃት አደርኩ፡፡ ነገሩ ጣመኝ ድገመኝ ሆነና በጉዞዬም መጽሄቷን ይዤ መሄድ ደከምኳት፣ ሰለስኳት፡፡ ስንት አጅኢብ ነገር ይዛለች አቦ !!
ከዚያ በኋላ ጊዜና አጋጣሚው በፈቀደልኝ ሁሉ የቮያጀሮችን ጉዞ መከታተል ጀመርኩ ፡፡ በልጅነቴ እሁድ እሁድ ጠዋት ሶስት ሰዐት ተኩል ላይ ይተላለፍ የነበረውን ‘’ሳይንስና ሕይወት’’ የሚል ፕሮግራም እከታተል ነበር፡፡ በልጅነቴ እንደ እኩዮቼ ውጭ ወጥቼ መጫወት ብዙም ስለማይፈቀድልኝ የነበረኝ ዋነኛ የጊዜ ማሳለፊያዎቼ ሬድዮና ንባብ ነበሩ፡፡ ከሬድዮ መርሐ-ግብሮች መካከል ይህ የሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ዝግጅት የማላልፈው ነበር፡፡ ሻምበሉ ጥዑም በነበረው ድምጹ ሰለ ፕላኔቶች፣ጨረቃ፣ የአፖሎ የጨረቃ ጉዞ እና የመሳሰሉትን ያስደምጠን ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ ሕዋ እና ስለ ሕዋ አካላት ትንሽ ፍላጎት አሳደረብኝ፡፡
እነ ኒል አርምስቶርንግ ጨረቃ ላይ ሲያርፉ ዕውቁ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ እንደ ኳስ ጨዋታ በቀጥታ ለአስር ደቂቃ ያህል አስተላልፏል፡፡ እንደማስታውሰው ጠዋት ላይ ነበር ፣ ስለዚህ ወይ እሱ ሲያርፉ በቀጥታ እያየ የተከታተለውን በድምጽ ቀድቶ ይሆን ወይም ልክ ያኔ እንዳረፉ ነበር ቀጥታ ነበር ያስተላለፈው አላውቅም፡፡
እንደገና በሰፊው ስለ ቮያጀሮች ጉዞ በደንብ የተከታተልኩትና መረጃ ያገኘሁትን ግን የነጻ ትምሕርት እድል አግኝቼ ኑሮዬ በቤልጀየም ከሆነ በኃላ ነው፡፡ በተለይም በ 1999 እ.ኤ.አ « ዘ ፕላኔትስ » በሚል ርዕስ ቢቢሲ ያቀረበውን ዘጋቢ ፊልም ካየሁ በኃላ በይበልጥ ብዙ ነገሮች ስለ ቮያጀር ተልዕኮዎች ግልጽ ሆነልኝ፡፡
እንግዲህ በዚህ መጣጥፍ ስለ ቮያጀሮች የማቀርበው የተገኘው ከዚህ የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም፣ ከናሳ መጣጥፎች፣ከብሪታኒካ ኢንሳይክሎፔድያ፣ ፣ ከቢቢሲ እና ከተለያዩ ከዩቲዩብ ከቀረቡ ዘጋቢ ፊልሞች የተቀነበቀበረ ነው፡፡
ክፍል አንድ የቮያጀርስ መርሐ–ግብር ምንድነው?
መንታዎቹ የቮያጀር መርሐ-ግብር የተጸነሰው በ 1960 ዎቹ ሲሆን አላማውም ራቅ ያሉትንና ግዙፎቹን ፕላኔቶች ለማሰስ ነው፡፡ መንኮራኩሮቹ መጀመርያ የታቀዱት ጁፒተርና ሳተርን፣ የሳተርንን ቀለበቶች እንዲሁም የነዚህን ሁለት ፕላኔቶችንና ትላልቅ ጨረቃዎቻቸውን ለማሰስ ነበር፡፡
ይህን ጉዞ ለማድረግ ይቻላል ወደሚል መደምደሚያ የተደረሰው
‘’ግራቪቲ አሲስትድ ማኖቨር’’ የተባለ አዲስ የህዋ ጉዞ ስልት ስለተገኘ ነበር፡፡
ይህ አዲሱ ዘዴ በስበት ኃይል የተደገፈ በረራ ተብሎ በአማርኛ ሊገለጽ ይችላል፡፡ እንግዲህ ፕላኔቶች በጸኃይ ዙርያ ሲሽከረከሩ ስበታቸው የሚፈጥረው ማዕበላዊ ኃይል እና ንቅናቄ አንድን የጠፈር መንኮራኩር በወንጭፍ ውስጥ እንዳለ ድንጋይ የማስፈንጠር ሁኔታን ስለሚፈጥር መንኮራኩሩ በተፈለገው አዲስ አቅጣጫ፣ በበለጠ ፍጥነትና በትንሽ ተጨማሪ የኃይል ፍጆታ ተተኩሶ እንዲበር የማድረጉ ስልት ነው በስበት ኃይል የተደገፈ በረራ የተባለው፡፡ ይህ ዘዴ በነቢብ ተጠንስሶ የማሪነር አስር መንኮራኩርን ወደ ሜርኩሪ በበለጠ ፍጥነትና በትንሽ ወጪ በማስኬድ ነቢቡ በፈቲነ ግብር ውጤታማነቱ ተረጋገጠ፡፡
ከዚህ በኃላ ነው እንግዲህ የጠፈር ተመራማሪዎች አንድን የጠፈር መንኮራኩር አርቆ ወደ ትልልቆቹና ሩቅ ፕላኔቶች ለማስወንጨፍ ማሰብና ማቀድ የጀመሩት፡፡ እስከዚያ ድረስ (1960) የጠፈር መንኮራኩሮች የሚላኩት ወደ ድንጋያማና ቅርብ ፕላኔቶች ማለትም ሜርኩሪ፣ ቬኑስና ማርስ ብቻ ነበር፡፡ በርግጥ የኃላ ኃላ እስከ ጁፒተርም በቀጥታ ከመሬት ማስፈንጠር ተችሏል፡፡ ከዚያ በላይ ግን አይታሰብም፡፡
ይሁንና የቮያጀርስ ተልዕኮ የተጸነሰውና ሊጀመር የበቃው ግን በዚህ ግኝት ብቻ አልነበረም፡፡
በመሰረቱ ሳይንስ ለአንድ ጥያቄ ወይም ችግር መልስ ወይም መፍትሄ ለማግኘት መጀመርያ የተለያዩ መላምቶችን ያስቀምጣል፣ ከዛ መላምቶችን በፈቲነ-ግብር ይሞክራል፣ የተሳካ የሆነውን ፈቲነ-ግብር ተከትሎ ነቢብ ይፈጥራል፡፡ መጠይቅ – ሀይፖተስስ – ኤክስፐሪመንት – ቲዎሪ
አንድን ጥያቄ ወይንም ችግር በዚህ ዘዴ ስናጠና እና መፍትሄ ወይም ነቢብ ስናወጣ አካሄዳችን ሳይንሳዊ ነው ይባላል፡፡ ከዚህም ተነስቶ ነው ፖለቲካል ሳይንስ ወይንም ማህበራዊ ሳይንስ የሚለው አገላለጽ ጥቅም ላይ የሚውለው፡፡
እንዲያም ስለተባለ ሳይንቲስቶች ሁሉም ጥያቄዎችና ችግሮች በዚህ ስልት ብቻ መፍትሄ ላይ ይደርሳሉ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዴ በእድልም አዲስ መፍትሄ ወይም ነቢብ ስራ ላይ ሊውል ይችላል፡፡
በቮያጀር አጀማመር ላይ የሆነውም ተመሳሳይ ነው፡፡
ጌሪ ፍላንድሮ የተባለ ብልህ ተማሪ የሶስተኛ ዲግሪውን መጣጥፍ አቅርቦ ምርምሩ ይበል ተብሎለት ለመመረቅ ሁለትና ሶስት ወር መጠበቅ ነበረበት፡፡ አሁን ተለውጦ እንደሆ አላውቅም እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት የሶስተኛ ዲግሪ ጽሁፍን ካቀረቡ በኃላ ዲግሪው የሚሰጠው ሁለትና ሶስት ወራት ዘግይቶ ነበር፡፡
እንዲያውም ብዙ ኢትዮጵያዊ ምሩቆች ጽሁፋቸውን እንዳጠናቀቁ ዲግሪያቸውን ሳይቀበሉ ወደ ሀገራቸው ይመለሱ እንደ ነበር የሩቅ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በኃላ በፖስታ ነበር ዲግሪያቸው የሚላክላቸው፡፡ እንዳሁኑ ዲግሪውም ተቀብሎም ቢሆን የማይመለስ ትውልድ በበዛበት ይህን ማመን ይቸግር ይሆናል፡፡
ለማንኛውም
በ 1964 የበጋ ወራት የናሳ ጄት ፕሮፐልሺን ላቦራቶሪ (ጄ ፒ ኤል) ለጌሪ ፍላንድሮ የአራቱ ግዙፍ ፕላኔቶችን ማለትም ጁፒተር ሳተርን ዩራኑስና ኔፕቹን በህዋ ውስጥ በዚያን ወቅት ያሉበትን ቦታና የጉዞ አቅጣጫ አጠንቶ ዘገባ እንዲያቀርብ የበጋ ስራ (ሰመር ጆብ) ሰጠው፡፡
ፍላንድሮ የፕላኔቶቹን ቦታና የሚከተሉትን አቅጣጫ በእርሳስ የስዕል ወረቀት ላይ በጥንቃቄ ሲስል አንድ ነገር ፍንትው ብሎ ታየው፡፡ ፕላኔቶቹ ያሉበት ቦታና መጓዝ የያዙት አቅጣጫ 1970 ዎቹ መጨረሻ ተመሳሳይ መሆኑ፡፡
ፈጣኑ የፍላንድሮ ጭንቅላት ወዲያው የመጣለት ሀሳብ አራቱንም ፕላኔቶች ከአስር አመት ብዙም ባልበለጠ ጊዜ በአንድ ጉዞ ለማዳረስ መቻሉ ነው!!!
ይህ የፕላኔቶች ጥምረት በ 176 አመት አንድ ጊዜ የሚያጋጥም ክስተት ነው፡፡
ቢንጎ!!
በተጨማሪም ይህ የታወቀበት ጊዜ ፕላኔቶቹ በአንድ አቅጣጫ መንጎድ ከሚጀምሩበት ጊዜ በአስር አመታት ቀደም ብሎ በመሆኑ በቂ የዝጅግት ጊዜ ነበረ፡፡ ይህንንም ለማድረግ በስበት ኃይል እገዛ በሚደረግ ማስወንጨፍ አራቱንም ፕላኔቶች መጎብኘት ይቻላል፡፡
በዚህም የትልቁ ጉዞ (ገራንድ ቱር) ተጸነሰ
ጋሪ ፍላንድሮም ለዚህ ግኝቱ የቅድሚያ እውቅና የሰጠው የብሪትሽ በይነ-ፕላኔታዊ ማሕበር (ብሪትሽ ኢንተርፕላኔታሪ ሶሳይቲ) ሲሆን እሱም በ1970 ኤም. ኤን ጎሎቪን የተሰኘውን ሽልማት ሰጥቶታል፡፡ ሰንብቶም ናሳ በ 1998 “የ ዘርፈ ብዙ የሩቅ ፕላኔቶች ተልዕኮ ንድፍና ኢንጂነሪነግ (ለቮያጀሮች ታላቁ ጉብኝት የምርምር ጎዞን ጨምሮ) ላበረከተው ሁሉ የላቀ ስኬት ሜዳይ በመሸለም አክብሮ አስከብሮታል፡፡
የትልቁ የምርምር ገዞ (ግራንድ ቱር) ጽንሰ ሐሳብ ምንድነው?
ግዙፎቹ ፕላኔቶች አንድ አካባቢ የመገኘታቸውን አጋጣሚ በመጠቀም በአንድ ጊዜ ግን በሁለት መንኮራኩሮች በ 1970 ዎቹ ከጁፒተር አንስቶ ሳተርንና ዩራኑስን ይዞ እስከ ኔፕቹን የሚደርስ ጉዞ በማድረግ አስፈላጊውን ምርምር ማድረግ ነው፡፡
ግን ይህንን በአይነቱ የመጀመርያ የሆነ ከምድር እስከ አምስት ቢሊዮን ኪ/ሜ የሚጠቀልል ከአስር አመት በላይ ሊፈጅ የሚችል ጉዞ ማድረግ ብዙ ችግር ያለበትና ስኬቱም እስከዚህ አስተማማኝ ስላልሆነ ናሳ ሁለት የጥንቃቄ እርምጃዎችን ወሰደ፡፡
በመጀመርያ ደረጃ ቢያንስ እስከ ሳተርን ያለውን ጉዞ የሚያስሱ ፋና ወጊ መንኮራኩሮችን መላክ፡፡ ሁለተኛም ለዋናው ጉዞ አንድ ሳይሆን ሁለት መንኮራኩሮችን መላክ ወሰነ፡፡
በጣም የተፈራው ደሞ መንኮራኩሮቹ በማርስና በጁፒተር መሐል የሚገኘውን የአስትሮይድ ቀለበት (ቤልት) በመባል የሚታወቀውን ቦታ አለችግር ማለፍ ይችላሉ ወይ የሚል ነው፡፡ አስትሮይድ ቤልት የቱቦ ቅርጽ ያለው አካባቢ ሆኖ በውስጡ በርካታ ጠጣርና ያልተወሰነ ቅርጽ ያላቸውን አስትሮይዶች ያቀፈ ነው፡፡ ስለዚህም አንድ መንኮራኩር በማርስና በጁፒተር መካከል ሲያልፍ ከነዚህ ድንጋዮች ቢጋጭ ጭራሹኑም ከጎዞው ሊሰናከል አነስ ሲልም ከመሳርያዎቹ የተወሰኑት ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ ይፈራል፡፡
በዚህም መሰረት ፒዮኔር 10 እና 11 የተባሉ አሳሽ ፋና ወጊ መንኮራኩሮች በ ማርች 2 ቀን 1972 (ፒኔዮኔር 10) እንዲሁም አፕሪል 6 ቀን 1973 (ፒዮኔር 11) ከኬኔዲ የህዋ ማዕከል ተመነጠቁ፡፡ ጁላይ 15 ቀን 1972 ፒዮኔር 10 የአስትሮይድ ቤልቱ ውስጥ ገብታ በፌብርዋሪ 15/1973 ምንም ችግርና ጉዳት ሳያጋጥማት ተሻግራው ወጣች፡፡
ይህም ማለት ቦታው ለመንኮራኩሮች አደገኛ ያልሆነ ነው ማለት ነው፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው የፒዮኔር 10 እና 11 ተልእኮ
- ከማርስ ባሻገር ያለውን ቦታ መፈተሸ
- በማርስና ጁፒተር መካከል የሚገኘውን አስትሮይድ ቤልት መርምሮ ወደፊት ለሚላኩ መንኮራኩሮች የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ማሳወቅ
- የጁፒተርና ሳተርን ሁኔታ ማጥናት
- ከተቻለም የጸኃይን ድንበርና ከድንበሩም ተሻግሮ ያለውን ሁኔታ አጥንቶ መረጃ መላክ ነበር፡፡
ከነዚህ ተልዕኮዎች የተገኘው መረጃ ለቮያጀር ስለ አስትሮይድ ቤልቱ ከላኩት መረጃ፣ በተጨማሪ መንኮራኩሮች ግንባት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አንዳንዴም በግንባታቸው መካከል ለውጥና መሻሻል እንዲደረግ የፒዮኔር አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ የፒዮኔር ተልዕኮ የቮያጀሮችን፣ የጋሌሊዮ እና የካሲኒ መንኮራኩሮችን መሰረት በመጣል ረገድ ትልቅ እርዳታ አድርገዋል፡፡
እሺ! አሁን እንግዲህ ቮያጀሮቹ ወደ ህዋ ይህን ሁሉ ርቀት አቋርጠው፣ አራት ግዙፍ ፕላኔቶች ጋ የሚደርሱት እንዴት ነው?
መጀመርያ በጊዜው ባለው ሮኬት የማስወንጨፍ ችሎታ መንኮራኩሩን ጁፒተር ማድረስ ይቻላል፡፡ ከዚያ በጥንቃቄና በፍጹም ስሌት መንኮራከሩ ጁፒተር የስበት ማዕበሉን በሚያስኬድበት መንገድ በትክክለኛው ጊዜ እንዲደርስ ይደረግና ሲደርስ የስበት ማዕበሉ መንኮራኩሩን ሳተርን ድረስ ያስወነጭፈዋል፡፡ በተመሳሳይ ጉዞውን መጥኖ በመቀየስ ሳተርን ከባቢ በትክክለኛው አቅጣጫ እና ጊዜ ሲደርስ -ወደ ኡራኑስ ይመነጠቃል – ከኡራኑስ በተመሳሳይ ወደ ኔፕቹን እንዲሁ ይደረስና ከኔፕቹን ከስልተ-ጸኃይ ወጥቶ ወደ በይነ-ከዋክብት አለም ጭልጥ!!
በነገራችን ላይ አሁን ቮያጀሮቹ ያሉት በዚህ ቦታ ነው
እንግዲህ ያኔ ሰለ ሩቆቹ ፕላኔቶች ብዙም የታወቀ ነገር አልነበረም። የቀረ ቀርቶ ስለ ድንጋያሞቹ የቅርብ ፕላኔቶች እንኳ የበረው መረዳት ይህን ያህል አይደለም :: የጊዜው ቴሌስኮፖችም ቢሆኑ ደከም ያሉ ነበሩ ፡፡ ቮያጀሮቹ የሚያከናውኑት ተግባር እጅግ የረቀቀ ሆኖ ነበር የተዘጋጀው ፡፡ ጁፒተር ደርሰው ዞረው በሚያልፉበት ቅጽበት የፕላኔቱን መልክ፣የከባቢ አየሩን ይዘት እና እንቅስቃሴ፣ የፕላኔቱን ኬሚካልና ፊዚካል ይዘት፣ የስበቱን ግፊት፣ኃይልና አካባቢያዊ ተጽእኖ፣ እንዲሁም በቅርቡ የሚገኙትን ጨረቃዎች ፎቶ፣ ኬሚካልና ፊዚካል ይዘት እና የመሳሰሉትን አጥንቶ በዳታ እና በፎቶ ወደ ምድር ይልካሉ፡፡ በተመሳሳይም ሳተርን ከነቀለበቶቹ እና ትልቁ ጨረቃውን ቲታንን፣ ቀጥሎም ዩራኑስንና ኔፕቹን በተመሳሳይ እያጠኑ ፎቶ እና ዳታ ያስተላልፋሉ፡፡ ከዚያም ወደ ተለያዩ የጸኃይ ስልት መውጫ ደረጃዎች ያለውን ነገር፣ የጸኃይ ስበት የሚያልቅበት አካባቢ እና ነቁጥ ላይ ያለውን ሁሉ እየመዘገቡ ይልካሉ፡፡
በጣም የገረመኝ ግን ይህ ሁሉ ሳይበቃ ከዚህ ከምድር መቆጣጠሪያ ጣቢያ ማለትም ጄት ፕሮፐልሽን ላቦራቶሪ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ያከናውናሉ፡፡ ለምሳሌ ቮያጀር አንድ የፕላኔቶችን ድንበር እንደተሻገረች ካሜራዎቿን አዙራ ሁሉንም ፕላኔቶች ፎቶ አንስታ እንድትልክ ስትታዘዝ ስድስት ሜትር ርቀት ያለው አልፋቸው የሄደችውን ፕላኔቶች (የቤተሰብ ፎቶ) አንስታ ልካለች፡፡
በኦገስት 25 ሀያ ሀያሁለት አመተ ምህረት ቮያጀር አንድ ስርአተ ፀኃይን አልፋ በይነ ከዋክት (ኢንተርስቴላር) ህዋ ላይ ስትገባ እህትዮዋ ቮያጀር ሁለት በኖቨምበር 5 ሀያ አስራዘጠኝ እዛው ቦታ ላይ ደርሳለች ፡፡
በሜይ 24 ሀያ ሀያአራት ቮያጀር አንድ ሰዐት 61.198 ኪ/ሜ እየከነፈች ከምድራችን 24.2 ቢሊዮን ኪ/ሜ ርቀት ላይ ስትደርስ እሕትየዋ ቮያጀር ሁለት ደግሞ በሰዐት 55.347 ኪ/ ሜ እየበረረች ከእናት መሬታችን 20.4 ቢሊዮን ኪ/ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
ከ47 አመት ጉዞ በኃላ ማለት ነው፡፡
ይህን ሁሉ መረጃ ከዚህ ሁሉ ርቀት ላይ የሚያስተላልፉትን መረጃ የሚቀበሉ በተለያየ የአለማችን ክፍሎች ዲፕ ስፔስ መቀበያ ሰሀኖች ተሰርተው ይተከላሉ፡፡
ቮያጀሮቹ የሚያስተላልፉትን መረጃ ለመቀበል ለዚሁ ሲባል የተለያዩትን ሲግናሎች ገጣጥመው በተገጠመላቸው ልዩ አንቴናዎች የሚቀበሉ ትልልቅ ሰሐን መሰል መሳርያዎች በጎልድስቶን (ካሊፎርኒያ)፣ በካምቤራ (አውስትራሊያ) እና በማድሪድ (ስፔይን) ተሰርተዋል፡፡
ክፍል ሁለት የቮያጀር መንኮራኩሮች ይዞታ
ከላይ የጠቀስናቸውን እጅግ ውስብስብና ከባድ ተግባሮችን ለመከናወን መንኮራኩሮቹ ምን አቋም ነበራቸው? እያንዳንዱ የቮያጀር መንኮራኩር 773 ኪ/ግ ክብደት አለው፣ከዚህም ውስጥ 105 ኪ/ግራሙ የተለያዩ ሳይንሳዊ መሳርያዎች ናቸው፡፡ እንዚህን መሳርያዎች በጥቅሉ ለማስተዋወቅ-
- ኤሜጂንግ ሳይንስ ሲስተም ማለትም ፎቶዎችን የማቀነባበር ስልት (ስርዐት)፣ በዚህ ውስጥ ረዥምና አጭር አንግል ያላቸው ፎቶ ማንሻዎች ይገኛሉ
- የራዲዮ ሳይንስ ሲስተም – ይህ ደግሞ የፕላኔቶችን ቁሳዊ ባህርያት ይመለከታል
- ኢንፍሬድ ኢንትፌሮሜትር ስፔክቶሜትር – ይህ መሳርያ አካባቢያዊ እና ሁላአቀፍ (ግሎባል) ኃይል ሚዛን እና የከባቢ አየር ቅንብርን (አትሞስፊሪክ ኮምፖዝሽን) ይመረምራል፡፡
- ልዕለ-ሐምራዊ ስፔክቶሜትር (አልትራቫዮሌት ስፔክቶሜትር)
- ማግኔቶሜትር – የየፕላኔቶቹ መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) እና እሱም ከጸኃይ ነፋሳት ጋር ያለውን መስተጋብር ያስተነትናል፡፡
- የደምውኃ (ፕላዝማ) ስፔክቶሜትር – የፕላዝማ አዮንን ማይክሮስኮፒክ ባህርያት ይመረምራል፡፡
- ሎው ኢነርጂ ቻርጅድ ፓርቲክልስ ዲቫይስ – የ አዮንን ፍሉክስስ እና ስርጭት ይለካሉ፡፡
- የአለማይ ጨረር ዲቴክሽን(ኮስሚክ ራዲዬሽን) ሲስተም – የአለማይ ጨረርን መገኛ እና ባሕርያት ያጠናል፡፡
- ፕላኔታሪ ሬድዮ አስትሮኖሚ ኢንቨስቲጌሽን – የጁፒተርን ሬድዮአዊ ልቀትን (ሬድዮ ኢሚሽን) ይለካሉ፡፡
- ፎቶፖላሪሜትር – የየፕላኔቶችን ምድራዊ ቅንብርን (ሰርፌስ ኮምፖዚሽን) ይለካል፡፡
- የደም-ውሀ ማዕበል ሲስተም – የየፕላኔቱን ሜጋቶስፌር ያጠናሉ፡፡
- ኮምፒዩተርስና ዳታ ሲስተም – የተለያዩና የተራቀቁ ኮምፒዩተርና ዳታ ሲስተሞች ስራቸውን በጥራት እንዲያከናውኑ እንዲረዱ የተገጠሙላቸው ስልቶች ፡፡
በነዚህ መሳርያዎች ቮያጀሮቹ ስራቸውን ሲያከናውኑ፣ ለአጠቃላዩ ሰራቸው የሚጠቀሙበት ኃይልስ?
የኃይል ምንጭ
እንግዲህ እንኳን ሀያ እና ሰላሳ አመት ሳያቋርጡ በከፍተኛ ፍጥነት በመብረር ከላይ የጠቀስናቸውን ስራዎች ለመስራት ቀርቶ ከአዲስ አበባ ናዝሬት ለመሄድ እንኳን የመኪናችንን ነዳጅ በሚፈለገው መጠን መሞላቱን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ መቸም ይህን ሁሉ ርቀት ለመሄድ የሚያስችል ነዳጅ መሸከም አይታሰብም፡፡ የጸኃይን ኃይል መጠቀም ቢሆን ከጁፒተር በኃላ የጸኃይ ኃይል እየደከመ ስለሚሄድ ተመራጭ አይሆንም፡፡
ለቮያጀሮቹ የኃይል ምንጩ ራድዮሶቶፕ ቴርሞኤሌክትሪክ ጄኔሬተር ነው (አር ቲ ጂስ) ሲሆን ይህም እንግዲህ ከሬድዮአክቲቭ ዲኬይ ፕሉቶኒየም 238 ሙቀትን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመቀየር ነው፡፡ ቮያጀሮቹም ለዚህ ጉዳይ ተዘጋጅቶ በተገጠመላቸው ደቦልቧላ ታንከር ህይድራዚነ ሞኖፕሮፕላንት ነዳጅ ተሞልቶላቸዋል፡፡ ይህም መሳርያዎቿን እስከ 2025 ሊየሰራቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከዚያ በኃላ ግን መሳርያዎቹ አንድ በአንድ ከመሬት እንዲጠፉ ይደረጋሉ፡፡
ቮያጀር አንድ የጠፈር መንኮራኩር
የኮሚኒኬሽን ጉዳይ
በነዚህ ሁሉ መሳርያዎች አማካይነት የሚያገኙትን መረጃ እና ምስሎች ወደ ምድራችን እንዴት ያስተላልፋሉ? በመሰረቱ የቮያጀር ጉዞ ገና ሲተለም አንዱ ጥያቄ ይህ ነበር፡፡
መረጃዎችን እና ግንኙነቶችን ለማሳለጥ ሁለት ረጃጅም (3.7ሜትር) እና ትልቅ አንቴናዎች ተገጥመውላቸዋል፡፡ አንዱ ወደላይ – ወደ ፕላኔቶችና ከዋክብት ፣ ሌላው ወደታች – ማለትም ወደ ምድር ተደግኖ መልዕትና ምስል የሚተላለፍበት፡፡ በነዚህም መልእክት ከቮያጀሮቹ ወደ ምድር የሚላክበት ብቻ ሳይሆን ከምድር መቆጣጠሪያው ትዕዛዝና መመሪያ ይላክበታል፡፡
ወርቅ ቅብ ሸክላ ማጫወቻ
The Voyager Golden Record
Cover of the Voyager Golden Record
እንግዲህ መንኮራኩሮቹ ምናልባት (ቢሰበር አናት) በዚህ ረዥም ገዞአቸው ላይ ከሌላ የሰለጠኑ ፍጡራን ጋር ከተገናኙ ተብሎ በግንባታቸው መጨረሻ ግድም በሁለቱም መንኮራኩሮች ውስጥ ልዩ ልዩ ምስሎች (ተንቀሳቃሽም፣ ፎቶም) እና ድምጾች የተቀረጹባቸው ሰላሳ ሴንትሜትር ሸክላ ማጫዎቻዎች ተገጥመውባቸዋል፡፡
አንደኛው ሸክላ የምድርን ጽምጽ ና ምስሎች (ሳይት ኤንድ ሳውንድ) የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ወርቅ ቅብ ነሐስ ሸክላ ደሞ ዋናው ሸክላ እንዴት እንደሚነበብ ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡
እነዚህን ሁለት ማጫወቻ ሸክላዎችና በውስጣቸውም የሚይዙትን ለመወሰንና ለማጠናቀር ናሳ አንድ፣ በታዋቂው የጠፈር ምርምር ሊቅ ካርል ሴጋ የሚመራ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር፡፡ ኮሚቴው ስራውን ለማጠናቀቅ አመት ወስዶበታል፡፡ በዚህም 116 ምስሎችና የተለያዩ ተፈጥሯዊ ድምጾች ተካተውበታል፡፡
ለምሳሌ ድምጾቹን የወሰድን እንደሆነ የማዕበል፣ የንፋስ፣ ሞገድ፣ መብረቅ፡፡ የወፎች ዝማሬ፣ የተለያዩ እንስሳት ድምጾች፡፡ የሚወለድ ሕጻን ለቅሶ ፣በ55 ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሰላምታዎች፡፡ በጊዜው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸኃፊ ኩርት ቫልድሀይምና የካርል ሴጋ ስድስት አመት ልጅ ኒክ በእንግሊዝኛ ያስተላለፉት የድምጽ መልዕክት፣ እንዲሁም የጊዜው የአሜሪካ ፕሬዚዴንት ጂሚ ካርተር የጽሁፍ መልዕክት፡፡ የእግር ኮቴ፣ ሳቅ እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የተወሰዱ ሙዚቃዎች ይገኙበታል፡፡
ከስዕል/ፎቶ መካከል ደግሞ – ባለ ቀለም እና ጥቁርና ነጭ ስዕሎች/ፎቶዎች፡፡ ስርዐተ-ጸኃይ ከነፕላኔቶቹ፣ የሰው ውስጣዊ አካል እና ውልደት፡፡ የሚመገብ ሰው፣ሽል ህፃን፣ እርጉዝ ሴት፤ በሩጫ ውድድር ላይ ያሉ ሰዎች፣ ጫካ፣ መሬት በህዋ ውስጥ የምትገኝበትን ነቁጥ እና የመሳሰሉትን ያሳያል፡፡ የተለያዩ እንስሳት አእዋፋት ተክሎች ተራራና ሸንተረር ወንዝ..ምግብ ነደቅተ ጥበባት (አርኪቴክቸር) እና የመሳሰሉ ወካይ ቁሳዊ ስዕላትና ምስሎችን ያጠቃላላሉ፡፡
የመስቀል ወፍና የጸደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
………………………………. ማን ያውቃል?
አሁንስ ቢሆን ቮያጀሮቹ ግዛተ ጸኃይን አልፈው ቀላዩን ሲቀዝፉ ሌሎች ፍጥረታትን ቢያገኙስ? ማን ያውቃል? ወይስ ሌሎች ፍጥረታት ቢያገኟቸው ? ስርዐተ-ጸኃይ የት ጋ እንደሚገኝ ከ ሸክላዎቹ የተረዱት እነዚህ ፍጥረታት እየከነፉ ቢመጡብንስ??
መላዕክት ከሆኑ መልካም፣ በላዔ-ሰብዕ ከሆኑስ?
ሰውረን ነዋ !! ኪራራይሶ ኪራራይሶ !!!
ከላይ የዘረዘርናቸው ሁሉም መሳርያዎች ከምድር አስፈላጊው ጥገናና መሻሻል (አፕዴቲንግ) በየጊዜው ይደረግላቸዋል፡፡ የጠፈር መንኮራኩሮቹ ስርዐተ-ጸኃይን እየለቀቁ ሲሄዱ የርቀት መልሶ መርሐ-ግብር ወይም ሪሞት ሪፕሮግራሚንግ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ስልት ተገጥሞላቸው ስለ ነበር የአምስት አመት ጊዜያቸው ሲያልቅ ተጨማሪ ተልዕኮ ለረዢም አመታት ለማከናወን ችለዋል፡፡
አስር ዘጠኝ ስምንት…….አንድ ዜሮ – ምንጠቃ !!!!
የቮያጀሮቹ ተልዕኮ ምንድነው?
እንግዲህ የቮያጀር መርሐግብር የአሜሪካ የጠፈር ጉዞ ሳይንሳዊ መርሐግብር ሲሆን ይህም የሚከናወነው በሁለት ቮያጀር አንድ እና ቮያጀር ሁለት በተባሉ የጠፈር መንኮራኩሮች ነው፡፡ ሁለት የጠፈር መንኮራኩሮችን ለተመሳሳይ አላማ የመላኩ ምክንያት አንዱ ቢበላሽ ሌላው ተልዕኮውን እንዲጥል በማሰብ ነበር፡፡
ሁለት ባላ ትከል አንዱ ቢወድቅ በሌላው ተንጠልጠል
የጠፈር መንኮራኩሮቹ የመጠቁት በ 1977 ሲሆን የአራቱን የዳር አገር ፕላኔቶች በ 1970ዎቹ መጨረሻ እና በ 1980 ዎቹ በአንድ አቅጣጫ መገኘት (ጆኦሜትሪካል አሬንጅመንት) በመጠቀም እንደ ቅደም ተከተላቸው በጁፒተር ሳተርን ኡራኑስና ፕሉቶ አጠገብ በማለፍ መረጃዎችን ሰብስበው ወደ መሬት እንዲያስተላልፉ ተዘጋጅተው የተሰሩ ናቸው፡፡
ቮያጀር 1 በጁፒተርንና ሳተርን አጠገብ እንድትበር ሲወጠን ቮያጀር 2 ደሞ በቀጥታ እነዚህን አልፋ ኡራኑስና ሳተርን እንድታጠና ተወሰነ፡፡ በዚህ የመጀመርያ መርሐ-ግብ የታሰበው ሁለቱ መንኮራኩሮች የዳር አገር ፕላኔቶቹን (ዘ አውተር ፕላኔትስ) ጨረቃዎቻቸውንና ቀለበቶቻቸውን ጨምረው በቅርብ እንዲያጠኑ ነበር፡፡ በዚህም የየፕላኔቶቹ ማለት ከባቢ አየራቸውን፣ ማግኔቲክ ፊልዳቸውን እንዲሁም ጂኦሎጂካል ባህርያቶቻቸውን መረጃ (ዳታ) ሰብስቦ ወደ ምድር መላክ ዋናው ስራ ሆኖ ተይዟል፡፡
ይህ በስኬት ሲጠናቅ ተልዕኮው ተከልሶ የመንኮራኩሮቹ ስራ በይነ-ከዋክብት ተልዕኮ ሆነ፡፡ቮያጀርሰስ ኢንተርስቴለር ሚሽን (ቪ አይ ኤም)፡፡ በዚህም መሰረት መንኮራኩሮቹ የጸኃይ ተጽዕኖ በከዋክብት መካከል ባለው ቀላይ ላይ እንዴት እንደሆነ መረጃ እንዲልኩ ተቀናበሩ፡፡ የዚህ ተልዕኮ ዋና አላማ የስርዐተ-ጸኃይን ጥናት አስፋፍቶ ከራቁት ፕላኔቶች በማለፍ ሂሊዮፓውስን (ማለት የጸኃይ ጨረር የበይነ ኮከብ ንፋስን የሚጫንበት ድንበር) መድረስ እና ከተቻለም ከዚያ በማለፍ መረጃና ምስልን ማስተላለፍ ነው፡፡
ሁለቱም መንኮራኩሮች የመጠቁት ከናሳ ኬኔዲ የህዋ ማዕከል ኬፕ ካናቬራል ፍሎሪካ ሲሆን ቮያጀር ሁለት በመጀመርያ በኦገስት 20 ቀን 1977 ስትነሳ ቮያጀር አንድ ደሞ ዘግየት ብላ ፈጣን መንገድን በመያዝ ሰፕተምበር 5 ቀን 1977 መጠቀች፡፡ ቮያጀር ሁለት ከቮያጀር አንድ በ15 ቀን ቀድማ እንድትመጥቅ የተደረገው የምትሄድበት መዳረሻ (ኡራኑስ እና ኔፕቹን) በጣም ሩቅ ስለሆነ ነው፡፡
በዚህም መሰረት እንግዲህ በኃላ የመጠቀችው ቮያጀር አንድ ማርች 5 ን 1979 ጁፒተር እንዲሁም ኖቨምበር 12 ቀን 1980 ሳተርን ስትደርስ፣ መጀመርያ የመጠቀችው ቮያጀር ሁለት ደግሞ በኦገስት 25 ቀን 1981 ሳተርን ደረሰች፡፡ እንደታቀደውም ቮያጀር ሁለት በሳተርን በኩል በማለፍ በፕላኔቷ የማግኔቲክ ግፊት በመጠቀም ወደ ኡራኑስ ተፈተለከች፡፡
ክፍል ሶስት ቮያጀር አንድ ጁፒተር ደረሰች
ቮያጀር አንድ ጁፒተር ደርሳ ካጋራችን መረጃ እና ዕውቀት በፊት ከራሷ ከፕላኔቱ ጋር እንተዋወቅ፡፡
ናሳ የጁፒተር ጀምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ፎቶ
እንግዲህ ጁፒተር እጅግ በጣም ትልቅ ፕላኔት ነው በስርዐተ ጸኃይ የሚወዳደረው ቀርቶ የሚጠጋው የለም፡፡ ሰባቱም ፕላኔቶች አንድ ላይ ተደምረው ጁፒተር 2.5 ጊዜ ይበልጣቸዋል፡፡ የጸኃይን አንድ ሺኛ ይከብዳል፡፡
ከጸኃይ አምስተኛው ፕላኔት የሆነው ጁፒተር 142,984 ኪ/ሜ መጠነ-ዙርያ (ዲያሜትር) ሲኖረው(የመሬትን አስራ አንድ ጊዜ ይሰፋል)፡፡ ይህም ማለት ጁፒተር ባዶ ቅርፊት ቢሆን 100 መሬቶችን በውስጡ ማቀፍ ይችላል፡፡ ከጸኃይ 778,000,000 ኪ/ሜ ይርቃል፣ የአየር ጸባዩ በአማካይ -110ዲግሪ ሴንት ግሬድ ነው፡፡ ጸኃይን ዞሮ ለመጨረስ 11.86 ዐመት ይወስድበታል፣ በሌላ አነጋገር የጁፒተር አንድ አመት በኛ አስራ አንድ አመት ከአስር ወር ገደማ ነው፡፡ በራሱ ዛቢያ ለመሽከርከር ደሞ 9.9 ሰዐት ይወስድበታል ወይም አንድ ቀን ጁፒተር ላይ 10 ሰዐት ብቻ ነው፣ በዚህም በስርዐተ-ጸኃይ በጣም አጭር ቀን ያለው ፕላኔት ነው፡፡ (ኢንሳ ብሪታ)
ጁፒተር ስያሜውን ያገኘው ከሮማውያን ዋና አምላክ ነው፡፡
ጁፒተር የጋዝ ፕላኔት ስለሆነ የመጠኑን ያህል ክብደት የለውም፡፡ ከመሬት ሲወዳደር የስበት ኃይሉ 2.4 ጊዜ ብቻ ነው የሚበልጠው፡፡ ጁፒተር በአብዛኛው ጋዝ ስለሆነ የሚቆምበት ቦታ የለውም እንጂ ቢኖረው አንድ እመሬት ላይ 100 ኪ/ግ የሚከብድ ሰው ጁፒተር ላይ 240 ኪ/ግ ይከብድ ነበር)፡፡ (ናሳ)
በወጣትነቴ ስለ ሀገራችን ዘፋኞች ንጽጽር ሲነሳ አንደኛ ጥላሁን ገሠሠ እልና ሁለተኛስ ስባል ጥላሁን ገሠሠ ነበር የምለው፡፡ ከሶስተኛ ጀምሮ ነበር ስም መጥራት የምጀምረው፡፡ ጁፒተርም እንዲሁ ከፕላኔቶች አንደኛ የምንለው ብቻ አይደለም፡፡ ማታ ማታ የጭለማ ሰማይን ስናይ ሶስተኛው ደማቅ ነገር ጁፒተር ነው፣ ማለት ከጨረቃ እና ከቬኑስ ቀጥሎ፡፡ ስለዚህም የሰው ልጅ ከጁፒተር ጋር ያለው ትውውቅ ከቅድመ-ታሪክ ጀምሮ ነው፡፡ የተሰየመውም በሮማውያን ትልቁ አምላክ ነው፡፡
አሁን አሁን እንደታወቀውም ከሁሉም ፕላኔቶች ቀድሞ የተሰራው ጁፒተር ነው፡፡ የጁፒተር ቁሳዊ ምጣኔ 90 በመቶ ሀይድሮጂን ሲሆን 25 በመቶ ደሞ ሒሊየም ነው፡፡ ይህ ግዙፍ ነገር በውስጡ ባሉ ቁሶችና ንጥረ ነገሮች የሚፈጥረው ጉልበት ኃይል ከጸኃይ ከሚያገኘው በጣም ይበልጣል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
መሬት ሙሉ ኃይሏን ከጸኃይ እንደምታገኝ ልብ ይሏል፡፡
የጁፒተር ቀይ ነቁጥ (ሬድ ስፖት)
የጁፒተር ዋና ትዕይንት ጎልቶ የሚታየው መሬትን የሚያህለው ቀይ ነቁጥ ነው፡፡ በርግጥ ሌሎች አነስተኛ ነቁጦችም አሉ ግን ትልቁ ቀይ ነቁጥ ከመሬት በሚበልጥ ስፋት ላይ የተንሰራፋ ትልቅ ሞገድ ነው፡፡ ወደ ግራ በኩል አዘንብሎ የሚንቀሳቀሰው ይህ ነቁጥ ከፕላኔቱ የምዕራብ ንፍቀ-ክበብ 22 ኛው ዲግሪ ላቲቱዩድ ላይ ይገኛል፡፡ በመጠኑ ግን ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ እየቀነሰ በመሄድ ላይ ያለ ማዕበል ነው፡፡
ከባቢ አየር
እንግዲህ ስለ ጁፒተር ከባቢ አየር ስናወራ በከፊል ስለ ሙሉው ፕላኔት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ጁፒተር የጋዝ ፕላኔት ስለሆነ ነው፡፡ ይህ እውነታ ለሳተርንም ይሰራል፡፡ በግዝፈት (ማስ) ከሄድን የጁፒተር ከባቢ አየር በሀይድሮጂን(76 መቶኛ) እና በሒሊየም (24 መቶኛ) የተመላ ነው፡፡ በመጠን(ቮሊዩም) ካየነው ደሞ 90 መቶኛ ሀይድሮጂንና 10መቶና ሂሊየም ይይዛል፡፡ እንዲህም ሲባል ግን ከባቢ አየሩ ሌሎች ንጥረ ነገሮች የሉትም ማለት አይደለም በጣም ባነሰ አምጣን (ፕሮፖርሽን) ካርቦን፣ኦክሲጅን፣ሰልፈር፣ኒዮን፣ አሞኒና፣ የውኃ ነጠብጣቦችና ሌሎችም አሉበት)፡፡ (ኢንሳክ.ብሪታኒካ)
የጁፒተር ከባቢ አየር ከደመናዎቹ በታች እስከ 3.000 ኪ/ሜ የሚደርስ ጥልቀት አለው
ምድረ-እምብርት (ኮር)
አንድን በከፊል ጥቅጥቅ ባለ ጋዝ የተገነባ ፕላኔት ምድረ-እምብርትን በትክክል ለማወቅ እስካሁን አስቸጋሪ ነው፡፡ ከተለያዩ የጥናት ውጤቶች ተነስቶ የሚደረስበት ግምት ምድረ-እምብርቱ ፈሳሽና ሜታሊክ ሀይደሮጂን ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ በተጨማሪም ቮያጀር ጁፒተር ከሌሎቹ ፕላኔቶች ትልቅና እጅግ ሰፊ ቦታን የሚሸፍን መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) እንዳለው ደርሳበታለች፡፡ ወሰኑ እስከ ሳተርን አካባቢ የሆነው ይህ ማግኔቲክ ፊልክ የጨረቃዋ ኢዮን እሳተ-ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከቮያጀር ጉዞ በፊት የሰው ልጅ ስለ ጁፒተር የነበረው ዕውቀት እጅግ ውሱን ነበር፡፡ ቮያጀር አንድ የስልተ-ጸኃይ ትልቁን ፕላኔት በተሻለ ገላልጣ እንድታሳይ ይጠበቃል፡፡
ምስል ከናሳ › አስራ አንድ ምድሮች አንድ ጁፒተር እንደሚሆኑ ምናባዊ ስእል
በዚህ የጁፒተር ምስል በቀኝ በኩል ወደታች ትልቁ ቀይ ነቁጥ ይታያል፡፡ በተጨማሪም የጁፒተር ስፋት ምን ያህል የኛን ፕላኔት ሊይዝ እንደሚችል ይጠቁማል
የጁፒተር ጨረቃዎች
በሌሎች ፕላኔቶች የሚገኙ ጨረቃዎች እንደኛዋ ጨረቃ ምንም እንቅስቃሴ የሌለባቸው በድን ቁሶች ተደርገው ይታሰቡ የነበረው ትክክል እንዳልሆነ ቮያጀር አረጋረጠች፣ ይልቁንም ኢዮ ከመሬትም በባሰ የእሳተ-ገሞራ ማዕከል ሆና ተገኝታለች፡፡ ጁፒተር 95 ጨረቃዎች እንዳሉት ተረጋግጧል፡፡ ጋሌሊዮ ጋሌሊይ መጀመርያ በሰራው ቴሌስኮፕ ጁፒተርን ሲያየው ዙርያውን አራት ጨረቃዎች ሲዞሩት ተመለከተ እና መሬት ብቻ ሳትሆን ሌላ የሕዋ አካልም በዙርያው የሚሽከረከሩ ጭፍራዎች (ሳተላይትስ) እንዳሉት ተረዳ፡፡ በዚህም መሬት የህዋ ማዕከል ናት ከሚለው የቫቲካን እምነት ጋር ሊጋጭ በቅቷል፡፡
አራቱ በመጀመርያ ቴሌስኮፕ ዕይታ ውስጥ የገቡት የጁፒተር ትልልቅ ጨረቃዎች ማለትም ኢዮ፣ኢሮፓ፣ካሊስቶ እና ጋኒመደ ናቸው፡፡ እነሱም የጋሌሊዮ ሳተላይቶች በመባል ይታወቃሉ፡፡ ቀደም ሲል መሬት ባሉ ቴሌስኮፖች እይታ በስርዐተ-ጸኃይ ትልቋ ጨረቃ የሳተርኗ ቲታን ነበረች፡፡ አሁን ቮያጀር እንደደረሰችበት ግን ጋኒመደ የተባለችው የጁፒተር ጨረቃ ከሁሉም የበለጠች ሆና ተገኝታለች፡፡ ከነዚህም ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሳይንቲስቶችን ቀልብ ስለሳቡት ስለሁለቱ ጨረቃዎች ትንሽ ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡
ኢዮ
ቮያጀር አንድ በጁፒተር ዙርያ የምታልፈው ከፕላኔቱ ጨረቃዎች ለጁፒተር ቅርብ በሆነው በ ኢዮ በኩል ነው፡፡ ስለዚህም ኢዮን ከጁፒተር በፊት በቅርበት ስታጠናው እጅግ ያልተጠበቀ ክስተትን ተመለከች፡፡ እስከ ቮያጀር ጉዞ ድረስ እሳተ-ገሞራ በምድር ላይ ብቻ የሚከሰት ነገር ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡ አሁን ቮያጀር እንደ ላከቻቸው ምስሎች ኢዮ ብዙ እሳተ-ገሞራዎች ያስተናገደች እና አሁንም እንኳ እየጨሱ በነበልባል የሚንተገተጉ እሳተ-ገሞራዎች በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ አሳየች፡፡ ቮያጀር እዚያው ከጁፒተር ሳትለቅ ዘጠኝ እሳተ-ገሞራዎችን መዝግባች፡፡ (ቢቢዲ ዶክ)
ይህ እንግዲህ አጃኢብ ነው፡፡ በመሬታችን በአንድ ጊዜ ከአንድ እሳተ-ገሞራ በስተቀር የተከሰተ አይመስለኝም፡፡ ይኸው አንዱ እንኳ በስንት ጊዜ አንዴ የሚታይ ክስተት ስለሆነ ሰበር ዜና ሆኖ የሚቀርብ ነገር ነው፡፡ የመሬትን አንድ አራተኛ በማታክለው በኢዮ ግን እሳተ-ገሞራ የአዘቦት ጉዳይ ነው፡፡ እሳተ-ገሞራዎቹ የሚተፉት እሳት እስከ ሶስት መቶ ኪ/ሜ ከኢዮ ምድር ወደ ላይ የሚወጣ ሲሆን በሰከንድ ኪ/ሜ በሆነ ፍጥነት ሌሎች ቁሶችም ወደ ላይ ይበተናሉ፡፡
ኢዮ ከኛ ጨረቃ ትንሽ የምትጠልቅ ናት፡፡ ወደ 4መቶ የሚጠጉ እሳተ-ገሞራዎች አሏት፡፡ ይህን ያህል ጂዖሎጂካዊ እንቅስቃሴ ሊኖራት የበቃው በፕላኔቱ እና በተቀሩት ሶስት ትላልቅ የጁፒተር ጨረቃዎች ስበት ውስጧን በጣም ስለሚስበው እንደሆነ ይገመታል፡፡
ኢሮፓ
ኢሮፓ ለጁፒተር ሁለተኛዋ ቅርብ ጨረቃ ስትሆን መጠኗ የኛን ጨረቃ 90 መቶኛ ነው፡፡ ይህች ድንቅዬ ጨረቃ በሲሊኬት ድንጋይ የተሰራች ስትሆን ብረትና ኒኬል የሆነ ምድረ-እምብርት ላይ የተቀመጠች ናት፡፡ በጣም ስስ ቢሆንም ኦክሲጅን የበዛበት ከባቢ አየር ተገኝቶባታል፡፡ በቅርብ እንደተፈጠረች የምትገመተው ኢሮፓ ውኃና በረዶ ቅልቅል ንጣፍ አላት፡፡ በዚህ ንጣፍ ላይ ብርማ ስንጥቅና ጭረቶች ይታያሉ፡፡ ክሬተሮች ግን በጣም ትንሽ ናቸው (ለዚህም ነው አፈጣጠሯ ሩቅ እንዳልሆነ የተገመተው)፡፡ ከዚህ ንጣፍ በታች በጨዋማ ውኃ የተመሉ ውቅያኖስ ያሏትና የነሱም የውኃ መጠን ከኛ ውቅያኖሶች በሁለት እጅ እንደሚበልጥ ይገመታል፡፡
ኢሮፓ (ናሳ) ከጁፒተር ጨረቃዎች አንዷ
በብዙ ረገድ ይህች ጨረቃ ለሕይወት ምቹ የሆኑ ነገሮችን ከምድር ቀጥላ የያዘች የህዋ አካል ናት፡፡ ስለዚህም ናሳ ይቺን ጨረቃ በቅርብ የሚያጠና “ኢሮፓ ክሊፐር” የተባለ መንኮራኩር በኦቶበር 2024 ይልካል፡፡ ገና በመጠናት ላይ ያለች ብትሆንም ኢሮፓ በስርዐተ-ጸኃይ ከሚገኙ አካላት ሁሉ በጣም ለስላሳ ንጣፍ (ሰርፌስ) ያላት እንደሆነ እና ይህም ንጣፍ ከስሩ የተቀበሩ የውኃ መጠናቸው ከመሬት ውቅያኖሶች የበለጠ እንደሆነ ለመናገር ይቻላል፡፡ (ኢንሳ.ብሪታኒካ)
ጁፒተር ቀለበት አለውን?
ሌላው ቮያጀር ያስተላለፈችው አዲስ ነገር ጁፒተር ቀለበት ያላት መሆኑን ነው፡፡ እስከዛ ጊዜ ድረስ የምናውቀው ሳተርን ብቻ በቀለበቶች የተከበበ ፕላኔት እንደሆነ ነበር፣ የሚታወቀውም ባለ ቀለበቱ ፕላኔት እየተባለ ነው፡፡ ሆኖም ጁፒተርም ቀለበት እንዳለው ቮያጀር ደረሰችበት፡፡ በእርግጥ ቀለበቶቹ እንደ ሳተርን በደንብ የሚታዩ ሳይሆን ፈዘዝ ያሉ ናቸው፡፡ ወደ በኃላ እንደተደረሰበትም ቀለበቶቹ የተፈጠሩት በጁፒተርን በኩል የሚያልፉ ሚቲዎራይቶች ከፕላኔቱ ጨረቃዎች ጋር ሲላተሙ የሚበተኑት ቁሶች የፈጠሯቸው ናቸው፡፡
እንግዲህ ከቮያጀር አንድ ግኝት ጋር በተዛመደ ያወቅነው ስልተ-ጁፒተር ጨረቃዎችና ቀለበቶችን ያቀፈ ሆኖ እነዚህ ጨረቃዎችና ቀለበቶች ኤሌክትሮንስ እና አዮንስ በሆነ ጥልቅ ጨረራዊ መግነጢሳዊ መስክ ተጠምደው የሚገኙ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ መግነጢሳዊ መስክ ሰባትመቶ አምሳ ሚሊዮን ኪ/ሜ ርዝማኔ ያለውና ሳተርን ጠረፍ የሚደርስ ነው፡፡(ቢቢሲ ዶክ)
ከጁፒተር ለጥቃ መሬት ትልቅና ሰፊ የማግኔቲክ ፊልድ ያላት እናት ምድራችን መሬት ናት፡፡
ክፍል አራት ቮያጀርና ሳተርን
እንግዲህ ሁለቱም የቮያጀር መንኮራኩሮች ሳተርንን ጎብኝተውታል፡፡ በዘጠኝ ወር ልዩነት ነው ፕላኔቱ ጋ የደረሱት፡፡ ቀድማ ቮያጀር አንድ ኖቨምበር 12ቀን 1980 ሳተርንን በ 64.200 ኪ/ሜ ከፍታ ስታጠናው ቮያጀር ሁለት ደግሞ ኦገስት 25 ቀን 1981 በ 41.000 ኪ/ሜ ከፍታ ጎብኝታዋለች፡፡
በጁፒተር እንዳደረግነው አሁንም የቮያጀርንና ሳተርን ግንኙነት ከማንሳታችን በፊት ሳተርንን በመጠኑ እንተዋወቀው፡፡
የሳተርን ምስል በቮያጀር ሁለት
ሳተርን ከጥንት ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ ቀልብን የያዘ ፕላኔት ነው፡፡ ሁሉም የጥንታዊ እምነቶች ማለት ይቻላል በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ስለ ሳተርን ይጠቅሳሉ፡፡ ሳተርን ስሙን ያገኘው ከሮማውያን የእርሻ እና የሐብት ንጉስ ሲሆን እሱም የጁፒተር አባት ነው፡፡ ሮማውያን ከዚህም አልፈው ስድስተኛ ቀንን በሳተርን ሰይመው “ሳቱርኒ ዲየስ” ወይም የሳተርን ቀን ብለውታል፡፡
ከቴሌስኮፕ መፈልሰፍ በኃላ የሰው ልጅ ስለ ሳተርን ያለው ግንዛቤ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ሰፊ መተዋወቅ የተገኘው ግን የተለያዩ መንኮራኩሮች ሳተርን ደርሰው መረጃ መላክ ከጀመሩ አንስቶ ነው፡፡ ሳተርንን ቀድማ የጎበኘችው ፒዮኔር አስራ አንድ ስትሆን እሷም በሰፕተምበር 1979 ከሳተርን 2000 ርቀት ላይ በማለፍ ምስልና መረጃዎችን ልካለች፡፡ ቀጥሎ ቮያጀሮች ከዚያም ካሲኒ እና ሁገንስ የተባሉ የጠፈር መንኮራኩሮች ሳተርንን ጎብኝተው ሰፊ መረጃ ልከዋል፡፡
ሁሉም በናሳ የተላኩ የአሜሪካ መንኮራኩሮች ናቸው፡፡
ልክ እንደ ጁፒተር ሁሉ ሳተርንም የአየር (ጋስ) ፕላኔት ነው፡፡ ከጸኃይ በርቀት ስድስተኛ፣ በትልቅነት ደሞ ሁለተኛው ፕላኔት ነው፡፡ ከጸኃይ 1.434 ሚሊዮን ኪ/ሜ የምትርቀው ይህ ፕላኔት ጸኃይን ዞራ ለማጠናቀቅ ሀያ ዘጠኝ አመት ከመንፈቅ ይፈጅበታል- በሌላ በኩል ደሞ ፕላኔቷ በራሷ ዛቢያ ለመሽከርከር 10.7 ሰዐት ትወስዳለች፡፡የሳተርን አንድ አመት የመሬት 29.45 አመት ሲሆን አንድ ቀን ደሞ 10.7 ሰዐት ነው፡፡ የሳተርን መጠነ-ዙርያ 120,536 ኪ/ሜ ሲሆን የምድራችንን ዘጠኝ ጊዜ ያህል ይሆናል፡፡ በክብደት ከሄድን ሳተርን የትልቅነቷን ያህል ከባድ አይለችም፣ ክብደቷ የጁፒተርን አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው፡፡ (ናሳ)
ከሁሉም ፕላኔቶች በቅዝቃዜ ሶስተኛ የሆነው ሳተርን አማካይ የአየር ባህርዩ (ቴምፕሬቸር) -140 ዲግሪ ሴንትግሬድ ነው፡፡ መንኮርኩሯ ፕላኔቷ ጋ የደረሰችው ብርቱካናዊ ቀለም ካላት ቲታን ጨረቃ በኩል አድርጋ ነው፡፡ ይህች ከሌሎች ጨረቃዎች በተለየ በወፍራም በከባቢ አየር የተከበበች ናት፡፡ በጣም ብርቱካናማ በሆነው ቀለሟ ምክንያት ከባቢ አየር እንዳላት በፊትም የተገመተ ቢሆንም አሁን ግን ከባቢ አየሩ በጣም ጥቅጥቅ ያለ መሆኑን ቮያጀር አስረገጠች፡፡ እንደ ፕላኔቷ ቬኑስ ሁሉ እዚህም ደመናው በጣም ወፍራም ስለሆነ የጨረቃዋን ገጽታ በደንብ ፈጽሞ የማይቻል አድርጎታል፡፡
ቀደም ሲል ቲታን በስርዐተ-ጸኃይ ከሚገኙ ጨረቃዎች ሁሉ ትልቋ አድርጋ ትወሰድ ነበር፡፡ አሁን ግን ቮያጀር አንድ ከቅርበት ባደረገችው ልኬት ቲታን ከጁፒተር ጨረቃ ያነሰች መሆኑን አረጋገጠች፣ ደረጃዋም ተሻሽሎ ሁለተኛ ሆነ፡፡
ከባቢ አየር
ሳተርን የጋዝ ፕላኔት እንደመሆኑ ስለከባቢ አየር ስንናገር በከፊል ስለ ፕላኔቱ ራሱ መናገራችን ልብ እየተባለ፡፡ ከጁፒተር ጋር ሲተያይ የሳተርን ከባቢ አየር ደማቅ አይደለም የፈዘዘ ነው፡፡ በኬሚካል አምጣን ረገድ ከባቢ አየሩ 96.3 መቶኛ ሀይድሮጂን፣ 3.25 መቶኛ ሒሊየም ሲሆን የተቀረው ኢቴን ና ሜቴን እንዲሁም ሰልፈር ይበዛበታል፡፡ በሰዐት እስከ 1.800 ኪ/ሜ የሚሄድ ንፋስ አለው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
የሳተርን ውስጣዊ ይዘት
ቮያጀር እንዳጠናችው የሳተርን ምድረ-እምብርት (ኮር) ውስጣዊ ይዘት መሰረቱ ድንጋያማ ሆኖ ከዚህ በላይ ጠለቅ ያለ ሜታሊክ ሀይድሮጂን ሲሆን መሐሉ ደሞ ፈሳሽ ሀይሮጂን፣ ውጪው አየር (ጋዝ) ነው፡፡ በሜታሊክ ሀይድሮጂኑ ውስጥ ያለው ኤሌክትሪካዊ ማዕበል የፕላኔቱን ማግነጢሳዊ መስክ እንደፈጠረ ይገመታል፡፡ ማግንጢሳዊ መስኩ ግን ከመሬት የደከመ ነው፡፡
ያው የተቀረው ማለትም የፕላኔቷ ዋና ክፍል ጋዝ ነው፡፡
በውጫዊው የከባቢ አየሯ ባለው አሞኒያ ክሪስታል ሳቢያ ሳተርን ፈዘዝ ያለ ቢጫ መስላ ትታያለች፡፡ ፕላኔቷ በስርዐተ-ጸኃይ ከውኃ የቀለለ እፍጋት ወይም ጥግጋት (ዴንሲቲ) ያላት ብቸኛ ፕላኔት ናት፡፡ በአጠቃላይ ውስጣዊው የፕላኔቷ ክፍል በጣም ሞቃታማ (11.7000ሴንቲግሬድ) ሲሆን ከጸኃይ ከሚቀበለው 2.5 ጊዜ የበለጠ ኃይል ወደ ኅዋ ይለቃል፡፡ ግዝፈቷ (ማስ1024 ኪ/ግራም) 568 ኪ/ግ ማለትም የመሬትን 95 ጊዜ ያህል ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት እንደገለጽነው የሳተርን መለያ የተስፋፋ ስርዐተ-ቀለበት ሲሆን እነዚህ ቀለበቶች በብዛት ቁርጥራጭ በረዶ፣ ውኃ እና በመጠኑ ደሞ ጠጠርና አቧራማ ቁሶች ያሏቸው ናቸው፡፡(ኢንሳ.ብሪታኒካ)
ከቮያጀር አንድ በኃላ በኖቨምበር 1980 ቮያጀር ሁለት ሳተርን ደረሰች፡፡ በፊት ለማስረዳት እንደሞከርነው ቮያጀር ሁለት በሳተርን በኩል እንድትሄድ የተፈለገው የፕላኔቷን መግነጢሳዊ መስክ ማዕበል በመጠቀም ወደ ኡራኑስ እንድትበር ለማስቻል ነው፡፡ የቮያጀር ተከታታይ ሳይንቲስቶች ቮያጀር ሁለትን ቀደም ሲል ቮያጀር አንድ ያላጠናቻቸውን የሳተርን ጨረቃዎች በደንብ እንድታስስ በተጨማሪም ቀለበቶቹን በደንብ እንድታተኩርባቸውና ሌላም ሳይንሳዊ መረጃ እንድትሰበስብ እና እንድትልክ አድርገው እንደገና ፕሮግራም አደረጓት፡፡
የሳተርን ጨረቃዎች
ከማንኛውም ሌላ ፕላኔት በበለጠ ሳተርን በ146 የታወቁ ጨረቃዎች የታጀበ ነው፡፡ እነዚህ ሳተርንን የሚዞሩ ጨረቃዎች በአይነትም በስፋትም እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ ከኳስ ሜዳ እምብዛም ከማይበልጡ ትናንሽ አንስቶ ከሜርኩሪ እስከሚበልጠው ቲታን ድረስ፡፡ ሰባቱ ጨረቃዎች ደማቅ ከመሆናቸው የተነሳ ጥርት ብለው መሬት ላይ ባሉ ቴሌስኮፖች ይታያሉ፡፡ ቮያጀር ሁለት በቲታን በኩል አልፋ ስለሆነ ወደ ፕላኔቷ ያመራችው የዚህን ጨረቃ ሁኔታ አስፋፍታ በማቅረቧ ስለ ቲታን ያለው ግምትና ፍላጎት ከፍተኛ ሆኖ ናሳን ሌላ መንኮራኩር እዛ አርፎ ጥናት እንዲያካሂድና መረጃ እንዲልክ አበረታትቶታል፡፡
ከበርካታዎቹ ጨረቃዎች ስለሁለቱ ለማተት ያህል
ቲታን
ይህ ጨረቃ በስርዐተ-ጸኃይ ካሉት ጨረቃዎች በትልቅነት ሁለተኛ ሲሆን ወፍራም ከባቢ አየር ያለው ብቸኛ የሕዋ አካል ነው፡፡ በናይትሮጂን እና ሜቴን የተመላው ከባቢ አየሩ በእጅጉ ወደ ሰማይ የጎነነ ብቻ ሳይሆን በጨረቃው ምድር ላይ የሜቴን ዝናብ የሚያወርድ ከባቢ አየር ነው፡፡ ዲያሜትሩ 5.150 ኪ/ሜ ሲሆን የጠቅላላ የፕላኔቱን ጨረቃዎች ዘጠና በመቶ ስፋት የሚይዝ ነው፡፡ ይህ ጨረቃ ዝናብ የሚዘንብበት፣ የእሳተገሞራ እንቅስቃሴ ያለበት፣ ንፋስና የሜቴን ኩሬዎች የሚታይበት በብዛት የምድራችን ጥንታዊ ሁኔታን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡(ናሳ)
ኤንሲላዱስ
ናሳ
በረዶአማዋ ይህች ጨረቃ በስርዐተ-ጸኃይ በጣም አብረቅራቂ እና ነጭ የሆነች አካል ነች፡፡ ከበረዶአማ ንጣፍ በታች ውቅያኖሶች እንዳሉ ከመታመኑም በላይ ሕይወትን ለመደገፍ የሚችል ሁኔታ የረበበባት ጨረቃ ሆና ተገኝታለች፡፡ ከምድረ-እምብርቷ ውኃና በረዶ የተቀላቀለበት ውሽንፍር 400 ሜትር በሰከንድ በሆነ ፍጥነት ይረጫል፡፡ ይህም ምን ያህል ውስጣዊ እንቅስቃሴ እንዳለ አመላካች ነው፡፡
ቀለበታማዋ ሳተርን
ከቮያጀሮቹ ጉዞ በኃላ ሁሉም ግዙፍ ፕላኔቶች የየራሳቸው ቀለበቶች እንዳሏቸው ከመታወቁ በፊት ሳተርን ብቸኛዋ ባለ ቀለበት ተብላ ትወደስና ትደነቅ ነበር፡፡ ከእኩያማማች እሕቶች አንዷ ብቻ ብትታጭ ከሌሎቹ ልቃ እንደምትታየው፡፡ አሁንም ቢሆን ግን ቀለበትን በተመለከተ ሳተርን በርካታ እና ትላልቅ ቀለበቶች ያላት እንደመሆኑ ከግዙፎቹ ዘመዶቿ ልቃ መታየቷ አልቀረም፡፡ ትልልቆቹ ቀለበቶችን አያይዘው እንዳይበተኑ የሚደግፏቸው ፓንዶራ እና ፕሮሚቲዩስ የሚባሉ እንደ “እረኛ” የሚጠብቋቸው ትናንሽ ጨረቃዎች አሏቸው፡፡ ሁሉም የተሰሩት በብዛት ከውኃና ከበረዶ ሆኖ ትናንሽ ድንጋያማ አካላትም አሏቸው፡፡ ለዚህም ይሆናል ፍንትው ብለው የሚታዩት፡፡
ምንም እንኳን መጀመርያ ያያቸው ጋሌሊዮ ቢሆንም በቅጡ አጥንቷቸው ቀለበት እንደሆኑ እና ፕላኔቷን እንደሚዞሩ የደረሰበት ግን ክርስቲያን ሁይግንስ ነው፡፡ ይህንን ግኝቱን ለመዘከር ይመስላል፡፡ ከካሲኒ የጠፈር መንኮራኩር ጋር አብራ የመጠቀችው እና ከሷም በመለየት በቲታን ላይ አርፋ በርካታ መረጃዎችን የላከችው መንኮራኩር በስሙ እንድትጠራ የሆነው፡፡ የሳተርን ቀለበቶች ከፕላኔቷ መቀነት (ኢኩዌተር) በ 6.630 እና 120.700 ኪ/ሜ መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡ በአማካኝ ሀያ ሜትር ውፍረት ያላቸው እነዚህ ቀለበቶች እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ ብዙ ምርምር ተደርጓል፣ ብዙ መላምቶችም ተሰጥተዋል፡፡(ኢንሳ. ብሪታ)
አንዱ መላምት ቀለበቶቹ ረዥም እድሜ እንዳላቸውና ከፕላኔቱ አፈጣጠር ጋር የተገናኙ የሚያምን ነው፡፡ ሌላኛውና ይበልጥ መረጃና ተአማኒነት ያለው ደሞ፣ ቀለበቶቹ ከ መቶ ሚሊዮን አመት በፊት ከሳተርን ጋር የተጋጨች ክሪሳሊስ የምትባል ጨረቃ ብታኞች እንደሆኑ የሚያትተው ነው፡፡ ቀለበቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚቲራይቶችና ከሌላም በራሪ አካላት ጋር እየተጋጩ በመትነን እየቀነሱ የሚሄዱ ሲሆኑ ረዢምም ቢሆን ከተወሰነ ጊዜ በኃላ ሙሉ በሙሉ የሚጠፉ ናቸው የሚል ግምት አለ፡፡
ለማንኛውም እስኪጠፉ ድረስ ቀለበቶቹ በሰባት ተከፍለው ኤ ቢ ሲ ዲ ኢ ኤፍ እና ጂ ተብለው ይታወቃሉ፡፡
ቮያጀር ሁለት የሳተርን ጉዞዋን አጠናቃ በፕላኔቱ ማግኔቲክ ፊልድ ማዕበል እንደገና በመወንጨፍ ወደ ኡራኑስ አመራች፡፡ በዚህን ወቅት አንስታ የላከችው የሳተርን ከፊል ጨለማ ምስል የናሳ ሳይንቲስቶችን ያስደመመ ነበር፡፡
ፎቶ
ክፍል አምስት ዩራኑስ
ቮያጀር ሁለት ዩራኑስ የደረሰችው በጃንዋሪ 24 ቀን 1986 ነው፡፡ እስካሁን እንደምናርገው የቮያጀር ሁለትን የኡራኑስ ውሎ ከመዘርዘራችን በፊት ከኡራኑስ ጋር እንተዋወቅ፡፡
ዩራኑስ ከጸኃይ 1.8 ቢሊዮን ኪ/ሜ ርቆ የሚገኝ ሰባተኛው ፕላኔት ሲሆን ግማሽ – ዙርያ(ዲያሜትር) 51.118 ኪ/ሜ፡፡ እንደ ጁፒተርና ሳተርን የጋዝ ሳይሆን የበረዶ ፕላኔት ነው፡፡ ወደ ፊት እንደምናየው ኔፕቹንም እንዲሁ የበረዶ ፕላኔት ነው፡፡ በክብደት ከተሄደ ከጁፒተርና ሳተርን ቀጥሎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)
ዩራኑስ የተገኘው ከአምስቱ ፕላኔቶች ቀጥሎ ነው፡፡ ሌሎቹን ፕላኔቶች የሰው ልጅ ያገኛቸው በቀጥታ ከምድር በመመልከት ሲሆን ኡራኑስን ለማግኘት ግን የቴሌስኮፕ መገኘትን ግድ ብሏል፡፡ ያኔም ቢሆን የጠፈር ተመራማሪ አስትሮኖሚስቶቹ ኡራኑስ ፕላኔት መሆኑን ከማረጋገጣቸው በፊት ጊዜ ወስደው ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ቀደምት የስነፈለክ ተመራማሪዎች አንድ ሰማያዊ አካል ፕላኔት መሆኑን የለዩት ብዙ መጠበብ በኃላ ነበር፡፡ ከሰማያዊ አካላት መካከል በቁጥር የሚበዙት ከዋክብት ናቸው፡፡ እነዚህ የህዋ አካላት ብርት ጥፍት፣ ወይም ብልጭ ድርግም የሚሉና ሁሌም በአንድ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ የሚታዩ ናቸው፡፡ ልጅ ሆነን ከተማርናቸው ቀደምት የእንግሊዝኛ መዝሙሮች አንዱ
Twinkle Twinkle, Little Star
How I wonder what you are
Up above the world so high
Like a diamond in the sky
Twinkle Twinkle Little Star
How I wonder what you are!
የሚል ነበር፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹየ ህዋ ከዋክብት ብልጭ ድርግም አይሉም አንድ ቦታ ረግተውም አይገኙም፡፡ ስለዚህም ማታ ማታ አንገታቸውን እስኪያማቸው አንጋጠው የሌሊት ሰማይን የሚያጠኑት የስነፈለክ ሊቃውንት እነዚህ ነገሮች እና ከዋክብት አንድ አይነት ነገሮች እንዳልሆኑ ተገነዘቡ፡፡ ከሊቃውንቱም የግሪኮቹ እነዚህን ነገሮች ፕላኔት አሏቸው፡፡ በጥንታዊ ግሪክኛ ፕላኔት ማለት ዘዋሪ (ዎንደረር) እንደማለት ነው፡፡
የናሳ ጀምስዌብ ቴሌስኮፕ ኡራኑስ ከነቀለበቶቹ ሲታይ፡፡ ዙርያውን የሚታዩት ሰማያዊ ዶቶች ጨረቃዎቹ ናቸው
በዚህም መሰረት ዩራኑስን በቴሌስኮፕ እርዳታ ለመጀመርያ ጊዜ 1781 ያገኘው ያገኘው የብሪታንያው ስነፈለክ ሊቅ ዊሊያም ሀርሸል ያገኘውን ነገር ወዲያውኑ ፕላኔት ከማለት ይልቅ ሌሎች ጠበብትን ማማከር መረጠ፡፡ አንዳንዶች ተወርዋሪ ኮከብ ሚቲዮራይት ሊሆን እንደሚችል ቢገምቱም ፕላኔትነቱ ጸንቶ መጠሪያ ስሙን ለማውጣት ግን ትንሽ ጊዜ ወሰደ፡፡ ባገኘው ሰው ስም ሀርሸል፣ ወይም በአግኚው አገር ታላቋ ብሪታንያ እንዲባል ምክረሀሳቦች ቀርበው ነበር ፡፡
ብዙ ስሞች በአማራጭነት የተነሱ ቢሆኑም በመጨረሻ ማርች 1782 ጆን ኤለርት ቦደ የተገኘውን ፕላኔት በላቲን የሰማይ አምላክ ኡራኖስ ዩራኑስ ብሎ እንዲሰየም ያቀረው ምክረሀሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ሰባተኛው ፕላኔት ዩራኑስ ተባለ፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ይህ ስያሜ ችግር አላጣውም፡፡ በእንግሊዝኛ ተናጋሪው ህዝብ ይህ ቃል መቀለጃ ከመሆን አላመለጠም፡፡ ይህ የሆነው በእንግሊዝኛ ዩራኑስ ስንል “ዩር አነስ” ተብሎ ስለሚሰማ ነበር፡፡(ኢንሳ. በሪታኒካ)
ሆሆይ!
ሆኖም ዩራኑስ በዚሁ ስሙ ጸንቶ ዘልቋል፡፡
እንግዲህ እስከ አሁን ዩራኑስ የተጎበኘው በቮያጀር ሁለት ብቻ ነው፡፡ ሳተርን በፒዮኔር፣ በቮያጀር አንድ በኃላም በካሲኒም ተጎብኝታለች፡፡ ጁፒተርም ቢሆን ከቮያጀር እና ፒዮኔር ሌላ በጋሌሊዮ የጠፈር መንኮራኩር በጥልቀት ለረዢም ጊዜ ተጎብኝተዋል፡፡ በዚህም መሰረት ስለ ዩራኑስ የሚታወቀው እና የሚነገረው በብዛት ከቮያጀር ሁለት በተገኘ መረጃ እና ምስል ነው፡፡ እኛም ትረካችንን በዚህ መስመር አስተካክለን እንቀጥላለን፡፡
በጄት ፕሮፐልሽን ላቦራቶሪ ሆነው ቮያጀሮችን የሚከታተሉት ሳይንቲስቶች ቮያጀር ሁለት ኡራኑስ ስትደርስ በላከቻቸው ምስሎች በጣም ነበር የተደበሩት፡፡ ከጁፒተር ብዝሐ-ቀለማት ከባቢ አየር እና አዮ ጨረቃ እሳተ-ገሞራ፣ የኢሮፓ ሰማያዊ ቀለም ትርኢት ሲደሰቱ የነበሩት ሳይንቲስቶቹ በኡራኑስ የፍዝ-አደንግዝ አረንጓዴ/ሰማያዊ ገጽታ ማዛጋት ጀመሩ፡፡ (ቢቢዲ ዶክ)
እንግዲህ ከቮያጀር ሁለት መረጃ በኃላ እንደደተደረሰበት ዩራኑስ እንደ ጁፒተር እና ሳተር ጠንካራ ውስጣዊ የኃይልና የሙቀት ምንጭ የለውም፡፡ በሆነ ምክንያት ይህ ውስጣዊ የኃይል ምንጭ ተዳፍኗል፡፡ ስለዚህም የዩራኑስ አየር እየተርመሰመሰ በፍጥነት ስለማይንቀሳቀስ ለማየት የቻሉት ቀለመቢስ ርጋታ ነበር፡፡
ሆኖም እዚህም ቢሆን የሚገርም ነገር አልጠፋም፡፡
ኡራኑስ ትንሽ ቆይተን እንምናየው ኔፕቹኝም የጋዝ ሳይሆን የበረዶ ፕላኔቶች ናቸው፡፡ ከቮያጀር ሁለት ከተገኘው መረጃ እና ኃላም በተራቀቁ ቴሌስኮፖች አማካይነት የሌሎች ከዋክብት ፕላኔቶችን በመመልከት እንደተደረሰበት ዩራኑስና ኔፕቹን በመጀመርያ ከጸኃይ አንደኛ እና ሁለተኛ ፕላኔቶች ነበሩ፡፡ የአሁኑ ቦታቸውን የያዙት ዘግየት ብሎ በስርዐተ-ጸኃይ ውስጥ በተከሰቱ ድብልቅልቆች ነው፡፡
ሌላው የዩራኑስ የተለየ ባሕርይ ፕላኔቱ ተገልብጦ የሚንቀሳቀስ አካል መሆኑ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው ዛቢያው (አክሲስ) 82.23 ዲግሪ ያዘነበለ ስለሆነ የዛቢያው ዙርያ ሽክርክሪት (አክሲስ ኦፍ ሮቴሽን) በጣም ያዘነበለ ነው፡፡ ስለዚህም አዟዟሩ ዳህራይ እንቅስቃሴ (ሪተሮገራድ ሞሽን) ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ በራሱ ዛቢያ ለመዞር(አንድ ቀን) 17 ሰዐት ከአስራ አራት ደቂቃ ሲወስድበት፣ ጸኃይን ለመዞር ደሞ 84 አመታት ይፈጃል፡፡ (ናሳ) በቀላል አነጋገር በዩራኑስ አንድ ቀን 17 ሰዐት ከአስራ አራት ደቂቃ ሲሆን አንድ አመት ደሞ የኛን 84 አመት ማለት ነው፡፡ በዚህ አዟዟር የደቡብና ሰሜን ንፍቀ ክበቦቹ 42 አመት በተከታታይ ጨለማ ከሰነበቱ በኃላ የ 42 አመት ተከታታይ ጸኃይ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡
በኛ አስተራረስ እንግዲህ በሰኔ የዘራ ገበሬ የሚያጭደው ከ42 አመት በኃላ በትሕሳስ ይሆናል !!
ይህም ሆኖ ግን በፕላኔቱ መቀነት (ኢክዌተር)ባለ ጠባብ አካባቢ ጸኃይ ብዙውን ግዜ ከላይ ስለሆነች የተፋጠነ የቀንና ሌሊት ቅብብሎሽ ያገኛል፡፡ አሜሪካና ራሽያ ዩራኑስ ቢሆኑ ዋናው ጦርነታቸው በዩክሬን ሳይሆን ሳህራ በረሀ ላይ ይሆን ነበር ማለት ነው፡፡
ሌላው ቮያጀር በላከችው ምስሎች የሚያስገርመው ነገር የዩራኑስ ጨረቃዎች ዩራኑስን የሚዞሩት እንደ ሌሎቹ ፕላኔት ጨረቃዎች ክሎክ ዋይዝ (ከምስራቅ ወደ ምዕራብ) የእናት ፕላኔታቸውን መስመር ተከትለው ሳይሆን በተገላቢጦችበ የአንቲ ክሎክዋይዝ መሰመር በኩል ነው፡፡
ሌላው ደሞ ሚራንዳ የተባለችው ጨረቃ ፎቶዋ ሲታይ አንድ ይዘት የሌለው በሰሜን ምስራቅ በኩል መስመርማ ቅርጾች በሌላ በኩል ደቦልቧላ ትዕይንቶች ተዘበራርቀው ይገኙባታል፡ (ቢቢሲ ዶክ)
እንግዲህ ለዩራኑስ ግልብጥ እሽክርክሪት፣ ዘንባላ መቀነት፣ ለጨረቃዎቹ ወለፈንዴ አዟዟር ምክኑ ምን ይሆን?
ይህን ጥያቄ በተሟላ ለመመለስ ሳይንስ ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም እስካሁን ለቀረቡት መላምቶች ለእውነት የቀረበ የሚመስለው፣ በጣም በጣም ጥንት አንድ መሬትን የሚያህል በራሪ አካል በዩራኑስ በኩል ሲያልፍ ገጭቶት ስላለፈ ምሕዋሩም የተዛባ (82.23ዲግሪ) አዟዟሩም የተለየ ሆነ፡፡ እነ ሚራንዳም(ጨረቃ) በዚህ ግጭት አካሏ ተበታትኖ እንደገና ተገጣጠመ፣ቀዶ-ተከላ?? (ኢንሳ.ብሪታ.)
በዚህም ሰበብ ሳይሆን አይቀርም ዩራኑስ ከተቀሩት ግዙፍ (ጃይንት) ፕላኔቶች በተለየ በጣም ደካማ ውስጣዊ ሙቀት እና ኃይል የምታመነጨው፡፡
ከባቢ አየር
ዩራኑስን በተመለከ በደንብ የተገኘ/የታወቀ ጠንካራ/ድንጋያማ ላዩን መሬት የሆነ ውስጣዊ አካል ስለሌለ በታየው ደረጃ ያለውን አካል በረዶአዊ ና አየራዊ ብለን እንጠራዋለን፡፡ የዩራኑስ ከባቢ አየር የተወሳሰቡ ደረጃዎች ባሉት የደመና መዋቅር የተሸፈነ ሆኖ በስርዐተ-ጸኃይ ከፍተኛውን ቅዝቃዜ (-224 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ) ያለው ነው፡፡ በይዘት በኩል ከሄድን የዩራኑስ ከባቢ አየር ሀይድሮጂንና (83% ሒሊየም(15%) የተመላ ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ በመጠኑ ሜቴን (2%) ተመዝግቧል፡፡ ውስጣዊ የኃይል ምንጩ ደካማ ስለሆነ ይመስላል የዩራኑስ ከባቢ አየር ንፋስ በሰዐት እስከ 900 ኪ/ሜ በሰዐት የሚበር ነው፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)
ምድረ-እምብርት
ዩራኑስ 17.000 ኪ/ሜ የቀለጠ ድንጋያማ መሰረት አለው፣ ይህም ክብደቱ መሬት አምስት ጊዜ ያህል ይበልጣል፡፡ እንደተቀሩት ግዙፍ ፕላኔቶች ሁሉ ዩራኑስም ቀለበቶች አሉት፡፡ ፊት ለፊት ሁለት ሰማያዊ ቀለበቶች ሲኖሩ ገባ ያሉት ቀይ ናቸው፡፡ የተቀሩት(የበዙት) ጥቁር ናቸው እንደ ጨረቃዎቹ፡፡(ናሳ)
ከዩራኑስ በርካታ ጨረቃዎች ትልልቆቹ አምስቱ እንደ ደረጃቸው ሚራንዳ፣ አሪየል፣ኦቤሮን፤ እና ቲታንያ ሲሆኑ ስማቸውን ያገኙት ከዊሊያም ሸክስፒር ተውኔት ገጸ ባሕርያት ነው፡፡ ኦቤሮንና ቲታንያ በፕላኔቱና በሌሎቹ ጨረቃዎች በሚገጥማቸው የስበት ግፊት ሳቢያ ፈሳሽ ውኃ ለመፍጠር የሚችል ሙቀት አላቸው ተብሎ ይገመታል፡፡
ተመልሶ እይታ
ቮያጀር ሁለት ዩራኑስ የደረሰችው በጊዜው በጋ/ጸኃያማ በሆነው የደቡብ ዋልታ በኩል ስለ ነበር አብዛኛው መረጃ የደቡቡ ንፍቀ ክበብን የተመለከተ ነው፡፡ ዩራኑስን ለመጀመርያ እና መጨረሻ ጊዜ ያየነው በ 1986 ቮያጀር ሁለት በአጠገቡ አልፋ ስለ ፕላኔቱ እና ስለ አምስቱ ዋና ጨረቃዎቹ በላከችልን ምስልና መረጃ ነው፡፡ በያኔው የቮያጀር ሁለት መረጃ መሰረት ዩራኑስ እና ጨረቃዎቹ ምንም እንቅስቃሴ የሌላቸውና ከሌሎች የስርዐተ ጸኃይ ጨረቃዎች የተለዩ መሆናቸውን ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ዩራኑስን የሚከላከው መግነጢሳዊ መስክ የተዛባ እንደሆነ መረጃው ያሳይ ነበር፡፡
እንደ ልማዱ ከሆነ አንድ መግነጢሳዊ መስክ ከከበበው ፕላኔት ከውቅያኖሱና ከጂኦሎጂካል ምክንያቶች የሚስፈነጠሩ ጋዝና ሌሎች ቁሶችን ጠምዶ እንዳይወጡ ያደርጋል፡፡ ቮያጀር ሁለት ግን የዩራኑስ መግነጢሳዊ መስክ ይህን ሲያደርግ አላየችም፡፡ ስለዚህም ዩራኑስም ሆነ አምስቱ ትልልቆቹ ጨረቃዎች ሙት ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ በጊዜው ይህ ትልቅ መገረምን ፈጥሯል፣ ምክንያቱም ይህ ከሌሎቹ ፕላኔቶችም ሆነ ጨረቃዎች የማይገጥም ስለሆነ፡፡ ይሁንና ናሳ በቅርቡ የበፊቱን ቮያጀር ሁለት መረጃ በድጋሚና በጥልቀት ሲተነትን፣ ቮያጀር ሁለት ዩራኑስ ጋ ስትደርስ አደገኛ የጸኃይ ማዕበል ፕላኔቱን ወሮት ነበር፡፡
መጥፎ ግጥጥሞሽ!
አዲሱ ትንተና እንዳረጋገጠው የጸኃዩ ማዕበል በፕላኔቱ ዙርያ ኃይለኛ የጸኃይ ንፋስን ስላስነሳ፣ በዚህም ቁሶች ከመበታተናቸውም ለጊዜው መግነጢሳዊ መስኩ ተዛብቶ ነበር፡፡ አስፈላጊው መስተካከል ተደርጎለት ያ የቮያጀር ሁለት መረጃ እንደገና ሲተነተን ግን ዩራኑስ ቆንጆ፣በረዶአማ እና በቀለበት የተከበበ ፕላኔት ነው፡፡ ዩራኑስም ሆነ ጨረቃዎቹ መደበኛ (ኖርማል) ናቸው፡፡ የዩራኑስ ሲስተምም ቢሆን በፊት ከተገመተው የበለጠ አጓጊ ናቸው፡፡በጨረቃዎቹም ቢሆኑ ከበታቻቸው አሳዎች የሚተረማመሱባቸው ውቅያኖስ ሊሆኑ እድሉ ጥቂት አይደለም፡፡
አዲሱን ግኝት በተመለከተ፣ የደብሊን ከፍተኛ ደረጃ ሳይንስ ተቋም አባል የሆኑት ዶክተር አፌልያ ዊቢሶኖ ሲናገሩ
‘’ይህ የሚያሳየን አንድን መረጃ ደግሞ እና ደጋግሞ መመልከት ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም፣ አንዳንዴ አዳዲስ የተደበቁ ነገሮች ሊገኙ ይችላሉ፡፡ በሰል ግኝቶች ደሞ ቀጣይ የኅዋ ምርምር ተልዕኮችን በተሻለ ለመንደፍ ይረዳናል’’
ክፍል ስድስት ኔፕቹን
በተወሰነ መልኩ በዩራኑስ የቮያጀር ሁለት ፎቶዎች ቅሬታ ላይ የነበሩት የጂ ፒ አል ሳይንቲስቶች መንኮራኩሯ ኔፕቹን ደርሳ በላከቻቸው የመጀመያ ፎቶዎች በጣም ተደመሙም ተካሱም፡፡ በስርዐተ- ጸኃይ የመጨረሻዋ ፕላኔት ምድርን ትመስላለች፡፡ ረዣዥም ብሩህ የምድራችን የመሰሉ ደመናዎች በኔፕቹን ከባቢ አየር ከፍታ ላይ ሲታዩ ሳይንቲስቶቹ በመገረም አፋቸውን ከፍተው በጸጥታ ይመለከቱ ነበር አንድም ነገር ኮሽ ሳይል፡፡
ነጫጭ ደመና ጣል ጣል ያለበት ሰማያዊ ሰማይ!
ናሳ ጀምስ ዌብ ስፔስ ቴሌስኮፕ ኔፕቹን
ኔፕቹንን ሰማያዊ መልክ የሰጣት በአየሯ የሚገኘው ሜቴን ነው፡፡ ይህ ኬሚካል ንጥረ ነገር በባህርዩ ሌሎችን ቀለማት ውጦ (አብዞርብ)ሰማያዊውን ብቻ ስለሚተፋ (ሪፍሌክት) ነው ፕላኔቷ ደማቅ ሰማያዊ የሆነችው፡፡ በሰማያዊው የኔፕቹን ሰማይ ላይ ጥቁር ነጥቦች ጣል ጣል ብለው ይታያሉ፣ እነዚህም የማዕበል ባህርይ አላቸው፡፡ ከነዚህ ሰፋ እና ወፈር ያለው “ትልቁ ጥቁር ነጥብ” ተብሎ ተሰየመ፣ እንደ ጁፒተሩ ትልቁ ቀይ ነጥብ፡፡ መሬትን ያክላል ስፋቱ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ማዕበል ከኔፕቹን ገጽ የጠፋ ሲሆን ሌሎች መጠነኛ ማዕበላት በተለያዩ የፕላኔቷ ገጾች ላይ ተከስተዋል፡፡
ቮያጀር ሁለት ኔፕቹን የደረሰችው ኦገስት 25 ቀን 1989 ነው፡፡ቮያጀር ሁለት እስካሁን ኔፕቹንን የጎበኘች ብቸኛዋ የጠፈር መንኮራኩር ናት፡፡ እንግዲህ ኔፕቹን ከጸኃይ ሶስት ሚሊዮን ኪ/ሜ ርቀት እንደመገኘቱ የሚደርሰው የጸኃይ ብርሐን እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ የመንኮራኩሯ ፎቶ ማንሻዎች በደንብ ጥሩ ምስል ለማውጣት በቂ ብርሐን አያገኙም፡፡(ቢቢዲ ዶክ)
ስለዚህም መሬት ያሉት የናሳ ሳይንቲስቶች የመንኮራኩሯን ኮምፒየተር ሲስተም እና የምስል ቀረጻ መሳርያዎችን አድሰው መርሀግብሮቹን ማሻሻል ነበረባቸው፡፡ አለበለዚያ ፎቶግራፎቹ ያንን ያህል ጥራት አያገኙም ነበር፡፡ ይህም ማለት ልክ መንኮርኩሯ በፕላኔቷ ሰሜን ዋልታ በኩል ከኔፕቹን የዛቢያ እሽክርክሪት ጋራ በተቀናጀ መልኩ ፍጥነቷን ሳትቀንስ ግን ዘንበል ብላ በፕላኔቷ ትልቅ ጨረቃ ቴትሮን በኩል እየበረረች ፎቶ እንድታነሳ መርሐግብሯን አስተካክለውታል፡፡ በሳተርም ጊዜ እንዲሁ መንኮራኩሮቹ በትልቋ የፕላኔቷ ጨረቃ ቲታን በኩል ነበር የገቡት፡፡
በዚህም ምክንያት መሬት ያሉት የናሳ መሐንዲሶች ከመንኮራኩሯ የሚላከውን ድምጽ ጎላ ብሎ እየተሰማ ምስሎቹም ጠርተው እንዲታዩ አስችሏል፡፡ ስለዚህም በዚያን ወቅት በመሬት መቆጣጠሪያ ጣቢያ የነበረው ስሜት እጅግ የጋለ ነበር፡፡ ከመንኮራኩሯ የሚላኩት ምስልና መረጃዎች ምድር ለመድረስ አራት ሰዐት ገደማ ይወስድባቸዋል፡፡ መንኮርኩሯ ኔፕቹን ደርሳ ጉዞዋን ጨርሳ እስክትወጣ ድረስ ሁሉም በየኮምፒዩተሩ ተሰክቶ በደስታ እና በአድናቆት የሚላከውን ይከታተላል፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)
ከማንኛውም ንፉግነት በጸዳ ሁኔታ በፓሳዲና (ካልፎርኒያ) የሚገኘው የቮያጀር መከታተያና መምሪያ ማዕከል ጂፒኤል የሚያገኛቸውን ምስሎች ሁሉ የጊዜው ቴክኖሎጂ በፈቀደው ፍጥነት ለተቀረው አለም አካፍሏል፡፡
በበነጋውም ቡድኑና ለማመስገን እና የሀገሪቱን ፓለቲካ ኃይል ምስጋና በአካል ለማቅረብ ምክትል ፕሬዚዳንት ዳን ኩዌል በጣቢያው ተገኝተው ነበር፡፡ ዘፈኑ በወርቃማ ሸክላዎች የተላከለት የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቼክ ኖሪስም ጊታሩን እየመታ “ጆኒ ቢ ጉድ” የተባለውንና በቮያጀር የተላከው ዘፈኑን ይዘፍን ነበር፡፡
ቼክ ኖሪስ እና ታዋቂው የህዋ ሳይንቲስት በጄት ፕሮፐልሽን ላቦራቶሪ በቮያጀር ሁለት ስኬት እያዜሙ ሲደንሱ (ናሳ)
ኔፕቹን ስምንተኛውና የመጨረሻው ፕላኔት ነው፡፡ ኔፕቹን የበረዶ ፕላኔት ሲሆን ከጸኃይ 4.5 ቢሊዮን ኪ/ሜትር የሚርቅና 49.528 ኪ/ሜ መጠነዙርያ ያለው ፕላኔት ነው፡፡ እኛጋ በ8 ደቂቃ የሚደርሰው የጸኃይ ብርሐን ኔፕቹን ለመድረስ ግን አራት ሰዐት ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ርቀቱ ምክንያት ይመስላል የከባቢ አየሩ ክፍል (-218°C) የአየር ጸባይ አስለዝግቧል፡፡ (ኢንሳ.በብሪታ)
ኔፕቹን በራሱ ዛቢያ ለመሽከርከር 16 ሰዐት ሲፈጅበት በጸኃይ ዙርያ ለመሽከርከር ደሞ 165 አመታት ይወስድበታል፡፡ ኔፕቹን ጸኃይ ሲዞር ዛቢያው 28 ዲግሪ ዘንበል ብሎ ሲሆን ይህም ከማርስና ከመሬት ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ እንደኛ አራት ወቅቶች ይኖሩታል፣ ዳሩ ግን ወቅቶቹ እያንዳንዳቸው ከአርባ አመት በላይ ይወስዳሉ፡፡
ኔፕቹን 16 ጨረቃዎች አሉት፡፡ ትልቋ ጨረቃ ትሪቶን ስትሆን የተገኘችውም ከፕላኔቷ መገኘት ከ 17 ቀን በኃላ ነው፡፡ ትሪቶን ከኔፕቹን 2.700 ኪ/ሜ ስትርቅ 354.760 ኪ/ሜ መጠነ-ዙርያ አላት፡፡ በስርዐተ ጸኃይ ከሚገኙት ጨረቃዎች ሶስተኛው ትልቋ ጨረቃ ናት፡፡
ቮያጀር ሁለት በትሪቶን በኩል አልፋ ኔፕቹን እንደመደረሷ ስለ ጨረቃዋ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አስተላልፋለች፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ፎቶዋ የተገኘው በቮያጀር ነው፡፡ ፕላኔቷ የምትሽከረከረው ደግሞ ከፕላኔቷ እሽክርክሪት በተቃራኒ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ሳይንቲስቶቹ ጨረቃዋ በፕላኔቷ ወይም ከፕላኔቷ ጋር የተፈጠረች ሳትሆን ከሌላ ቦታ ተፈጥራ በኔፕቹን በኩል ስታልፍ ፕላኔቷ ስበት የተጠለፈች ነች ብለው እንዲገምቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)
ትሪቶን ከዜሮ በታች እስከ -391 ዲግሪ ፋራናይት የአየር ጸባይ በማስመስገብ በስልተ – ጸኃይ የመጨረሻዋ ቀዝቃዛ አካል ነች፡፡ ይህም ሆኖ ቮያጀር ሁለት በላከችው ምስል ከምድሯ 8 ኪ/ሜ ወደ ላይ የሚተኑ ፍል ጉነት/ውርውር ፍልውሃ (ጋይሰርስ) አሏት፡፡ ይህም ውስጣዊ ሙቀት እንዳላት አመላካች ነው፡፡ ይበልጡንም ከባቢ አየር ያላት ጨረቃ ስትሆን ይህም ከባቢ አየር የሙቀት መጠኑን እየጨመረ የመጣ ነው፡፡
ትሪቶን እንደ አንዳንድ ጨረቃዎች በፕላኔቷ ዙረርያ የምታደርገው ዑደት በጊዜ ብዛት ከፕላኔቷ እያራቃት ሳይሆን እያቀረባት የሚሄድ ነው፡፡ ከፕላኔቷም ያላት ርቀት እምብዛም ስለሆነ ከ 3.5 ሚሊዮን አመታት በኃላ ከኔፕቹን መጋጨቷ አይቀሬ እንደ ሆነ ይገመታል፡፡ በዚህም ግዜ ኔፕቹን እንደ ሳተርን ያለ ምናልባትም የበለጠ ያማረ የቀለበት ዙርያ ይኖራት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ወደፊት የሳተርን ቀለበቶች የምናጣበት እድል ሰፊ ቢሆንም የኔፕቹን ቀለበቶች ስለሚተኳቸው ችግር አይኖርም፡፡
ለአሁኑ ኔፕቹኝ አምስት ቀለበቶች እና አራት ቀለበት አከል ቅስቶች(አርክ) አሉት፡፡ እነዚህ ቀለበቶች ምናልባትም በሲልከንና ካርቦን ቁሶች የተሸፈኑ በረዷማ አካላት ናቸው፡፡
ቮያጀር ሁለት የላከችው የኔፕቹን ዋና ቀለበቶች ፎቶ
ኔፕቹን በሂሳብ ስሌት የተገኘ የመጀመርያ ፕላኔት ነው፡፡ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች የዩራኑስ ሽክርክሪት የሚያሳየውን የተወሰነ መዛባት ሲያስተውሉ ለዚህ ክስተት ከቀረቡት መላምቶች ሚዛን ያነሳው አንድ ሌላ ትልቅ የህዋ አካል በተለይም ፕላኔት የፈጠረው የስበት ተጽዕኖ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ተነስተው በሂሳብ ስሌት የዚህን ፕላኔት መገኛ ካጠኑት የሂሳብ ሊቆች ፈረንሳዊው ለ ቬር እና እንግሊዛዊው ጆነ ኮች አዳምስ ተለይተው ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ለየቅል ባደረጉት ጥናት ፕላኔቱ በሰማይ ላይ ሊገኝ የሚችልበትን ትክክለኛ አካባቢ ለመጠቆም ችለዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ጆን ጎተፍሬድ በ 1846 በቴሌስኮፕ ፕሉቶን ሲያገኝ ሁለቱ የሒሳብ ሊቃውንትም ተገቢውን እውቅና አግኝተዋል፡፡ከተገኘ እስካሁን ገና አንድ አመቱ ነው ማለት ይሆናል(165 የመሬት አመት)፡፡ ስሙ የተወሰደው ከሮማውያን የባሕር አምላክ ኔፕቱን ነው፡፡(ናሳ)
ለነገሩ ጋሌሊዮ ጋሌሊይ ኔፕቹንን በቴሌስኮፑ አግኝቷት ነበር፡፡ ይሁንና ፕላኔት መሆኗን ስላልደረሰበት ኮከብ ብሎ ነበር የሰየማት፡፡ ከሁሉም ፕላኔቶች ኔፕቹን በጣም ነፋሳማ ናት፡፡ ምንም እንኳ ከጸኃይ የምታገኘው ኃይል ውሱን ቢሆን የኔፕቹን ነፋሳት ከሁሉም የፈጠኑ ናቸው፡፡ የምዕራብ አቅጣጫን ተከትለው የሚነጉዱት እነዚህ ነፋሳት በሰዐት 2000 ኪ/ሜ ይሄዳሉ፡፡ከዚህም በላይ ቮያጀር ሁለት በተገጠመላት ፕላኔታሪ ሬድዮ አስትሮኖሚ መሳርያ ከ ስልሳ በላይ መብረቆችን መዝግባለች፡፡ ትልልቅ እና ትንንሽ ማዕበላትም በሽበሽ ናቸው፡፡
የፕላኔቱ ከባቢ አየር 85 መቶኛ ሀይድሮጂን 15 መቶኛ ሂሊየምና ሁለት በመቶ ደሞ ሜቴን ነው፡፡የኔፕቹን ከባቢ አየር በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፣ ቶፖስፌር እና ሰትራቶስፌር ተብሎ፡፡ በሁለቱ ማዕከል ያለው ትሮፖ ፓውዝ፡፡ ውስጣዊ ይዘቷን በተመለከተ ምድረ-እምብርቷ (ኮር) ከብረት፣ኒኬል እና ሲልኬትን የያዘ ነው፡፡ ምድረ ማዕከሏ (ማንትል) ቢሆን ውኃ፣አሞኒያ እና ሜቴን አሉት፡፡ እንደ አንዳንድ ጥናቶች ከሆነ የምድረ-አምብርቷ ጫፍ ተንሳፋፊ ጠጣር አልማዞች የያዘ የካርቦን ውቅያኖስ እንደሆነ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
የጁፒተርን ያህል ባይሆንም ኔፕቹንም ቀላል የማይባል ማግኔጢሳዊ መስክ አላት፣ እንዲያውም ከመሬት ሰላሳ ጊዜ ኃይለኛ ሆነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በፕላኔቷ የተመዘገው አውሮራ (ፖሎች ላይ የሚታይ የደማቅ ቀለማት ሕብር) ደካማ ነው፡፡ ምናልባትም የጸኃይ ንፋሳትና ትናንሽ ቁሶች ኔፕቹን ሲደርሱ ኃይላቸው ከርቀቱ አንጻር ስለሚቀንስ ይሆናል እንደ መሬት አውሮራዎች ጉልህ ያይደሉት፡፡
እንግዲህ ኔፕቹን ጠንካራ ሰውነት (ሶሊድ ቦዲ) ስላልሆነች ከባቢው አየር የተለያየ አዙሪት (ሮቴሽን) ያደርጋል፡፡ ስለዚህም ሰፋ ባለው የኔፕቹን ወገባዊ ክፍል (ኢኳቶርያል ዞን) ኡደቱን ከፕላኔቱ አማካይ 16.1 ሰዐት በተለየ በ18 ሰዐት ሲያከናውን፤ በዋልታዎቹ አካባቢ ግን ፈጠን ብሎ በ12 ሰአት ዑደቱን ይጨርሳል፡፡ ማለት ረዥም እና አጭር ቀናት በአንድ ፕላኔት የተለያዩ ስፍራዎች ይከሰታል ማለት ነው፡፡(ዝኒ ከማሁ)
በኔፕቹን ላይ ቮያጀር ያየችው የአየር ሁኔታ መለዋወጥ ፕላኔቷ ኃይለኛ ውስጣዊ ሙቀት እንዳላት አመላካች ነው፡፡ ከጸኃይ ካላት ረዢም ርቀት አንጻር የምትቀበለው ሙቀት አንስተኛ ሆኖ ይህ ውስጣዊ ሙቀት ከየት ተገኘ? በአንድ በኩል በፕላኔቷ ምድረ- እምብርት ውስጣዊ ፍትጊያው ከፍተኛ ስለሆነ እና ፕላኔቷ ስትፈጠር የነበረው ሙቀት ከፍተኛ ሆኖ እስካሁን ሊተርፋት ስለቻለም ይሆናል፡፡ አፈጣጠሯን በተመለከተ ተቀባይነት ያገኘው ግምት ግዙፎቹ የበረዶ ፕላኔቶች ማለትም ዩራኑስና ኔፕቹን መጀመርያ ጸኃይ አጠገብ ተፈጥረው በኃላ ግን በሂደት ወደ ርቀት የመጡ እንደሆነ ነው፡፡
ኤ ቲን ብሉ ዶት ፈዛዛ ሰማያዊ ነጥብ
ቮያጀር ሁለት ሳተርንን ስትለቅ ካሜራዎቿ ፊታቸውን ወደ ምድር መልሰው ሁሉንም ፕላኔቶች ያቀፈ አንድ “የፕላኔቶች ፋሚሊ ፒክቸር” እንዲልኩ ሀሳብ ቀረበ፡፡ በጊዜው የቮያጀር ትልቁ ጉዞ ተልዕኮ ኢሜጅ ዳይሬክተር የነበረችው ካሮሊን ሮኮ ነበረች ሐሳቡን ያቀረበችው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ወዲያው ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ባልደረቦቿ ሀሳቡ በስራ ላይ ሊተገበር ስለመቻሉ ምን ማስረጃ እንዳላት ጠየቋት፡፡ ምንም አልነበራትም ግን ቮያጀር ተልዕኮዋን ስላጠናቀቀች በሙከራው የሚደርስ መሰረታዊ ችግር ስለሌለ ብንሞክርስ ብላ አሳመነቻቸው፡፡
በዚህም መሰረት አልፋቸው የሄደቻቸውን፤ አሁን በደንብ የማይታዩትን ፕላኔቶች ፎቶ አንስታ እንድትልክ ታዘዘች፡፡
ከአምስት ሰአት ከምናምን በኃላ ፎቶው ምድር ደረሰ
በርግጥም የሚመጣው ፎቶ ጥርት ያለ በየቤታችን ግድግዳ ላይ እንዳለው የቤተሰብ ፎቶ እንዲሆን አልተጠበቀም ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ስድስት ሜትር በላይ የረዘመው ፎቶ ሳይንቲስቶቹን አስደምሞ ነበር፡፡ ሜርኩሪ በኃይለኛው የጸኃይ ጨረር ሳቢያ አልተነሳችም፡፡ ማርስ በማነሷ አልወጣችም፡፡ የቀሩት ፕላኔቶችም እንደ ግዝፍናቸው ሳይሆን አነስ አነስ ብለው ተነስተዋል፡፡ በኃላም ካሮሊን ከፎቶው ላይ የችውን አቧራ ማራገፍ ጀመረች፡፡ ሆኖም አንድ ጠጠር ብላ ያየቻትን አቧራ ለመጥረግ ብትሞክር አቧራይቱ እንዴት ተደርጎ!! ብላ ገገመች፡፡
ሳይንቲስቶቹ ልብ ብለው ሲያይዋት ነገሯ አቧራ አልነበረችም፣ የምድራችን የመሬት ምስል እንጂ፡፡ ይቺ ሚጢጢ ሰማያዊ ነጥብ እናት መሬት ሆና ተገኘች!! (ቢቢሲ ዶክ)
የሰውን ልጅ ባዶ ኩራትና መጠግረር ልብ በሉ፣ ከህዋ አንጻር ከአንዲት ትንሽ ሰማያዊ ጠጠር በሆነ ቦታ ላይ ያለን፣ አንድ ከኳስ ሜዳ ያነሰ ሚቲዮራይት ቢገጨንን እኛም ሚጢጢ አሸዋ የምንሆን ምናምኖች!!
ቮያጀር አንድ ፌብርዋሪ 14 ቀን 1990 ከጸኃይ 6 ቢሊዮን ኪ/ሜር ርቀት ላይ አንስታ በላከችው የፕላኔቶች ቤተሰባዊ ፎቶ ላይ ምድራችን ስትታይ (ፔል ብሎ ዶት!)
ክፍል ሰባት በዚህ አመት፣ ማለትም ከምድር ከተወነጨፉ ከ47 አመት በኃላ ቮያጀሮች የት ናቸው?
ከኔፕቹን በኃላ እስከ አሁን ድረስ የቮያጀሮችን የጉዞ መስመር በአጭሩ ከማስቃኘታችን በፊት የኢንተር ስቴላር ስፔስን (በይነ ኮከባዊ ስፍራ) ትርጉም እናስቀምጥ፡፡ ኢንተርስቴላር ሰፔስ (በይነኮከባዊ ህዋ) ማለት የጸኃይ ስበት የሚያበቃበት የሌላ ሰማያዊ አካል ስበት የማይጀምርበት ወይም የሌለበት በከዋክት መካከል የሚገኝ ሕዋ ነው፡፡
ቮያጀር አንድ ከላይ የጠቀስንላችሁን የፕላኔቶችን ቤተሰባዊ ፎቶ በ ፌብርዋሪ 14 ቀን 1990 አንስታ ከላከች በኃላ ወደ ኢንተርስቴለር ህዋ አመራች፡፡ ቮያጀር ሁለት ደሞ ኔፕቹንን በሰፕተምበር 1998 ተሰናብታ እንዲሁ ወደ በይነ ኮከባዊ ህዋ ነጎዱ!! ቮያጀር አንድ በ 39.000 ቮያጀር ሁለት ደሞ በ 35.000 ማይል በሰአት እየከነፉ ስርዐተ-ጸኃይን ለቀው የመውጣት ጉዎአቸውን ቀጠሉ፡፡
በይፋ እንደተቀመጠው ቮያጀር አንድ በኦገስት 2012፣ ቮያጀር ሁለት ደሞ በኖቨምበር 2018 በይነ ኮከባዊ ህዋ ውስጥ ገቡ፡፡
መቼም በ 1977 ቦያጀሮቹ ከምድር ሲለቁ ጉዞአቸው ከአራት አመት አልፎ 47 በላይ ይሆናል ብሎ ማንም አልገመተም ነበር፡፡ ይሁንና ከአንዱ ስኬታማ ጉዞ (ለምሳሌ ጁፒተርና ሳተርንን ሲጎኙ) ወደሚቀጥለው (ለዩራኑስ እና ኔፕቹን)፣ ከዚያም ወደ በይነ ኮከባዊ ህዋ እንዲቀጥሉ እየተደረገ ይኸው እስከዛሬም እየበረሩ፣ መረጃ እየላኩ ነው፡፡ ምድር ያሉት የሕዋ መሐንዲሶች የመንኮራኩሮቹን መሳርያዎች እያደሱ፣ የኮምፒዩተር መርሀ-ግብሩን እያሻሻሉ፤ የኃይል አጠቃቀሙን እየከለሱ (የተወሰኑ መሳርያዎች መስራት እንዲያቆሙ በማድረግ) እስካሁን ደርሰዋል፡፡
በ2025 ሁሉም የመንኮራኩሮቹ መሳርያዎች እንዲጠፉ ይደረግና ዝም ብለው እስከቻሉ ወይም ሌሎች የሰለጠኑ ፍጡራን እስኪያገኟቸው ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በ 2024 ቮያጀር አንድ ከምድር 24 ቮያጀር ሁለት ደሞ 20 ቢሊዮን ኪ/ሜ ርት ላይ ናቸው
ይህን መጣጥፍ እውቁ የስነ-ሕዋ ሊቅ ካርል ሳጋን በ 1994 “ፔል ብሉ ዶት” በሚል ርዕስ ከጻፈው መጽሐፍ፣ ስለ መጨረሻው የቮያጀር የምድር ፎቶን ጥልቅ ትግርጉም በገለጸበት አረፍተ ነገር እናሳርገው
“ከዚህ ርቀት(6 ቢሊዮን ኪ/ሜ) ላይ ሆነን ምድርን ስንመለከታት ብዙም የሚስብ ነገር የላትም፡፡ እስኪ እንደገና ይህን ሰማያዊ ነጥብ አስቡት፡፡ ያ እዚህ ነው፣ እሱም ቤታችን ነው፣ ያ ነጥብ እኛ ነን! እዚያ ነጥብ ላይ የምናቀው ሁሉ፣ የምንወደው፣ እያንዳንዱ ፍጡር በፊትም የነበረ አሁንም ያለ!! የደስታችንና ስቃያችን ቦታ፡፡ የኁልቀ-መስፈርት እምነት፣ርዕዮት እና ምጣኔ ሐብታዊ ነቢቦች ድምር መፍለቂያ፣መኖርያ እና መጥፊያ፡፡ እያንዳንዱ አዳኝ፣ቀለብ ለቃሚ፣ጀግና እና ፈሪ፣ ፈላስማ እና አጥፊ፣ ንጉሥና ገበሬ፣ ፍቅረኛ፣ ወላጅ እና ታዳጊ ህጻን፣ አዲስ ነገር ፈጣሪና አሳሽ፣መልዐክና ዲያቢሎስ፣-
አንድ ላይ ይኖራሉ፡፡ ከጸዳለ ጸኃይ በታች ተጠልለው እና ተንጠልጥለው!!” (ኢንሳ ብሪታ)
ምንጮች
britannica.com › Science › Astronomy Solar system | Definition, Planets, Diagram, Videos, & F
britannica.com › … Voyager | Space Exploration, Interplanetary Travel ..
Internet Archivebbcthe planets bbc documentary 1999 full movie from archive.org12 Jul 2023
science.nasa.gov › solar-system Exploration)
science.nasa.gov › mission › voyager-stories)