ቀኑ ደርሶ ዶናልድ ትራምፕ ኋይት ሐውስ ግብቶ ስራውን ጀምሯል፡፡ እስካሁን እንዲተገበሩ ያዘዛቸውም ሆነ በይፋ ይደረጋሉ ብሎ የወሰናቸውን ነገሮች አስቀምጧል፡፡ አንዳንዶቹ የተጠበቁም ቢሆኑ ለአሜሪካም ሆነ አለም የማይበጁ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሹኑ በጊዜ ሂደት ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለፍጥረታት በአጠቃላይ አጥፊነት ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ በከባቢ አየር ጥበቃ ላይ የወሰዳቸውና ለመተግበር በአጀንዳ የተያዙት፡፡
በዚህ መጣጥፍ ሁሉንም የፕሬዚዳንቱን ውሳኔዎች ሳይሆን፣በሲመተ በአሉ ላይም ሆነ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ሲናገራቸውና በፊርማውም ሲደነግጋቸው ከነበሩት ውስጥ ትኩረታችን የሳቡትን ሁለቱን ብቻ እናቀርባለን
ፕሬዚዳንቱ ትዕዛዛቱን እየፈረሙ
መጀመርያ ስለ ስደተኞች
መቸም የትራምፕ ነገር በስመ አቡ ‘’ስደተኛ’’ ነው፡፡ እሱ ራሱ ታድያ የስደተኞች የልጅ ልጅ ነው፡፡ ስለ ትራምፕ ስደተኛ ወላጆች በመጣጥፉ መጨረሻ ላይ እንመለስበታለን፡፡ ለአሁኑ በጀመርነው እንቀጥል፡፡
ጃንዋሪ 21 ቀን 2025፣ማለትም ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ስደትና ስደተኝነትን በተመለከተ የሚከተሉትን እርምጃዎች ወስዷል፡፡
- የአሜሪካን ሰሜን ወሰን የአስቸኳይ ጊዜ ተደንግጎ ዝግ ተደርገዋል
- በወሰን በኩል የሚቀርቡ የስደተኝነት ጥያቄዎች ቆመው ድንበሩ ተዘግቷል
- አስፈላጊ ሲሆን ወታደሮችን እንደሚላኩ ተገልጿል፡፡ እስከ አሁንም 1500 ወታደሮች የጠረፍ ጠባቂ ፖሊሶችን ለማገዝ ወደ ድንበሩ ተልከዋል፡፡
- በአሜሪካ የሚወለዱ የውጭ ዜጋ ልጆች ያገኙ የነበረውን የነበረውን የዜግነት መብት ሰርዟል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እንጂ ይህ ትዕዛዝ በዋሽንግተን ዲስትሪክ ዳኛ ጆን ኮግኸኖር በጊዜዊነት በስራ ላይ እንዳይውል ታግዷል
- ስደተኞችን ተቀብሎ የማስተናገድ ስራ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል
- ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ እምነቶች የነበራቸው መብት ተሸሮ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች በፈለጉት ጊዜ ከነዚህ ተቋማት ውስጥ ስደተኞችን ማሰር እንዲችል ስልጣን ተሰጥቶታል
ከላይ ከተዘረዘሩት አንዳንዶቹን ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡ በወሰን በኩል የሚቀርቡ የስደተኝነት ጥያቄዎች ታግደው ድንበሩ ተዘግቷል ሲባል : –
‘’ህጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን ጥያቄ መቀበል ቆሞ ድንበሩ ይዘጋል፡፡ይህም ማለት ወረቀት የሌላቸው ስደተኞች በመግቢያ በሮች ላይ የስደተኝነት ጥያቄ ማቅረብ አይችሉም፡፡ ይህም ምንም ህጋዊ ማጣራት ሳይደረግ እነዚህ ስደት ጠያቂዎችን የመመለሱ ሂደት ይከናወናል፡፡’’ (THE WHITE HOUSE)
ስደተኞችን ተቀብሎ የማስተናገድ ስራ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓልሲባል : – ‘’ይህ ትዕዛዝ በጊዜያዊነት የአሜሪካ የስደተኞች ማስተናገጃ ፕሮግራም ከ ጃንዋሪ 27 ጀምሮ ተሰዋጭ ትዕዛዝ እስካልተሰጠ ድረስ፣ ማንኛውንም በአሜሪካ ስደተኝነት ለመጠየቅ የሚመጣን ሰው እንዳያስገባ ታግዷል፡፡ (Npr January 20, 2025)
እንግዲህ ትራምፕ ይሳካለትም አይሳካለትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወረቀት የለሽ ስደተኞችን ሊያስወጣ አቅዷል፡፡ ካለፈው የፕሬዚዳንትነት ዘመኑ አፈጻጸም አንጻር ይህ እቅድ ሙሉ በሙሉ የመፈጸም እቅዱ አጠራጣሪ ነው፡፡ በርካታ ህጋዊ እና የሎጀስቲክ ተግዳሮች ይጋረጡታል፡፡ በ 2022 እንደተጠቀሰው በአሜሪካ 11 ሚሊዮን ያልተመዘገቡ ስደተኞች አሉ፡፡ ትራምፐ በመጀመርያው የፕሬዚዳንትነት ዘመኑ ማሰወጣት የቻለው ከ 350.000 በላይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ይህ እንግዲህ ከሱ በፊት ከነበረው ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጊዜ እንዲወጡ ከተደረጉት 432.000 ሰዎች ጋር ሲተያይ ያነሰ አፈጻጸም ነው፡፡ (MinnPost)፡፡
እንዲህም ቢሆን ግን ለአመታት ወደ አሜሪካ ለመሄድ ለሚፈልጉ ሰዎችና እና እዛው ለሚኖሩ ስደተኞች ስደተኞች መጪው የትራምፕ አራት ‘’ዘመነ ፍዳ’’ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ምን መፍትሄ ይኖራል?
አንዱ ብዙም የማያስተማምነው ግን ሊኖር የሚችለው ከኮንግረሱ የሚመጣ ተቃውሞ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ሬፖብካኖች ኮንግረሱን ተቆጣጥረውታል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለት አመት በኃላ ሌላ የኮንግረስ ምርጫ አለ፡፡ አሁን ሬፐብሊካኖች በተወካዮች ምክር ቤት ያላቸው ብልጫ በሶስት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ዲሞክራቶች ከበረቱ ከሁለት አመት በኃላ መልሰው ሊቆጣጠሩት እድል ይኖራቸዋል፡፡
ሁለተኛው ተስፋ በዲሞክራቶች ቁጥጥር ስር ያሉ እንደ ካሊፎርኒያ ያሉ ግዛቶች ናቸው፡፡ ከወዲሁ እነዚህ ግዛቶች በአፈጻጸም ረገድ አሁን ትራምፕ ለሚከተለው እርምጃ እንደማይተባበሩ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ይህ ከላይኛው እድል የተሻለ ነው፡፡
ሶስተኛው እና የበለጠ አስተማማኙ ፍርድቤቶች ናቸው፡፡ እንደ ዲሞክራሲነቷ አሜሪካ በስራ ላይ የሚውል፣ በሶስቱ የመንግስት አካላት : ማለትም በአስፈጻሚው፣ በህግ አውጪው (ኮንግረስ) እና በህግ አስፈጻሚዎች(ፍ/ቤቶች) መካከል ቼክ ኤንድ ባላንስ አለ፡፡ማለት አንዱ ሌላውን ይከታተላል ይቆጣጠራልም፡፡ ስለዚህም የትራምፕ አካሄድ እንደፈለገው ሁሉንም ማድረግ አይችልም፡፡
እስቲ አሁን ደሞ ትንሽ ስለ ዶናልድ ትራምፕ ስደተኛ አያቶች እንተርክ፡፡ ይህን ታሪክ ያገኘነው ከ HISTORY The Trump Family’s Immigrant Story, by Natasha Forest, A&E Television Networks, July 13, 2018 ከሚለው ምንጭ ነው፡፡
የትራምፕ አያቶች ፍሬድሪክ እና ኤሊዛቤት ትራምፕ
ዶናልድ ጆን ተራምፕ የስደተኞች ልጅ እና የልጅ ልጅ ነው፡፡ በአያቱ ጀርመን ሲሆን በእናቱ ስኮትሽ ነው፡፡ የ አባቱም ሆነ የናቱ ወላጆች ማለት አያቶቹ አሜሪካ የተወለዱ አይደሉም፡፡ ከወላጆቹም ቢሆን እናቱ የተወለችው ስኮትላንድ አፍ መፍቻ ቋንቋዋም ጋሊክኛ ነው፡፡
አባትየው የተሳካለት የሬል እስቴት ባለቤት ሚሊዮኔር ነበር፡፡ ወደ ስኮትሽ እናቱ ስንሄድ ግን ታሪኩ ለወጥ ያለ ነው፡፡ በ 1930 ዎቹ አጋማስ ፍሬድ ትራምፕ ማለት የዶናልድ ትራምፕ አባት ዘነጥነጥ ብሎ ወደ አንድ ፓርቲ ይሄዳል፡፡ እዛም ሁለት እሕትማማቹችን ያገኛል፡፡ ከሁለቱም ወጣቷ ሜሪ አን ማክሎድ በጊዜው የቤት ሰራተኛ ስትሆን ወደ ስኮትላንድ ለመመለስ እያሰበች ነበር፡፡
ድንገት በዚች የቤት ሰራተኛ እና በሬል ስቴት ከበርቴው መካከል የፍቅር እሳት ይቀጣጠላል፡፡(ኢቢዳ ጃለላ) ፍቅራቸውም ቀጠለ፡፡ ‘’እነሆም የሰው ልጅ እናትና አባቱን ይተዋል፡፡ከሚሽቱም ይጣበቃል፡፡ ሁለቱም አንድ አካል አንድ አምሳል ይሆናሉ’’ እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፣ ፍሬድ እና ማሪ ተጋብተው እነ ዶናልድ ትራምን ወለዱ፡፡ ማሪ ትራምፕን የዶናልድ አባትን ካገባች በኃላ ኑሮዋ ተለወጠ፡፡ ህይወቷንም ጸጋ መላው፡፡
የትራምፕ ወላጆች ሜሪ እና ፍሬድ ትራምፕ
እንግዲህ ይህ የዶናልድ ትራምፕ አለምአቀፋዊ የዘር ሀረግ በአንጻራዊነት ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ልዩ ያደርገዋል፡፡ ካለፉት አስር ፕሬዚዳንቶች ትራምፕ እና ባራክ ኦባማ ብቻ ናቸው ከአሜሪካ ውጪ ከተወለደ ሰው የተገኙት፡፡ ባራክ ኦባማ በአባቱ ዶናልድ ትራምፕ በእናቱ፡፡
የራሱ የትራምፕ ቅርብ ቤተሰብ እኮ አለምአቀፋዊ የዘር ሀረግ ያላቸው ናቸው፡፡ የዶናልድ ትራምፕ ከሶስቱ ሚስቶቹ ሁለቱ ከቼክ ረፓብሊክና ከስሎቫንያ የተገኙ እና ቆይተው የአሜሪካን ዜግነት ያገኙ ናቸው፡፡ ከአምስቱ ልጆቹ አንዷ ቲፋኒ ብቻ ነች አሜሪካ ከተወለዱ አሜሪካኖች የተወለደችው፡፡ ሌላዋ ሴት ልጁ ኢቫንካ በሀገሪቱ ታሪክ ከአሜሪካ የመጀመርያ ቤተሰብ (ፈርስት ፋሚሊ) የመጀመርያዊ አይሁዳዊት አባል ነች፡፡
ይህን ሁሉ የምንለው እሱ ራሱም ስደተኛ ሚስት አግብቶ የወለደ፣ በመጀመርያ የፕሬዚደንትነት ዘመኑ ለሚስቱ ቼክ( የቀድሞ ቼኮስሎቫኪያ) ቤተሰቦች የአሜሪካ ዜግነትን ያሰጠ ግለሰብ መሆኑን ሳንረሳ ነው፡፡
ልብ በሉ ራሱ ትራምፕ ክልስ ነው፣ ከጀርመን እና ከአሜሪካ
እንግዲህ እሱ ራሱ ከነቤተሰቡ እንዲህ የተከላለሰ ሰው ለምንድነው አሜሪካ ከተወለዱ አናትና አባት ከተገኙት ፕሬዚዳንቶች በበለጠ መጤ ጠል የሆነው?
የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ
ሁለተኛ ስለ ከባቢ አየር ጥበቃ
በበዐለ ሲመት ንግግሩ በባይደን አስተዳደር ዘመን የተወሰዱ እና እየተወሰዱ የነበሩ ከአካቢ ጥበቃ እና የአየር ብክለትን የተመለከቱ ውሳኔዎች በከፊል በኤክስደቲቭ ኦርደር እንዲታገዱ ፈርሞ ደንግጓል፡፡ ለምሳሌ
1 – ለታዳሽ የኃይል ምንጮች ለማሳደግ ይደረግ የነበረውን ማበረታቻ በከፊል እንዲቀነስና አንዳንዱም እንዲቆም አድርጓል ለምሳሌም የንፋስ ኃይልን (ዊንድ ሚልስ) (The Washington Post)
2. ግሪን ሀውስ ሀውስ አፌክትን የሚያመጡና የሚያባብሱ ቅሬተ አካል ነዳጆች ምርትና አሰሳ እንዲጠናከር ደንግጓል (nature)
3. አሜሪካን ከፓሪሱ ስምምነት ተፈራራሚነት አስወጥቷል
በዚህ ድርጊቱ በባይደን አስተዳደር አሜሪካ ለአለም የአየር ብክለት ያላት ድርሻ እንዲቀንስና እዚያው አገሯ ላይም በከተሞች ያለው አየር ጤናማ እንዲሆን የተወሰዱትን እርምጃዎች በሙሉ በዜሮ ሊያባዛቸው ተሰንቷል፡፡
ትራምፕ ያለው እጅግ ውሱን እውቀት የአካባቢ ብክለት እና የአየር ንብረት መዛባት በሰው ልጅ ላይ እያመጡ ያለውን ጥፋት ለመረዳት የሚያስችለው አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሩቅ ሳይሄድ እዚያው አሜሪካ በየጊዜው የሚደርሱትን የጎርፍ እና አውሎነፋስ አደጋዎች፣ቁጥራቸው እና የሚያደርሱት የጥፋት መጠን እየጨመረ መሄድ ሊያሳስበው በተገባ ነበር፡፡ በቅርቡ እንኳን የደረሰው የሰደድ እሳት ጥፋት በቂ አመላካች ነው፡፡ ትራምፕ ግን ካለው የመረዳት ችሎታ ውሱንነት አንጻር ይህን መገንዘብ አልቻለም፡፡
ይሁን እንጂ ትራምፕ ብልጥና ጭንቅላቱም በማገናዘብ ረገድ የሚናቅ አይደለም፡፡ ይህ ሰው አምስት ልጆች እና አስር የልጅ ልጆች አሉት፡፡ ጓደኛውና በአሁኑ ወቅት ዋና ቀራቢው ኤሎን መስክ የአየር ጸባይ ለውጥ የዘመናችን ዋና ችግር ነው ይላል፡፡ ታድያ አያት ትራምፕን የአሁኑ ኢ ሳይንሳዊ ተግባሩ ለአስሩ የልጅ ልጆቹ እና የነሱንም ልጆች አለም፣ አሁን በሚያደርገው ስራ አየበከለ፣ እድሜአቸውም እሱን ሳያክሉ እንዲሞቱ እያደረገ እንደሆነ ቢመክረው አይሰማም ትላላችሁ?
በመጀርያ ፕሬዚዳንትነቱ ወቅት የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ የነበረው ጆን ቦልቶን ከትራምፕ ጋር ባሳለፈው የስራ ዘመን ከገረመው ነበር አንዱ ‘’የሰውየው የማወቅ ጉገት እጦት ነው(ኪሪዮሲቲ)፡፡ ሌላው በአብሮት ለተወሰነ ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የሰራው ሬክስ ቲለርሰን ትራምን ‘’ደደብ’’ (ሞሮን) ብሎ በመግለጹ ተቃቅረው ነበር፡፡
በግሌ ከትራምፕ አስቂኝ እና አስደንጋጭ ሀሳቦች አንዱ በኮረና ቫይረስ ጊዜ የተመለከትኩት ነው፡፡ ነገሩን ያየሁት በ ሲ ኤን ኤን ቀጥታ ስርጭት ላይ ነበር፡፡ ጊዜው ኮረና ቫይረስ በአሜሪካ ብዙ ሚሊዮኖችን የነደፈበት፣ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩት በየእለቱ የሚሞቱበት ወቅት ነበር፡፡
በዚህን ወቅት በየእለቱ ማታ ማታ የፌዴራሉ የኮረና ወረርሺን ተከላካይ ቡድን በዶክተር አንቶኒ ፋውቺ እየተመራ ገለጻዎችን የሚያደርግበት እና ምክሮችን የሚለግስበት ፕሮግራም ነበረው፡፡ በሁሉም ዋና ዋና የቲቪ ጣቢያዎች ይተላለፋል፡፡ ከዶክተር ፋውቺ በተጨማሪ ሌሎች አንድ ወይም ሁለት የጤና ዶክተሮች እንዲሁ ይኖራሉ፡፡ ወደ በኃላ በኃላ በስንት ምክርና እግዚኦታ እስኪያቆም ድረስ ዶናልድ ትራምፕ በፕሮግራሙ ላይ በቀጥታ ይሳተፍ ነበር፡፡ ፕሬዚደንትም ሆኖ እይታ አይጠግብም፡፡
ታድያ የሱ ጣልቃ ገብነት ንትርክም ያስነሳ ነበር፡፤ የጭምብልን (ማስክ) አስፈላጊነት ስለማያምንበት እነ ዶክተር ፋውቺ እየደጋገሙ ጥቅሙን ሲመክሩ በገጹ ሹፈት ይነበብ ነበር፡፡ አንዳንዴ ግን ጣልቃ ገብነቱ አዝናኝ እና አስቂም ይሆናል፡፡ በአንዱ መሰል ፕሮግራም ዶክተር ፋውቺ እና አሁን ስሟን የዘነጋሁት ደጋግማ የምትቀርብ ዶክተር እንዲሁም ትራምፕ ነበሩ፡፡ ዶክተር ፋውቺ ቤታችንን እና ግቢአችንን በዲስ ኢንፌክታንት ብናስነፋው ቫይረሱን ለመግታት ሊኖረው የሚችለውን ድርሻ በማስረዳት ላይ እንዳሉ፣ ትራምፕ ዘሎ ጣልቃ ይገባና
‘’አዎን ትክክል ነው፡፡ እንዲያውም ለምንድነው ዲስ ኢንፌክታንቱን በመርፌ አድርጋችሁ በሽተኞችን የማትወጉት፡፡ እመኑኝ…’’ ብሎ ሊቀጥል ሲል፣ ሴቷ ዶክተር ደንግጣ ከመቀመጫዋ በመነሳት
‘’ ኖው ኖው ኔቨር’’ ብላ ስትጮህ እኔም በጣም እስቅ ነበር፡፡
‘’ዘይሀኾነ ኾይኑ’’ ዶናልድ ትራምፕን የአሜሪካ ህዝብ ይበጀኛል ብሎ መርጦታል፡፡ ስለዚህ ‘’ምሁርም’’ ሆነ እነ ሬክስ ቲለርሰር እንደሚሉት ‘’ሞሮን’’ ፕሬዚዳንት ሆኗል፡፡ ደሞም ብልጥነት ፈጣን አሳቢነት እንዳልጎደለው በደንብ ማየት ይቻላል፡፡ ከአራት በፊት ከምናውቀው ትራምፕ ያሁኑ በርጋታ ለረዢም ደቂቃዎች (አንዳንዴ ሰአታትን) ሀሳቡን አቀናጅቶ የሚናገር ነው፡፡
ከሁሉም ከሁሉም ግን ህዝቡ በሚፈለገው መጠን ይሁነኝ ብሎ መርጦታል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ግን የሚያምነው ህዝቡ ብቻ እንደመረጠው አይደለም፡፡ ዶናልድ ትራምፕም ጃንዋሪ 20 ቀን 2024 በሹመት ስነስርአት ላይ ለጭንቅላቱ ከታለመው ጥይት የዳነው አሜሪካን ታላቅ ለማረግ እግዚአብሔር ለመሪነት ስለመረጠው እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስታት ለነገሱበት ዙፋን የተመረጡት በእግዚአብሔር እንደሆነ ነበር የሚገልጹት፡፡ አፄ ሐይለ ስላሴም ራሳቸውን ሲገልጹ ‘’እኛ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ’’ ብለው ነበር፡፡ ለነገሩ ሁሉም የዘውድ አገዛዞች ጉልላት የሚሆነው ዋናው ግለሰብ (ንጉሱ) እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሰው እንደሆነ ነው የሚገልጸው፡፡
‘’ሺ አመት ያንግስዎ! ስዩመ እግዚአብሔር፣ ዶናልድ ትራምፕ ንጉሠ ነገሥት ዘ አሜሪካ’’ እንበል ይሆን?
የፕሬዚዳንትነት ቃለ መሀላ ሲፈጸም
ምንጭ
HISTORY The Trump Family’s Immigrant Story, by Natasha Forest, A&E Television Networks, July 13, 2018
nature, news 21 jan 2025
MinnPost by Elliot Spaga, AP 09/23/2024
The Washington Post, 23 Jan 2025
THE WHITE HOUSE, PROCLAMATION, January 22, 2025