የስንክሳር በይነ-መረብ ወርሀዊ መጽሄት የጠቅላላ ዕውቀት መንሸራሸሪያ መጽሄት ስትሆን በውስጧም አለም-አቀፍ ግንኙነቶች፣ባህልና ስነ- ጥበብ፣ታሪክ፣አሰሳ፣ከመጽሐፍት ሰፈር፣ ሳይንስ፣ እና አካባቢ ጥበቃን የሚመለከቱ መጣጥፎች ይቀርቡባታል፡፡
የመጽሄቷ ተልዕኮ
አለም-አቀፍ ግንኙነቶች፣ ባህልና ስነጥበብ፣ ታሪክ፣አሰሳ፣ ከመጽሐፍት ሰፈር፣ሳይንስ፣እና አካባቢ ጥበቃን ርዕስ ያደረጉ መጣጥፎችን በማቅረብ በተማሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በከፊል የሚንጸባረቀውን የጠቅላላ እውቀት ጥማት ለማርካት የራሳችንን እና የሌሎችን አስተዋጽዖ አጣምሮ ማበርከት ነው፡፡
የመጽሄቷ ራዕይ
መጽሄቷን በ 2030 ከላይ በጠቀስናቸው ርዕሶች አሉ የተባሉ ልሂቃን የሚጽፉባት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቀለም ቀመስ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤትና በዲያስፖራ የመጽሄቷ ቋሚ ተከታታይ የሚሆኑባት፣ በነዋይ ረገድም ዳብራ ሀገር-በቀል ጠቀሜታ ያላቸው በአመት ከአራት ያላነሱ የምርምርና ጥናት ጽሁፎች የሚቀርቡባት ተወዳጅ የበይነ መረብና እንዲሁም የህትመት መጽሄት ማድረግ ነው፡፡
የመጽሄቷ ግብ
የሚቀርቡት መጣጥፎች በተቻለ መጠን አስተማሪ፣ መረጃ ሰጪ እና አዝናኝ የሆነ ይዘት ያላቸው ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም ጽሁፎቹ እያስተማሩ እውቀትና መረጃን የሚሰጡ ይህንንም በሚየዝናና መልክ የሚያቀርቡ ሆነው የወገኖቻችንን የማንበብ ባህል ማዳበር ግባችን ነው፡፡
የዚህ መጽሄት ወጣኒ የሆንኩት ታዬ መሐመድ የተባልኩ ግለሰብ ነኝ፡፡ እድገቴ የሐረርጌ ባህል ተጽዕኖ ያረፈበት ሲሆን ሸዋና ሐረርጌ ድንበር ላይ በምትገኘው የአዋሽ ሰባት ኪሎ ልጅ ነኝ፡፡ በኑሮም በመመላለስም ድሬዳዋን አዘውትሬአለሁ፡፡ እናቴ አማራ ሆና ኦርቶዶክስ ክርስትያን ስትሆን፣ አባቴ አማራ/ወርጂ እና ሶማሌ ሆኖ የእስልምና እምነት ተከታይ ነበር፡፡ በነዚህ ወላጆች አማካይነት እንደማደጌ ማንነቴ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ
ልሁን ብልም የማልችል ግለሰብ ነኝ፡፡ በዚህ ላይ ከልጅነት እስከ እውቀት (ከ1– 25) አመት በተከታታይ እና በከፊል የኖርኩት፣ አማራ፣ አርጎባ፣ሶማሌ፣አረብ፣ አፋርና ግሪክ እንደ ሻማ ቀልጠው በውህደት በኖሩባት ትንሿ ሜትሮፖሊታን አዋሽ ሰባት ኪሎ ለገሀር ስለሆነ በስነ-አምሮ ረገድ ውሁድነት ይጫነኛል፡፡
በዚያች የምድር ባቡር ኩባንያ ትልቅ ተጽዕኖ በነበረባት ከተማ በአማርኛ ተነጋግረን፣ በአረብኛ እና ሶማልኛ ተሳድበን፣ በጥራዝ ነጠቅ አርጎብኛ እና ፈረንሳይኛ ተቃልደን በመግባባት አድገናል፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ልዕልት ሰብለወንጌል አንደኛ ደረጃ አዋሽ ሰባት ኪሎ፣የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አዲስ አበባ ካዛንቺስ አስፋወሰን ት/ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን ዳግማዊ ምኒሊክ/ኮከበ ጽባህ አዲስ አበባ እና መተሀራ ስኳር ፋብሪካ ት/ቤት ተምሬአለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካና አለም አቀፍ ግንኙነት
የመጀመርያ ዲግሪ፣ በዴቨሎፕመንት ፖሊሲ ድህረ ምረቃ ዲፕሎም እና በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ከአንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ በኮመ-ላውደ (በማዕረግ) ተመርቄአለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በአስተዳደር መምሪያ፣ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፣ማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ፣ እና ያርድስቲክ ኢንተርናሽናል የርቀት ትምህርት ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት በዲንነትና ፕሬዚደንትነት አገልግያለሁ፡፡ ሲቪዋ አነሰች መሰለኝ? አንድ ነገር ልጨምርበት – ከ1966 በኃላ በነበረው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተራ ተሳታፊ ሆኜ ከቆየሁ በኃላ ከ1969 መጀመርያ እስከ 1971
መግቢያ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ መጀመርያ በኢህአወሊ ከዚያም በላብ አደሩ ክንፍ በሴልና በኃላም ደረጃ እድገት አግኝቼ በዞን ደረጃ ተንቀሳቅሻለሁ፡፡ ለዚህም አገልግሎቴ በመርቲ ስኳር ፋብሪካ ፖሊስ ጣቢያ ማረፍያ ቤትና በናዝሬት ወህኒ ቤት አንድ አመት እርማት ተደርጎልኛል፡፡
ማንበብና ውኃ ዋና አፍቃሪ ነኝ፡፡ ዕውቀት ከውቅያኖስ የጠለቀ፣ ከከዋክት የበዛና ከሕዋም የሰፋ ስለሆነ አንዱ ከሌላው እየተቀባበለ የሚረዳውና የሚማማረው ነገር ነው፡፡ ስለሆነም እኔና ጓደኞቼ ያለችንን እጅግ ትንሽ እውቀትና መረጃ በአንድ መደረክ አቅርበን፣ከሌሎች ከኛ በእጥፍ ድርብ ከሚያውቁ ለማወቅ፣ለመረዳት፣ እና ለመታረም ይህች የበይነ-መረብ መጽሄት መማማሪያ፣ መረጃ መቀባበያ እና መዝናኛ እንድትሆነን
እነሆ ስንክሳርን !
በዚህ የመጀመርያ እና መተዋወቂያ እትም
- የመጽሔቷን አላማ እና ግቦች የሚገልጽ ማብራሪያ
- የመጽሔቷን አዘጋጅ ማንነት ለማስተዋወቅ ትንሽ ገለጻ
- በአለም አካባቢ አዲስ አመት እንደመግባቱ ስለ ግሪጎሪሳዊ ቀመር ትንሽ ማብራሪያ
- በዚህ ሰሞን ዋና የአለም-አቀፍ ክስተት ስለሆነው የሶርያ ለውጥ የተዘጋጀ መጣጥፍ
- በባህልና ሰነ-ጥበብ አምድ ደግሞ በተከታታይ ከምናቀርባቸው ጽሁፎች ስለ አዋሽ
- ሰባት ኪሎ የቅድመ ፌዴራሊዝም አኗኗራችን የመጀመርያውን ክፍል እናስነብባለን፡፡
- በቅርቡ ኃይት ሀውስን ስለሚረከቡት ዶናልድ ትራምፕ መጠነኛ ማስተዋወቂያ
- በሚሉ ርዕሶች መጣጥፎችን አቅርበናል፡፡
በዚህ መጽሄት የምንጠቀምባቸው ወራት እና የዘመን አቆጣጠራት የአውሮፓ መሆኑን ቀደም ብዬ ከይቅርታ ጋር እገልጻለሁ፡፡ በዚህ መጽሄት ዝግጅት ባለቤቴ ወ/ሮ የምስራች መኮንን የአርትዖት ስራውን በማከናወንና በአጠቃላይ የመጽሄቷን ዝግጅት እና አቀራረብ በማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ አቶ ታጠቅ ደሞ ድረ-ገጹን ከመስራት አስንቶ ሁሉንም የቴክኒክ ስራ በማከናወን መጽሄቷ ነፍስ እና ስጋ ኖሯት እንድትታተም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ሁለቱንም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
መልካም ንባብ