(ትንሿ ሜትሮፖሊታን – አዋሽ 7 ኪሎ)
ክፍል አንድ
ያለፈው አልፎ አልፏልና
ዳግም ላይመለስ ሄዷልና
እንደ ጥንቱ መሆን ቀርቷልና
ዛሬ ሌላ ሆኖ ቀርቧልና
(ግጥም ተስፋዬ ለማ፣ ዘፋኝ ጥላሁን ገሠሠ)
የልጅነት እድገታችን በአዋሽ ሰባት ኪሎ – የቅድመ-ፌዴላሪዝም ትውስታ
በስንክሳር አይን ስንመለከተው እድገታችን በአዋሽ ሰባት ኪሎ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ሰይድ ሰቃፍ
እስቲ ትንሽ ስለ ሰይድ ሰቃፍ እናውራ፡፡ ሲጀመር ሰይድ ሰቃፍ ትክክለኛ ስማቸው ሰቃፍ ዑመር ነው፡፡ ነገር ግን ዝርያቸው ከነቢዩ መሐመድ ሰለሚቆጠር ‘‘ሰይድ‘’ የሚባለው ማዕርግ ስለሚሰጣቸው ነው ሰይድ ሰቃፍ እያልን የምንጠራቸው፡፡
የነቢዩ መሐመድ ዝርያዎች ቁርያሽ ከሚባል ጎሳ ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ የነበሩ ሲሆን የኛዎቹ አረቦች የየመን ዝርያ በተለይም ሀድረሞት ከተባለ አቢይ ጎሳ ፈልቀው ዘቅሩሪ፤ሸቡጢ እና በመሳሰሉት ንዑስ ጎሳዎች የተከፋፈሉ በብዛት፣ሰቃፍ ዑመርና ጃዕፈር ዘይን ደሞ ከሰሜን የመን የፈለሱ ናቸው፡፡ እንዴት ዝርያቸው ከነቢዩ እንደተገናኘ አላህ ይወቀው፡፡
(በዚህ መጣጥፍ አንተ እና አንቱን በማደባለቄ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ባለታሪኮችን ደባልቀን እየጠራናቸው ስላደግን ነው)
ሰቃፍ ዑመር፤መልካቸው ካደግሁ በኃላ ያየሁትን የሊዎን ትሮትስኪን ፎቶ ግራፍ ቁርጥ ነው፡፡ የጺህማቸው አሿሿል እና የጎሪጥ አስተያየታቸው፤ እንዲያው ሌላ ሌላውም፡፡ እንደ ብዙዎቹ አረጋዊ የአዋሽ 7 ኪሎ አረቦች (የመናውያን) በንግድ ይተዳደራሉ፡፡ በንግድ ይተዳደራሉ እንበል እንጂ ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ አንስቶ በትክክል ምን እንደሚነግዱ ትዝ አይለኝም፡፡ ብቻ ከአዋሽ 7 ኪሎ ሲጠፉ ‘‘ለንግድ ወጥተው ነው’’ እንባላለን፡፡ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ ግን ከብት እየገዙና እያስገዙ ወደ ሳዑዲ መላክ ትልቁ ስራቸው ነበር፡፡
ዋና የእህል ነጋዴም ነበሩ; መጋዘናቸው በተለያዩ የእህል አይነቶች የተሞላ ነበር፡፡ቅቤም በታኒካ እያስሞሉ ወደ የመን ይልካሉ ከከብት ሌላ፡፡ ሳምንትም ሁለት ሳምንትም ጠፍተው ይመለሳሉ፡፡ ቤታቸው አረብ ሰፈር ነው፡፡ ይህ ሰፈር የድንጋይ ቤቶች አለሲሚንቶ እርዳታ እንዲሁ በጭቃ ብቻ ግን በሚያስተማንም መልኩ ተሰርተው የተደረደሩበት ሰፈር ነው፡፡ ዘቅጡጣ (ጠባብ መተላለፊያ) ይበዛዋል፡፡ የሰይድ ሰቃፍ ቤት ግን ወደ መስጊዱ በሚወስደው የአቧራ መንገድ ላይ ከተደረደሩት አንዱ ሆኖ ቢያንስ ፊት ለፊቱ በሲሚንቶ ልስን የተሰራ ቤት ነው፡፡
ልጅ እያለን በአዋሽ ባንክ አልነበረም እና ሰዉ በርከት ያለ ገንዘብ መዘርዘር ሲፈልግ ሰቃፍ መጋዘን ሄዶ እሳቸው ነበር የሚዘረዝሩለት፡፡
እኔ ነፍስ ሳውቅ ሰቃፍ አበበች ባቡ ቡና ቤት ጎን አንድ የእህል መጋዘን ነበራቸው፡፡ በዚያ በኩል ሳልፍ የጊዜው ሀብታም አረቦች እዚያ ፈርሸው ሲቅሙ አይ ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ መጋዘኑም ተዘግቶ ሰቃፍ ምንም ሲሰሩ ወይም ሲነግዱ አላቅም ነበርና ገቢያቸው ይገርመኝ ነበር፡፡ በፊት በፊት አሁን ለገሐሩ መዳረሻ ልጅ ሆነን ኳስ የምንጫወትበት ሜዳ እንዳለ የሰቃፍና ግራዝማች መካሻ እህል ማጠራቀሚያ ነበር አሉ፡፡ ሰቃፍ ትልቅ የእህል ነጋዴ ነበሩና አንድ ኤል ኤል ፉርጎ ሙሉ እህል እያስወረዱ ይሸጡ ነበር አሉ፡፡
ታሪካቸውን የኃላ ኃላ ስሰማ ከአደን መርከብ ላይ ሀማል (ጫኝና አውራጅ) ሆነው እየሰሩ ጅቡቲ ሲደርሱ አንድ ትትርናቸውን ያየ አፍደምና ጂማ ሱቆች የነበሩት አረብ አብረው እንዲሰሩ አግባብቶ ኢትዮጵያ ያስገባቸዋል፡፡ ያኔ ለየመን አረቦች ኢትዮጵያ መምጣት ትልቅ ነገር ነበር፡፡ እዚህ የመጡት ነግደውም ሆነ ሰርተው ቶሎ ይከብራሉ፡፡ የመን ላሉት ዘመዶቻቸውም በሀዋላ ብር ከመላካቸውም በላይ ከአለፍ አገደም እየሄዱም ቤተሰቦቻቸውን ደጉመው ስለሚመለሱ ይቀናባቸው ነበር፡፡ የሚገርመኝ ከአዲስ አበባ እስከ ድሬዳዋ ካሉት የባቡር ከተሞች እንደ አዋሽ አረቦች የሚበዙበት ከተማ አልነበረም፡፡
ሰይድ ሰቃፍን ይበልጥ የማስታውሳቸው በንዴታቸው ነው፡፡ ሲናደዱ ቀይ ፊታቸው ይበልጥ ፍም ይመስልና ሮዝማን ሲጋራቸውን በላይ በላይ እያቦለሉ በኃይል ይተነፍሳሉ፡፡ ያኔ ከፊታቸው ራቅ ማለት ይበጃል፡፡ አንዴ ሌሊት ተኝተው ቀን የቃሙት ጫት እንቅልፍ ነስቷቸው ከብዙ ሮዝማንስ ሲጋራ በኃላ ትንሽ ሸለብ ሲያደርጋቸው፤ ባለቤታቸው ለወተቷ ሲሉ በቅርብ የገዟት ላም ‘‘እምቧ’’ ብላ ስትጮህ ቀሰቀሰቻቸው፡፡ ብዙ ተራግመው ባለቤታቸውን ወቅሰው ከሌላ ብዙ ሙከራ በኃላ ትንሽ ሸለብ ሲያደርጋቸው አሁንም ላሜ ቦራ ‘‘እምቧ’’ ብላ ስትቀሰቅሳቸው
‘‘ሀዲክ አል ከብሽ ማትስኩት?’’ ማለትም ‘‘ይቺ ላም ዝም አትልም?’’ አሏቸው፡፡ ባለቤትየው
‘’ አይዞህ የአብዱረህማን አባት ትተኛለች፡፡ አንተ ብቻ ተረጋጋ እና ተኛ’’
ብለው አባብለው አስተኟቸው፡፡ ትንሽ ቆይቶ እሳቸውም ሸለብ እንዳረጋቸው ላሚቱም ስትጮህ እንደ ቀስት ተወርውረው ከመኝታቸው ተነሱና ወጡ፡፡ የፈረደባትን ላም በዚያ ውድቅት ሌሊት ከታሰረችበት ከግቢው ፈትተው ወደ ውጭ አባረሯት፡፡
‘‘ሌሽ ወራባ ይአኩለሃ’’’ ጅብ ይዘነጣጥላት ብለው፡፡ ትንሽ ቆዩና ባለቤትየው ሊወጡ ሲሉ ቆጣ ብለው
‘‘ዌን ትምሺ?’’ የት ትሄጃለሽ ብለው ጠየቁ
‘‘ቤት አል ቡል’’
ማለትም ሽንት ቤት ብለው መለሱላቸው እና ቀስ ብለው የግቢውን አጥር ከፍተው ላሚቱን ትንሽ ወረድ ብሎ ካለው ከነአቶ መኪ ሐቢብ ቤት ችግሩን አስረድተው ከግቢያቸው እንድታድር አደረጉ፡፡
ሌላ ጊዜ ደሞ ፍየል ቤታቸው ታስራ ታድራለች፡፡ በበነጋው ሰይድ አሊ በረት ሄዳ እንድትቀመጥ ነው ነገሩ፡፡ ፍየሏ የምትቆየው እስከ ጾም ፍቺ ሲሆን ለኢድ አልፈጥር ታስባ የተገዛች ናት፡፡ ሰኞ በቀላል ዋጋ ስላገኟት ነበር ከበዐሉ አስቀድማ የተገዛች፡፡ ያን ለት ማታ ግን ‘’ሚአአአ’’ እያለች አላስተኛ አለቻቸው፡፡ አፏን አስረው ዝም ሊያሰኟት ሞከሩ አልተቻለም፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ገደማ አረዷት፡፡ ትልቁን ልጃቸውን አብዱረህማንን በዚያ ውድቅት ቀስቅሰው
‘’ገፋፊ ፈልግ’’ ብለው ላኩት
ታድያ ንዴታቸው ጊዜያዊ ነው፤ ቶሎ ስለሚበርድላቸው፡፡ ለዚያ ጊዜ ከፊታቸው ገለል ማለቱ ይመከራል፡፡ ምክንያቱም ሲናደዱ ‘’ቅያማ ያቆማሉ’’ ስለሚባል፡፡ ቅያማ ማለት ተፍጻሜተ አለም ነው፡፡
ከሰይድ ሰቃፍ ንዴት እኩል ዝነኛ የነበረው ግሩዲንግ ሬዲዮናቸው ነበር፡፡ መለስተኛ ቁም ሳጥን የመሰለው ሬደዮናቸው የማያመጣው ጣቢያ የለም፡፡ በተለይም ከሱ ትንሽ መለስ የሚለው ኤቨሬዲ ባትሪ ድንጋይ የተገጠመለት ሰሞን ከማርስም ጣቢያ ቢኖር ይስባል እያልን የምንቀልደው ትዝ ይለኛል፡፡ ጣቢያ መፈለጊያው ትንሽዬ አምፑል ስላለችው ያበራል፡፡ ሰይድ ሰቃፍ ታድያ የማያዳምጡት የአረብ ጣቢያ የለም፤ ኦምዱርማን – አልቃሂራ፤ ኤደን፣ ጂቡቲ… አንዳንዴ ታድያ ጣቢያው ጥርት ብሎ አልደመጥ ሲላቸው ግሩዲንጉን ከመሬት ይወረውሩታል፡፡ ብረት ለበስ የምንለው የሰይድ ሰቃፍ ግሩዲንግ ትንሽ ዝም ይልና መልሶ ይሰራል፡፡
ለብዙ አመታት እንዲህ እናደንቀው የነበረው ሬድዮ የግብጹ ጀማል አብደል ናስር የሞቱ ጊዜ ግን የሱም ፍጻሜ ሆነ፡፡ እንግዲህ ያን ሰሞን ሰይድ ሰቃፍ በቀን 26 ሰአት ነበር ግሩዲንጉን ያሰሩት የነበረው፡፡ በዚህን ግዜ ታድያ አራት አምስቴ ከመሬት ሲያላትሙት መቻል አቃተው፡፡ድብደባው ይብዛበት ወይም የናስር ሞት አንጀቱን በልቶት እንደሆነ አይታወቅም እሱም ሞተ፡፡
ሰይድ ሰቃፍ አምስት ልጆች ነበሩት ሶስቱ ሲኖሩ ትልቁ ልጅ አብዱረህማንና የመጨረሻው አብደላ የሚባለው ሞተዋል፡፡ ባለቤቱን ሰዎች በስማቸው ሲጠሯቸው ትልቅ ጠብ ይፈጠር ነበር
‘‘ኡማ አብዱረህማን (የአብዱረህማን እናት) ነው ማለት ያለባችሁ እንጂ እንዴት ባለቤቴን በስሟ ትጠራላችሁ’’
እያለ ብዙ ጊዜ ቅያማ (የምጽአት ቀን) ያቆም ነበር፡፡ አንድ ሰው ሰቃፍ ጋ ጫት ለመቃም ሄዶ እየመረቀነ ሲሄድ ውስጥ እግሩን ወደ ሳቸው አዙሮ ከደቀነ ቅያማ ያቆማሉ፡፡ በርጫው ተበጠበጠ ማለት ነው፡፡ በአረቦች ባህል አንድ ሰው ውስጥ እግሩን ካሳየህ ሰደበህ ማለት ነው፡፡
ባለቤቲቱን ቢየሁሉ ከሚባል ከጋራ ጉምቢ ወዲያ ካለ አገር ነው ያገቧቸው፡፡ ሰኞ ሰኞ በሚውለው የአዋሽ ገበያ የቢየሁሉ ገበሬዎች ማሽላና ሌላ ሌላም ምርታቸውን ይዘው መጥተው ይሸጣሉ፡፡ ከገበያ መልስ ጊዜ ካላቸው አንዳንዴ እነ ሰይድ ሰቃፍ ቤት ሰላም ሊሏት ሲመጡ ነው እንግዴህ የስም አጠራር አለመግባባቱ የሚፈጠረው፡፡ ወደ ኃላ ግን ገበሬዎቹ የአረቦቹን ስርአት ስለተለማመዱ ጠቡም እየቀረ ሄዶ ነበር ከአንድ ጊዜ በስተቀር፡፡
መቼም የመጨረሻ ልጅ ትንሽ ሞልቀቅ ይላል ነጻነቱም ከቀደሙት ለቀቅ ያለ ነው፡፡ አባትና እናት የመጀመርያ ልጃቸውን በስነስርአት ለመያዝ ጠንከር እንደማለታቸው ከሶስት አራት ልጆች በኃላ የሚመጣውን የመጨረሻ ልጅ፤ እየደከሙ ስለመጡ ይመስላል ብዙ ነጻነት ይሰጡታል፡፡ በክሪ የሰይድ ሰቃፍ የመጨረሻ ልጅ ሲሆን አባትየው ካረጀ እና ከደከመ በኃላ የተወለደ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ታላላቆቹ አባቱን ብዙም አይፈራም፡፡ አባትየውም የትንሽ ልጅን ጣዕም ለመጨረሻ ጊዜ የሚያጣጥመው በበክሪ መሆኑን ስለተረዳ የበለጠ ያሞላቅቀው ነበር፤የበለጠ ስለሚወደውም ከአይኑ ሊያጣው አይፈልግም፡፡
አንድ ሰኞ ለታ ታድያ የሚስታቸው ዘመዶች የሆኑ የቢየሁሉ ገበሬዎች እህላቸውን ሸጠው ወደ አገራቸው ሊመለሱ ሲሉ አንድ ትንሽ ቆንጆ ልጅ በመንገዳቸው ላይ ብቻውን ጉድጓድ ሰርቶ ብይ ሊያስገባ ሲሞክር ያዩታል፡፡ ቆመውም የማን ልጅ እንደሆነ ሲጠይቁት የዘመዳቸው ልጅ እንደሆነ ሲረዱ ስመው አጫውተውት በማግባባት ለትንሽ ቀን አብሮአቸው እንዲከርም ይዘውት ወደ ቢየሁሉ ይሄዳሉ፡፡
ከሰአት ወደ ዘጠኝ ሰአት ግድም ሰይድ ሰቃፍ በክሪን ውለዱ ቢል ከየት ሊገኝ፡፡ ጫቱን ትቶ ልጁን ፍለጋ መጋላውን ሲያስስ ሰዎች ልጁን የአብዱረህማን እናት ዘመዶች ቢየሁሉ ሲወስዱት እንዳዩ እነሱም አባቱ ፈቅዶለት የሄደ ስለመሰላቸው ሊያስቀሩት እንዳልሞከሩ ነገሩት፡፡ ሮዝማንስ ሲጋራውን በላይ በላዩ እያቦለለ ቤት ገብቶ የፈረደባትን ባለቤቱን ደበደባት፡፡ የሷ ዘመዶች ያመጡት ጣጣ ስለሆነ፡፡ ትልቁ ልጁን አብዱረህማንም አልተረፈም፡፡
‘‘ትንሽ ወንድምህን የመጠበቅ ግዴታ አለብህ’’ ብሎ፡፡
ከሶስት ቀን በኃላ በክሪ ሲመጣ እንዲሁ ምሱን ቀመሰ፡፡ ከትንሽ ቀን በኃላ በዚህ ጣጣ የሌሉበት ሌሎች ቢየሁሉዎች የአብዱረህማንን እናት ሊጠይቁ ቤቱ መጥተው አገኛቸው፡፡ በጨዋ ደንብ ሰላምታ ሰጥቶ ካስገባቸው በኃላ እነማን እንደሆኑና ከየት እንደመጡ ሲጠይቃቸው፤ ገና
‘‘ከቢየሁሉ ነው የመጣነው’’ ከማለታቸው ቱግ ብሎ
‘‘ቢየሁሉ! ደሞ አሁን ምንቀራችሁ? በቀደም ልጄን አስኮበለላችሁ አሁን ደሞ እናቱን ልትወስዱ ነው?’’ ብሎ አባረራቸው፡፡
ሌላ ጊዜ ደሞ በረመዳን ወቅት ነው፤ ሰይድ ሰቃፍ ለስግደት ወደ መስጊድ ይሄዳሉ፡፡ አዋሽ ሰባት ኪሎ እንግዲህ ሞቃት ነው፤ሙቀቱ ደሞ ቱኻን ያፈላል፡፡ ሰዉ ታድያ ቱኻኑ ሲበዛት አልጋውን ጸኃይ ላይ ያውልና ማታ ያገባዋል፡፡ የጸኃዩ ሀሩር እንኳን ቱኻን ሰውም ይገላል- ተሰጥተው ከዋሉበት፡፡ ታድያ ያን እለት እግር የሌው ሽቦ አልጋ መንገዱ ላይ ተዘርግቶ ኖሮ የሰይድ ሰቃፍን አውራ ጣት ጥፍር አንድሎ ለቀቀው፡፡ ጣታቸውን ስለማይቆረጡት ጥፍራቸው ረዥም ኖሮ ከስሩ ተመንድሎ ደም በደም አረጋቸው፡፡ ከሕመሙም በላይ በረመዳን ደም ከፈሰሰ ጾሙ ስለሚጨናገፍ ሰቃፍ በንዴት ብው አሉ፡፡ አያጤሱ ነገር ጾም ላይ ናቸው፡፡ ባለቤቱ ማን እንደሆነ ጾምና ሙቀት ያደከማቸውን ጎረቤቶቻቸውን እየጮሁ እየቀሰቀሱ ቢጠይቁ መልስ አጡ፡፡ ባለቤቱን ካወቁ እንደማይምሩት የሚያውቀው ሰው መረጃ ነፈጋቸው፡፡
በንዴት ቁና ቁና እየተነፈሱ ጢማቸውን እያፍተለተሉ ቆዩ እና አንድ ሀሳብ መጣላቸው፡፡ ወዲያው ቀና ሲሉ ሙሳ አሊ እንለው የነበረ ወጣት ልጅ በዚያ ሲያልፍ አዩና አስቆሙት፡፡ በል፣ ብለው አልጋውን ካንድ ጫፍ አስያዙና እሳቸው ከሌላው ወገን ይዘው ከከተማው አውጥተው ጥለውት ተመለሱ፡፡ ንዴቱም በረደላቸው፡፡
ወደ በኃላ የአልጋውን ባለቤት ፈልገው አገኙትና
‘’አልጋህን ስንት ነበር የገዛኸው?’’
‘’አምስት ብር’’
‘’ሌላ ትኋን የሌለው አልጋ ግዛ’’ ብለው አስር ብር ሰጡት
እንግዲህ በየአመቱ ረመዳን ሲገባ ሰይድ ሰቃፍ ከሰው እንደተጣሉ ነው፡፡ አዋሽ አርጎባ ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው ከመጋላው ጀምሮ እስከ መኪና መንገዱ ድረስ ባለው ሰፈር አርጎባዎች፤ አረቦችና የሁለቱ ድብልቅ የሆኑ ክልሶች ይኖራሉ፡፡ ታድያ ረመዳን ሲገባ በቀኑ ላይ ብዙ ጊዜ አይግባቡም፡፡ ደመና ሆኖ ጨረቃ የማትታይበት ምሽት አለ፡፡ ያኔ አርጎባዎቹ ጨረቃን በአይናችን ካላየን ጾሙን አንጀምርም ባይ ሲሆኑ፡፡ አረቦቹ በተለይም ሰይድ ሰቃፍ
‘‘በሬድዮ መካ-መዲናን ሰምተናል፤ረመዳን የሚገባው ነገ ነው’’ ሲሉ አርጎባዎቹ
‘‘እኛ በቆርቆሮ አናምንም፤ ጨረቃን ስላላየን ነገ አንጀምርም’ ብለው ያንጎራብጣሉ’’፡፡
አብዛኛው የመኒ ቢጀምሩ ባይጀምሩ የራሳቸው ጉዳይ ነው ብሎ ራሱ ግን ጾሙን ሬድዮኑን በሰማበት አካኋን ይጀምራል፡፡ ሰይድ ሰቃፍ ግን ትክክለኛ ቀኑን ለማስረዳት ይከራከራሉ፡፡ አንድ ጊዜ…
‘’እኛ በቆርቆሮ አናምንም’’
ብለው ድርቅ ሲሉባቸው አፈፍ ብለው ከሳቸው በማይጠበቅ ቅልጥፍናና ፍጥነት ከተከራካሪዎቻቸው በአንዱ ቤት ጣሪያ ላይ ወጥተው ቆርቆሮውን ሊነቅሉ ሲታገሉ በብዙ ገላጋይ ይወርዳሉ፡፡ ቆርቆሮ ካስጠላህ ቤትህ ጣሪያ ላይ ምን ያደርጋል በሚል ሀሳብ፡፡
ሰይድ ሰቃፍ ልጆቻቸውን በደንብ በስነስርዐት ነበር ያሳደጉ፡፡ ከሌሎቹ አረቦች ሲተያዩ የተማሩ ነበሩ እና ልጆቻቸውን ጊዜ ቤት እስከ አስራ ሁለት ድረስ በጣቶቻቸው ላይ ያሉ መስመሮችን በመነካካት እንዲችሉ አስተምረዋቸው ነበር፡፡ እኛ አቡነ ዘበሰማያት እንበል አስራ ሁለት እንደምንለው አይነት ሆኖ እነሱ ግን በሌላ ስልት ይነካኩና መልሱን ይናገሩ ነበር፡፡ ልጆቹ ምስጢሩን ሳይነገሩን ከአገር ወጥተዋል፡፡ አስተዳደጋቸው ጥሩ እንደ መሆኑ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም በትምህርት ደህና ደረጃ ደርሰው በአቡዳቢና ሱዑዲያ ደህና ስራ ይዘዋል፡፡ ትልቁ ልጃቸው አብዱረህማንን ነቀምቴ ልከው አረብኛ ማንበብና መጻፍ እንዲሁም ሰዋስው ያስተማሩ ብቸኛ አረብ ሰቃፍ ነበሩ፡፡ ወደ በኃላ አብዱረህማን አደን ሲሄድ ይህ የአረብኛ ዕውቀቱ ብዙ እንደረዳው ነግሮኛል፡፡
ሰይድ ሰቃፍ ቢሆኑ የበኩር ልጃቸው አብዱረህማን ለአገራቸው አፈር አብቅቷቸው ያረፉት አደን ሄደው ትንሽ ከኖሩ በኃላ ነው፡፡ ታድያ እዚያ እንደገቡ ከአርባ አመት በፊት ትተዋቸው ወደ አበሻ ምድር የሄዱትን ባለቤታቸውን እንደገና ለማግባት ጠይቀው ነበር አሉ፡፡ እንደ ህጉ ከሆነ ያስኬዳቸዋል፤ ሳይፈቷቸው ስለሄዱ እንደገና ‘’የኔ ነች’’ ቢሉ ኪታቡ አይለከክላቸውም፡፡ ግን ሴትየዋ ‘’ሞቼ ነው ቆሜ’’ ብላ ስላገረገረች አልቀናቸውም፡፡
ብዙም ሳይቆዩ ሞቱ፤ እንደተመኙት በተወለዱበትና ባደጉበት መንደር አሸለቡ!