(ትንሿ ሜትሮፖሊታን – አዋሽ 7 ኪሎ)
ክፍል ሁለት
ደብረሳሌም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን
ይህች ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ያሰሯት ቤተክርስትያን (ቤ/ክ) ከህይወቴ አራቱን አመት ያሳለፍኩባት ነች፣ በቄስ ተማሪነት፡፡ በቅጥር ግቢው ያለውን የመቃብር ስፍራ የባረኩት በኃላ ፓትርያክ የሆኑት አቡነ ባስልዮስ ሲሆኑ በዚህም ምክንያት እዚያ መቀበር የሚፈቀድላቸው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ እንደመታደል ሆኖ ከነዚህ አንዷ እናቴ ሙላቷ እንግዳወርቅ ምንዋልኩለት ትገኛለች፡፡
የአዋሽ ቤ/ክ በጣልያን ጊዜ ጽላቱ ተደብቆ ጫካ ውስጥ ሲኖር መምሬ ማሞ አብረው በሳቢል ጓሮ ገደል ተደብቀው ይጠብቁትና ይንከባከቡት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ በድብቅ የሚረዷቸው ግለሰብ ነበሩ፡፡ እኚህ ግለሰብ በእምነት ሙስሊም ቢሆኑም የክርስትያኖቹን ችግር አይተው እርዳታቸውን ከመስጠት አልተገቱም፡፡ መምሬ ማሞ በድብቅ የቤ/ክርስትያኑን አልባሳት ከተማ ያመጡና እኚህ ግለሰብ ቤት አስቀምጠው ይመለሳሉ፡፡ እሳቸውም አልባሳቱን በኩሊ ወንዝ አስልከወው ያሳጥቡና አልባሳተ በመጡበት አኳኃን፣ ማለት በድብቅ ይመልሱላቸው ነበር፡፡ ይህንን ወግ የነገረኝ በቤተክርስትያኗ በትርፍ ጊዜው እንደ ዲያቆን ያገለግል የነበረው ሟቹ አቶ ከበደ ተክሌ ነው፡፡
ነፍስ ይማር ጋሽ ከበደ
ስለ መምሬ ማሞ ሌላው ትዝ የሚለኝ አንድ አጋጣሚ ነው፡፡ እኔ ወደ መጋላ ስሄድ እሳቸው ደሞ ከመጋላ ወጥተው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ሸበቶ ጠጅ ቤት አካባቢ ተገናኘን፡፡ ከመተላለፋችን በፊት ሰላምታ መስጠትና መስቀላቸውንም መሳለም ስላለብኝ ቆሜ ጠበቅኃቸው፡፡ ለብቻቸው እያጉተመተሙ ፈገግ ይላሉ፡፡

ሰላምታ ተሰጣጥተን እንደጨረስን
‘’ምንድነው ብቻዎን እያነጋገረ ፈገግ የሚያስደርግዎት? ስላቸው ፈገግ ብለው፣ ያቺ ሀሌም የማትለየውን ነጭ ጭራቸውን እያወዛወዙ –
‘’ አሁን ወዲህ ስመጣ መሐመድ ሐሰን አበበች ባቡ ሆቴል ቁጭ ብሎ ሲተክዝ አየሁት፡፡ ያው እንደምታውቀው ከስሮ ሱቁን ዘግቷል፡፡ በጣም አሳዘነኝና፣ ‘’አይዞህ መሐመድ አትተክዝ መቸም ቢሆን እግዚአብሔር ሳይደግስ አይጣላም’’ አልኩት፡፡ እሱም ራሱን እየነቀነቀ ‘አይ መምሬ! የመጣላት የመጣላት ምን አስደገሰው?’ ብሎ ያለኝን እያሰብኩ ነው፡፡’’ ብለውኝ ተሳስቀን ተለያየን፡፡
መምሬ ማሞ ከታቦት ጋር ጫካ ውስጥ አምስት አመት ተጉላልቶ እስከመኖር የጠነከረ የኦርቶዶክስ ተከታይነት ያላቸው ነበሩ፡፡ ከነጻነት በኃላም የሚወዷትን ቤ/ክ በግልጽ ማገልገል ቀጠሉ፡፡ የቄስ አስተማሪ ሆነው በርካታ ዘመነተኞቼን (ኮንቶምፖራሪስ) አስተምረዋል፡፡ በመጨረሻ የደም ብዛት ተጠቂ ሆነው ነበር፡፡ እየከፋም ሲመጣ ይጥላቸው ጀመር፡፡ ሰዉ ጉዳዩን ከመናፍስት አያይዞ ‘’ሰይጣን ጣላቸው’’ ብሎ ቅዱሰ-ቅዱሳን መግባትም ሆነ ታቦት መሸከም ተከለከሉ፡፡ ሊሞቱ አንድ ቀን ሲቀራቸው እየዞሩ የክርስትና ልጆቻቸውንና ሌላም የሚግባቧቸውን ’’አለ ዛሬም አታገኙኝ ደህና ሁኑ እያሉ’’ ተሰናበቱ፡፡ በበነጋው አለምን ተሰናበቷት፡፡
ነፍስ ይማር!
ሌላው የደብረሳሌም ቅድስት ማርያም ቤ/ክ የጊዜያችን ቀሲስ መምሬ መኮንን ናቸው፡፡ ቀኛዝማች ወረደ የአዋሽ ወረዳ ገዢ ሆነው ሲመጡ መምሬ መኮንን በድምጻቸው፤ በሽብሸባቸውና በከበሮ አመታታቸው ወደዷቸው፡፡ ራሳቸው ቀኛዝማች ወረደም የቤተክህነት ትምህርት ስላላቸው የመምሬ መኮንንን ስጦታ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ወዲያውኑም የማዘጋጃ ቤቱ ጸኃፊ አደረጓቸው፡፡ በነገራችን ላይ ታላቆቻችን እንደነገሩን ቀኛዝማች ወረደ ወደ ቢሯቸው ሲገቡ ለጥ ብሎ እጅ ያልነሳ ሰውን አምስት ጅራፍ ያስገርፉ ነበር፡፡ ’’የመንግስት ተምሳሌት’ኮ ነኝ’’ ይላሉ፤ እሳቸውን እጅ መንሳት ጃንሆይን እጅ እንደ መንሳት እየቆጠሩ፡፡
የመምሬ መኮንን እናት ጠጅ ቤት ነበራቸው፡፡ ታድያ ጠጃቸው ኃይለኛ ነው፡፡ አንድ ቀን አንዱ ገብቶ አዞ ይጠጣል፡፡ አስደገመ – ሶስተኛ ብርሌ ሲያዝ ወጡና ጣቶቻቸውን ጆሯቸው ከትተው ’’ኡ ኡ’’ ብለው ሰፈሩን ቀወጡት፡፡ የፖሊስ ያለህ እያሉ! ሰዉ ግልብጥ ብሎ ወጣ፤
’’ምንድነው? ምን ሆነዋል’’
’’የኔ ጠጅ ኃይለኛ ነው፡፡ አንዱን ብርሌ ብቻ ቀስ ብለው ሳይሆን ዥው አድርገው ከጠጡት ያሰክራል፡፡ ከደጋገሙትማ ያማል፤ይኼኛው ሁለቱን በአንዳንድ ትንፋሽ ገልብጦ ሶስተኛ ቅጂልኝ ነው የሚለው፡፡ ይሞትብኛል አስወጡልኝ’’ አሉ፡፡
ሰውየው ደንግጦ ሂሳቡን ከፍሎ ውልቅ አለ፡፡ ከልጃቸው አንዱ ሐጂ ዳኜ መስለሙን በጭራሽ መቀበል አልቻሉም ነበር፡፡ የጓደኛዬ አባት የአስር አለቃ አምዛ በሽርም ክርስትያን ሲሆን እንዲሁ ክርስትናው አልተዋጠላቸውም፡፡ ጋሽ አምዛ አንዳንዴ በሬ ቅርጫ እያረደ ይሸጣል፤ እሳቸው ግን አንዴም ገዝተውት አያውቁም፡፡ ለምን ቢባሉ
‘’አምዛ በሽር ብሎ ክርስትያን፤ ዳኜ ወልደማርያም ብሎ ክርስትያን አላውቅም’’ ይሉ ነበር፡፡
ያኔ የናቴን ቤት የተከራየ ዶክተር ዮደር የተባለ አሜሪካዊ ሚሲዮን ነበር፡፡ ከቤቱ አለፍ ብሎ የውኃ ቢርካ አለ፤ እዛ በርሜላቸውን ተራ አስይዘው ሲመለሱ ዮደር ጋ ጎራ አሉና ክንዳቸውን ቀስረውለት
’’ደሜን ለካ አንተ! ምን ይመስላል?ድመት አይን’’
ለካቸው፤ የልብ ምታቸውንም ለካና
’’ልብዎ በደንብ አይመታም፡፤ በጣም ደካማ ነው’’ አላቸው፡፡
ዝም ብለውት ቤታቸው ሄደው አንድ ብርሌ ጠጅ ገልብጠው መጡና
’’ለምጣም ሶላቶ አሁን ለካ እስቲ!’’
ከትንፋሻቸው ነገሩ የገባው ዶክተር ዝርዝር ውስጥ ላለመግባት
’’አሁን ልክ ነው ማማ’’ አላቸው
’’ድሮስ ጥልያን መብል እንጂ ምን ያውቃል!’’ ብለው
ሂሳቡንም ሳይከፍሉት ወደተሞላው በርሚላቸው ሄዱ፤ በኩሊ አስገፍተው ቤታቸው ሊያስወስዱ፡፡
መምሬ መኮንን ረዘም ያሉ ቀጭን መልከ መልካም፣ ድምጸ መረዋ ቄስ ነበሩ። ቅስናውን በተጨማሪነት የሚሰሩት ሲሆን በዋናነት የማዘጋጃ ቤቱ ጸሃፊ ናቸው። በስልሳ ሰባት ይሁን ስልሳ ስምንት አንዴ አብረን ታስረን ነበር። ከቤትና የከተማ ትርፍ ቤት አዋጅ በኃላ ሁለት ክፍል ቤት ሰብረው አንድ አድርገዋል ተብሎ ነበር የታሰሩት። እኛ ደሞ የተከማቸ የመንግስት እህል ለደሀ በማከፋፈላችን ጣሊያን በሰራው የአስተዳደሩ ቢሮ ስር ባለው እስር ቤት ገብተናል። በዚያ አጋጣሚ ብዙ ነገር አጫውተውን ነበር።
‘’መምሬ ጉቦ በልተው ያውቃሉ?“
“ስሙ እንጂ፣ አለቃችን ከአዲስ አበባ ለጉብኝት እመጣለሁ ብለው የሚያሳውቁን ገና ከመድረሻቸው ሶስት ወር በፊት ነበር። እንግዲህ ምን ማለታቸው ነው? ተሰናድታችሁ ጠብቁኝ ነው። በዚያን ግዜ እኛም በርትተን ከቦታ ምሪት ፈላጊዎችም፣ከከብት ነጋዴዎች ቀረጥም፣ከንጽህና ጉድለት ቅጣትም… ብቻ በዚህም በዚያም ብለን ለአለቃችን የሚገባቸውን እናዘጋጃለን። እኔኮ መጀመርያ በወር አስር ብር የሚከፈለኝ ቀሲስ ነበርኩ፣ከዚያችው ባጠራቀምኩት 50 ብር ጉቦ ሰጥቼ ነው ማዘጋጃ የተቀጠርኩት። ታድያ ለጉቦ የከፈልከኩትን 50 ብር በምን እመልሳለሁ በጉቦ ነው እንጂ!!” አሉን
ለጥምቀት ታቦት ሲወጣ መምሬ መኮንን ያንን ትልቅ ከበሮ ተሸክመው ሲደልቁት ያላቸው እንቅስቃሴ እና ማማር አሁንም ፊቴ ላይ አለ። አድጌ አዲስ አበባም ሌላ ቦታም ጥምቀት አይቻለሁ ከበሮዋን እንደ መምሬ መኮንን የሚያሳምራት ግን አልገጠመኝም።
‘’በጎል በጎል
ሰብአሰገል
በጎል
ሰብአሰገል
በጎል ሰብአሰገል ሰገዱለት’’ እኛም ሰገዱለት እያልን እንቀበላቸዋለን።
ይህን አዘማመራቸውን በጣም እንደምወደው ስነግራቸው
‘’መዝሙሩ’ኮ የዲያቆኖች ነው፣ ጎበዝ ዲያቆን ስለሌለ ነው እኔ የምዘምረው” ብለውኛል። እንኳን ደህና ዲያቆን ጠፋ፣ አለበለዚያ ያንን የመምሬ መኮንን ጣፋጭ ድምጽ ስንሰማ አናድግም ነበር፣ ያንን ውብ የከበሮ ንቅናቄያቸውንና ምታቸውን እያየን ባልተደሰትም፣ ዛሬም በትዝታ ይህንን ባልጻፍንም።
አንዴ ወርቄ ከምትባል ፊናንስ ሰፈር ጫፍ ላይ ቡና ቤት ከነበራት ሴትዮ ጋር ይጋጫሉ። ምን እንዳረጓት እንጃ አንድ እሁድ ቤተ ክርስቲያን ምሰሶውን ተደግፋ ታማርራለች።
“እመቤቴ የዚህ ቄስ ነገር አታሳይኚም! እንዲህ ሲበድለኝ አንድ አትይኚም?” ትላለቸ እያማረረች። መምሬ መኮንን ከቤተክርስትያኑ ወጥተው
“አንቺ እኔን ነው የምታሳብቂ፣ እስቲ ማርያም አንቺን ከውጭ የምትለፈልፊውን ነው ወይስ አኔን ከቅድስተ ቀዱሳኑ ከውስጥ የምነግራትን ነው የምትሰማ ቆይ” ብለው ይገቡና ቆይተው ይወጣሉ።
“በይ የፈለግሺውን ለፍልፊ እኔ እንደሆነ ከውስጥ እውነቱን ነግሬያታለሁ” ሲሏት ተሳሳቀው ይታረቃሉ።
ተሊላ ጫካ በጊዜው በአዋሽ ትልቁን ሆቴል ቤት የከፈቱ ነበሩ። ወደ በኃላ ሞተው ጉራጌ አገር ይቀበራሉ፣ልጃቸው አቶ ብርሐኑ ተሊላ በየአመቱ ሙት አመታቸውን እየደገሰ ያበላል። ታድያ አንዴ መምሬ መኮንን ባሉበት “ዘንድሮ ትንሽ ብቻ ነው የምደግሰው አንድ ስድስት ሰባት ሰው ብቻ ነው የምጠራው፣ በምትኩ ለነዳያን እመጸውታለሁ” ይላል።
መቼም አራት ሰው አይደለም ሁለት ሰው ብቻ እንኳ ቢጠራ አንደኛው እሳቸው እንደሚሆኑ አልተጠራጠሩም። ይሁንና በነጋታው ስምንት ሰው ሳይሆን አንድ አስራ አንድ የሚሆኑ የከተማው ዋና ዋና ሰዎች ሲጠሩ እሳቸው ተዘለዋል።
“ቆይ ብቻ” ብለው በየሰዉ ቤት እየገቡ
“እንዴ ምንትሰራላችሁ? ብርሀኑ ተሊላ እየጠበቃችሁ አይደል’ንዴ? ትላንት ነው’ኮ ንገርልኝ ያለኝ፣ የኔ ነገር፡፡የአቶ ተሊላ ሙት አመት ነው፤ ድል አድርጎ ደግሷል በሉ…” በማለት ሰዉን ወደ ብርሐኑ ተሊላ ቤት ነዱት። ባልጠበቀው የሰው ጎርፍ የደነገጠው ብርሐኑ ተሊላ ልጆች እየላከ ከሉካንዳ ስጋ እያስገዛ በጥሬ ስጋ እና በ ጥብሰ ያልጋበዛቸውን እንግዶች ሸኘ። ማ ጉድ እንደሰራው የገባው ግን ወዲያው ነበር። የሚመጡት ሰዎች
“እንዴት ነህ አቶ ብርሐኑ፣ እኔ’ኮ አሁን ገደማ ነው መምሬ መኮንን ቤት መጥተው ‘ብርሐኑ ጠበል ጸዲቅ ቅመሱልኝ ብሏል’ ያሉኝ፣ አረፈድኩ’ንዴ” እያሉ ሲገቡ መምሬ መኮንንን አለመጥራቱ ያስከተለበትን ቅጣት በጸጋ ተቀበለው፡፡
መምሬ መኮንን አራት ወንድሞች እና አንድ ናዝሬት መምህርት የሆነች ጎዝጉዥ የምትባል እህት ነበራቸው። አንዱ ወንድማቸው ዳኜ ወልደ ማርያም የሰለመ ጊዜ በጣም ተናደው ነበር። ይባስ ብሎ መካን ተሳልሞ “ሀጂ ዳኜ” ሲሆን ግን እያንገራገሩም ቢሆን እውነታውን ተቀበሉት። ይሁን እንጂ ሐጂ ዳኜ ናዝሬት አውራጃው ፍ/ቤት ስሙን ሐጂ ዳኜ ሙክታር ሊያሰኝ ሲል ከፍ/ቤት በተቃውሞ ቀርበው ረትተውታል።
ለክርክር ናዝሬት ሲሄዱ ከችሎት መልስ መምህርት እህታቸው ቤት ለምሳ ተጠርተው ሲሄዱ ሀጂ ዳኜም እዚያው ነበር፣ የሌላው ወንድማቸው ልጅ ጴንጤዋ አበበችም እንዲሁ።ማዕዱ ሁሉንም እንዲያስተናግድ ሆኖ ነበር የተዘጋጀው እና በዚህ በኩል ችግር አልነበረም። ግን ማን ይባርከው? ቀደም አሉና መምሬ
“በስመ እግዚአብሔር ይትባረክ” ብለው ሲቆርሱ ሀጂ ከተል ብሎ
“ቢስሚላሂ ሮማን ወረሂም” ብሎ ተከተለ። አበበችም እጆቿን ግንባሯ ላይ ተክላ
“በኢየሱስ ስም የተባረከ ይሁን” አለችና ሁሉም በሉ
በደርግ ጊዜ ስለ ሀይማኖት ክርክር ሲነሳ በድፍረት በአደባባይ ይሰብኩ ነበር። እስር ቤት እያለን የሕብረተሰብ እድገት ህግን ልናብራራላቸው ስንሞክርም አልተቀበሉንም ነበር።
“የባርያ ስርአተ ማህበር ላላችሁት ግን ከናንተ ይልቅ በሽር ከሊሉ እና መኪ ሐቢብ ቢያብራሩ ይሻላል” ብለው አሹፈውብናል”። በሽር ከሊሉ እና አቶ መኪ ሀቢብ ቀደም ሲል ባርያ ይሸጡ ይለውጡ ነበር ተብለው ይወራባቸዋል።
ከዚሁ ክርክር ሳንወጣ አንዱ
“ተዉ እባካችሁ ከዚህ ማለቂያ የሌለው ክርክር እንውጣ፣ ሀሳብ ቀደመ ቁስ ቀደመ ከአዋሽ መቼም ጀነት የሚገባ የለም” ሲል መምሬ ተቆጡና
“ለምን የለም? ቢቀር ቢቀር ሁለት ሰው ገነት መግባቱ ያለቀለት ጉዳይ ነው” ይላሉ
“እነማን ናቸው ሁለቱ?” ብሎ ጠየቀ አንዱ
‘’ከእስላም ሐጂ ዳኜ ከክርስትያን መምሬ መኮንን’’
መምሬ መኮንን ሰበካቸው በጣም ደስ የሚል ንግግር አዋቂ ነበሩ፡፡ እንዳሁን ሀይማኖቶች ሳይካረሩ ለእስላሞች ኢድ መስጊድ ሄደው ንግግር ሲያደርጉ ትዝ ይለኛል፡፡ በተለይ ኢድ አል አድሀ ሲሆን በዐሉ የብሉይ ኪዳንን ታሪክ ተከትሎ ስለሆነ ያንን ጠቅሰው ይናገሩ ነበር፡፡ ‘’አብርሐም አንድ ልጁን ለእግዜር መስዋዕት ሊያደርግ ሲል እግዚአብሔር በልጁ ፈንታ እንዲሰዋ በግ የላከለትን በመዘከር ነው ኢድ አል አድሀ የሚከበረው፡፡’’ በማለት፡፡ በእርግጥም እስላሞችም በዚህ በዐል በግ የሚያርዱት ከዚህ ተነስተው ነው፡፡
በደብረ ሳሌም ቤተክርስትያን ታቦት ሲወጣ ብዙ የእስላም ልጆች መጥተው ስነስርአቱን ይከታተሉ እንደነበር የሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ መምሬ መኮንን አንድ ልጅ ብቻ ነበር ያላቸው፡፡ እሱንም ተፈሪ ብለው ስም አወጡለት፡፡ ተፈሪ መኮንን፡፡ ያኔ ታድያ ግረየስ የሚባል ጆሮ ጠቢ ነው ተብሎ የሚታማ እና የሚፈራ ረዳት ባቡር ነጂ’ (‘‘ኤድ ኮንዲክተር’’) ነበር፡፡ እና አንድ ቀን መምሬ መኮንን ልጃቸውን ከጎናቸው አድርገው ወደ ለገሀር ሲሄዱ፣ ከኤድ ኮንዲክተር ገብረየስ ይገናኛሉ፡፡ ሰላምታ ተለዋወጡና መስቀላቸውን አሳልመውት ሊሄዱ ሲሉ
‘’መምሬ መኮንን ልጅዎ ይሄ ነው እንዴ?’’
ብሎ ይጠይቃቸዋል
“አዎን ልጄ ነው፣ ተፈሪ፣ በል በሁለት እጅህ ጨብጠው ጎንበስ ብለህ’’
ይሉታል፡፡ መጨባበጡ እንዳለቀ ረዳት ባቡር ነጂው ገብረየስ
‘’ተፈሪ ብለው ሲጠሩት ሰማሁ ልበል? ተፈሪ መኮንን መባሉ ነው?’’ ሲላቸው
መምሬ መኮንን ፈጠን ብለው
“ በደንብ አልሰማኸኝም ማለት ነው፡፡ ‘ተፈራ’ ነው ያልኩት፡፡ ተፈራ መኮንን!”
አሉት ኮስተር ብለው፡፡
በእስር ቤት ቆይታችን ይህንን ጉዳይ አንስቼላቸው ነበር፡፡
‘’አየህ፣ ነገሩ እንዴት ነው፣ መቸስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ‘ተፈሪ መኮንን’ ይባሉ የነበሩት ከመንገሳቸው በፊት ነው፡፡ እንደዛም ቢሆን የናንተ ስም መኮንን ከሆነ ልጆቻችሁን ‘ተፈሪ’ ብላችሁ እንዳትሰይሙ አላሉም፡፡ ግና ነጭ ለባሽን ማመን አይቻልም፡፡ የሚያወራው ምንም ነገር ካጣ ‘መምሬ መኮንን ልጁን ተፈሪ ብሎታል፡፡ የጃንሆይን ስም መሻማቱ እኮ ነው፣ አይ መንጠራራት ብሎ ቢያሳብቅብኝስ ማን ያቃል፡፡ በመጨረሻ አንኳ ተከራክሬ ረትቼ መለቀቄ አይቀርም፡፡ ቢሆንም እስኪጣራ ለምን ልጉላላ?’’
ብለው አጫውተውን ነበር፡፡ ዛሬን አያጫውቱንና
ለገሀር
እንደተቀሩት ባቡርን ተከትለው የተቆረቆሩና ያደጉ ከተሞች አዋሽ 7 ኪሎም የተስፋፋችውና ያደገችው ኩባንያ (የምድር ባቡር ድርጅት የቀድሞ አጠራር) ጣቢያውን አዋሽ ላይ ከተከለ በኃላ ነው፡፡ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ አማካይ ርቀት ላይ በመገኘቷ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከድሬዳዋና አዲስ አበባ ቀጥሎ ዋናዋ የባቡር ጣቢያ ሆነች፡፡ የባቡር ኮንዲክተሮች (ሹፌሮች) እና ሸፍተራኖች (የእቃ ባቡር ኃላፊዎች) የሚቀያየሩት አዋሽ ጣቢያ ላይ ነው፡፡ የድሬዳዋ ኮንዲክተሮች ባቡሩን ከድሬዳዋ አዋሽ ካደረሱ በኃላ አዋሽ ላይ አንድ ቀን እረፍት አድርገው፤ የአዲስ አበባ ኮንዲክተሮች ከአዲስ አበባ አዋሽ ድረስ ያመጡትን ባቡር ድሬዳዋ ያደርሳሉ፡፡ የአዲስ አበባ ኮንዲክተሮችን ባቡሩን እንዲሁ አዋሽ ካደረሱ በኃላ አንድ ቀን እረፍት አድርገው የድሬዳዋ ኮንዲክተሮች አዋሽ ድረስ ያመጡትን ባቡር ይዘው አዲስ አበባ ያደርሳሉ፡፡
የአዋሽ ለገሐር፡፡ ፊት ለፊት ባለ ቀይ ጣራው ዋናው ቢሮ ነው፡፡ በግራ በኩል ያለው ዲፖ
ነገሩን ትንሽ እናፍታታው
ያኔ የምድር ባቡር (ከአሁን ወዲያ በያኔው መጠሪያው ኩባንያ የምንለው) አስተዳደራዊ አወቃቀሩ ማለት በኢትዮጵያ በኩል አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ተብሎ በሁለት ይከፈላል።የድሬዳዋ ባቡር ነጂዎች፣የአዲስ አበባ ሸፍትራኖች፣ የድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ፖሊሶች …እየተባለ። የሰራተኛ ማህበሩ እንኳን የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ሴንዲካ ተብሎ ሁለት ነበር።
እንግዲህ አንድ ባቡር ከድሬዳዋ ተነስቶ አዲስ አበባ ሲሄድ እስከ አዋሽ ድረስ ባቡር ነጂውና ረዳቱ (ኤድ ኮንዲክተር)፣ ሸፍትራኑ (የመጓጓዣ ሂሳብ ተቀባይ) እና ፖሊሶቹ የድሬዳዋ ናቸው።ባቡሩ አዋሽ ሲደርስ የመንገደኛ ከሆነ ለምሳ አንድ ሰአት ያርፋል የእቃ ከሆነም ያድራል።የድሬዳዋዎቹ ሰራተኞች በአዲስ አበባ ምድቦች ተተክተው ባቡሩ ጉዞውን ይቀጥላል። የድሬዳዋዎቹ የመጡበትን ባቡር ለአዲስ አበባዎቹ አስረክበው የአዲስ አበባውን ባቡር ይዘው ወደ ድሬዳዋ ይመለሳሉ፡፡የአዲስ አበባዎቹም እንዲሁ።
ከምድር ባቡር ሰራተኞች ሸፍ ደስትሪክቱ (የሀዲዶችን ደህንነት፤የለገሀሩን ቅጥር ቤቶችና ተቋማት ይዘት ይህን ከሚያከናውኑ ሰራተኞች ጋር የሚቆጣጠር)፤ሸፍ ደሀልቱ (ለገሀሩንና የባቡሮችን እንቅስቃሴ እና ይህን የሚያከናውኑ ሰራተኞችን የሚቆጣጠር) እና ዋናው ስልከኛ በቀጥታ ቤታቸው ውኃ ይገባላቸዋል፡፡ ዴፖውና ቡፌ ደ ላጋርም እንዲሁ፡፡ ከዚያ ውሀ ልማቱ እና የኩባንያው ክሊኒክም እንዲሁ ውኃ ገብቶላቸዋል፡፡ ከምድር ባቡር ውጪ ውኃ የገባላቸው ቀደም ሲል የሰብለወንጌል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ በኃላም እናቴ ሰርታ ታከራየው የነበረው ቤትና የትዬ አበበች ባቡ ቡና ቤት ብቻ ናቸው፡፡
ስለዚህም የአዋሽ ለገሀር ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ለገሐሮች ቀጥሎ ትልቁ ነበር፡፡ ጣቢያው ጽ/ቤት ጎንና ጎን ትልልቅ መጋዘኖችን ከነሱም ወደ ባቡሩ እቃ በቀላሉ እንዲጫንበት ከፍ ያለ በሲሚንቶ የተገነባ ጫፉ ሾል ያለ ቅርጽ ያለው ግንባታ አሁንም አለ፡፡ ባቡሮች ማነቭር (ፎርጎ የሚቀያየርበት እንቅስቃሴ) የሚያደርጉባቸው በርካታ ሀዲዶች አሉ፡፡ አንዱ የባቡር ጣቢያውን ድንበር ዘልቆ እስከ ያኔው መጋላ ደረስ ይሄዳል፡፡ ከባቡሩ ጣቢያ ጎን ትልቁ የአዋሽ ቡፌ ደላጋር ይገኛል፡፡ ይህ ለከተማው እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ትልቁና ዘመናዊው ሆቴል ነው፡፡
በኔ ጎረምሳነት ጊዜ ለገሀር የደመቀ ሰፈር ነበር፡፡ በተለይ ኦተራይ (አውቶ ሬይል ወይም የሀዲድ መኪና) ስትገባና ስትወጣ፡፡ ኦተራይ ከድሬዳዋ ስትመጣ ኮንትሮባንድ እቃም አብሮ ስለሚመጣ ፍተሻው ግርግሩ ሌላ ነው፡፡ ሰላማዊ መንገደኛም ሆነ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎቹ ከድሬ ዳዋ እስከ አዲስ አበባ ባለ ጉዞአቸው ምሳ የሚበሉት አዋሽ ነው፡፡ ቡፌ ደላጋር እና ቅርብ በሆኑት ምግብ ቤቶች ከሚመገቡት በተጨማሪ እዛው ባቡር ስር ምግብ፣ ሻይ፣ ቡና፣ ቆሎ፣ ጉልጉል፣ አትክልት በኃላም የዘንባባ መጥረጊያ የሚሸጡት ሰዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ ልክ ኦተራይ ገብታ ስትቆም ”አለ ቆሎ፣ አለ እንጀራ፤ አለ ቡና ሻይ፤መጥረጊያ…” ጩኸትና ሁካታው ትልቅ ገበያ የቆመ ያህል ነበር፡፡ በኃላማ በአንድ ቀን ሁለት ኦተራይ (አንድ የአዲስ አበባ ሌላው የድሬዳዋ) አንድ ላይ ሲመጡ የበለጠ ደምቃ ነበር ለገሀር፤ ለአንድና ለሁለት ሰአት ቢሆንም፡፡
ሌላው ለገሀር በጣም የሚደምቅበት ጊዜ ቀስ ነጂ ሲመጣ ነበር፡፡ ቀስ ነጂ ለኩባንያ ሰራተኞች ደሞዝ የሚከፍል ባቡር ነበር፡፡ በነጭ ፎርጎ ውስጥ ደሞዝ ከፋዩ ይቀመጥና ሰራተኛው በየተራ እየመጣ ደመወዙን ይወስዳል፡፡ በሌሎች ኤል ኤል ፎርጎዎች ደሞ በአንዱ ጋዝ፤በሌላው ማሽላ በሶስተኛው ትልቅ አራት ማዕዘን ሳሙና ይታደላል፡፡ ጋዝና ማሽላውን ከተወሰነ ደመወዝ በታች የሚያገኙ ሰራተኞች ብቻ የሚወስዱት ሲሆን ሳሙናው ግን ለሁሉም ነበር የሚታደለው፡፡ ያን ቀን ፌሽታ ነው፣ ለገሀር ብቻ ሳትሆን አዋሽ ራሷም ደሞዛቸውን በተቀበሉት ሰራተኞች ግርግር ትደምቃለች፡፡ ሱቆች በደብተር እየመዘገቡ በዱቤ የሰጡትን ሸቀጥ ክፍያ ይቀበላሉ፤ቡና ቤቶች ደመወዝተኞችን ለማስተናገድ ሽር ጉድ ይላሉ፤ ጫት ተራና ጉልትም ሰርግና ምላሻቻ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ መጥተው በየተራ አዋሽ ለገሀር ለአንድ ቀን የሚያርፉት የባቡር ሰራተኞችም ሌላው የለገሀር ጌጦችና ትዝታዎች ነበሩ፡፡ ለአባቴ የአዲስ አበባዎቹ ባቡር ነጂዎች ገዘብ እየሰጣቸው ጋዜጣ አንዳንዴም መጽሄት ይዘውለት ይመጣሉ፡፡ የድሬዳዋዎቹ የኤረር ብርቱካን/መንደሪን ያመጡልን ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ እንደ ኤረር ብርቱካንና መንደሪን የሚጣፍጥ ሀገር ቤትም ሆነ ውጭ ሀገርም አልገጠመኝም፡፡ የባቡር ሰራተኞች ተጫዋቾች፤ ተዝናኞችና እርስ በርስም የሚተሳሰቡ ነበሩ፡፡
ሌላ ጊዜም ቢሆን ደርግ ሲመጣ ቀዘቀዘ እንጂ እህልና ከብት ሲጫንና ሲወርድ ትርምሱ ደስ ይል ነበር፡፡
ባቡር ታድያ ከተገለበጠ ወይም ሰው ከገጨ አደጋ ነበር፡፡ በባቡር አደጋ የሞቱ ሰዎች ነበሩ በተለይም አንድ የመተሀራ ጥርሰ ፍንጭት ጎረምሳ የኮንትሮባንድ ነጋዴ አይረሳኝም፡፡ ባቡር ሄዶበት ብልሽትሽቱ ወጥቶ ሞተ፡፡ መተሀራ ድረስ ሄደን ቀበርነው፡፡
ሌላው በባቡር ቀኝ እጁን አጥቶ አሁን ትልቅ ነጋዴ ሆኖ ወልዶ ከብሮ የሚኖረው አብሮ አደጋችን ጉደሌ ወይም መሐመድ ሰዒድ ነው፡፡
አዋሽ ትንሽ ከተማ ናት አንዱ ሌላውን ያውቃል፤ ኦተራይ ስር የምንሄድ ታድያ ግርግሩን በመውደድ ብቻ ሳይሆን አዲስ ሰው ለማየት ነበር፡፡ ኮንትሮባንድ ሻጮችና ፊናንስ/ጉምሩኮች ሌባና ፖሊስ ሲጫወቱም አንድ ትርዒት ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ በአንድ ጊዜ ሁለት ባቡሮች ማለትም ከአዲስ ወደ ድሬ እና ከድሬ ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱት ኦተራዮች ከ ሰባት እስከ ስምንት ሰአት ድረስ ሲቆሙ ምድሩ ቀውጢ ይሆን ነበር፡፡
መስከረም ሁለት ሊቃረብ ሲል ደሞ የባሻ ደለሳ (የምድር ባቡር ፓሊስ አዛዥ እና የከተማው አብዮት ጥበቃ አዛዥ) አብዮት ጠባቂዎች ተጨማሪ ትርዒት ነበሩ፡፡ የፊናንስ ፖሊሶች ኮንትሮባንዲስቶችን ሲከታተሉ የባሻ ደለሳ አብዮት ጠባቂዎች ደሞ ጸጉረ ልውጥ ያስሳሉ፡፡ አንድ ቀን ከአብዮት ጠባቂዎቹ አንዱ አንድ ዋርካ የሚያህል አፍሪካዊ ይዞ ባሻ ደለሳ ጋ ይመጣል፡፡ ባሻ ደለሳ ፖሊስም ሆነ አብዮት ጠባቂ ሰው አስሮ ሲያመጣላቸው ሰውየውን መጀመርያ በጥፊ ከመቱት በኃላ ነበር ማንነቱንና ለምን እንደተያዘ የሚጠይቁት፡፡ ታድያ የባሻ ደለሳ ጥፊ ተራ ጥፊ አይደለም፤ እንደ ሰውነታቸው የእጃቸው መዳፍም ሰፌድ የሚያክል ስለሆነ በዚያ አንዴ ጥፊያቸውን የቀመሰ ወድቆ ነበር የሚነሳ፡፡
ይህን አፍሪካዊም እንዲሁ ጥፊ አላሱት፣ ግን ንቅንቅም አላለ፡፡ ብቻ እየጮኸ በፈረንሳይኛ ይለፈልፋል
‘‘ከስከቱፌ? ሴኔፓ ጁስት. ዠስዊ አዚል ፖለቲክ…’’ እያለ
‘‘ማነው እሱ ለምንድነው ያመጣኸው?’’ ብለው ጠየቁ
‘‘ኧረ ጸጉረ ልውጥ ነው፤ አያዩትም እንዴ አማርኛ እንኳ አይችልም እኮ፤ የሶማሌ ሰርጎ ገብ ይመስለኛል’’ አላቸው፡፡
‘‘በል አቆየው’’ ብለው ሄዱ፡፡ ሰውየው ቢለፈልፍ ቢጮህ የሚሰማው አጣ፡፡ የተሳፈረበትም ኦተራይ ትታው ሄደች፡፡ ባቡሩን ሸኝተው ሲመለሱ ሰውየውን የጣቢያው ሰራተኞች ከበውት ደረሱ
‘‘ማነው እሱ አወቃችሁት?’’ ብለው ሲጠይቁ
አንደኛው የባቡር ጣቢያው ሰራተኛ (ፈረንሳይኛ ይችላል)
‘‘እንዴ ባሻ ይሄ እኮ መንግስት የፖለቲካ ጥገኝነት የሰጠው ዛየራዊ ነው፤ ምን አርግ ብላችሁ ነው የያዛችሁት፡፤ ከመንገዱ አስታጎላችሁት እኮ’’፡፡
‘’ይኼ ነዋ ሳያጣራ ያመጣው ብለው አብዮት ጥበቃውን’’ በጥፊ አላሱት፤በቁሙ ሁለቴ ከዞረ በኃላ በሶስተኛው በጀርባው መሬት ላይ ተዘረጋ
‘‘ምን እናርገው‘’ ቢባሉ ንዑስ እዝ መምሪያ ውሰዱት ስላሉ በዚያው የጣቢያው ሰራተኛ አማካይነት ወደ ኮኖሌል ገብረየሱስ የአንደኛ ክፍለ ጦር ንዑስ እዝ መምሪያ ኃላፊ ጋ ወሰዱት፡፡ ዛየሩ ይለፈልፋል
‘‘ዠ ስዊ ዛየርዋ፤ አፍሪካን፡፡ ኑ ሶም ሴ ላ ሜም ፖ’’ ይላል የእጁን ቆዳ እየሳበ፡፡ ኮኖሌሉም
‘‘ሰዐት ጠፋብኝ ነው የሚለው?’’ ብለው ጠየቁ፡፡ ቱርጁማኑ ሳቁን አፍኖ
‘‘አይደለም፡፡ እሱ የሚለው እኔ ዛየራዊ ማለት አፍሪካዊ ነኝ፡፡ እንደናንተው ቀለሜ ጥቁር ነው፡፡ አንድ ዘር ነን ነው የሚለው…’’ ብሎ ሳይጨርስ ኮኖኔል አቋረጡት
‘ሂድ! እንዴ! ይኼ ጣፉርዲያም ባሪያ፤ ከኔ ጋር አንድ ዘር ነኝ ይላል እንዴ?’ አሉ
‘’ለማንኛውም ምን አርጉኝ ነው የሚለው?’’
‘’ባቡሩን አስመልጠውት ከጉዞው አስታጎለውታል፤ መጠለያም የለው’’
‘’ታድያ በሚቀጥለው ባቡር በነጻ ሸኙታ፤ ለባሻ እንግርለታለሁ፡፡ እስከዛ እዛው ለገሀር ከናንተ ጋ ይቆይ፡፡ በቋንቋም ስለምትግባቡ ያጫውታችኃል‘’ ብለው ሸኙት
በደርግ ዘመን እንግዲህ የአዋሽ ኗሪዎች ገቢ የሳምንቱ ሰኞ ገበያ ብቻ መሆኑ ቀርቶ በመንገደኛ እና በእቃ ባቡር የሚመላሰው ኮንትሮባንድ ንግድ ሆኖ ነበር፡፡ እውነት ለመናገርም የከተማው ህዝብ የኑሮ ደረጃም በተያያዘ ተሻሽሎ ነበር፡፡
ከ ቢፌ ደላጋር (የፈረንጅ ምግብ ቤት) በስተቀኝ የውኃ ልማት ቢሮ ከዚያም ለጥቆ የባቡር ክሊኒክ አለ፡፡ ከባቡር ጣቢያው በስተኃላ የሰራተኞች ቤቶች በብዛት ይገኛሉ፡፡ በነዚህም ቤቶች በርካታ ሶማሌ ኦሮሞ፣ እና አማርኛ ተናጋሪዎች ይኖራሉ፡፡ በዴፖው ባቡር የሚፈተሸበት ጉድጓድ አለ ከሱ አጠገብም የባቡር ኮንዲክተሮች እና ሸፍተራኖች ማረፊያ ክፍሎች (ሻምበሮች) አሉ፡፡ የዴፖው ግቢ በአትክልቶች የተሞላ ነው ቢርካም (እንደ ቦኖ ውኃ ማደያ አይነት) አለው፡፡ ከዴፖው ተያይዞ ሙሉ አልጋ እና የመኝታ ቤት እቃ ያላቸው መኝታ ቤቶች፤የጋራ ሽንት ቤትና መታጠቢያ ቤቶች፤ የውኃ ቢርካ እና በድንጋይ የተሰሩ የልብስ ማጠቢያዎች፤ እንዲሁም በተለያዩ አትክልቶች ያጌጠ አፀደ ጽጌ ይገኛል፡፡
እንግዲህ አዋሽ በኩባንያ ምክንያት እመርታዊ እድገት አሳይታለች፡፡ ከመንደርነት ወደ ከተማነት የተለወጠች ሆነች፡፡ ጣልያንም ትንሽ ለእድገቷ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ከጣልያን ስራዎች አሁን የቀረው አንድ አሮጌ ሐውልት ነበር፡፡ ይህ ሐውልት በልጅነታችን የበለጠ ያምር ነበር፡፡ በየብሄራዊ በአላቱ ኖራ ይቀባል፡፡ ዙርያውን በሰንሰለት የተያያዙ ጥሩ ቅርጽ ያላቸው የድንጋይ ግንባታዎች ነበሩ፡፡ይመስለኛል ጣልያን ባንዲራ የሚሰቅልበት ሐውልት ሳይሆን አይቀርም፡፡ አሁን አርጅቶ መለመሉ ብቻ ቀርቷል፡፡ ውሀ እና ኮረንቲን ለከተማዋ ያስተዋወቀው ግን ቀደም ብሎ ኩባንያ ነው፡፡ ነዋሪውም በቁጥርም በአይነትም በረከተ፡፡ በፊት በከተማዋ አማሮች፤ አርጎቦች ፣ሶማሌዎችና፣ አፋሮች (ኢትዮጵያውያን) ሲሆኑ በኃላ ግን አረቦች እንዲሁም ከባቡር ጋር የመጡ ፈረንሳዮች ግሪኮችና ጣልያናዊ ዜጎች ይኖሩባት ነበር፡፡
የጣሊያን ሐውልት
ስለዚህም አዋሽ እኛ ስናድግባት ትንሿ ሜትሮፖሊታን ነበረች፡፡
የቡፌ ደላጋር ባለቤት ማዳም ኪኪ አሲማ ኮፕሎስ ከነ ሶስት ልጆቿ፤ የያኔው ሸፍደስትሪክ ጣልያኑ ደፒያኖ ከፈረንጅ ክልስ ባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ጋር፤በኃላ የአጂፕ ባለቤት የነበረው ጣልያኑ ጋርጆሌ… አረቦቹ እና የተወሰኑም ሱዳኖች ነበሩ፡፡ በሐይማኖትም ኦርቶዶክስ እና ሙስሊም ዋናው ኃይማኖቶች ሲሆኑ እነ ጋርጆሌ ግን ካቶሊኮች ነበሩ፡፡
ዋናው ለገሀር ስልክ ቤት እና ግሼው (ገንዘብ ቤቱ) ተብለው ይከፈላሉ፡፡ በመሀል ትልቅ የብረት ሚዛን ያለበት በረንዳ አለ፤እቃ እዚያ እየተመዘነ ነው ታሪፍ የሚወጣለት፡፡ ከስልክ ቤቱ ጀርባ ትልቅ መጋዘን ከመጋዘኑም ፊት ለፊት ሁሌም የቆመ ፉርጎ ይገኛል፡፡ ስልክ ቤቱ ሶስት ስልኮች ነበሩት፤ ሁለቱ ተለቅ ያሉት አንዱ ወደ ድሬዳዋ አንዱ ወደ አዲስ አበባ የሚያገናኙ በየመስመሮቹ ካሉ ጣቢያዎችም ግንኙነት የሚደረግባቸው ናቸው፡፡ የመካከለኛው ትንሹ ስልክ ከጅቡቲ የሚያገናኝ ነው፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና በዚህ ስልክ አባቴ በመንግስቱ ነዋይ ግርግር ጊዜ አዋሽ መጥተው ለከተሙ የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋዜጠኞች መልዕክት ያስተላልፍላቸው እንደነበር ነግሮኛል
‘’በኃላ ደሞ አሜሪካን ጋዜጠኞች መጡ፤ ዶላር እያሳዩኝ ‘ቼንጅ’ እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡ ደሞም ትንሽ ይዋሻሉ፤እዚህ ሆነው ልክ ከአዲስ አበባ አስር ማይል ርቀት ላይ ነን እያሉ ነበር የሚያስተላልፉት’’ ብሎ አጫውቶኛል፡፡
አሁንም ነገርን ነገር ያነሳዋልና ስለ ስልኩ ላጫውታችሁ፡፡ እንግዲህ ምድር ባቡር ኢትዮጵያን ከስልክ ጋር ያስተዋወቀ ነው፡፡ ከፈረንሳይ ጋር በተደረገው ስምምነትም የኢትዮጵያ መንግስት ስልኩን እንዲጠቀም ፈቃድ ሰጥቶታል፡፡ የስልኩ አሰራር መጀመርያ ከጣቢያ ወደ ጣቢያ የሚደረግ አይነት ነበር፡፡ ለምሳሌ ከአዋሽ ድሬዳዋ መነጋገር ቢፈለግ መጀመርያ ከአዋሽ አርባ ከዚያ የአርባው ስልከኛ ከኮራ የኮራው ከአሰቦት የአሰቦቱ ከአፍደም የአፍደሙ ከሚዔሶ የሚዔሶው ከቢኬው የቢኬው ከኤረር የኤረሩ ከድሬዳዋ ያገናኛል ማለት ነው፡፡ በኃላ እኛ ነፍስ ስናቅ እደ ጥበቡ (ቴክኖሎጂው) ተሻሽሎ አዲስ አበባ ሳንትራል በመደወል ከሁሉም ጣቢያዎች መገናኘት ተቻለ፤ቀጥሎም በኢትዮጵያ ቴሌፎን መጠቀም ሲጀምሩ የትኛውም ጣቢያ ከየትኛውም በቀጥታ መገናኘት ችለው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ባቡርም ቆመ፡፡
ከምድር ባቡር ምስረታ ጋር አብሮ የገባው ስልክ እስከ አምሳዎቹ መጨረሻ ድረስ አዋሽን ስልክ ካላቸው ጥቂት የሀገራችን ከተሞች አንዷ አድርጓታል፡፡ በልጅ እያሱ ላይ መፈንቅለ መንግስቱ ሲሸረብ መዒሶ ከተማ አካባቢ የነበረውን ጦርነት እነ ፊታውራሪ ተክለኃዋርያት ከአዋሽ ነበር የሚዘግቡት፡፡
ከዴፖው ጎን ቀጭን የሀዲድ መስመርን አልፎ የጣቢያው ኃላፊ (ሼፍ ደ ሀልት) መኖርያ አለ፡፡በኃላ አባቴ እድገት አግኝቶ ሼፍ ደ ሀልት ሲሆን እኛም ከኖርንበት ቤታችን ወጥተን ሼፍ ደ ሃልቱ ቤት ኖረንበታል፡፡ አባቴ ሞቶ ከለገሀር ከመውጣታችን በፊት እዚህ ቤት ለአምስት አመት ያህል ቆይተንበታል፡፡ ሰፊ ቤት ሲሆን ዙርያውን በወይን፤ በብርቱካን በዘይቱና፣ ሎሚ፣ አጥ፣ እና ቴምር ዛፎች የተከበበ ነው፡፡ ሁለት ትልልቅ ልብስ ማጠቢያ ቢርካዎች አሉት ከነሱ ፊት ለፊት ገላ መታጠብያ ቤቱ ይገኛል፡፡ ቤቱ ሰፊ በረንዳና ሁለት ትልልቅ መኝታ ቤቶች አሉት፡፡ አንደኛው እንደሳሎንና የኔ መኝታ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ከሱ በስተኃላ አንድ ማድቤት አንድ እቃ ቤትና አንድ የሰራተኛ ማደሪያ ክፍሎች አሉ፡፡
እንደ ሳሎን እና የኔ መኝታ ቤት ሆኖ የሚያገለግለው ክፍል ገረዶች ሲቀጠሩም እዚያው ነበር የሚያድሩት፡፡ ልጅ ሆኜ ያው ዝም ብዬ ነበር የምተኛው፡፡ ስጎረምስ ግን ገረዶቹን መከጀል አመጣሁ፡፡ ከገቡት ገረዶች ሁሉ ትዝ የምትለኝ ሐይማኖት የምትባል ከአዲግራት የመጣች ጠይም አጭር ሴት ናት፡፡ ድንግሌን የወሰደችው እሷ ስለሆነች ከተቀያየሩት አራት እና አምስት ገረዶች ሐይማኖት አሁንም ትዝ ትለኛለች፡፡
ከሼፍ ደሃልቱ ቤት ቀጥሎ አሸዋማ ሜዳ አለ ከሱ ቀጥሎ ተለቅ ያለው የሸፍ ዲስትሪክቱ ቤት ይገኛል፡፡ ልጅ ሆነን ደፒያኖ የሚባል ፈረንሳዊ ሸፍ ዲስትሪክ፤ ክልስ ባለቤቱ ኑርያና ሁለቱ ልጆቹ ይኖሩ ነበር፡፡ በዚያች አሸዋማ ሜዳ ላይ ከደፒያኖ ልጆች እና ከአባቴ በፊት ሸፍ ደሀልት የነበረው የሶማሌው ኡመር አሊ ልጆች ጋር ኳስ ስንጫወት አድገንበታል፡፡
ሴሴ የሚባለው የእቃ ባቡር
በሁለቱ ትልልቅ ቤቶች መሐል ከአሸዋማዋ ሜዳ መጨረሻ ላይ የልጅነት ህይወቴን ያሳለፍኩባት ቤት ትገኛለች፡፡ ይህች ቤት ሰፊ ግቢ ትንሽ በረንዳ ሁለት መኖርያ ክፍሎች ሌላ አነስ ያለ ግቢ ማድቤት የሰራተኛ መኖርያና ሽንት ቤት አላት፡፡ ከጎኗ ጣሊያን ያቆመው ሐውልት; ከሱ ቀጥሎም የመንግስት ቴሌ ቢሮ አለ፡፡ ከጣሊያኑ ሐውልት ቀጥሎ የደብረሰላም ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን አለች፡፡ ከቤተክርስትያኗ ከፍ ብሎ ደሞ የመሰረት ድንጋዩን ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የጣሉት የሰብለወንጌል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኛል፡፡
ከቤታችን ኃላ ካለው ቴሌ ጎን ፖሊስ ጣቢያው ፤ፍ/ቤቱ፤ የከተማው አስተዳደር (ባለ አንድ ፎቅ ጣሊያን የሰራው ህንጻ) እና በቅርብ የተገነባው ማዘጋጃ ቤቱ ይገኛል፡፡ አስተዳደሩ ስር እስር ቤቱ ነው የሚገኘው፡፡ ከዚያ በስተጀርባ ሰፋ ያለ የእግር መንገድ ሲኖር ቀጥሎ እስከ አስፋልቱ ድንጋይ ቤቶች ያሉበት ሰፈር ነው፤ አማርኛ ተናጋሪዎች ይበዙበታል፡፡ የዳይሬክተሩ ቤትም እዚያ ነበር፡፡
በከተማው ኤሌክትሪክ ያለው በለገሀር ሲሆን በቤታችን ቧንቧ ያለንም እኛ፤ ሼፍ ደሃልቱ፤ ሼፍ ደ እስትሪክቱ፤ ቡፌ ደላጋር፤ ዴፖ፤ የውሃ ልማት ቢሮውና ክሊኒኩ ብቻ ነበር፡፡ ከሼፍ ደሃልቱ ቤት ጀርባ ትልቅ ቢርካ አለ፤ ለቀረው የኩባንያ ሰራተኛ እና ለከተማው ውሃ በበርሚል እና በባሊ ይከፋፈላል፡፡ በጥምቀት ጊዜም ቢርካው እንዲሁ ሀይማኖታዊ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በምድር ባቡር ክልል የመንግስት ፖሊስም ሆነ አስተዳደር ወደ በኃላም ቀበሌ አይገባበትም፡፡ ምድር ባቡር የራሱ ፖሊስ ጣቢያ ከለገሃሩ ጀርባ አለው፡፡ የፓሊስ ጣቢያው አዛዥና ፖሲሶቹ ከኛ ቤት በስተግራ ባሉ አራት ወይም አምስት ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ፤ ቤቶቹም የኩባንያው ቤቶች ናቸው፡፡
ባቡሮቹ
ባቡሮችን ለሁለት መክፈል ይቻላል የእቃና የመንገደኛ፡፡ ከነዚህ ውጪ ያለው ለሀዲድ ጥገና ወቅት ሸፍ ደ ስትሪኮች የሚጠቀሙባት ደረዚን ነች፡፡ ደረዚን የሀዲድ ላይ ባጃጅ ነች ባለ አራት እግር ከመሆኗ ሌላ፡፡
ጂቦ ባቡር በከሰል የሚሄደው ጥቁር ባቡር ነበር፡፡ ይህ ባቡር ሲሄድ የሚያወጣው ድምጽ ‘‘ይዤሽ ከተፍ፤ይዤሽ ከተፍ’’ የሚል ይመስላል፡፡ ይህ ባቡር ስራ ካቆመ ዘመን የለውም፤ እኔም ትዝ የሚለኝ እንደ ቅዠት ነው፡፡ ናዝሬት ላይ ግን እስከ ስልሳዎቹ አጋማሽ ድረስ ለማነቭር አገልግሎት ላይ ይውል ነበር፡፡ ማነቭር ፈረንሳይኛ ቃል ሲሆን የባቡር ፉርጎዎችን ለማስተካከል እና ቦታ ለማዘዋወር በከተማ ውስጥ የሚከናወን የባቡር እንቅስቃሴ ነው፡፡ አንዴ አንድ አሜሪካዊ ናዝሬት ላይ ጂቦ ባቡር ማነቭር ሲሰራ አይቶ በትልቅ ስሜትና መገረም ፎቶ ሲያነሳው እንደዋለ ሰምቻለሁ፡፡ አገሩ በጥንት ፊልሞች ላይ የሚያየውን ሙዚየም የገባ ሎኮሞቲቭ እዚህ በቁም ነገር ስራ ላይ ሲያየው ምን ያድርግ?
ጂቦ ባቡር የሚባለው በከሰል የሚንቀሳቀሰው የእፋሎት ባቡር አዋሽ ዲፖ እንደቆመ
ቤቤ የሚባለው የእቃ ባቡር ነው፡፡ እቃ የጫኑ ፉርጎዎችን የሚስብ፡፡ ከእቃ ባቡሮች ትልቁ እና ብዙ ፉርጎ የሚስበው ሴሴ የሚባለው ነበር፡፡ ይህ በመጨረሻ የመጣ የእቃ ባቡር ነበር ኢትዮጵያ የገባው በ 1957 አካባቢ ነው፡፡ በጣም ትልቅ ባቡር ሲሆን ብዙ ግዜ ግን ሀዲዱን ስቶ የመገልበጥ አደጋ ይደርስበት ነበር፡፡ እንደሰማሁት ምክንያቱ ከባቡሩ ሳይሆን ከሀዲዱ ነበር፡፡ ከተዘረጋ የቆየው ሀዲድ ዘመናዊ ባቡሮችን ማስተናገድ ይሳነው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ያኔ ኩባንያ የሚገዛቸው ባቡሮች በሙሉ በእውቅ የሚሰሩ በዚያ ጥንታዊ ሀዲድ ላይ መሄድ የሚችሉ ብቻ ነበሩ፡፡
ሁሉም ባቡሮች ስሪታቸው ፈረንሳይ ሲሆን አንዷ ብቻ ከስዊትዘርላንድ የመጣች ነበረች፤ ስሟም ኤስ ኤል ኤም ይባል ነበር(ስዊስ ሎኮሞቲቭ ማኑፋክቸሪንግ)፡፡ ፉርጎዎችም እንዲሁ አይነት አይነት ነበራቸው፡፡ አብዛኛዎቹ በር እና ጣርያ ያላቸው ከተማ ውስጥ ካሉ እንደ ቤትም ሊያገለግሉ የሚችሉ ነበሩ፡፡ ፈሳሽ የሚጭኑት በቦቴ መልክ የተሰሩ ሆነው ‘’ስቴርና’’ ይባላሉ፡፡ መኪና ለመጫን የሚያገለግሉት ፉርጎዎች ክፍት ናቸው፡፡
የእቃ ባቡሮች በቁጥራቸውም ይጠራሉ፡፡ ሸመን ደ ፌር (ኩባንያ) የስራ ቋንቋው ፈረንሳይኛ ስለነበር እኛም ባቡሮቹን የምንጠራቸው በዚያው በፈንሳይኛ ስማቸው ነው፡፡ ከሁሉም ትዝ የሚለኝ ስዋሳን ሴት (67) ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰራተኛው ‘‘ስዋሳን ሴት ሰርቶ ለሴት’’ ስለሚሉ ነው፡፡ ሸፍ ደ ትራኖቹ ከደሞዛቸው ሌላ ብዙ ገንዘብ ቢያገኙም በሴት ይጨርሱታል ለማለት ይመስለኛል፡፡ ሴሴ ደሞ ጥሩምባው ከሌሎች የተለየ ነበር፤ ልክ ‘‘ፋም’’ የሚለውን ቃል የሚያወጣ ይመስላል፡፡ ፋም በፈረንሳይኛ ሴት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም
ይላል ሴሴ፣ ይላል ሴሴ፤ ፋም ፋም ይላል ሴሴ
ሸፍትራን ስለሺ ኮንዲክተር ደምሴ
ተብሎም ተዘፍኗል፡፡ ሼፍ ደትሬይን ወይም በተለምዶ ሸፍትራን የእቃ ባቡሮች ለሚሄዱበት ጎዞ ኃላፊ ማለት ነው
ሸፍትራን ስለሺ ማለት ኮሚክ የሆነ ሰው ነበር፡፡ ድምጹን መቀያየር ይችልበታል፡፡ አንድ ቀን በጣም በጠዋት ኡመር አሊ (ጎረቤታችን የነበረው) ቤት ጠጋ ብሎ እንደ ላሊበላዎች እያዜመ ሲለምን፤ ኡመር አሊ በከፊል የእንቅልፍ ስሜት ተነስቶ ሁለት ብር ሰጥቶታል፡፡ ቀንም
‘‘ኡመር አሊ ሌሊት ምን ሲያደርግ እንዳደረ አላውቅም፤ ጠዋት እንደ ላሊበላ ሳዜምበት ምንም ሳይለየኝ ገንዘብ ሰጠኝ’’ እያለ መሳቂያ አድርጎት ነበር፡፡ የአማርኛ ዘፈኖችን በፈረንሳይኛ እየተረጎመ ይዘፍንልን ነበር
ሲጋራ አጬሳለሁ ላንቺ ስል ላንቺ ስል
በሚወጣው ጭስ ውስጥ አገኝሽ ይመስል
የሚለውን
ሸ ፊየም ለ ሲጋሬት ሴ ፑር ቷ ሴ ፑር ቷ
ከራዮን ተ ትሩቬ ደ ላ ፊሜን ሶርቷ
ይለው ነበር፡፡
ለእንግሊዝኛም አይሰንፍም
አሽከር አበባው ናልኝ፣አሽከር አበባው ናልኝ
ሌቱም አይነጋልኝ
የሚለውን የጠለላ ከበደ ዘፈን በእንግሊዝና እንዲህ ይለዋል
ሰረቫንት ፍላወር ካም ካም፣ ሰረቨንት ፍላወር ካሚንግ
ናይት ዊል ኖት ቢ ሞርኒኒግ
ሌላ አንድ ሬድዋን የሚባል የድሬዳዋ ኮንዲክተር (ባቡር ነጂ) ነበር፤ብስል ቀይ ሲሆን አማርኛ ትንሽ ይቸግረዋል፡፡ አባቴ እንደ ነገረኝ ከሆነ ቀደም ሲል አንድ ገብረየሱስ የሚባል ኤድ ኮንዲክተር ነበር (የባቡር አውታንቲ)ይህ ረዳት ባቡር ነጂ ነጭለባሽም ነው ተብሎ ይታማል፡፡ ታድያ አንድ ቀን ገብረየስ በሆነ ነገር ሬድዋንን ያናድደዋል፤ ሬድዋንም በአረብኛ የሚቀጥለውን ገጠመበት
ኤድ ኮንዲክተር ገብረየስ
አንተ በሳስ
ትሽቲ ረሳስ
ዋህድ ፎቀል ራስ
በግርድፉ ወደ አማርኛ እንመልሰው ካልን
አንተ ገብረየስ
የወጣልህ በሳስ
አንድ የጥይት ቀላህ
መልቀቅ ነበር ባንተ ራስ
ወደ መንገደኛ ባቡሮች ስንሄድ ልጅ ሆነን የምናቃት ባቡርም ፎርጎም ሆና የምታገለግል ‘’ኦተራይ’’ የምትባል ባቡር ነበረች፡፡አባቴ እንደነገረኝ ከሆነ ኦተራይ ‘‘አውቶ ሬይል’’ ወይም የሀዲድ ላይ ባቡር እንደማለት ነው፡፡ወደ በኃላ እንደሰማሁት ደሞ ኢጣልያኖች ሊቶሪና የምትባል የመንገደኞች ባቡር ካስመጡ በኃላ ሎተሪና ቀስ በቀስ ኦተራይ ሆነች፤ለነገሩ በኃላም ቢሆን ኦተራይን ሊቶሪና የሚሉ ትንሽ አልነበሩም፡፡ ይቺ ባቡር ከአገልግሎት የወጣችው ቄስ ትምህርት ቤት እያለሁ ነው፡፡
ወደ አዲሳባ እና ድሬ የሚሄዱት ኦተራዮች አንድ ላይ በአዋሽ ለገሐር
አዲሷ ኦተራይ የመጣችበትን ቀን አልረሳውም፡፡ ይህን ጉድ ለመመልከት የአዋሽ 7 ኪሎ ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ ነበር፤ ከቄስ አስተማሪዬ አባ ፍስሀ እና ከአይነ ስውሩ መሪጌታ ሞላ በስተቀር፡፡ ሰው ሳትጭን ግን አርፍዳ ነበር የመጣችው፤ ሰራተኞቹ በሯን ከፍተው ሲያሳዩን ትምህርቴን ረስቼ እዛው አርፍጄ ነበር፡፡ ስመለስ ታድያ አባ ፍስሀ የተቀበሉኝ በጉማሬ ነበር፡፡ ቅጣቱ አግባብ ስላልነበረው ነው መሰለኝ ከዚያ በላይ የገረፉኝን ረስቼ ይቺኛዋ ግን የህሊና ጠባሳዋ እስካሁን አልለቀቀኝም፡፡ በፍርድ ከሄደ በሬዬ አለፍርድ የሄደች ዶሮዬ ትቆጨኛለች እንደሚባለው፡፡
ሁለተኛዋ ኦተራይ ሎኮሞቲቯ መጀመርያ ላይ አንደኛ እና ሁለተኛ ማእረግን አንድ ላይ የያዘ ሲሆን መሀሉ ላይ የአዋሽ ቡፌ መጠጥና ፣የፔርሙዝ ቡናና ሻይ መሸጫ ነበረው፡፡ ፉርጎዎቹ ሶስተኛ ማዕረግ ናቸው፡፡ ወደ በኃላ የመጡት ኦተራዮች ግን ሎኮሞቲቩ አንደኛ ማእረግ ሲሆን ሁለተኛ ማእረግ ራሱን የቻለ አንድ ፉርጎ ሆኖ ሶስተኛ ማእረጎቹ ሌሎች ሁለት ወይም ሶስት ተሳቢዎች ነበሩ፡፡
እነዚህ ኦተራዮች ከመቶ አንድ ጀምሮ እስከ መቶ አምስት ቁጥር ስለነበራቸው አምስት ነበሩ ማለት ነው፤ወደ መጨረሻ ግድም መቶ ስድስትና መቶ ሰባትም ተገዝተዋል፡፡
ምድር ባቡርን በሃላፊ ግስ መግለጽ እንደ እኔ ላለ ባቡር ስር ላደገ ሰው አሳዛኝ ነው፡፡ ሰው አላፊ ጠፊ ነው፤ ለኛ ግን ምድር ባቡር የዘላለም ነበር፡፡ ይህንን ተፍጻሜተ ሸመንደፌር ሳያዩ ያለፉት እናት እና አባቴ እድለኞች ናቸው ያሰኛል፡፡
ሶስተኛው የባቡር አይነት የጃንሆይ ባቡር ነበር፡፡ ታድያ ባቡር ሳይሆን ፉርጎዎች ናቸው በአንድነት የጃንሆይ ባቡር ይባሉ የነበሩት፡፡ እነዚህ ነጫጭ ሁሌም ንጹህ የሆኑ ፉርጎዎች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ከምድር ባቡር ፖሊስ ጣቢያ ቀጥሎ ባለው ዲፖ ይቆሙ ነበር፡፡ ንጉሰ ነገስቱ ለፍልሰታ ድሬ ዳዋ ሲሄዱ ብቻ ነበር የሚጠቀሙባቸው፡፡ አንዳንዴም ሲያሰኛቸው ከፍልሰታ ውጪም ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ሲሆኑ በብዛት ግን አገልግሎታቸው ለፍልሰታ ነበር፡፡ የጃንሆይ ባቡሮች ሁለት ናቸው አንደኛውን ንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛውን የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ሻርል ደጎል በስጦታ ያበረከቱላቸው ነበሩ፡፡
እዚህ ላይ አንድ አባቴ የገረኝ ታሪክ ትዝ ስላለኝ ላጫውታችሁ፡፡ ነገሩን ግልጽ ለማድረግ ያኔ ጂቡቲ በፈረንሳይ ቅኝ ስር ነበረች፡፡ ጅቡቲዎች፣ ‘’ነጻነት ትፈልጋላችሁ ወይስ በፈረንሳይ ስር መቆየት ይሻላችኃል?’’ ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡ በተካሄደው የህዝብ ድምጽ፣ አብዛኛው የጅቡቲ ሰው ከፈረንሳይ ስር መቆየትን መርጦ ነበር፡፡ በኃላ በ ጁን 1977 ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው ሌላ የህዝብ ድምጽ ነው ጂቡቲዎች ነጻነትን መርጠው አገር የሆኑት፡፡
እንግዲህ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትቀላቀል የምጽዋ እና የአሰብ ወደቦችን መጠቀም ጀመረች፡፡ ይህ ደሞ የምድር ባቡር ኩባንያን ገቢ እና የጅቡቲን የምጣኔ ሐብት እንቅስቃሴ ጎዳው፡፡
ብልሁ ፕሬዚዳንት ሻርል ደጎል ታድያ አስቀድመው ለጃንሆይ ቆንጆ ቆንጆ ባቡሮችን ከላኩ በኃላ ለጉብኝት መጡ፡፡ ለዚህ ጉብኝት ሲመጡ በአይሮፕላን ቢሆንም የተመለሱት ግን በባቡር ነበር፡፡ አንድ ሌሊትም አዋሽ ቡፌ ደ ላጋር ‘’ፕሬዚደንታል ስዊት” አድረዋል፡፡ በዚህ ጉዞአችው ቀዳማዊ ኃይለስላሴን አግባብተው ኢትዮጵያ የተወሰነውን የገቢ እና ወጪ እቃዎቿን እንደቀድሞው በጅቡቲ በኩል እንድታስገባ አስደርገዋል፡፡
ጃንሆይም ለቁልቢ ድሬዳዋ ድረስ በአውሮፕላን መሄድ ሲችሉ ሁሌም የሚሄዱት በባቡር ነበር፡፡
አንዴ ከትምህርት ቤት እኔና አሻ ሸርጢ የምትባል ቆንጅዬ ሶማሌ ልጃገረድ ተመርጠን ለጃንሆይ አበባ ሰጥተናል፡፡ ፈገግ ብለው አበባውን ሲቀበሉን አሁንም ምስላቸው ፊቴ ላይ አለ፡፡ ያኔ ነበር የጃንሆይን ባቡር ተጠግቼ በሰፊው መስኮት በኩል ያየሁት፡፡ አንድ አንድ ባለ አምስት ብር ገንዘብ ለሁለታችንም ሰጡን፡፡ ቤት ስንደርስ እናቴ ያንን አምስት ብር ወስዳ ሌላ አምስት ብር ሰጠችን፡፡ ደርግ መጥቶ እስኪቀየር ድረስ አምስቱ ብር አልተመነዘረም ነበር፡፡
ጂቦ ባቡር አዋሽ ዲፖ ሲገባ
ሳቢል ጓሮ እና ጋራ ጉምቢ
ከለገሀር በስተጀርባ ትልቁ ገደል ሳቢል ጓሮ እና ጋራ ጉምቢ ይገኛሉ፡፡
የሳቢል ጓሮ ገደል ወደ ጎን ርዝመት ያለው ሲሆን ገደልነቱን በልጅነቴ ጥልቅ እንደሚመስለኝ ሳይሆን መጠነኛ ነው፡፡ ከሳቢል ጓሮ ገደል በስተግራ መጨረሻው ላይ የአዋሽ ወንዝ ያልፋል፡፡ ከተማው መጠሪያውን ያገኘው ከዚህ ወንዝ ነው፡፡ ትንሽዬ ፏፏቴም አለች፡፡ በክረምት አዋሽ ሲሞላ ከላይ ከደጋው አገር ያጥለቀለቃቸውን ከተሞች ግሳንግስ የማድቤት እቃ ሳይቀር ይዞ ይመጣል፡፡ ከተማው ውኃውን የሚያገኘው ከዚህ ወንዝ ነው፡፡ ኩባንያ አንድ ቤት ሰርቶ ማሺን በመትከል ውኃውን ስቦ ለገሀር ካመጣው በኃላ በድንጋይ በተሰራው ትልቁ ቢርካ እንዲጠራቀም ይደረግና ለኩባንያው ስራተኞች እና ከዚያ የተረፈውም ለከተማው ነዋሪዎች ይከፋፈላል፡፡
በአንድ ወቅት የዚህ ማሽን ሰራተኛ ስመጥሩው ኦሮምኛ ዘፋኝ አሊ ቢራ ነበር፡፡ በዚያ ጸጥታ በነገሰበት የአዋሽ ወንዝ አጠገብ የወፎችን ዝማሬ እና የፏፏቴውን ድምጽ እየሰማና እና በነሱም እየታጀበ ሽቦ ጊታሩን እየመታ ይዘፍን ነበር፡፡ይህ በግምት አንድ ኪሎሜትር ጥልቀት ባለው ገደል ውስጥ በሚገኘው የውሃ ማሽን ያለበት አንድ ክፍል ውስጥ ሲሰራ በአካባቢው ልምላሜና ውበት በእጅጉ ይመሰጥ ነበር፡፡ አሊ ቢራ በ71 ወይም በ72 ዓመተ ምህረት ለኢትዮጵያ ሬድዮ በሰጠው ቃለመጠይቅ፤ በዚህ ቦታ ለአንድ አመት ከስምንት ወር ገደማ የሰራ ሲሆን የመጣው ከሙዚቃ ሸሽቶ በሌላ ሙያ ለመሰማራት ነበር፡፡ ነገር ግን በወንዙ አወራረድ በጋራው (ጋራ ጉምቢ) ግርማ ሞገስ እና በአካቢው ልምላሜ እየተደመመ ይልቁንም ሙዚቃን ይበልጥ መውደድና ልምምድ ማድረግ ያዘ፡፡ አሊ ቢራ ከዘፈናቸው ዘፈኖች አብልጦ የሚወደውን ‘’አዋሽ ነመሹኪሳ’’ ን በደንብ ያቀነባበረው በዚህ ወቅት እንደ ነበረ ተናግሯል፡፡
የኩባንያ የውኃ ሞተር ሲበላሽ ባለ አህያ የሆኑ ሰዎች አዋሽ ወንዝ ወርደው በአህያቸው በጫኗቸው ታኒካዎች ውኃ ሞልተው በመሸጥ ጥሩ ገቢ ያገኙ ነበር፡፡ በሁዳዴ አሳ እያጠመዱ የሚሸጡም አሉ፡፡ ሴቶችና ወጣቶች እንጨት ሰብረው ለማገዶ ይጠቀሙበታል ይሸጡታልም፡፡ ከሰኞ ገበያ እና ከምድር ባቡር ቀጥሎ አዋሽ ወንዝና ሳቢል ጓሮ ተጨማሪ የስራ እና የገቢ ምንጭ ነበሩ፡፡
ከገደሉ በላይ ጋራ ጉምቢ ከነግርማ ሞገሱ ተገጥግጧል፡፡ አዋሽ ላይ ሲደርስ ጋራ ጉምቢ ይሁን እንጅ ይህ ከታች ከሐረርጌ አንስቶ ወደ ሸዋ የሚዘልቅ የተራሮች ሰንሰለት አካል ነው፡፡ ከጋራ ጉምቢ በስተኃላ ሌላ አለም ያለ አይመስለኝም ነበር ልጅ ሆኜ፡፡ አሁንም ሳየው ጋራ ጉምቢ ደስ የሚል ቅርጽ ያለው መጠነኛ ተራራ ነው፡፡ በተለይ ሰማያዊው ድንጋያማው ተራራ አሿሿሉ ፓርማውንት ፒክቸርስ ማስታወቂያ ላይ ያለውን ሰማያዊ ተራራ ይመስላል፡፡
አንድ ጊዜ አንድ አሜሪካዊ አገር ጎብኚ አዋሽን ሊጎበኝ በባቡር ይመጣል፡፡ በአሜሪካ ሚሲሲፒ ትልቅ ወንዝ እንደመሆኑ ሚሲሲፒ ከተማውም እንዲሁ ትልቅ ነው፡፡ ታድያ አዋሽ ትልቅ ወንዝ እንደመሆኑ አዋሽ የሚባለው ከተማም እንዲሁ ትልቅ መስሎት ነበር የመጣው፡፡ ከኦተራይ ሲወርድ ወጣትና ትንንሽ ሴቶች ’’አለ ቆሎ፤ አለ ሙዝ፤ አለ ጉልጉል፤ ጫት ጫት…’ እያሉ ሲከቡት ደንግጦ ነበር፡፡